አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፅመው ጥቃት በቃላት አይገለፅም። በጆሮ ሲሰማም ደስ አይልም። ጆሮን ከመጎርበጥ አልፎ በእጅጉ ይቀፋል። የቡድኑ አባላት ሰው ስለመሆናቸው ለማመንም ይከብዳል፡፡
ዓለም በቃኝ ያሉ የ85 ዓመት መነኩሴን በመድፈር የሚያገኘው ምን እንደሆነ ሲያስቡት ደግሞ ቡድኑ የሰው ስብስብ ሳይሆን የአውሬዎች ነው ለማለት አያዳግትም፡፡ ቡድኑ በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ በሆኑትና የ85 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ በሆኑ መነኩሴ እማሆይ በላይነሽ አለሙ (ስማቸው ተቀይሯል) ላይ የፈፀመው የአስገድዶ መድፈር በእርግጥም አውሬነቱን ያመለክታል።
እርሳቸው እንደሚናገሩት የተደፈሩት በውድቅት ሌሊት ነው። አሸባሪ ቡድኑ በራቸውን አንኳኳ።
ቢከፍቱለትም ባይከፍቱለትም የሽብር ቡድኑ በሩን መስበሩ አይቀርም ነበር። ዓለም በቃኝ ያለች መነኩሴ ሰይጣን ካልሆነ የሰው ልጅ ደፍሮ የሚያገኘው ደስታ ይኖራል ብለው ባያስቡም በሩን ከሚሰብረው ከፈቱለት። ጥፊና ጡጫው የካንቦሎጆ ኳስ እንጂ በአንዲት መነኩሴ የሚሰነዘር ሳይመስለው መሬት ጥሎ ደበደባቸው። ‹‹እዚያው የወደቁበት ላይም የፍላጎቱን ፈፀመብኝና ምንኩስናዬን አረከሰው። አበስኩ ገበርኩ! ይሄ አውሬ እንጂ ሰው ነው ማለት ይቻላል? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ጥቃቱ የደረሰባቸው እናት በጥቃቱ ቆመው መራመድ የማያስችል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በስነ ልቦናቸው ላይ የደረሰውማ እጅግ ከባድ ነው፡፡ የሕወሓት ጁንታ ቡድን ሰው ሆኖ መፈጠሩን የማያጠራጥረው የክፋት ትረካ ተዘርዝሮ አያልቅም። በደቡብ ወሎዋ ሐይቅ ከተማ እንዲሁ በውድቅት ሌሊት በር እያንኳኳና በጠራራ ፀሐይ ሕፃናትና ታዳጊዎችን እንዲሁም እንደ እማሆይ በላይነሽ ያሉ እናቶችን አስገድዶ በመድፈር አዋርዷል።
ይህንንም የዓይን ምስክሩ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ሰዒድ ይናገራሉ። እናቶችና ታዳጊ ሴቶች በቡድኑ አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ መደፈራቸውንና አካላዊ ጥቃትም የደረሰባቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ደፍረው የገደሏቸውና ከነቤታቸው ያቃጠሏቸው እንዳሉም ይናገራሉ፡፡
በአፋርና በአማራ ክልል በሕወሓት ጁንታ ቡድን እጅግ ዘግናኝና ለጆሮ በሚቀፍ ሁኔታ ተገድደው በአሰቃቂ ሁኔታ የተደፈሩና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የደረሱባቸው በርካታ ተጎጂ ታዳጊ ሴቶችና እናቶች መኖራቸውን ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የወጣ መረጃ ያመለከታል። የቡድኑን ድርጊት አሁንም ማስቆም ባይችልም ይሄ መረጃ በጀርመንና በአሜሪካ ድምፅ፣ አሾሼትድ ፕሬስና አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በኩል ለዓለም ደርሷል።
የዓለም ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሰው ፆታዊና አካላዊ ጥቃት እንዲቆም በጋራ ቢጮሁም ጥቃቱ ዛሬም አለመቆሙን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአንዲት ወይዘሮ ምክንያት አካሏ ላይ ጥቃት የደረሰባት የአስር አመቷ ሕፃን ስጦታ ዘለዓለም ማሳያ ነች።
ሕፃኗ እንደተናገረችው ወላጆቿንም ሆነ የመጣችበትን አካባቢ አታውቀውም። ግን ወይዘሮዋ በአካሏ ላይ ስታደርስባት የቆየችው ጥቃት አሁን የሆነ ይመስል ዛሬም በዕድሜ ያልዳበረውን ሰውነቷን በድንጋጤ ሲያርገፈግፈው ይስተዋላል። ወጣት ሀብለድንግል ታከለ የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ሕፃናት መከላከል ተሐድሶና ማቋቋሚያ ድርጅት የአዲስ አበባ ፕሮግራም ኃላፊና የስነ ልቦና ባለሙያ ሲሆኑ ሕፃኗ በወይዘሮዋ የጉልበት ብዝበዛና በአካሏ ላይ ድብደባ ተፈፅሞባት ወደ ድርጅቱ እንደመጣች ይናገራሉ፡፡
ትልልቅ የአዋቂ ልብሶችን ከማሳጠብና ቤት ከማፀዳት ጀምሮ የማታሰራት የሥራ ዓይነት እንዳልነበርም ይገልፃሉ፡፡ በየጊዜው በምታደርስባት ድብደባ እጇ እንደተሰበረ፣ ማጠፍና መዘርጋት እንደማትችልና በደረሰባት ድብደባም በጀርባዋ ላይ ትልቅ ጠባሳ እንደሚታይ ባለሞያዋ ያስረዳሉ፡፡
ወይዘሮዋ በሕፃኗ ብልት ውስጥ ሚጥሚጣ እየጨመረች ታሰቃያት እንደነበርና የምታሳድራትም እጅግ ቀዝቃዛና እርጥብ ያለበት መታጠቢያ ክፍል ውስጥ እንደነበርም ይገልፃሉ፡፡ የምታበላት ምግብ የተበላሸና የምታቀርብላትም በቡታ ጋዝ ዕቃ እንደነበርም ባለሞያዋ ገልፀው፤ ወይዘሮዋ በፖሊስ ልትያዝ የቻለችውም ድርጊቱን ያዩ ጎረቤቶች ለወረዳው ፖሊስ ሴቶችና ሕፃናት
በደብዳቤ በመጠቆማቸው እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ በወቅቱ ወደ ሞኖሪያ ቤቱ ሲሄዱ ሕፃኗን ያገኟት ቀዝቃዛው መታጠቢያ ቤት ውስጥ ቁጭ ብላ በቡታጋዝ ዕቃ ሴትየዋ የሰጠቻትን የተበላሸ ምግብ ስትመገብ እንደነበርም ባለሞያዋ ያስረዳሉ፡፡ ልጅቷን ይዘው ሲወጡ ሴትየዋን ወደ ቤት ስትመለስ መንገድ ላይ እንዳገኟትና በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለችም ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮዋ ጉዳዬ በሸሪያ ሕግ ይታይልኝ በማለቷ በዚሁ ሕግ እንዲታይላት ስለመደረጉም ይገልፃሉ፡፡ እንደ ባለሞያዋ ገለፃ ወይዘሮዋ ሕፃኗን ከገጠር ነው ያመጣኋት ትበል እንጂ ከየትኛው አካባቢ እንዳመጣቻት ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነችም። ሕፃኗም ወይዘሮዋ ጋር መኖሯን እንጂ ከየት እንደመጣችና የማን ልጅ እንደሆነች አታውቅም። ከዚህ ሕፃናት የደረሰባቸውን ጥቃት ሊናገሩ ስለማይችሉ እንደ ሥነ ልቦና ባለሙያ ሕፃናቶቹን ማማከር ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ሕፃን ስጦታን በማጫወትና በሌሎች ዘዴዎች የደረሰባትን እንድትናገር ተደርጓል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ሕፃን ስጦታ በድርጅቱ መጠለያ ውስጥ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላት ትገኛለች። የሴቶችና ሕፃናትን ጥቃት በትምህርት ሰጪ ድራማ መልክ አዘጋጅታ የምታቀርብ ድንቅ ልጅ ለመሆንም በቅታለች፡፡ በሕፃኗ ላይ የተፈፀመው ጁንታው ከፈፀመውና እየፈፀመ ካለው አሰቃቂ ጥቃት ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ትኩረት እንደሚሻ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ «እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ» በሚል መሪ ሃሳብ አሸባሪው ቡድን በሴቶችና ሕፃናት ላይ ያደረሰውን ፆታዊ ጥቃት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ የተደረገበት አንዱ መንገድ መሆኑን የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ አዘዝ ተናግረዋል፡፡ የሕወሓት ጁንታ ቡድን በከፈተው ጦርነት በሴቶችና ሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጥቃት አድርሷል።
ሕፃናትና ሴቶችን እየደፈረ የተለያዩ አሰቃቂና ዘግናኝ አካላዊ ጥቃቶችንም ፈፅሟል፡፡ ባለፈው እሁድ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ አሸባሪው የሕወሓት ጁንታ ቡድን እነዚህና መሰል በሴቶችና በሕፃናት ላይ የፈፀማቸውንና እየፈፀማቸው ያሉትን ጥቃቶች ለማውገዝ ነው፡፡ የሰልፉ ዓላማ አሸባሪው ቡድን በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ፆታዊና አካላዊ ጥቃት ለዓለም ማህበረሰብ በተለይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቡድኑን የሚደግፉት ምዕራባውያን ተረድተው ከድርጊቱ እንዲታቀብና ጫና እንዲያደርጉበት ብሎም በየትኛውም መንገድ ለእሱ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቆሙ ነው።
ጥቃቱን በሚያወግዘው ሰልፍ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር አባላትን ጨምሮ በሴቶች ማህበር፣ በሴቶች ሊግና በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ ከ40 ሺህ በላይ ሴቶች ተሳትፈዋል፡፡ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ አዘዝ እንደተናገሩት፣ የማህበሩ ተባባሪ አባል የሆኑት 40 ሺህ ወንድ አጋሮች በሰልፉ ተሳትፈዋል።
ድርጊቱንም አውግዘዋል። ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት አሁንም ላለመቆሙ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ነዋሪ በሆነች በአንዲት የሰባት ዓመት ሕፃን ላይ የደረሰው አስገድዶ መድፈር ምሳሌ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ሕፃኗ በ16 ዓመት ታዳጊ ወጣት መደፈሯንና ማህበሩ ወጣቱ ለሕግ እንዲቀርብ ማድረጉንም ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ከወጣቱ ወላጆችና ጎረቤቶቻቸው የተገኘው ምላሽ ጥሩ እንዳልነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ሰፊ የአመለካከት ችግር እንደነበረባቸውም አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሕፃናትና ሴቶች ምርመራና እንክብካቤ ኃላፊ ኮማንደር አፀደ ወርዶፋ እንደሚሉት ችግሩ ቢኖርም አብዛኛው ማህበረሰብ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በችልታ ያያል፡፡ አንዳንድ ወንዶችም መደፈርን እንደ ቀላል ጉዳይ የሚያዩበት ሁኔታ አለ።
ችግሩ በሕፃናት ላይ የሚያሳድረውን የስነ ልቦና ጉዳት በቅጡ አይረዱትም፡፡ ድርጊቱ በወንጀል እንደሚያስጠይቅም ግንዛቤው የላቸውም፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ሳይነቃባቸው ወንጀሉን በመደበቅና በማድበስበስ የሚያልፉት ብቻ የሚመስላቸው ነው ተብሎም ይገመታል። እንደ ቤተሰብ ሲታይ አባትም ሆነ እንጀራ አባት አልያም ወንድም፣ አጎትና ሌላ የቤተሰቡ አባል የመድፈር ወንጀል መፈፀሙ በማስረጃ እየተረጋገጠ ድርጊቱን ስለመፈፀም ያለማመን ችግርም ይታያል፡፡ ተገድደው የተደፈሩ ሕፃናትና በተለይም ዕድሜያቸው የማገናዘብ ችሎታ ላይ የሚገኝ ሴቶች የወንጀል ድርጊት ፈፃሚ ምልክቶች እንዳይጠፉ በማድረግና መረጃ ሳይጠፋ ወደ ሕግና ሕክምና አገልግሎት በመምጣት በኩል የግንዛቤ ክፍተት አለ፡፡
ይህም በምርመራ ሂደት ተፅዕኖ ያደርጋል። እንደ ማህበረሰብም ጥቃቶችን ከማጋለጥ ይልቅ አሜን ብሎ የመቀበል ችግር ጎልቶ ይታያል። ኃላፊዋ እንደሚገልፁት በተለይ በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ወንዶች ድርጊቱን የሚፈፅሙት ሆን ብለውና የሚያስጠይቃቸው ወንጀል መሆኑን እያወቁ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የወንጀል ድርጊቱን የሚፈፅሙትም በጥንቃቄ ነው፡፡ የሚያስጠይቃቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳይገኝባቸው አስቀድመው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ድርጊቱን ተጠንቅቀው ስለሚፈፅሙትም መረጃው በቀላሉ አይገኝም። ከምርመራ አንፃር ወንጀሉን መፈፀማቸውን የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂም የለም። ለምሳሌ የጥቃቱ ሰለባ የሆነቸው ሕፃን ቤተሰቦቿ በቅርብ ላይኖሩ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ ጉዳዩ ቶሎ ለሕግ ላይቀርብ ይችላል። ጊዜ በገፋ ቁጥር በጥቃቱ የደረሰባት ቁስል የመዳንና የማገገም ሁኔታ ስለሚኖረው ለወንጀሉ ማስረጃ የመሆኑ ዕድል እያነሰ ይሄዳል።
በአጠቃላይ በምርመራ ሂደት ውስጥ ለምርመራ ደጋፊ እንጂ ማስረጃ የሚሆን መረጃ ላይገኝ ይችላል። አንድን ጉዳይ ውስብስብና ከባድ ከሚያደርገውም አንዱ ጉዳይ ይኸው ነው። ለምርመራ ሂደቱ ደግሞ የተፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ ከተጠርጣሪው ጋር ማገናኘት ግድ ይላል። ወንጀሉ መፈፀሙን ማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ ማግኘት እጅግ ወሳኝ ነው። እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ በነዚህ ምክንያት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ምርመራ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነው። ከውጪ ሲታይ ቀላል ሊመስል ቢችልም አንድን ጉዳይ መርምሮ ውጤት ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ችግር አለበት። የሴቷን ጉዳይ መርምሮ ቃል ተቀብሎ በዚያው ልክ የሚበቃ አይደለም።
በርካታ ማስረጃዎች ያስፈልጉታል። ‹‹ከተማችን ላይ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ትንሽም ቢሆን አለ። ይሁንና የጥቃት ትንሽ የለውም። አንድም ቢሆን ከባድ ነው፡፡›› ይላሉ ኃላፊዋ፡፡
በብዙ ጫናዎች ውስጥ ጥቃት ቢፈፀምም ካለው ስጋት አኳያ ሪፖርት ላይደረግ የመቻሉን ጥርጣሬም እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ጥቃት ለመኖሩም አንዲት በእሳቸው ቢሮ አገልግሎት እየተሰጣት ያለችን ወጣት ሴት ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ወጣቷ በመደፈር ነፍሰ ጡር ለመሆን መገደዷንም ተናግረዋል፡፡ ወጣቷን የሚያግዛትንና የሚደግፋትን መፈለግ የፖሊስ ኃላፊነት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አኳያም የሚያስፈልጋትን ድጋፍ ሁሉ እንድታገኝ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ የተደፈሩ ሴቶች ከላያቸው ላይ መረጃ ሳይጠፋ ወደ ፖሊስ መምጣታቸው፤ ውስብስብና ከባድ ሊሆን የሚችለውን የምርመራ ሂደት የተቃና ለማድረግ ይረዳል።
በ1997 ዓ.ም ጉዳዩን አስመልክቶ የወጣው የወንጀል ሕግ እስከ 13 ዓመት ባሉት ሕፃናት ላይ የሚፈፀመው በከባድ ወንጀል እንደሚያስቀጣም ተደንግጓል። ከ13 ዓመት በላይ ሲሆን ቅጣቱ ቀላል ነው ማለት ባይሆንም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ወንጀሉን በበቂ ሁኔታ ማስረዳት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ዳኛው ግራና ቀኝ ዓይቶ የሚጠቀማቸው የቅጣት ማክበጃና ማቅለያዎች አሉ። ዘርፉ ከፍርድ ቤትና ከአቃቢ ሕግ ጋር በመቀናጀት በዚህ መልኩ ተጎጂ ሕፃናትና ሴቶች የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል። በተለይ 991 የአስቸኳይ ጊዜ የነፃ ስልክ ጥሪ መቀበያ ተጎጂዎቹ በልዩ ሁኔታ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ ዓይነተኛ መፍትሄ ሆኗል።
ነፃ መሆኑ በራሱ አንድ ጥቅም አስገኝቷል፡፡ የስልኩ ቴክኖሎጂ ዘመናዊ በመሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚደውሉ ተጎጂዎችን ድምፅ ማሰማትና መቅረጽም ያስችላል። ስልኩ ቢቋረጥም ያሉበትን ቦታ ይጠቁማል። ያሉትን ግንኙነቶች ሪፖርት ያደርጋል። በወቅቱ የተመደበው ባለሙያ ተጎጂዎቹ ባሉበት አካባቢ ካለው መርማሪ ጋር ተገናኝቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ያስችላል።
ተጎጂዋ ሪፈር ከተደረገች መረጃው ስለሚላክ ሂደቱ ቀላል ይሆንላታል። ባለፈው ሐምሌ በተጀመረው በአገልግሎቱ ተጎጂዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የበለጠም እንዲጠቀሙበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ከዚህ ውጪ በጉዳዩ ዙርያ አሁን ባለው የጦርነት ሁኔታ እንደ አገር ጥቃቱ ተባብሷል። ግን አዲስ አበባ ከተማ ሠላም ነች። በሠላምና ፀጥታ በኩልም ሆነ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ይኖሩባታል ተብሎ የሚሰጋባት አይደለችም።
ኅብረተሰቡ በብሎክ አደረጃጀት ገብቶ አካባቢውን መጠበቁ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን አካላዊ ጥቃት ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኃላፊዋ ይናገራሉ፡፡ ስለ ችግሩ እርስ በእርስ እንዲወያይ ግንዛቤ፤ እንዲኖረው በቤተሰብም ሆነ በአካባቢ ያሉ ጥፋተኞችን አሳልፎ ለሕግ እንዲያቀርብ ዕድል የሚሰጥ እንደሚሆንም ያስባሉ።
ይሁንና ሳይዘናጉ አካባቢን ነቅቶ ማጥናትና መጠበቅ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ይመክራሉ። እንደ አዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሕፃናትና ሴቶች ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው የመከላከል፤ ተፈፅሞ ሲገኝ ምርመራና ክትትል በማድረግና መረጃ በማደራጀት ረገድ በተቀናጀ የአንድ ማዕከል የምርመራ ቡድን እየተሰራ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡ ሥራው በዘርፉ አስተባባሪነት በከተማው ባሉ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2014