ይህ ሞትን ንቆ ሞትን ራሱን ያስበረገገ ሰው ከፊል ታሪክ ነው! ይህ የአገርንና የቤተሰብን ኃላፊነት በደሙ ፍሳሽ በአጥንቱ ክስካሽ ለመጠበቅ ዘብ የቆመ ሰው ቁንጽል ማስታወሻ ነው !! ይህ ህይወቱን ገብሮ አገር በክብሯ እና በማዕረጓ ህዝቦቿ በአንድነትና በሰላም እንዲኖሩ ለመታደግ የታገለ የአንድ ሰው ሽራፊ ታሪክ ነው!! ሁለት ራሱን ሆኖ የመቶዎችን ጥይት የተቋቋመ አገሩ እንዳትቆሽሽ ህዝቡ እንዳይዋረድና እንዳይሰቃይ በነፍሱ የተወራረደ የጀግንነትን ሚዛን የደፋ የእሸቴ ሞገስ አጭር ታሪክ ነው።
ባለፉት ሰሞናት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተሰራጨው የሽብር ደዌ የበረታ ፈተና አስከትሏል። ማን ለአገሩና ለህዝቡ እንደቆመ ማን በልቡ ታምኖ በጀግንነት ሰገነት ላይ እንደተውጣጣ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ አሳይቷል። እሸቴ ሞገስ አሁን በቃል ልናነጋግረው በአካልም ልናየው አንችልም።
ግን ለአገሩ ክብር የከፈለው የህይወት ዋጋ ያሳየው ጀግንነት አብሮን አውሎ አብሮን ያሳድረዋል ተወላጆቹንም የክብር ታሪክ መጎናጸፊያ ያጎናጽፋቸዋል። ህዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ሸዋሮቢትንና ሳላይሽን እሸቴ ሞገስንና የአሸባሪውን የሕወሓት ታጣቂዎችን አገጣጥሟቸዋል።
እሸቴ ሞገስ የ56 አመት ጎልማሳ ነበር በቀወት ወረዳ ማፉድ ሳርአምባ አካባቢ ነው የተወለደውና ያደገው። ከትውልድ ቦታው ቅርብ በሆነችው ሸዋሮቢት ቤት ሰርቶ ቤተሰብ መስርቶ እያረሰና እየነገደ ይኖራል። የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ ሸዋ ሮቢት እስኪደርሱም ድረስ ከከተማው ሰው ጋር ተግባብቶና ተከባብሮ ሲኖር ነበር። ቁመቱ የተዘናጠፈ የሚባል ረጅም አቋሙ የተስተካከለ ጠይም ዝምታንና ኮስተር ማለትን የሚመርጥ ነበር ይላሉ ቤተሰቦቹ።
እሸቴ ትጥቅ አሳማሪ ነው። እንደ ብዙዎቹ የአካባቢው ሰዎች ዝናር በወገቡ የታጠቀው ጠመንጃ በትክሻው የያዘው ገና የ15 አመት ታዳጊ በነበረበት ጊዜ ነው። አሁን በጎልማሳነቱም ጊዜ የክላንሽኮቭ ጠመንጃ ታጥቋል። በህዳር ወር መጀመሪያ ሕወሓት ለጥፋት ያሰማራቻቸው ታጣቂዎች ከሚሴን አልፈው ወደ አጣዬ ተጠጉ።
ያን ጊዜ ጀምሮ እሸቴ በሚታወቅበትና ቃሉ በሚደመጥበት የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪውን ከማስተባበር አልቦዘነም። “አካባቢያችንን አናስደፍራትም፤ በሬሳችን ላይ ካልሆነ ሸዋሮቢትን አናሳልፈውም” እያለ ሲያስተባብር ቆይቷል። በሸዋሮቢት ውጊያ ሆነ እሸቴም ከልጁ ጋር ሆኖ ተዋጋ። ግን ለጊዜው አሸባሪዎቹ አይለው ሸዋሮቢትን ያዙ። እሸቴ ሞገስ ከግቢው ምሽግ ሰርቶ “እዚሁ ተዋግቼ እሞታለሁኝ እንጂ አላፈገፍግም” ብሎ ሞገተ።
እናቱ ካሉበት ድረስ ተጠርተው “በአጠባሁህ በጡቴ” ብለው ለምነው ሸዋሮቢትን አስለቀቁት። እሸቴ ያን ጊዜ ከልጁ ከይታገስ እሸቴ ጋር ሆኖ ከሽዋሮቢት በስተምስራቅ በግምት 15 ኪሎ ሜትር ወደ ምትርቀው ሳላይሽ ሄደ።
ሳላይሽ የዘመዶቹ አካባቢ ነውና አሰፋ ታዬ ከሚባለው ዘመዱ ቤት ደረሰ። የሕወሓት ታጣቂዎች ሳላይሽን ተሰራጩባት እሸቴ ያንን ቦታ ትቶ እንዲያፈገፍግ ተመከረ ያን ጊዜ ግን አሻፈረኝ አለ። “አፈግፍጌ የት ልደርስ ነው? ለአካባቢያችንስ እኛ ካልተዋጋንለት ማን ይመጣል?” አለ። ይህ ቃሉ የማይሽረውና የማይገስሰው ቁርጠኛ ኪዳኑ ነበር።
የሕወሓት ታጣቂዎች እሸቴ ያለበትን ቤት ከበቡት። ብዙ ናቸው፤ ግን ብዛታቸው አላስፈራውም። “አንድ አንበሳ እኮ ነው ሽላም አስደንባሪ” የሚለውን ብሒል አስቦ ሊሆን ይችላል። የክላሹን ቃታ ሞልቅቆ ጥይቱን አቀባበለ፤ ልጁ ሽጉጡን መዘዘ፤ ተኩስ ተከፈተ፤ ምድር ቀውጢ ሆነች። አካባቢው በጥይት ታረሰ። እሸቴ ሞገስ ወትሮም ድር ይበጥሳል የሚባል ተኳሽ ነበር ይላሉ የሚያውቁት ሁሉ።
ጥይት ያለ መላ አይተኮስም ከሚባሉት ተኳሾች ጋር የሚወዳደር ነበርም ይላሉ። እያነጣጠረ ተኮሰ አምስቱን ግንባራቸውን እየነደለ ጣላቸው። ተኩሱ ሲበዛበት ከነበረበት የአሰፋ ታዬ ግቢ ወጥቶ በማሽላ ውስጥ ገባ። ያን ጊዜም ልበ ሙሉ እንደሆነ ነበር ሞት ከፊቱ ሲያገጥበት “ወግድ” አለው እንጂ አልፈራውም።
በእዚያ የጭንቅ ሰአት ተረጋግቶ ለእህቱ ባል ስልክ ደወለ። እሸቴ ሞገስ በጠላቶቹ ምሽግ ከበባ ውስጥ ሆኖ ህዳር 17/20 14 ዓ.ም ከቀኑ 8:30 ላይ ያስተላለፈው መልዕክት “ሳላይሽ አሰፋ ታዬ ቤት ውስጥ መሽገን ከበቡን አሁን ይሄን የምነግርህ እኛ እየሞትን ነው፤ እንድታስተላልፍልን ነው። አሰፋ ታዬ ቤት ውስጥ እኔ አምስቱን፣ ይታገሱ አንዱን በሽጉጥ ገደልናቸው። ከእዚያ እኔ ከገደልኩት ላይ ጠብመንጃ ማርኮ እንደገና ሁለቱን ደገማቸው። ሲበዙብን ወደ ኋላ አፈገፈግንና በኋላ በር ወደ ላይ ግልብጥ ስንል ተንደርድረው ሲመጡ ሁለቱን ደገምኳቸው። እኔ እና ልጄ 9 ገለናል፤ ቅዱስ ሚካኤል ምስክሬ ነው።
” እሸቴ እና ልጁ 9 አሸባሪዎችን በጥይት እንደረፈረፏቸው ቅዱስ ሚካኤልን ብሎ ምሎ በስልኩ ተናገረ። ወደ ማሽላው እርሻ ሲገባ ልጁ ይታገስ በጥይት ተመቶ ህይወቱ አለፈ። የመጀመሪያ ልጁ ይታገስ እሸቴ በ31 አመቱ ጠላቶቹን እየተፋለመ በአባቱ አጠገብ ወደቀ። አባት የልጁ አስከሬን አጠገቡ ተዘርግቶም የሚያስበው ገድሎ ስለመሞቱ እንጂ ስለመኖሩ አልነበረም።
በልጁ አሟሟት ሳይሆን በልጁ ሞት ሊያለቅስ ሞከረ፤ ግን ለጀግና እንደማይለቀስ ሲገባው ወዲያው ተወው። እርሱም ገድሎ ለመሞት ቆርጧል። የስልክ ንግግሩን ቀጥሏል። ንግግሩ ጎሽ ሰብሮ እንደያዘ አንበሳ እንጂ ለመሞት የተቃረበ መሆኑን ያረጋገጠ ሰው ድምጽ አይመስልም ነበር።
የስልክ ልውውጡ… “…አዳምጠኝ ይታገስን ገደሉብኝ። ይሰማሀል? በደንብ ያዝልኝ። የሞተው የቱጋ መሠለህ እኔም አሁን ከሬሳው ጋር ነኝ። ከበውኛል፤ እዚያው ነው የምሞተው፤ አሰፋ ታዬ ቤት ከታች በኩል የእሱ ማሽላ አለ፤ በኋለኛው በር ሬሳችን እዚያ ነው የሚሆነው። መዝግብ በኋላ ይሄን በሰማይ ነው የምከፍልህ። 9ኙን ገለን እኛ በመጨረሻ ወደማሽላው ስንንሸራተት መቱብኝ፤ … አላለቅስም ግን ብቻችን ነን እኔና እሱ ብቻ…” በጀግንነት ባልደፈርም ባይነት ጠላቶቹን ከፊቱ የጣለው እሸቴ ሞገስ በስልክ በሚያወራው የእህቱ ባለቤት ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ቢመከርም እንቢ አለ። “እኔ ሬሳ እየጠበኩ ነው፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አላፈገፍግም እዚያው ነው የምሞተው” ለጠላት ጀርባዬን አላሳይም አለ። ከስልኩ ምልልስ በኋላ ስንቶቹን እንደገደለ ምንስ እንደተፈጠረ የሚያውቁት ገዳዮቹ ብቻ ነበሩ።
በኋላ እንደተረጋገጠው ግን ከእዚያ የስልክ መልዕክት በኋላ በሸጥና በፈፋ መካከል እየተወረወረ ተዋጋቸው። ጥይቱ መሬት የማታርፈው እሸቴ ሞገስ ጠላቶቹን ደጋግሞ ሳይጥል እንደማይቀር የታመነ ነው። ራሱን ብቻ ሆኖ መትረየስንና ስናይፐር፤ ዲሽቃና ላውንቸር ከያዙት ጠላቶቹ ጋር ለሰአታት ተፋለማቸው። ጥይት መተካት አይችልም በብዙዎችም ተከቧል ለማምለጥም አይፈልግም።
እሸቴ ሞገስ ወደቀ !! በኋላ እንደተረጋገጠው ከፊት ለፊት ሲዋጋ ከኋላ ተሹለክልከው የመጡ አሸባሪዎች ጥይታቸውን አፈሰሱበት። ለአገሬ ክብር ለህዝቤ ሰላም ለቤተሰቤ ጽናት ግንባሬን እሰጣለሁ ያለው እሸቴ ሞገስ ቃሉን ጠብቆ ደሙን አፈሰሰ። የጀግንነትን እና የክብር ሞትን ለትውልድ መማሪያ እንዲሆንም በደማቅ ቀለም ጽፎ አለፈ። እሸቴ ሞገስ ለአገሩ ክብር ህይወቱን ለመስጠት በመዘጋጀቱ ኢትዮጵያን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ተወጣ።
የልጄን አስከሬን ትቼ አልሄድም በማለቱም የአባትነት ታማኝነቱን በእዚያ ጭንቅ ሰአትም አረጋገጠ። በዚያች ሰአት ሌላ ነገር ይቀረው ነበረ፤ ቀሪ ቤተሰቦቹስ፤ ታዳጊ ልጆችም አሉት። ከሞት ጋር በተፋጠጠበት በእዚያ ጊዜም ልጆቹን አልረሳቸውም። ስለዚህም እንዲህ ብሎ በስልክ ለሚያወራው ዘመዱ አደራ ሰጠ። “…ሌላውን አዳምጠኝ።
የቀሩት ልጆቼ ማሳደጊያ መኪና እዚሁ ሊቃጠል ነው፤ ያው እነሱ ስለሚያውቁት ያቃጥሉታል። ለመንግሥት አሳውቅልኝ። ልጆቼን አደራ፣ ልጆቼ በርሀብ እንዳይሞቱብኝ፣ አደራ ለመንግሥት አሳውቅ” ሲልም የመጨረሻውን ቃሉን አስተላልፏል። ጀግንነቱን ለአገር ልዕልና ያዋለው እሸቴ ሞገስ አደራውን ሰጥቷል።
ህይወቱን የሰጠው እኛ ቋሚዎቹ የተወረወረብን ቋጥኝ እንዳያጎብጠን፣ ቀና ብለን እንድንሄድ፤ ከተመረዘ የሽብር አየር ወጥተን የሰላም አየር እንድንተነፍስ ብሎ ነው። እናም አደራው ምቾታችንን እንዳይሸራርፍብን ለሌላውም መስዋዕትነት ከብረንና አጊጠን ለመኖር ለምንፈልገው ሁሉ መሆኑን አያከራክርም። አደራው በየጦር ግንባሩ የአሸባሪዎችን ጥቃት ለመመከት ለህዝባቸው አንድነትና ለአገራቸው ሰላም ሲሉ የወደቁትን ጀግኖች ሰዎች ጭምር እንድናስብ የሚጎንጠን ነው። የእሸቴ ሞገስ ገድልም የብዙ የመከላከያና የልዩ ኃይል የፋኖ የሚሊሻና የፖሊስ አባላት ገድል ነው።
የጠላታቸውን ጉሮሮ ፈልቅቀው የአሸባሪዎችን ግንባር በርቅሰው ህይወታቸውን የሰጡንን ጀግኖቻችንን የሚዘክርና ዝንታለም የሚወደስ ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው። አገር የምትድነው የምትተላለፈውም ሞትን በናቁ ጀግኖቻችን ነው። ጀግናም ምንጊዜም ሞተ አይባልም፤ ክብር ለጀግኖቻችን። ምንጭ ሸገር 102.1 ሬድዮ ከዚሁ ጋር በተያያዘ… የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ባስተላለፉት መልዕክት “…የጀግኖቻችን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍፁም አንረሳም።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዚህ የሕልውና ዘመቻ እንደ እሸቴ ሞገስ ለህልውናቸው፣ ለሕዝብና ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ቤተሰቦች በመንከባከብና በማገዝ አደራውን ይቀበላል…” ሲሉ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014