የቋንቋ ምሉዕነት ሲፈተን፤
“ማንኛውም ቋንቋ በራሱ ተናጋሪዎች ዐውድ ምሉዕ ነው:: ማኅበረሰቡም ባህሉን፣ ወጉን፣ እምነቱን፣ አካባቢውን፣ ደስታውንና ሀዘኑን፣ ምሬቱንና ብሶቱን እና አጠቃላይ መስተጋብሩን ለመግለጽ ቋንቋው ራሱን ችሎ ለማግባባት በቂ ነው::” የሚለው ሳይንሳዊ ብያኔ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ክፉኛ የተፈተነ ይመስላል::
መፈተን ብቻም ሳይሆን ቋንቋዎቻችንን ቋንቋ ያሰኙት ውሱን ሆሄያትም ተባብረውና ተደጋግፈው ቃላት በመመስረት መከራችንን ለመግለጽ ፈተና ላይ እንደወደቁ በሚገባ ተረድተናል:: በግፈኞች ድርጊት የሚፈተነው አገርና ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ስሜትንና እውነታን አጥርቶ ለመግለጽ ለካስ ቃላትም ግራ ተጋብተው ይፈተናሉ ወደ ማለቱ ድምዳሜም እየደረስን ነው:: እናብራራው::
አሸባሪው ሕወሓት በወረራቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የፈጸማቸውን እኩይ ተግባራትና የጭካኔ ድርጊቶች በሁሉም አቅጣጫና መስመር በምልዓት ተገላልጦ ለማሳየት የተሞከረ ሊመስለን ይችላል:: በፍጹም በበቂ ሁኔታ አልተገለጸም:: የሚዲያ ተቋማት በድምጽ፣ በጽሑፍ፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በፎቶግራፍ ያደረሱልን የተወሰነውን እውነታ ቆንጥረው ነው::
ጋዜጠኞቹ ራሳቸው የግፍ ትራዤዲ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ተገኝተው ያዩትንና የሰሙትን መዓት በቃላት መግለጽ ተስኗቸው ሲቸገሩ አስተውለናል:: የዓይን ምስክሮችና የጉዳቱ ሰለባዎች የነገሩንም ኢምንት የሚሰኘውን ክስተት ብቻ ነው::
በተቃወሰ ስሜት (trauma) መሰቃየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይግለጹት ቢባልስ በምን የቋንቋ ብርታት ሊያብራሩት ይችላሉ? የተፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊቶች ከቃልም ሆነ ከምስል ገላጭነት እጅግ ከፍ ብለው የገዘፉ ናቸው የምንለው ስለዚሁ ነው:: ጭካኔ ዓይነት አለው:: ሁሉንም የግፍ ዓይነት ለመግለጽ ግን ቋንቋ አቅመ ቢስ ነው::
አገሬ ከአሁን ቀደም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ኃይላት እጅጉን በርካታ የሚሰኙ የመከራ ዶፍ ቢዘንብባትም ሳትንበረከክ በአሸናፊነት ተወጥታ ደማቅ ታሪክ አስመዝግባለች:: የአሸባሪው ሕወሓትን መሰል አሰቃቂ የግፍ ዓይነቶችን በተመለከተ ግን ቀደም ባሉት ዘመናት አይደለም በእኛ በሌሎች አገራትም ቢሆን ስለመፈጸማቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም::
ዕድል ይሉት ክፉ አጋጣሚ ረድቶት የወንበዴነት ባህርይውን ሳይለውጥ የመንግሥትን ሥርዓት ተቆጣጥሮ በዋነኛነት ሲመራ የነበረው ቡድን “ሕዝቤ፣ ሀገሬ” እያለ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር ኢትዮጵያን ወክሎ ለሃያ አምስት ዓመታት ያህል እንዳሻው እየፋነነና እየቀላመደ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር ሲበደር፣ ልማት አለማሁ በማለት ሲፎክር፣ እርዳታ ተቀበልኩ፣ ዲፕሎማሲውን ዘወርኩ እያለ ሲዘባነን እንዳልነበረ ሁሉ በበረሃ ውስጥ ሲዶልተው የኖረውን የኪዳን ቃሉን አልረሳ ብሎ አገር ለማጥፋት ሞራሉን አበከተ፤ የህሊናውን ዳኝነትም ወደ ጎን አድርጎ የማይዳፈሩትን ተዳፈሮ ተዋረደ::
በዓለም አቀፍ ታላላቅ መድረኮች ላይ ሲቀመጥ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፊቱ አስቀምጦ ታላቅ ሉዓላዊት አገር “እየመራሁ” ነው በማለት ከመንግሥታት ጋር ሲደራደርና ሲከራከር የመኖሩን ትዝታና ታሪክ አሽቀንጥሮ በመወርወር ያችንው “መርቺያት ነበር” የሚላትን አገር ካላንኮታኮትኩ እንቅልፍ አይወስደኝም ብሎ በመማል ንጹሐን ዜጎችን በመጨፍጨፍና አስከሬናቸውን ሰብስቦ በማቃጠል ምድሪቱን ከል አለበሰ:: የምስኪን ወገኖቻችን እምባ እንደ ዝናብ እንዲንዠቀዠቅ በአረመኔያዊ ተግባሩ አረጋገጠ:: የግለሰቦችንና የአገርን ሀብት እያጋየ የትዕቢት ቆፈኑን አሟሟቀበት::
ያሻውን እየዘረፈም ለትግራይ ክልል በገጸ በረከትነት እነሆ በማለት ግዳዩን ጥሎ አሳየ:: ደብቆ ያኖረውን የጭካኔ ጭንብል ከቀበረበት አውልቆ ሕዝብ ሲጨፈጭፍ፣ ሲያርድና ሲያፈናቅል፣ ሰራሁት ያለውን መሠረተ ልማት ሲያወድምና ሲያፈርስ፣ አልበቃ ብሎትም በመቶ አስራ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ጦር ሰብቆ ሲዘምት ምን ተሰማው ከማለት ይልቅ ምን ስም እንስጠው ብሎ ቋንቋችንን መሞገቱ ይቀላል:: “ወደፊት ግፉ!” እያለ በመንዳት ያሰማራቸው ጀሌዎቹ ሕጻናትን፣ እህቶችን፣ እናቶችንና በድንግልናና በንጽህና ራሳቸውን ጠብቀው በፈጣሪያቸው ፊት እየቃተቱ ኑሯቸውን ገዳም ውስጥ ያደረጉ ደናግል መነኩሲቶችን ሳይቀር እንዲደፍሩ ማጀገኑ ጭካኔ ወይንም ኢ ሰብዓዊነት ተብሎ ብቻ የሚወገዝ አይደለም::
ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት በብዕር ጉልበት የሩቅ ተራኪ ሆኖ ለማሳየት ይቅርና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ራሳቸው የወደቀባቸውን ይህንን ክፉ በላ አስረዱ ቢባሉ ለገለጻ መቸገራቸው አይቀርም:: ይሞከርስ ቢባል ከቡሆ ዕቃ እስከ ማንኪያ፣ ከሌማት እስከ ድስት፣ ከኪዮስክ እስከ ባንክ፣ ከፋብሪካ እስከ ጤና ተቋም፣ ከትምህርት ቤት እስከ ቤተ እምነት፣ ከመንግሥት ተቋማት እስከ መሠረተ ልማት ማቃጠላቸውን፣ ማውደማቸውንና ማብከታቸውን እንደምን በስዕላዊ ገለጻ መተረክ ይቻላል? ይከብዳል::
በምስኪን የገበሬ ማሳ ላይ እሳት መልቀቅ፣ በመስክ ላይ በተሰማሩ ዱዳ እንስሳት ላይ አረር እያርከፈከፉ መፍጀት፣ ከእንስሳ ባህርይ የማነስ ምልክትነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የግፉን ክብደት በቋንቋ አሳክቶ ሙሉውን ሥዕል ለማሳየት በጭራሽ የሚሞከር አይደለም::
ቋንቋም ይደኸያል፣ ቃላትም ያጥጣሉ ማለት ይሄኔ ነው:: በከንቱ ዓላማና በተበለጥን ቅንዓት፣ በሥልጣን መንገብገብ፣ በእንሻላለን ክፉ እብሪት ተወጥረው የትዕቢታቸው ጽዋ ጢም ብሎ ገንፍሎ ስላሰከራቸው እነሆ ቋንቋ ሊገልጸው የተቸገርንበትን ግፍ ሲፈጽሙ ወራትን አሳለፉ:: ደማቸው በከንቱ የፈሰሰው የንጹሐን ዜጎች ነፍስ ወደ ቅን ፈራጅ አምላክ እየጮኸ እንደሚፋረድ እንደምን “የሃይማኖት አባቶቻቸው” አላስተማሯቸውም? አልመከሯቸውም? እንደምንስ የጽዮን ማርያም ተሳላሚና የነጃሺ መስጊድ ሰጋጅ እናቶቻቸው አልገሰጹዋቸውም? የመከራውን ዓይነትና ብዛት መልክ አሲዞ ለመተረክ በእጅጉ ያዳግታል::
የቋንቋ ምሉዕነት ሲማሩት እንጂ በተግባር ሲኖሩት ለካንስ ጎዶሎ ነውና? እንግዲያውስ የንጹሐንን ደም በማፍሰሳቸው የሚደርስበቸውን የፈጣሪ ቅጣት በተመለከተ የቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረታዊ አስተምህሮ ከአሁን ቀደም አልሰሙ ከሆነ ለተመኙት ሲኦል ዝግጅት ሊያግዛቸው ስለሚችል እነሆ ካቃጠሏቸውና ካወደሟቸው ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ ጥቅስ መዘን እናስታውስ::
“በግፍ የታረዱ ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች በታላቅ ደምጽ እየጮኹ ቅዱስና እውነተኛ አምላክ ሆይ እስከ መቼስ አትፈርድልንም? ስለ ፈሰሰው ደማችንስ ስለምን አትበቀልልንም? እያሉ ቀንና ሌሊት ወደ ፈጣሪ ዙፋን ይጮኻሉ”፤ (ራእይ 6፤9 -10)::
እርግጥ ነው በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና ሕዝብ መርቆ በሸኛቸው ደም መላሽ ልዩ ጥምር ኃይላት አማካይነት እጃቸው በደም፣ ነፍሳቸው በእርኩሰት የተጨማለቀው የሕወሓት መሪዎችና ጦረኞች ዋጋቸውን እጅ በእጅ እየተቀበሉ እንዳሉ ከድሉ ዜና እየተረዳን ነው:: ፍርዱ ምድራዊ ብቻም ሳይሆን በፈጣሪ ፊት ጭምር ተዘጋጅቶ እየጠበቃቸው ስለሆነ ወደ ናፈቁት ዘለዓለማዊ ሲኦላቸው ሲደርሱ እጥፍ ድርብ ዋጋ መቀበላቸው እንደማይቀር ከወዲሁ ቢዘጋጁበት ይበጃቸዋል::
ይህ የግፈኞች ተግባር የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ክብር ይበልጥ አደመቀ እንጂ አላደበዘዘውም:: የተዳፈነ የመሰለውን የጀግንነት አቅም አፍክቶ አወጣው እንጂ አልሸፈነውም::
በራሳቸው የተንኮል ሴራ የከፋፈሉትን ሕዝብ ወደ አንድነት አምጥቶ አስተቃቀፈ እንጂ እንዳሰቡትና እንደ ቃዡት ሊያለያየን አልቻለም:: በፌዴራል ሥርዓት ሽፋን ሲያውጠነጥኑት የኖሩት መርዝ መከነ እንጂ አልሰራላቸውም:: ይህ መከራ ይዞ የመጣው በረከት (A blessing in disguise) እንዲሉ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ሲዘሩት የኖሩት ሴራ ወደ ራሳቸው ተገልብጦ ፈጅቶ ለበለባቸው እንጂ አልጠቀማቸውም::
በመላው ዓለማት የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን ካሁን ቀደም በታሪካችን ውስጥ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ የተሳሰሩት ይኼው አገራዊ ፈተና ምክንያት ሆኖ ነው:: የአፍሪካ አገራት በአዲስ መንፈስ የፓን አፍሪካኒዝምን መርህ እየመረመሩ አህጉሪቱ ከእንቅልፏ እንድትባንን ቅስቀሳው እየተጋጋለ ያለው እነዚሁ እኩያን የጫሩት እሳት ወደ በጎነት ተለውጦ የተስፋ ወጋገኑን ማድመቅ ስለጀመረ ነው::
ይህ የዘመናችን ፈተናና የአሸናፊነት ድል ወደሚቀጥሉት ዘመናት ተላልፎ ለቀጣይ ትውልዶች ትልቅ የኩራት ገድል ሆኖ እንደሚተረክ የዛሬዋ ጀንበር ለነገዋ ደማቅ ፀሐይ ታሪኩን እንደምታሸጋግር ጽኑ እምነት አለን:: በመከራ ውስጥ ነጥረው የወጡት መሪዎቻችንና ጀግኖች ዛሬ በብቃታቸው፣ ነገ በሽበታቸው አልፎም በህልፈታቸው እንደ አገር ታዳጊ እየተዘከሩ ሲወደሱ እንደሚኖሩ ጥርጥር አይገባንም::
ታሪክ ሁሌም ነግቶ እስኪመሽ ድረስ ይጓዛል እንጂ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ደክሞት አያሸልብም:: ስለዚህም ነው ታሪክ ውሎ ገብ አይደለም የሚባለው:: ሁሌም ተጓዥ ነው:: መዝገቡ የተገለጠ፣ ብዕሩም በቀለም የተሞላ ነው:: የጀግኖች ውለታ፣ የሕዝብ ደጀንነት፣ የተጋድሎው አስደናቂ ገድል እየተመዘገበ ነው::
ወደፊትም ስንዳው ይቀጥላል:: የከሃዲያኑም የከረፋ ታሪክ እንዲሁ ጎን ለጎን እየተመዘገበ ነው:: መቼም ሕወሓት ይሉት ጉድ ለታሪክም ሆነ ለምን ይሉኝ ይሉኝታ ቁብ መስጠት ባህርይው ስላልሆነ ያልሆነውን እንዲሆን አንገፋፋውም እንጂ ውርደቱና ክፋቱ ነገ ለልጅ ልጆቻቸው አንገት ማስደፊያ እንደሚሆን ይጠፋቸዋል ማለት አይቻልም:: የትግራይ ሕዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆም ብሎ እንዲያስብ ቢመከር ክፋት አይኖረውም::
ጎረምሶቻቸውን ለወረራና ለእልቂት መርቀው የሸኙት እናቶችም ሆኖ ያለ ውዴታቸው ከብብታቸው ሥር በግዳጅ ልጆቻቸው ተነጥቀውባቸው ለእሳት የተማገዱባቸው አደዬዎች ሁለቱም በፈጣሪ ፊት ንሰሐ ገብተው ምህረት ቢማጸኑ ይበጃቸዋል::
ጉዳዩን ከዚህም ከፍ እናድርገው ከተባለም ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለጨካኝ መሪዎቻቸው “ልጆቻችንን የት አደረሳችሁ?” በማለት ቢሞግቷቸው መልካም እርምጃ ይመስለናል:: “ተገድጄ ነው ወደ ጦርነት የገባሁት” እያሉ የአዞ እምባ እያነቡ ያሉት አንዳንድ ምርኮኞችም ቢሆኑ ውጤቱን ለወላጆቻቸውና ለአካባቢያቸው ማኅበረሰብ በግልጽ ቋንቋ እንዲያስተላልፉና በስምሪት ሰጭዎቻቸው ጦር አሰባቂዎች ላይ በቁጣ ገንፍለው እንዲወጡና ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲሰለፉ ግልጽ መልእክት ሊያስተላልፉላቸው ይገባል እንጂ ቃላት እያሽሞነሞኑ ብቻ ባይልፈሰፈሱ ይመረጣል::
ኢትዮጵያ ትናንትም ሆነ ዛሬ ወይንም ነገ በአሸነፊነቷ ኮርታ ትኖራለች እንጂ ለጠላቶቿ እንደማትንበረከክ ትምህርት ሰጥታለች:: የሕዝቧ የአንድነት መንፈስም እነሆ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በምድር ዙሪያ እያስተጋባ የምሥራች አበሰረ እንጂ ጠላቶቻችን እንደተመኙት አንገት ደፍተን ሙሾ አልተቀመጥንም::
ለካስ መከራንም፣ ድልንም፣ ደስታንም ለመግለጽ ቋንቋ ውስን ነው? ቃላትም ደካማ ናቸው? ክብር ድል ላጎናጸፉን ጀግኖቻችን! ክብር መሪነትን በሕይወታቸው ተወራርደው ላሳዩን ጠቅላይ ሚኒስትራችን! ክብር በደጀን ለተሰለፈው የኢትዮጵያ መላው ሕዝብ! ክብር ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ባለመሰልቸት አገራቸውን ላኮሩ የኢትዮጵያ ልጆች! ክብር በፈተና ወቅት ታምነው ከጎናችን ለቆሙ ኤርትራዊያን ውድ ወገኖቻችን! ክብር ድጋፋቸውን አብዝተው ለሰጡን ወዳጅ መንግሥታት! ብዙ ምስጋና ጸሎታችንንና ምህላችንን ተቀብሎ ለሰማው የኢትዮጵያ አምላክ! ክብር ለሚገባው ሁሉ የክብር አድናቆታችን ይድረስልን:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014