በፖሊስ ጣቢያ እየተጣደፈች የገባችው ወይዘሮ ፊቷ ላይ ግራ መጋባት ይነበባል:: ይህን ያዩ የቢሮው ፖሊሶች በትህትና ተቀብለው ወንበሩን አመላከቷት:: ወይዘሮዋ ጥቂት እንደተረጋጋች ጉዳይዋ ምን እንደሆነ ተጠየቀች::
ከጥቂት ዝምታ በኋላ የተጨነቀችበትን ግራ ያጋባትን ጉዳይ ማብራራት ጀመረች:: ተረኛው ፖሊስ የወይዘሮዋን ቃል በጥንቃቄ እያዳመጠ መመዝገብ ጀምሯል:: ሴትየዋ ከቀናት በፊት የሰባት ዓመት ሴት ልጇ ከቤት እንደወጣች ያለመመለሷን እያስረዳችው ነው::
ሁኔታውን የሰሙ የፖሊስ አባላት በሆነው ሁሉ ደነገጡ:: አንዲት የሰባት ዓመት ህጻን ከቤት ወጥታ ያለመመለሷ እውነት በእጅጉ አስደነገጣቸው:: ፖሊሱ ከአመልካችዋ ወይዘሮ የተቀበለውን ቃል በአግባቡ መዝግቦ እናትን በሚችለው ሁሉ ማጽናናት ያዘ:: ጉዳዩ በቀላሉ የማይታይና አሳሳቢ ነው:: ህጻናት ድንገት ከቤት ሲጠፉ የሚያጋጥማቸው አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል:: ይህ እውነት የገባቸው የፖሊስ አባላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጡ::
ከደሴ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ጋር በመጣመር ፍለጋውን ማጣደፍ እንደሚኖርባቸው ወሰኑ:: የጣቢያው ፖሊሶች እናትን በማጽናኛ ቃል ሲሸኙ የልጇን ጉዳይ ችላ እንደማይሉት ቃል በመግባት ነበር::
ፍለጋ …
ፖሊስ ውሎ አላደረም:: የህጻኗ መሰወር ሪፖርት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ይበጁኛል የሚላቸውን መረጃዎች ሰበሰበ:: በማግስቱ ወላጅ እናቷን ይዞ፣ ጎረቤት ወዳጅ አስከትሎ ፍለጋውን ጀመረ:: የደሴ ከተማ አስተዳደር ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። ወዳጅ ዘመድ ጎረቤቱ ተጨንቀዋል:: ልጅን ያህል ነገር ከቤት ወጥታ የመቅረቷ ጉዳይ እያሳሳባቸው ነው::
ሁሉም እናትን ለማጽናናት፣ ‹‹አለንሽ›› ለማለት ተቸግረዋል:: እውነታው ከቃላት በላይ ቢሆንባቸው ብዙ አወጉ፣ ተወያዩ መፍትሄ ያሉትን አማራጭም ዘየዱ:: ዝምታን ያልፈለጉት ወዳጅ ዘመዶች የህጻን በፀሎት ብርሃኑን ፎቶግራፍ አሳትመው በየቦታው ለጠፉ:: የተጻፈውን ለሚያዩና መጥፋቷን ለሚሰሙ ሁሉ በተማጽኖ ‹‹አፋልጉን›› ሲሉ አወጁ:: የልጅቷን ምስልና ሁኔታ ያዩ መንገደኞች በሀዘኔታ ደረታቸውን ደቁ:: እሷን መሰል ህጻን ባዩ ቁጥር በዓይናቸው እየተከተሉ በጥርጣሬ እየቃኙ ማጣራት ቀጠሉ:: ምርመራውን የያዙት የፖሊስ አባላት ዓይንና ጆሯቸው አላረፈም::
ሁሉም የጠፋችውን ህጻን ከናፈቀቻት እናቷ ሊያገናኙ መትጋት ይዘዋል:: የምርመራና የክትትል ቡድኑ ከአካባቢው ሰዎች ጋር ተጣምሮ እየሰራ ነው:: በየጊዜው የሚገኙ ጥቆማዎች አይታለፉም‹‹በየአፍታው የሚሰሙ መረጃዎች አይናቁም:: ፖሊስ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጥርጣሬና በጥንቃቄ መንቀሳቀስ ጀምሯል:: እስካሁን ይህ ነው የሚባል መረጃ አልተገኘም:: ማንም ግን ተስፋ አልቆረጠም:: ትንሽዬዋን፣ ቆንጅዬዋን ታዳጊ በፀሎት ብርሃኑን ከእጁ ሊያስገባ እየጣረ ነው::
ከስድስት ዓመት በፊት …
አበባ ሙህዬ የአንድ ዓመት ልደቷን ካከበረች ቀናት ያስቆጠረች ህጻን ልጇን እንደያዘች ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቀች:: ከዓመታት በፊት አብሯት ከነበረው የልጇ አባት ጋር በአብሮነት አልቆየችም:: ያለ ስምምነት የቆየው ጎጆ በፍቺ ሲዘጋ ትዳሩ ከመፍረስ አልዳነም:: ባልና ሚስቱ ሲለያዩ አበባ ከህጻን ልጇ ጋር ቀረች:: አሁን ደግሞ ከሌላ ወጣት ጋር መግባባት፣ መቀራረብ ጀምራለች::
አቡበከር መሐመድ የከባድ መኪና ሾፌር ነው:: አበባን ካወቃት ጀምሮ በትዳር እንዲጣመሩ ፍላጎቱ ሆኗል:: ይህ ስሜት የእሱ ብቻ አልሆነም:: ሀሳቡ የሷም ጭምር ሆኖ በአንድ ጎጆ መኖር ጀምረዋል:: አባወራው የአበባን ልጅ እንደ ልጁ ተቀብሏል:: ህጻንዋ ‹‹የእንጀራ አባት›› የሚለው ትርጉም የገባት አይመስልም ::
አቡበከርን በፍቅር እያየች እንደ አባቷ ትቀርበዋለች:: በአብሮነት የተጀመረው የጥንዶቹ ህይወት ክፉ ደጉን እየተሻገረ ስድስት ዓመታትን ቆጥሯል:: አልፎ አልፎ የሚያጋጫቸው አለመግባባት በቅያሜ ቀናትን ይሻገራል::
በኩርፊያ ሲከርሙ ሆዳቸው በቅያሜ ይሻክራል:: በአጋጣሚ መነጋገር ሲጀምሩም ዳግም የሚያጋጫቸው ሰበብ አይጠፋም:: ችግሩ ሳይፈታ ሌላ ችግር ይደረባል:: በእርቅ አይሰነብቱም፣ ዳግም ተጣልተው ፊትና ጀርባ ይሆናሉ ይህ እውነት የባልና ሚስቱ የየዕለት መገለጫ ሆኗል::
በጎጇቸው ሰላም ይሉት የለም:: የትዳራቸው መሰረት ተናግቷል:: እነሱን የሚያስታርቅ፣ ጠባቸውን የሚያሸንፍ ሽማግሌ ጠፍቷል:: ከቀናት በአንዱ ቀን የጥንዶቹ እህል ውሃ ሊቋጭ ግድ ሆነ:: አቡበከርና አበባ ከነአካቴው ተለያዩ:: ትናንት በፍቅርና ሰላም የደመቀው ጎጆ በሰላም ማጣት ሰበብ ተዘጋ::
ትዳር ያሰረው ህይወት መተሳሰብ ያጸናው የስድስት ዓመታት አብሮነት በመለያየት ተደመደመ:: አበባ የቀድሞው ህይወቷ ተመለሰ:: የሰባት ዓመት ህጻን ልጇን ይዛ ከብቸኝነት ዓለም ገባች::
አሁንም ፍለጋ…
ህጻን በፀሎት ብርሃኑን የበላ ጅብ አልጮኸም:: አሁንም ወዳጅ ዘመድ ተጨንቋል:: በከተማው አራት አቅጣጫ የተለጠፈው አሳዛኙ ፎቶግራፍ ለብዘዎች ሰላም አልሰጠም:: ምስሉን ያየ ሁሉ ከልቡ ይረበሻል::
የፖሊሶች ዓይን ጆሮዎች ስራ አልፈቱም:: መረጃዎችን ለማግኘት የሚያነፈንፉ ብርቱዎች በየአቅጣጫው ተሰማርተዋል:: ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድንገት ስለመሰወሯ ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ በፍለጋ እየባዘነ ነው:: አሁንም አንዳች የረባ መረጃ የለም:: ህጻኗን ‹‹አይተናል፣ ስለሷ ሰምተናል›› የሚል ጠቋሚ ሳይገኝ ቀናት ተቆጥረዋል::
ጠቋሚዎቹ… አንድ ቀን ረፋድ ከፖሊስ ጣቢያው የደረሱ ሰዎች ከአንድ ስፍራ አይተናል ስላሉት ጉዳይ ለፖሊሶች አስረዱ:: ጠቋሚዎቹ የሰጡት መረጃ የሚናቅ አልሆነም:: ፖሊስ ሰዎቹ አየነው ያሉት አጠራጣሪ ጉዳይ የት እንደሚገኝ ጠየቀ:: ከሰዎቹ በቂ መረጃ ተቀብሎም ቦታው እንዲቃኝ፣ እንዲፈተሸ የምርመራ ቡድን አዋቀረ:: አሁን የፖሊስ ምርመራ ቡድን ሰዎቹ ከጠቆሙት ስፍራ ተገኝቷል:: የተባለው እውነት ሆኗል:: ቡድኑ ስፍራውን በአግባቡ አጥሮ ጥንቃቄ የተመላበት ምርመራ ለማድረግ ተዘጋጅቷል::
መርማሪው ኃይል ከተባለው ቦታ ሲደርስ አጠራጣሪውን የማዳበሪያ ቋጠሮ ከስፍራው አግኝቷል:: ፖሊሶቹ ጥንቃቄ በሞላው እርምጃ ጠጋ ብለው ተመለከቱ:: በተቋጠረው ማዳበሪያ ላይ በግልጽ የሚታየው ነገር ደም መሆኑን ለማረጋገጥ አልተቸገሩም:: የምርምራ ቡድኑ በተቋጠረው ማዳበሪያ ውስጥ ያለውን ምስጢር ለማወቅ ጥንቃቄ የተሞላበት ፍተሻ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል:: በውስጡ የሚገኘው እውነት ያለአንዳች ስህተት በበቂ መረጃ እንዲረጋገጥ ሙያዊ እገዛቸው ያስፈልጋል:: ይህን ጠንቅቀው የሚያውቁት የምርመራ ቡድኑ አባላት አስፈላጊውን ሁሉ አድርገው ቋጠሮውን መፍታት ጀመሩ::
የቋጠሮው ምስጢር …
ፖሊሶቹ ጠብቆ የታሰረውን የማዳበሪያ አፍ ፈተው ሲጨርሱ የተመለከቱትን አስደንጋጭ ነገር እንደዋዛ መሸፈን አልቻሉም:: ሁሉም በድንጋጤ ተውጠው ክው እንዳሉ ቀሩ:: የማዳበሪው ቋጠሮ ሲፈታ የትንሽዬዋ ህጻን አስከሬን ብቅ አለ:: ለደቂቃዎች በዝምታ የተዋጡት የምርመራ ቡድኑ አባላት በስፍራው የከበቧቸውን ተመልካቾች ገለል አድርገው ምርመራቸውን ጀመሩ:: ለቀናት ደብዛዋ የጠፋውን የህጻን በፀሎት ብርሃኑን መጨረሻ ያረጋገጠው ፖሊስ አስከሬኑን በጥንቃቄ ሲመረምር ትናንሽ እጆቿ በዛንዚራ የጨርቅ ቅዳጅ ጠብቀው መታሰራቸውን አስተዋለ::
ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ወደፊቷ ቀረብ ብሎ የደማውን የአካል ክፍል አጤነ:: የህጻኗ አፍና የአፍንጫዋ አካባቢ በጥፍር የመቧጨር ምልክት አለው:: ፖሊስ ይህን ለመገመት አልተቸገረም:: ማዳበሪያው እንደተቋጠረ አስከሬኑ የድመት ጥቃት አጋጥሞታል:: ተጨማሪ ምርመራዎች እንደተጠናቀቁ የሟችን በድን ወደ ሆስፒታል አድርሶ ወላጅ እናትን ለተጨማሪ ጥያቄዎች አስጠራ::
እናት ወይዘሮ አበባ የጠፋችባት ልጇ መጨረሻ በዚህ መልኩ መቋጨቱ ከሀዘን ጥሏታል:: ፊቷን እየነጨች ፣ ከመሬት እየተንከባለለች ታለቅሳለች:: ሁኔታዋን ያየ የሰማ ሁሉ አብሯት እያዘነ ያነባል:: ፖሊስ ከሀዘኗ ጥቂት እስክትረጋጋ ጠብቆ በግድያው የምትጠረጥረው ሰው ይኖር እንደሆን ጠየቃት:: አበባ በአንገቷ የሚወርደውን ትኩስ ዕንባ ከፊቷ እየሞዠቀች በትካዜ መናገር ጀመረች:: መርማሪው የእናት አበባን ቃል በጥንቃቄ እየመዘገበ በደንብ እንድታወራ፣ እንድትናገር ይገፋፋታል:: ከንግግሯ መሀል ደጋግማ የጠራችውንና በወንጀሉ ዋንኛ ተጠርጣሪ ያደረገችውን ግለሰብ ስም አድምቆ ጽፏል:: የሟች እናት በእርግጠኝነት የወንጀሉ ፈጻሚ ነው ያለችው በቅርቡ በፍቺ የተለየችውን አቡበከር መሐመድ ሆኗል::
ወይዘሮዋ ከግለሰቡ ጋር በትዳር ስድስት ዓመታትን አሳልፋለች:: ያም ሆኖ ባልዋ ለጭካኔ እንደማይመለስ ተናግራለች :: ማንም እንደሚያውቀው ሰውዬው ለህጻን በፀሎት የእንጀራ አባቷ ነው:: አበባ ባሏ ለልጇ በስጋ ስለማይወልዳት ግድያውን እሱ እንደፈጸመው እርግጠኛ ሆናለች:: ፖሊስ ቃሏን ተቀብሎ ተጠርጣሪውን ማሰስ ጀምሯል:: የደሴ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሦስት ነዋሪዎችና ጉዳዩን የሰሙ ሁሉ ስሜታቸው ከሀዘን ተሻግሯል:: ነዋሪው በህፃኗ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ለቁጣ እየጋበዘው ለበቀል እያነሳሳው ነው:: ግለሰቡን ባለበት ለመያዝ የፎከሩ በርካቶች ክፉ ነገር ደግሰዋል:: ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ቅጣቱን ሊሰጡት፣ ስቃዩን ሊያሳዩት የሚሹት በርክተዋል:: እናት አበባ በትካዜ እንደታጠፈች፣ በሀዘን ልብስ እንደጠቆረች የልጇን እንጀራ አባትና ገዳይ የመገኛ ቦታ ጠቁማለች::
ግለሰቡ የከባድ መኪና ሾፌር ነው:: ከከተማ መውጣቱን የጠረጠሩ ፖሊሶች መመለሻውን ጠብቀው ከእጅ ሊያስገቡት ተጣድፈዋል:: የነዋሪው ቁጣ ተቀጣጥሏል:: የአካባቢው ሀዘን በርትቷል:: ነዋሪው ግለሰቡ በፖሊስ እጅ ከመያዙ በፊት ለማግኘት ፍለጋ ጀምሯል:: አብዛኞቹ ጥቃት ለማድረስ እየዛቱ እየፎከሩ ነው:: ይህን ያወቀው ፖሊስ ተፈላጊው በፈላጊዎቹ እጅ ቀድሞ እንዳይወድቅ በጥንቃቄ ተንቀሳቀሰ:: እንደታሰበው ሆኖ ተጠርጣሪው አቡበከር ከሚያሽከረክረው ሲኖትራክ ጋር ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ በቁጥጥር ስር ዋለ:: አቡበከር በድንገት ከፖሊስ እጅ መውደቁ አስደንግጦታል:: ከካቴና የገባው ተፈላጊ የሚጠየቀውን ለመመለስ፣ የሚባለውን ለመስማት ዘግጁ አልሆነም:: ደጋግሞ ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ይናገራል:: እየጮኸ ፣ እያለቀሰ ሁኔታውን ሊያስረዳ ይሞክራል:: ዕንባውን ያዩ ሁሉ ተናደዱበት:: ሁኔታው፣ ክህደቱ አበሳጫቸው:: ፖሊስ ቃሉን ተቀብሎ ወደ ማረፊያ ሲሸኘው የአቡበከር ለቅሶ አልተቋረጠም::
የተቃውሞ ሰልፍ…
የደሴ ከተማ ነዋሪ ህጻኗ ተደፍራ እንደተገደለችና መላ አካሏ እንደተቆራረጠ ሰምቷል:: ይህ ወሬ በአገሩ ተቀባብሎ የከፋ ቁጣን ቀስቅሷል:: የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ‹‹ነግ በኔን›› ፈጥሮም ህዝቡን ለተቃውሞ ሰልፍ አጠራርቷል:: አሁን በሺዎች የሚቆጠሩ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የህጻን በፀሎት ብርሃኑን ፎቶግራፍና መፈክሮችን አንግበው አደባባይ ወጥተዋል:: የሟች እናት ‹‹ፍትህ ይሰጠኝ ፣ አገር ይፍረደኝ›› ስትል አምርራ እያለቀሰች ነው:: ይህን ያዩ፣ የሰሙ ሁሉ ሀዘናቸው በርትቷል::
አብዛኞቹ ንዴታቸው አይሏል:: የዛን ቀን በርከት ያሉ ወጣቶች እየጮሁ ተጠርጣሪው ወደሚገኝበት ጣቢያ ደረሱ:: የግቢውን ዙሪያ ገባም ከበቡ:: በታላቅ ተቃውሞ ተውጠው ህጻንዋን ደፍሮ ህይወቷን የነጠቀው የእንጀራ አባት ተላልፎ እንዲሰጣቸው ጠየቁ :: ፖሊስ በህግ ቁጥጥር ስር የዋለን እስረኛ አሳልፎ እንደማይሰጥ አስታወቀ:: ወጣቶቹ ምላሹን በቀላሉ መቀበል አልቻሉም:: በስፍራው የተገኙት የከተማው ከንቲባ ጨምሮ ሁኔታውን በአግባቡ ለማስረዳት ሞከሩ:: የሰማቸው፣ ያመናቸው የለም:: ከፖሊሶች ጋር ውዝግቡ ቀጠለ:: ወጣቶቹ ጣቢያውን በድንጋይና ዱላ መደብደብ ጀመሩ:: ግለሰቡን እንስቀል፣ እንቁረጥ ሲሉም ጠየቁ:: ፖሊስ ሃሳቡን ተቃውሞ፣ ጥቃቱን ተከላክሎ ወጣቶቹን ከአካባቢው በተነ::
ዳግም ምርመራ…
ፖሊስ አሁንም ሀዘንተኛዋን እናት እያጽናና ከቤቷ ተገኝቷል:: ለተጨማሪ ምርመራዎችም ወደ ጓሮ ዞሯል:: ሁሉንም በጥንቃቄ የሚፈትሹት የምርመራ ቡድኑ አባላት በድንገት ዓይናቸው ከአንድ ቅዳጅ ጨርቅ ላይ አረፈ::
የቢንቢ መከላከያ ቁራጭ ዛንዚራ ነው:: የፖሊሶች ትውስታ ወደ ኋላ ተመለሰ:: የህጻንዋ እጅና እግር ከታሰረበት ቁራጭ ጋር አንድ አይነት ነው:: ፖሊሶቹ ፈጠን ብለው እናትን ስለቀሪው ቅዳጅ ጠየቋት:: አስቀድማ እንደጣለችው ተናገረች:: ሁሉም በዓይናቸው ተናበቡ:: ጨርቁ ተጣለበት ከተባለው ስፍራ ሲሄዱ ቀሪውን ቅዳጅ አገኙ:: አሁን የምርመራው አቅጣጫ ተቀይሯል:: ጨርቁ ተገኝቶ አበባ ስትጠየቅ ከቀናት በፊት እንደ እናት ልትቀጣት ስትሞክር ድንገት በእጇ ላይ እንደቀረችባት አምናለች:: ከዛ በላይ በልጇ ላይ የፈጸመችውን ግድያ መደበቅ አልተቻላትም:: ፖሊስ ቃሏን ተቀብሎ በቁጥጥር ስር ሲያውላት ያለጥፋቱ የታሰረውን አቡበከር መሐመድን በይቅርታ ከእስር አሰናበተ::
የኢንስፔክተር ደሳለኝ ሙሉቀን የደሴ ከተማ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ የሥራ ሂደት መሪ ናቸው:: ፖሊስ ወንጀሉን በተለያዩ ማስረጃዎች አስደግፎ መዝገቡን ለዓቃቤህግ ክስ ማሳለፉን ተናግረዋል::
ውሳኔ…
የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የደቡብ ወሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልጇን ገድላ ንጹህ ለመምሰል በሞከረችው ወላጅ እናት ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል:: ፍርድ ቤቱ ግለሰቧ በገዛ ልጇ ላይ በፈጸመችው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል እጇ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ትቀጣልኝ ሲል ወስኗል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014