ኢትዮጵያ በከባድ የህልውና ፈተና ውስጥ ብትሆንም ወቅታዊውን ጉዳይ ከመቋቋም ባለፈ ታላላቅ አገራዊ ራዕዮችን ከግብ ለማድረስ እየተጋች ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ቀጣይ ዲጂታል ኢኮኖሚንና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚደገፍ እድገትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አንዱ ነው። የዘርፉ አመራሮች በወቅቱ የህልውና ጦርነት ላይ ያተኮሩና የአገሪቷን አሸናፊነት የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩም ጎን ለጎን ግን ዋናውን የሃዲድ መንገድ ባለመሳት የአራተኛው ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታውንም አልዘነጉም።
ለዚህ ነው ከሰሞኑ በታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ በርከት ያሉ መረጃዎች እየደረሱን የሚገኙት። ለዛሬም ኢትዮጵያን የተመለከቱ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ጋር የተያያዙትን ጥቂቶቹን መራርጠን እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተነዋል። መረጃውን ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አግኝተነዋል።
«ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት አቅሙና ጥበቡ ያላት አገር ናት» ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ መናገራቸውን የሰማነው በዚህ ሳምንት ነው። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄነሪስ ሉንዱኪስት ጋር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና በሌሎች ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረው ነበር።
ውይይታቸውን በማስመልከትም ስዊድን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ይህንን ልምድ መውሰድ እንደምትፈልግና ድጋፍም እንደምትሻ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ስዊድን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ በምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ በ አይ ሲ ቲ እና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ያለባትን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ስዊድን ቀደም ሲል ስታደርግ የነበረውን ትብብርና ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሚስተር ሀንስ ሄነሪስ ሉንዱኪስት በቴክኖሎጂና ሥራ ፈጠራ፣ በትምህርትና ግብርና ዘርፍ ኢትዮጵያን ለመደገፍ አገራቸው ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ከ13 በላይ የስዊድን ካምፓኒዎች እንዳሉ የገለፁት አምባሳደሩ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ በስዊድን በኩል ያለውን ስጋት አንስተዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት አቅሙና ጥበቡ ያላት አገር መሆኗን ለአምባሳደሩ አረጋግጠውላቸዋል።
የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክርቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ከሰሞኑ በሶማሌ ክልል መመስረቱ የሚታወስ ነው። ይህን በማስመልከት ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በመልዕክታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሥራንና ሀብትን ለመፍጠር የምትመች አገር ለመገንባት ርዕይን በመሰነቅ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በተለይ የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚገነባበትን ከባቢያዊ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ልማት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል አቅም እንዲገነባ እና ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ምርምር ለሥራና ሀብት ፈጠራ አበርክቶ እንዲኖራቸው አልሞ እየሠራ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
«አገራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ጋር በትብብርና በቅንጅት ተግባራትን ያከናውናል» የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ለአብነት ከሶማሌ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት Livestock Project እና Local Online Service ትግበራና የሳይንስ ካፌ ማቋቋም ዋንኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ተግባራት ዘርፍ ተሻጋሪ (Cross Sectoral) እንደመሆናቸው የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይሻሉ፡፡ ዘርፉ ለጠቅላላ አገራዊ ምርት እድገት ያለውን አስተዋፅኦ የመምክር፣ የመገምገም እና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ዓላማ ያለው ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ምክርቤት መኖሩን አውስተዋል፡፡ መሰል ምክር ቤቶች በሁሉም የክልል እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲቋቋሙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ፋና ወጊ ሆኖ የምክር ቤቱ ምስረታ እንዲሳካ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊና የምክርቤቱ ሴክሪታሪያት ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ክልሉን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እያደረገ ላለው ጥረት አመስግነዋል፡፡
ዘርፉ የሕዝቡ ኑሮ እንዲሻሻልና የክልሉ እምቅ አቅም በቴክኖሎጂ ታግዞ ለተጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የድርሻውን እንዲያበረክት ያስችለዋል፡፡ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን ለመቀበል ቀዳሚ ነው ያሉት ክብርት ፋጡማ የምክርቤቱ መቋቋም የክልሉን ሕዝብ ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ወቅቱንና የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ድጋፎችን በሌሎች ዘርፎችም ጭምር ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ስነ-ምህዳር በቴክ-ኢንተርፕርነርሽፕ ለወጣቶች በኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር በቴክኢንተርፕርነርሽፕ ሥራን በመፍጠር የሀብት ባለቤት ማድረግ የሚያስችል የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ፣ ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮዎችና ከተመረጡ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በኢኖቬሽን ስነ-ምህዳርና በቴክ-ኢንተርፕርነርሽፕ ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከሰሞኑ መስጠቱ የሚታወስ ነው:: የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ባስተላለፉት መልዕክት ብዙ የወጣት ኃይል ላላት አገራችን ሥራን በመፍጠር ወጣቶች የሀብት ባለቤት እንዲሆኑ የባለሞያውን አቅም ማጎልበት ወሳኝና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁሪያ አክለውም ያለፈውን ተሞከሮ በማስታወስ አዲስ ቅንጅታዊ አሠራርን በመፍጠር፣ አደረጃጀቶችን በመከለስና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ማጎልበት የሚያስችል የሰው ኃይልን በመፈጠር ሥራ ላይ እንዲውል መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ራሳቸውንና አገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ሊገለገሉበት እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያ ዘመቻ ለመቀልበስና ተስፋን ለመሰነቅ የሚያስችል «ተስፋ ለኢትዮጵያ» የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ዘመቻ መጀመሩን አስመልክቶ ነበር ይህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት። ንቅናቄው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ መቀልበስ የሚያስችል እና በአገራችን በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ጫና ውስጥ የገቡ ዜጎችን ስነ ልቦና ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በንቅናቄው በርካታ ወጣቶች በኢትዮጵያ ላይ ስላላቸው የወደፊት ተስፋ የተመለከተ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ የዲጂታል ዓለሙን ጨምሮ በተለያየ መልኩ እየደረሰባት ያለውን ዓለም አቀፍ ጫና ተቋቁማ እያሸነፈችና ወደ ከፍታዋ እየተጓዘች መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ራሳቸውንና አገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂውን የገቢ ምንጭ ለማድረግ፣ የአገራቸውንና የዜጎቻቸውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እና የአገራቸውን በጎ ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ሊጠቀሙበት ይገባዋል ብለዋል።
ጊዜው የኢትዮጵያን በጎ ነገሮች የሚነገሩበት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት በዜጎች ላይ የደረሰውን የሥነ ልቦና ጫና ለመቅረፍ ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሀሰት ዘመቻዎችን ለመመከት፣ ሌሎች አገራት ስለኢትዮጵያ በጎ መረጃ እንዲይዙና በጎ እንዲያስቡ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል። ሰዎችን የሚያጋጩ፣ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡና አሉታዊ አስተሳሰብ ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን ማስወገድም የዘመቻው አካል ነው።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ሌላው ባሳለፍነው ሳምንት ከሰማናቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ውስጥ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ትግበራ ነው። በዚህ መሠረትም ትግበራው የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ሕጎችን ባከበረ መልኩ የሙከራ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል። ከዚህ ትግበራ ጋር ተያይዞም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የብሔራዊ መታወቂያ የሙከራ ሥራ ያለበትን ደረጃ በመመልከት ከፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል። የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ በተለያዩ የፌደራል የመንግሥት ተቋማት ላይ እየተተገበረ ይገኛል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል በ2018 ዓ.ም ሕፃናትን ሳይጨምር 95 ከመቶ ለሚሆኑ ዜጎች መታወቂያውን ለማዳረስ ይሰራል ብለዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ፍትሃዊ አሠራርን ለመዘርጋትና ዜጎች በኦንላይን አገልግሎት ላይ ያላቸውን እምነትን ለመጨመር ብሔራዊ መታወቂያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ለዜጎች የመረጃ ጥበቃ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለፕሮጀክቱ ስኬት ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። መታወቂያው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀውንና በመጽደቅ ሂደት ላይ ያለውን የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ የሚደነግጋቸውን ሕጎች ባከበረ መልኩ የሙከራ ሥራው እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።
ፖላንድ ኢትዮጵያ ፖላንድ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እደግፋለሁ ማለቷ የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በኢትዮጵያ ከፖላንድ አምባሳደር ሚስተር ፕሪዝሚይስላው ቦባክ ጋር ሁለቱ አገራት በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ዙሪያ መምከራቸው አይዘነጋም።
ሚኒስትሩ ፖላንድ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ከፖላንድ ልምድና ድጋፍ ማግኘት ትፈልጋለች ብለዋል። «ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሠራች ነው» የሚሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ ፖላንድ በተለይ በኤሌክትሮኒክ መንግሥት እና ኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ ያላትን የዳበረ ልምድ መውሰድ እንፈልጋለን ብለዋል።
አምባሳደር ፕሪዝሚይስላው ቦባክ በበኩላቸው አገራቸው በኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ፣ በታክስ አስተዳደር፣ በዳታ ኢንተግሬሽን፣ በጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ሲስተም ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራ ፖላንድ ለመደገፍ ዝግጁ ናት ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በዘርፉ ልምድ የሚወስዱባቸውን እድሎችም እናመቻቻለን ብለዋል። ሁለቱ አገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ሥራ ለመግባትም ከስምምነት ደርሰዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2014