ያለወትሮው ተዘግቶ ያረፈደው ግቢ አሁንም በጭርታው ዘልቋል። እንዲህ መሆኑ ለብዙዎች የተለመደ አይደለም። እስከዛሬ ግቢው ማልዶ ይከፈት ነበር። ወፍ ሳይንጫጫ መባተል የሚጀምሩት የቤቱ ዕማወራ ከብቶችን አልበው፣ ከሜዳ ያሰማሩ ነበር። በዚህ ሰዓት በሬዎቹ ወደ እርሻ፣ በጎቹ ወደግጦሽ ይሄዳሉ። አሁን ግን በዚህ ግቢ የወትሮው ልማድ እየታየ አይደለም። ዝምታው ነግሷል። ጭርታው ብሷል።
ሰዓቱ እየረፈደ ነው። የጠዋቷ ፀሐይ አመል ተቀይሮ፣ማቃጠል ይዛለች። የመንደሩ ሰዎች ክፉኛ ተጨንቀዋል። በበረቱ ያሉ ከብቶች እንደተዘጋባቸው ይጮሀሉ። ዶሮዎቹ፣ በጎቹ ከወትሮው ልማድ የሚያገናኛቸው ጠፍቶ ይራኮታሉ። የቤቱ አባወራና የባለቤታቸው ድምጽ ፈጽሞ አይሰማም።
ጎረቤቶቹ ጆሯቸውን ጥለው አዳመጡ። አንዳች የሚሰማ ነገር የለም። በጥንቃቄ ዓይናቸውን ተክለው፣ ኮቴያቸውን አጥፍተው ሁኔታውን አጣሩ። አሁንም የግቢው ዝምታ ያስፈራል። ይሄኔ በአጥሩ ጥግ የቆሙት ሰዎች ድንጋጤ ጨመረ። ሁሉም እያሰቡ ተጨነቁ። እየተጨነቁ ስጋት ገባቸው።
ሰዓቱ እየገፋ ዝምታው እየባሰ ሲሄድ የመንደሩ ሰው ፍርሐት አደገ። ከተሰበሰቡት መሐል ጥቂቶቹ አጥሩን ዘለው ወደውስጥ ለማለፍ መከሩ። ሀሳባቸውን ያወቁ ሌሎች ዘለው እንዲገቡ ገፋፏቸው። የታሰበው አልሆነም። ወንዶቹ ከአጥሩ ወጥተው ወደግቢው ለመዝለል ከማሰባቸው የኃይለኞቹ ውሾች ጩኸት አስደንብሮ መለሳቸው።
ጎረቤቶች የባልና ሚስቱ ድምጽ መጥፋት አስገርሟቸዋል። ከአንድ አይሉት ሁለቱም ብቅ ያለማለታቸው የተለመደ አይደለም። ይህን የሚያውቁ የቅርብ ሰዎች ሀሳብ እየመዘዙ ብዙ ገመቱ። መላምት አስቀምጠውም ይሆናል ያሉትን ጠረጠሩ። ጥርጣሬቸው ከግምት አላለፈም። በይሆናል ብቻ የመጣ መፍትሔ የለም።
አሁንም የመንደሩ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ዳግም መከሩ። ጭር ካለው ግቢ ዝምታ ከዋጠው አጸድ መግባት ግድ መሆኑ ተወሰነ። ካሉት መሐል ጠንካሮቹ ተመርጠው ወደውስጥ ዘለሉ። ኮቴና ድምጽ የሰሙት ኃይለኞቹ ውሾች ግቢውን በኃይለኛ ጨኸታቸው አደባለቁት። ሰዎቹ ለውሾቹ የማያቋርጥ ድምጽ ጆሮ አልሰጡም። ራሳቸውን ተከላክለው ወደ ውስጥ አለፉ።
ከግቢው ውጭ ያሉት ሰዎች ውስጥ ካሉት ሰዎች ምላሽ እየጠበቁ ነው። የውስጠኞቹ እንደታሰበው በቶሎ አልወጡም። ውጭ ያሉት ጠባቂዎች ከውሾቹ ጩኸት ያለፈ ድምጽ አይሰማቸውም። እየጨነቃቸው፣ እየተቁነጠነጡ ሰዎቹን ጠበቁ። አሁንም ከሰፊው ግቢ የሚመጣ ፈጣን ምላሽ አልተገኘም። ሁሉም በትካዜ ተውጠው ግምታቸውን ሰነዘሩ። አብዛኞቹ በጤና አለመሆኑን ተናገሩ፣ ገሚሶቹ ቸር እንዲያሰማቸው ተመኙ፤ ሌሎች ደግሞ በዝምታ ተውጠው የሚሆነውን ጠበቁ።
ድንገት የተሰማው ደማቅ ጩኸትና ለቅሶ የሁሉንም ቀልብ ወስዶ ድንጋጤን ፈጠረ። የአስደንጋጩ ድምጽ መነሻ ከየት እንደሆነ የገባቸው ጎረቤቶች ጆሯቸውን አቁመው ድምጹን ለመለየት ሞከሩ። አልተሳሳቱም፣ ድንገቴው የጩኸት ድምጽ የተሰማው ከአዛውንቶቹ ባልና ሚስት ግቢ ነው። ደጅ ያሉት እየተሯሯጡ ከግቢው በር ተኮለኮሉ። በሩ ከውስጥ ሲከፈትላቸው ጊዜ አልሰጡም። እየተገፋፉ፣ እየተደናበሩ ወደመሐል ዘለቁ። ከደቂቃዎች በኋላ ስፍራው በሰዎች ጩኸት ተደባለቀ። የሆነውን ያላመኑ በርካቶች ራሳቸውን ይዘው፣ደረታቸውን እየደቁ ፣በዕንባ ታጠቡ። አካባቢው በእሪታ ድምጽ ተናወጠ። በኡኡታ ተደባለቀ።
ዕድሜ ጠገብ ጥንዶች …
በርካታ ዓመታትን የተሻገረው የጥንዶቹ ትዳር ለብዙዎች አርአያ ሆኗል። ሁለቱም ከልጅነት እስከ ዕውቀት በኖሩበት አርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ በበርካቶች ይታወቃሉ። ባልና ሚስቱ በጉራ ሲሊንጎ ቀበሌ ክፉ ደጉን ተጋርተው አሳልፈዋል። በላሎ ጨካ ጎጥም በፍቅር ኖረው በመከባበር ዘልቀዋል።
ሁለቱም ከወጣትነት ዕድሜ አንስቶ በዘለቁበት መንደር መልካምነታቸውን የሚመሰክሩላቸው ጥቂቶች አይደሉም። ብርቱዎቹ ጥንዶች የዕድሜ ባለጸጎች ናቸው። ለሰባ ዓመታት በኖሩበት አካባቢ ያያቸው ሁሉ ያከብራቸዋል፣ ይታዘዛቸዋል። ሁለቱም ከተናገሩ ይታመናሉ። ቃላቸው ይሰማል፤አንደበታቸው ይደመጣል።
አቶ ጉተማ ኩራ ከወይዘሮ ደብሪቱ ተፈራ ጋር ያቀኑት ጎጆ እንደነሱ በዕድሜ ገፍቷል። ሁለቱም ጥረው ግረው በጽናት ኖረውበታል። በግቢው ያሉት ከብቶች የቤቱ ሲሳይ ናቸው። በረከታቸው ለእርሻና ለማጀት እየዋለ ለሌሎችም ተርፏል።
ሸበቶው አዛውንት አቶ ጉተማ ለቤት ፣ለኑሯቸው ደከመኝን አያውቁም። ከጠንካራዋ ሚስታቸው ጋር ተጣምረው የቤታቸውን ጎዶሎ ይሞላሉ። ይህ ብቻ አይደለም፣ ጉተማ ሰው አክባሪና ቀና ናቸው። እሳቸው ካሉ የመንደሩ ሰብል በዝንጀሮ አይጠቃም። የእኔ ብቻ ሳይሉ ለሁሉም ይታዘዛሉ። በቅርብ የሚያውቋቸው መልካምነታቸውን ይመሰክራሉ፣ ታዛዥነታቸውን ይና ገራሉ።
ወይዘሮ ደብሪቱ በዕድሜ ገፍተዋል። ሁሌም ገበያ ደርሰው ሲመለሱ በታላቅ ድካም ነው። ቅንነታቸውን የሚያውቁ በርካቶች ጥንካሬያቸውን ያደንቃሉ። ለአንድም ቀን ሳያርፉ፣ ደፋ ቀና ማለታቸው የተለመደ ነው። ዘወትር ከከብቶቻቸው አይለዩም። በስራ ሲባትሉ ውለው ያነጋሉ። ማለዳ ከዕንቅልፍ ሲነቁ ውስጣቸው ለስራ ብርቱ ነው። ላሞችን አልበው፣ ከብቶች አሰማርተው ወደማጀት ሲመለሱ በተለመደ ጥንካሬ ነው።
ባልና ሚስቱ ከአብራካቸው ያገኙት የልጅ ፍሬ የለም። እንዲህ መሆኑ ግን ለፍቺ ዳርጎ ለመለያየት አልሰጣቸውም። ዓመታትን የዘለቁበት ሰፊ ጎጆ በፍቅር አከባብሮ፣ በመተሳሰብ አጣምሮ ዘመናቸውን አሳምሯል። ሕይወታቸውን አስውቦ፣ ዕድሜያቸውን አርዝሟል።
ጥንዶቹ አዛውንቶች ሕይወትን ለብቻቸው ሲኖሩት አልቆዩም፣ ካገኙት ሊያጋሩ ከቀመሱት ሊያቃምሱ፣ አስበው የዘመድ ልጆች ይዘዋል። በእነሱ ቤት ልኑር ያለ ካሻው ደርሶ ያሰበውን እንዲያገኝ መሶባቸው ሙሉ ነው። እነሱ፣ እንደ ልጅ ሊያዩት፣ እሱም እንደ እናት አባት ሊቆጥራቸው፣ ቤታቸው ክፍት ነው።
አቶ ጉተማና ወይዘሮ ደብሪቱ የዘመድ ልጆችን ሲያሳድጉ በሙሉ ፈቃዳቸው ነው። አንዳንዶቹ እነሱን መስለው ከእነሱ ዘልቀዋል። ገሚሶቹ ጥቂት ኖረው ዓመል አጥተው ርቀዋል። አዛውንቶቹ የሚኖረውን ሲቀበሉ የሚሄደውን ሲሸኙ ኖረዋል። አንዳንዶቹ ከእነሱ አድገው፣ለቁምነገር በቅተዋል። ትዳር ይዘው፣ ልጆች ወልደው ስመዋል።
ጌታቸው ከዘመዶቻቸው ልጆች አንደኛው ነው። እሱ ዓመታትን በዘለቀበት የአዛውንቶቹ ግቢ እንደልጅ ሆኖ አድጓል። ካላቸው በረከት እየተካፈለ፣ ከሰጡት ሲሳይ እየተቀበለ ሲኖር የጎደለበት አልነበረም። ጌታቸው ዕድሜው ከፍ እንዳለ ትዳር መያዝ ፈለገ። ይህ ሀሳቡ የገባቸው አሳዳጊዎች በይሁንታ ትዳሩን መርቀው በክብር ሸኙት። ሌሎች ከእነሱ ግቢ እየኖሩ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀዱ።
ጌታቸው ከግቢው ከወጣ ጀምሮ ሰላም አይሰማውም፤ ከአሳዳጊዎቹ እየተጋጨ ጠብ ያነሳል። ሰበብ እየፈለገ ፣ምክንያት እየፈጠረ ይጣላል። የዓመሉን መቀየር ያወቁ አንዳንዶች ምክንያቱን ይጠይቃሉ። አለኝ የሚለውን ቅሬታ እያነሳ፣ ተከፋሁ የሚለውን እውነት ይናገራል። መካሪዎቹ ቃሉን ሰምተው፣ የራሳቸውን ሀሳብ ይሰጣሉ። እስከዛሬ ከእነሱ የኖረውን ዓመት እየቆጠሩ፣ያሳለፈውን ጊዜ እያስታወሱ ይበጃል ያሉትን ያነሳሉ፡
እሱ ሰዎቹን ባገኘ ቁጥር ስለ ድህነቱ፣ ስላለበት ችግር ያወጋል። ሁሌም ከእነሱ ሲመክር መላ ያገኘ፣ ይመስለዋል። የሚሰጡት ምክር፣ የሚያሳዩት መንገድ መፍትሔ እንዳለው ያስባል። የጌታቸው መካሪዎች ካደገበት ወጥቶ በችግር መቆራመዱ ያሳስባቸዋል። እንዲህ መሆኑን እያነሱም ቁስሉን ሲነኩት ይውላሉ። የአሳዳጊዎቹን ሀብት ንብረት እየቆጠሩ፣ ከእጃቸው ባለው ሲሳይ መጠቀም እንዳለበት ይመክሩታል።
አሁን ጌታቸው ጠዋት ማታ ማሰብ ጎጆ ከወጣ ወዲህ ኑሮ እየተመቸው አይደለም። ይህን ሲያስብ ልጅነቱን የገፋበት፣ ኑሮውን የቀየረበት ግቢ ውል ይለዋል። ከአሳዳጊዎቹ ሳለ ችግር ይሉትን አያውቅም። ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ፣ ነበር። ከመካሪዎቹ ሲውል ያለፈውን ዓለም ያስታውሱታል። ንብረት መውሰድ፣ ከሀብት መጠቀም አለመቻሉን እያነሱ ያስቆጩታል።
ጌታቸው አንዳንዴ ብቅ እያለ አሳዳጊዎቹን ይጎበኛል። ግቢውን ሲቃኝ፣ ሰፊውን ቤት ሲመለከት የራሱን ሕይወት ያስባል። ከብቶቹ፣ በጎቹ፣ እርሻና ንብረቱ ያጓጓዋል። በቦታው ራሱን ተክቶ፣ ቤተሰቡን አስገብቶ በህልም ዓለም ይጓዛል። መለስ ብሎ ከራሱ ማጀት፣ ከትዳሩ ጓዳ ሲደርስ ሕይወት ያስጠላዋል። ድህነቱ ይብሳል፤ እጁ እያጠረ፣ ኪሱ እየሳሳ ይፈትነዋል። ይህኔ የአሳደጊዎቹን ዓለም ያስባል። እነሱን ከራሱ አወዳድሮም ኑሮውን ይለካል። ንዴት ይይዘዋል። በብስጭት እየተከዘ፣ ይውላል። በየቀኑ እንደነሱ መሆንን ፣ ያለችግር መዝለቅን ያልማል።
የጌታቸው መካሪዎች ሀብት ንብረት ማግኘት እንዳለበት መምከር ይዘዋል። እሱም ቢሆን በምክራቸው ከተስማማ ቆይቷል። ፍላጎቱ ሞልቶ የልቡ እንዲደርስ ይሆናል ያሉትን አስይዘውታል። በጉዳዩ ሲያስብበት ከርሞ ከውሳኔ ደርሷል። ያሰበውን ለማግኘት ፣የቻለውን ያደርጋል። ሁሉም መካሪዎች ሀብት ንብረት በዋዛ እንደማይገኝ አምነዋል።
አሳዳጊዎቹ የለፉበት፣ የደከሙበትን በቀላሉ አይሰጡ ትም። ጥሪታቸው የሕይወታቸው መልክ፣ የልጅነታቸው ወዝ ነው። ንብረታቸው የትዳራቸው፣ የአብሮነታቸው ፍሬ ነው። ይህን እውነት ሁሉም ያውቃል። እንዲያም ሆኖ ከእጅ ለማድረግ መላና ዘዴ አይጠፋም። በዚህ መላ ሁሉም አምነው ተስማምተዋል። ንብረት ለማግኘት፣ ሀብት ለመውረስ መንገዱ ቀላል አቋራጭ አለው።
ግንቦት 16 ቀን 2011ዓም
ምሽት ሁለት ሰዓት ከሰላሳ ሆኗል። ጌታቸው እና ሁለቱ ሰዎቹ ከተቃጠሩበት ቦታ በሰዓቱ ደርሰዋል። በእጃቸው የያዙትን ወደ ኋላ እየሸሸጉ፣ ዙሪያ ገባውን ይቃኛሉ። በስፍራው ማንም ዝር አላለም። አካባቢው በጨለማ ተውጧል። ገና በጊዜ ዝምታ የወረሰው ሰፊ ግቢ ጭር እንዳለ ነው።
በእሱ መሪነት ከአጥሩ ሲጠጉ የግቢው ውሾች ጨኸት ተቀበላቸው። በጭርታ የቆየው ዝምታ ፈጥኖ ተሰበረ። ይህኔ ጌታቸው ጠጋ ብሎ ውሾቹን አባበለ። ቀድመው ስለሚያውቁት ጭራቸውን እያወዛወዙ፣ በዝምታ ቀረቡት። ሁለቱ ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደውስጥ አለፉ።
የውሾቹን ድንገቴ ጩኸት የሰሙት አቶ ጉተማ የቤቱን በር ከፍተው ወደውጭ ወጡ። አሁን ውሾቹ እየጮሁ አይደለም። እየተጠራጠሩ ጆሯቸውን ጥለው አዳመጡ። ኮሽታና ድምጽ የሰሙ ቢመስላቸው ደጋግመው ማነው? ማነው? ማለት ጀመሩ። አስቀድሞ ጥግ የያዘው ጌታቸው ጉተማ አጠገቡ እስኪጠጉለት ጠበቀ። እንዳሰበው ሆነለት። ሽማግሌው ጀርባቸውን እንደሰጡ ቀረቡት። ጊዜ አላጠፋም። በያዘው መጥረቢያ አንገታቸውን መቶ ጣላቸው። በዚህ አልበቃም። ወዲያው ስሜ ተስፋዬ የተባለው መጥረቢያውን አንስቶ ደገማቸው።
እንዳይነሱ የወደቁትን አዛውንት ሲያዩ የመጀመሪያው ሥራ መጠናቀቁ ገባቸው። ቀጣዩን ለመከወን ኃላፊነት የተሰጠው ፈቃዱ የተባለው ተባባሪ ሮጦ ወደ መኖሪያ ቤቱ ገባ። በሩን ከፍቶ ማጀት ከመዝለቁ እመት ደብሪቱን አገኛቸው። ማንነቱን እስኪጠይቁት አልጠበቀም። ፈጥኖ አፋቸውን አፈነ፣ ትንፋሻቸውንም አሳጠረ። ወይዘሮዋ ጥቂት ታግለው ተሸነፉ። ለመነሳት አልሞከሩም።
አሁን የያዙት እቅድ በታሰበው መንገድ ተጠናቋል። ምሽቱ ሳይገፋ ቀጣዩን ለመፈጸም መፍጠን አለባቸው። የአዛውንቶቹን አስከሬን እየጎተቱ ከግቢው ማሳ ሲወስዱ መቅበር እንዳለባቸው አውቀዋል። ይህን ከማድረጋቸው በፊት አተላ ማግኘት አለባቸው። በጉድጓዱ ዙሪያ አተላውን ከደፉ አስከሬኑን በቀላሉ ጅቦች ያገኙታል። ከልምድ ይህን የሚያውቁት ሶስቱ ሰዎች ሟቾቹን እየጎተቱ ካዘጋጁት ጉድጓድ ከተቷቸው ። ዙሪያውን አተላ ደፍተውም አፈር ከላዩ መለሱ።
የፖሊስ ምርመራ…
ማግስቱን በግቢው ዙሪያ ሲጨነቁ ያረፈዱት ጎረቤቶች ወደውስጥ ሲዘልቁ ያዩትን እውነት ለፖሊሶች አመለከቱ። መረጃው የደረሰው የጥዬ ወረዳ ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ምርመራውን ጀመረ። በዕለቱ በአካባቢው ያገኛቸውን ነዋሪዎች ለእማኝነት ይዞም ጥልቅ ፍተሻውን ቀጠለ።
ፖሊስ ወንጀሉን ማን ፈጸመው የሚለውን ለማወቅ በራሱ ዘዴ ምርመራውን ቀጠለ። የወረዳውን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሲሳይ ካሳዬን ጨምሮ መርማሪ ፖሊስና የወንጀል መካላከል ቡድን አባላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጡ። ወንጀሉ ያለመረጃ የተፈጸመ በመሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻው ሆነ።
የምርመራው ቡድን አባላት እያንዳንዱን መረጃ በማስረጃ ለማስደገፍ ጥረታቸውን ቀጠሉ። ከኅብረተሰቡ የተውጣጣ ሰባት አባላት ያሉት ቡድንም ሌት ተቀን ምርመራውን አፋጠነ። ሁሉም ነዋሪ በቀናዎቹ ባልና ሚስቶች የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት አሳዝኖታል። ውሎ አድሮ ውስብስቡ ቋጠሮ ሊፈታ ምልክቶች ታዩ። ወንጀሉ የተፈጸመው በቅርብ ሰዎች ሊሆን እንደሚችል የጠረጠሩ በርካቶች ማሳያዎችን አቀረቡ። ፖሊስ ጉዳዩን በዋዛ አልተወውም። ተጠርጣሪውን አቅርቦ በጥያቄ አጣደፈው።
ጌታቸው ያደረገውን አልደበቀም። በዕለቱ ከነ ግብረአበሮቹ ወደግቢው ዘልቆ አሳዳጊዎቹን በግፍ እንደገደላቸው አመነ። በተቀበሩበት ጉድጓድ ዙሪያ የተደፋው አተላ ጅቦችን ለመጥራት የታሰበ ዘዴ እንደነበርም ተናገረ። ፖሊስ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመ ጠየቀው። ሀብት ንብረታቸውን፣ ወስዶ በውርሱ ለመጠቀም እንደነበር አልደበቀም።
ፖሊስ ሁለቱን ግብረአበሮች ጠርቶ ጠየቀ። ፈቃዱ ኩራ ሁሉንም ሳይክድ አመነ። ስሜ ተስፋዬ የተባለው ተከሳሽ ግን በወንጀሉ ፈጽሞ እንደሌለበት ምሎ ተገዝቶ ካደ። ፖሊስ የሁሉንም ቃል በጥንቃቄ አስፍሮ ለቀጣዩ ክስ መዝገቡን ወደ ዓቃቤ ህግ አሳለፈ።
ውሳኔ…
ሐምሌ 12 ቀን 2011 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ ጌታቸው ጉታና በግብረአበሮቹ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ አንደኛው ድርጊቱን ባለማመኑ በይደር ሲያቆው፣ በሁለቱ ላይ ግን ብይኑን አሳለፈ ። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ሁለቱ ተከሳሾች እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ይቀጡልኝ ሲል ፍርዱን ሰጠ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014