ጅምላ ጨራሽ ኬሚካል መሳሪያ ደብቃለች በሚል ሓሳዊ ምክንያት ምዕራባውያንን ሁሉ በማሰለፍ በኢራቅ ላይ በተደረገው ዘመቻ ቢሊዮን ዶላሮች ተከስክሰው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨፍጭፈው፤ ኢራቃውያን መክፈል የማይገባቸውን ዋጋ ከፍለውና መሪያቸው ሳዳም ሁሴን በግፍ ተገድለው ሲያበቁ በስተመጨረሻ የተሰጠው ምክንያት እጅግ አሳፋሪና “በኢራቅ ተደብቆ ይገኛል የተባለው ኬሚካል መሳሪያ የለም መረጃው ፍጹም ውሸት ነው” የሚል ነበር።
የአሜሪካና የምዕራባውያኑ ዓይን አውጣነትና ይሉኝታ ቢስነት በዚህ ብቻ ሳያበቃ ለሊቢያውያን ከሊቢያውያን በላይ አሳቢ በመምሰል ሊቢያውያንን ከአምባገነን መሪያቸው ለመገላገል በሚል “አዛኝ ቅቤ አንጓች” እሳቤም አሉ የተባሉ መሣሪያዎች በሊቢያ ምድር ላይ ተጥለው፤ መሬቷ በአውዳሚ የጦር መሣሪያዎች ታርሶ፤ ለቁጥር የሚታክት ሕዝቧ ጭዳ ሆኖና መሪዋ ሙዐመር ጋዳፊ በግፍ እንዲሞቱ ከተደረገ በኋላ ለሊቢያና ለሊቢያውያን ጠብ ያለ ነገር እስካሁንም አልታየም።
ይልቁንም አይ.ኤስ.ኤስን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ሽብርተኛ ድርጅቶች መፈልፈያና መናኸሪያ የሆነች ሊቢያን ፈጠረ እንጂ! ከእነዚህ ሁለት ማሳያዎች በተጨማሪም በአሜሪካ ፊት አውራሪነትና በምዕራባውያን አጫፋሪነት በተለመደና በሰለች ስልት በአሮጌ ሴራ በየመን፣ በሶሪያና በአፍጋኒስታን ተላላኪና አሻንጉሊት መንግሥት ለማስቀመጥ በማሰብ የተካሄዱ ዓይን ያወጡ ጣልቃ ገብነቶች አገራቱን አፍርሰው ሕዝቦቻቸውን ለመከራ ዳርገዋል።
በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች እጅግ አሳፋሪው ነገር በቴክኖሎጂና በዕውቀት መጥቀዋል በሥልጣኔም ዓለምን እየመሩ ነው ተብለው የሚታሰቡት አሜሪካና ሽሪኮቿ ምዕራባውያን ሴራቸውን ለማስፈጸም የሚሄዱበት መንገድ አሮጌ፣ ተቸካይና ቆሞ ቀር መሆኑ ነው።
ይሄንን እውነታ ቆም ብሎ ላስተዋለና ለተገነዘበው ሰው የአሜሪካና ሸሪኮቿ ምዕራባውያን ስምና ድርጊት ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይሉትን ዓይነት ነገር መሆኑ ግልጽ ይሆንለታል።
ከላይ ለማሳያ ያህል የተወሰኑ አገራትን ታሪክን አነሳን እንጂ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማንነት በቅጡ ያልተገነዘቡት እነዚህ ጣልቃ ገብ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እንደፈለጉት የሚዘውሩትንና ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚላቸውን ዓይነት መንግሥት ለማስቀመጥ በአገራችን ላይ ሴራ ሲተበትቡና ሲያስፈጽሙ የኖሩበትም ሁኔታ ትናንትም ዛሬም ተመሳሳይ እንደሆነና ቢያንስ ቢያንስ ወቅታዊ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ያላገናዘበ ስለመሆኑ ፀሐይ የሞቀውና አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን።
ለዚህ አርቲክል መነሻነት ሁነኛ መሰረት ይሆናልና የአሜሪካና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተዘጋጀው አዲስ ወግ መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተናገሩትን እናንሳና ቀጣይ ጉዳዮችን መመልከታችን እንቀጥል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት አሜሪካና ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነትም በ1983 ዓ.ም አካባቢ በኢትዮጵያ ከተከሰተው ጋር ለማነጻጸር “ኢትዮጵያውያን ከታሪክ መገንዘብ ያለብን፤ አሁን ላይ ያለው ጦርነት ባህሪ እንዳለ 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ ተካሂዷል።
” እውነታው ይሄ ከሆነ ዘንዳ እኛ ኢትዮጵያውያን ከታሪክ ተምረን ዳግም የውጭ ኃይሎች እጃቸውን በአገራችን ጉዳይ አስገብተው የተኮላሸና አገር አፍራሽ ዓላማቸውን እንዳያስቡ ቀድሞና አሁን ጣልቃ ገብነቱና ጫናው ምን መልክ እንደነበረውና ተመሳስሎሹ ምን ይመስል እንደነበር እንመልከት።
የሚዲያ ውክቢያና ሽብር መፍጠር እንደ ስትራቴጂ በደርግ ዘመነ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የነበረውን ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር በተደረገ አጭር ቅኝት በወቅቱ ከነበረው የመረጃ ነፃነት አለመኖር ጋር በተያያዘ የምዕራባውያንን መገናኛ ብዙኃን በተለይም ቪኦኤ እና ዶቼቬሌን መከታተል እንደወንጀል ከመቆጠሩም በላይ የሚያስቀጣም ነበር። አንድ ነገር ሲከለከል ለማግኘት መጓጓት የሰው ልጅ ባህሪ ነበርና በርካታ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጥንቃቄና ድምጽ እየቀነሱ በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፈውን መልዕክት እንደታማኝ የመረጃ ምንጭ ይጠቀሙበት ነበር።
በወቅቱ በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን በሚተላለፈው መልዕክት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ሠራዊትን ዝናና አቅም እጅግ አጋኖ የሚያቀርብ በየዕለቱና በየወቅቱም ድል እያደረጉና በትረ መንግሥቱን ለመቆጣጠር በስኬትና በፍጥነት እየተጓዙ እንደነበር የሚያሳይ ነበር።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የወቅቱን መንግሥት ህጸጾች እየፈለጉ እየጨማመሩና እያጋነኑ ጭራቅ አድርገው በመሳል በአገር ውስጥም በውጪም ተቀባይነቱን እንዲያጣ ለማድረግም አስበው፤ አቅደውና ተቀናጅተው ይሰሩም ነበር።
በዚህ ላይ ሊካድ የማይችለው እውነታ የደርግ መንግሥት በርግጥም ሰብዓዊ መብቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጥስና በዚህም በአገር ውስጥ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻ ያለበትና በውጭውም ዓለም ገጽታው የጠለሸ መሆኑ ነው።
ይሁንና በዚህ እውነታ ላይ ተመስርተው ያከናውኑ የነበረው የሚዲያ ዘመቻ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ከማዘንና ከመቆርቆር የመነጨ ሳይሆን በአገሪቱ ተላላኪና ዓላማቸውን የሚፈጽም አሻንጉሊት መንግሥት ለመፍጠር ስለነበር የተጋነኑ፣ ፍጹም ሐሰት የሆኑና አንዱን ወገን አጀግኖ ሌላኛውን የሚያንኳስሱ መረጃዎች በስፋት ይለቅቁ ነበር።
ይኸም ተግባራቸው በአገር ውስጥ ሕዝቡ የሕወሓትን ጦር እንዲፈራና እንዲሸበር ብሎም ወኔው እንዲሰለብ በማድረግ ወደዚህ ከተማ ተጠጉ በተባለ ቁጥር ሕዝቡ በፍርሃት አካባቢውን እየለቀቀ እንዲፈናቀል ከማድረጉም በላይ ይኸንን ግርግርና የሽብር ዘመቻ እንደመልካም ዕድል በመጠቀም የአሸባሪው ሕወሓት ኃይል በርካታ አካባቢዎችን በቀላሉ እንዲቆጣጠር ረድቶታል።
ከዚህ አለፍ ሲል ሕዝቡ መግሥትን እንዳያምንና ከጎኑ እንዳይሰለፍ በማድረግም የኃይል መመናመን እንዲደርስበትና እንዲሸነፍ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። ለውድድር ወደውጪ አገር የሄዱና በዚያው የኮበለሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችንና አገር ከድተው የኮበለሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ስደት በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ከመጥላት ጋር የተያያዘ መሆኑን አብዝተው በመግለጽም ተስፋ መቁረጥ እንዲበረታና በወቅቱ የነበረው መንግሥት እያበቃለት ነው ተብሎ እንዲታሰብም ማድረግ ችለዋል።
ምንም እንኳን ያኔና አሁን በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ፈጽሞ የተለያየ ቢሆንም እነዚሁ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ለዓላማችን ስኬት እንቅፋት ሆኖብናል ብለው የሚያስቡትን የኢትዮጵያ መንግሥት ማስወገድን ዓላማ አድርገው ያረጀና ያፈጀ ታሪካቸውን ደግመው እየተገበሩ ስለመሆኑ እየታየ ነው።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አየነው ስለሺ “በሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከአገር መውጣት የምዕራባውያን ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበረበት ታሪክ በግልጽ አስቀምጦታል።
ለእነርሱ ታዛዥ የሆነ አሻንጉሊት መንግሥትና መሪ በማስቀመጥ አገሪቱን እንደልባቸው ለማሽከርከር አሁንም ይህን ድርጊታቸውን ለመፈፀም እየጣሩ ነው” የሚል ሃሳብም ከላይ የገለጽነውን ጉዳይ እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ነው።
የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ደግሞ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑትን ፊስቡክንና ትዊተርን የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችንም ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ መጠቀማቸው ነው።
ለማንም ግልጽ እንደሆነው አሸባሪው ሕውሓት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ጥቃት ፈጽሞ እርምጃ መወሰድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በተቀናጀ ሁኔታ በኢትዮጵያ ግጭትን በማስፋፋትና ይህንን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነት የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት ለመጣል ዓይናቸውን በጨው ታጥበው፤ ሕሊናቸውን ሽጠውና ቆመንለታል የሚሉትን መርሕ ረግጠው ትዝብት ላይ የጣላቸውን የሚዲያ ዘመቻ አፋፍመዋል።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን መምህሩ ዶክተር ሳምሶን ሲናገሩ ”የአሜሪካና ምዕራባውያን ሚዲያዎች በደርግና አሁን ባለው መንግሥት ላይ እያደረጉ ያሉት ማዋከብ ተመሳሳይ ነው። ብቸኛ ልዩነቱ አሁን ላይ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ መኖሩ ብቻ ነው እንጂ ሁሉም አካሄድ አንድ ነው ማለት ይቻላል።
አሁን ያለው የማኅበራዊ ትስስር ገጹን የሚዘውሩት ያው አሜሪካኖቹ ናቸው።ስለዚህ የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅምን ነው የሚያስከብሩት።በቅርቡ እንኳ የጥላቻ ንግግር ያልሆነውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ንግግር ከማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አንስተዋል” ብለዋል።
በዚህ ሂደት እጅግ አስገራሚው ነገር ምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን በአገራችን ላይ አሁን የከፈቱት አፍራሽ የሚዲያ ዘመቻ በቴክኒክም በታክቲክም ተመሳሳይ መሆኑ ነው። ይሄንን በተጨባጭ መረጃዎች ለማሳየትም ያህል በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ለመክሰስና ስሙን ለማጠልሸት ይጠቅመናል ብለው የመረጡት ጉዳይ ልክ እንደ ደርግ መንግሥት ሁሉ በሰብዓዊ መብት ጥሰትም ስም መንግሥትን መክበብ ነው።
ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ መምሰልን ለጣልቃ ገብነት እንደ መሳሪያ ሌላውና እጅግ በጣም በሚያስገርም መልኩ አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን ጋሻ ጃግሬዎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እንደ መሣሪያ የተጠቀሙት በፊትም አሁንም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም መንግሥታቱን መወንጀል ነው። በዚህ ዙሪያ አስደናቂው ነገር የደርግ መንግሥትና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና መንግስት በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ፍጹም የማይመሳሰሉ ሆነው ሳለና ይኸንንም እነዚህ ጣልቃ ገብ አገራት እያወቁትም ጭምር የደርግ መንግሥትን ሲወነጅሉበት የኖረውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ክስ አሁን ባለው መንግስት ላይ ደግመው ሲያነሱት ተደጋግሞ ታይቷል።
የደርግ መንግሥት ከነበረው ባህሪና በሕዝቦች ላይ አድርሶት ከነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ምንም እንኳ ጉዳዩን የሚያነሱት የሰብዓዊ መብት መጓደሉ አሳስቧቸው ባይሆንም መሬት ላይ የነበረው ተጨባጭ እውነታ የተጋነነ ክሳቸው ጆሮ እንዲያገኝና ተጽዕኖ እንዲፈጥሩ አስችሏቸው ነበር።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ግን ቀደም ሲል ሕወሓት መራሹ መንግሥት በሕዝብ ላይ ሲያደርስ የቆየውን ከጥፍር መንቀል እስከ ከአውሬ ጋር ማሰር የመሳሰሉ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስቆመ፤ ለሰብዓዊ መብት መከበር ጉልህ ድርሻ ያላቸውን የዴሞክራሲ ተቋማት የመሰረተና ያጠናከረ ቢሆንም የእነዚሁ ኃይሎች ፍላጎት በመሰረቱ የሰብዓዊ መብት መቆርቆር አልነበረምና በዚያ ዘመን ደርግን በሚከሱበት ልክ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያነሱ አሁን ላይ ያለውን መንግሥት ሲከሱና ይኸንንም መሠረት አድርገው በአገራዊ ጉዳያችን ዙሪያ ጣልቃ ለመግባት ሲሞክሩ ይታያል።
ይኸን እውነታ ስንመለከት እጅግ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህና አሁንም ጭምር በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ሕዝቦች ላይ የግፍ ግፍ እየፈጸመና ሰብዓዊ መብቶችን እየጣሰ ያለውን አሸባሪውን ሕውሓት አንድ ጊዜም ሲወቅሱት አለመሰማታቸውና አለመታየታቸው ነው።
ይኸንን ጉዳይ በሚመለከት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሲያብራሩ “ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ መቀሌን ለቀን ለመውጣት ስናስብ ነዳጅ፣ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች የሆኑ አቅርቦቶች ለሶስት እና ለአራት ወር በሚበቃ መልኩ እንዲቀመጥ አድርገን ነው።
ይኸ አሸባሪ ጁንታ ግን ለትግራይ ሕዝብ የእርዳታ አቅርቦት ለማሰራጨት የተላኩ መኪናዎችን ለሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ በይፋ እየተጠቀመ ይገኛል። ሆኖም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጠዋት ማታ መንግሥትን ሲከሱ ውለው የማያድሩት አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት አንዳችም ቃል ሲተነፍሱ አለመታየቱ ነው ብለዋል።” በእነዚህ መረጃዎች ከላይ የጠቀስናቸው ጉዳዮች አሜሪካና ምዕራባውያን አጋሮቿ ወቅታዊ ሁኔታውንና ልዩነቱን እንኳን ሳያገናዝቡ አገርን ለማፍረስ ተላላኪ መንግሥትን ለማስቀመጥ ያረጀ ያፈጀ ዘዴን በድጋሚ እየተጠቀሙ እንደሆነ ያሳየናል።
ሽብር መፍጠርን እንደተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሩሲያን ያንበረክክልኛል በሚል እሳቤ ታሊባንን በአፍጋኒስታን ያስጸነሰች፤ ያሳደገችውና ያፋፋችው አሜሪካ በኋላ ላይ እጅግ ውድ ዋጋ ያስከፈላትን ይህንን የሽብር ኃይል በጦር መሳሪያና በፋይናንስ ከመደገፍ ውጪ የታሊባንን ሰባራና ሰንጣራ ድርጊቶች በመገናኛ ብዙኃኗ እጅግ አጋና በማቅረብ ለደረቀ አጽሙ ሥጋና ደም ያለበሱት አሜሪካውያኑና ሸሪኮቻቸው ነበሩ።
እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ታሊባን የሌለውን የጀግንነት ምስል በመፍጠርና በፕሮፖጋንዳ የታሊባንን ሕዝብ በማሸበር እንዲፈራና የማይቆረጥም ባቄላ እንዲሆን አድርገውታል። ይሄንን ቦታ ተቆጣጠረ፣ ወደዚህ እያመራ ነው፣ ይኸን ያህል ደመሰሰ የሚሉት ዜናዎቻቸው በምዕራባውያኑ ለታሊባን መጠጠር ያበረከቱት ገጸ በረከት ነበር።
በደርግ ዘመን መንግሥትም የአሜሪካና ምዕራባውያን ሚዲያዎች ጭፍን በሆነ ሁኔታ ሐሰት የተሞላበት ዜና ጭምር በመጠቀም የሕውሓትን የድል ዜናዎች በማጉላት የሠራዊቱ ሞራል እንዲላሽቅ ሕዝቡ በፍርሃት እንዲዋጥና በዚህም መነሻነት በትረ ሥልጣኑን በቀላሉ እንዲቆጣጠር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ቪኦኤ ዶቼ ቬሌና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በየቀኑ በምሽት ስርጭቶቻቸው ሕወሓት መራሹ ኃይል ይሄንን ከተማ ተቆጣጠረ፤ ይሄንን ያህል ኃይል ደመሰሰ፣ እገሌ የተባለ ባለሥልጣን አገር ጥሎ ኮበለለ፣ እገሌ የተባሉ ዲፕሎማት በኢትዮጵያ እጅግ የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ፤ እገሌ የተባለ አገር ኤምባሲውን ሊዘጋ ነው። ዜጎቹንም ሊያስወጣ ነው በሚል አገርንና ሕዝብን የሚያሸብሩ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን መሥራት የሰርክ ተግባራቸው አድርገውት ኖረዋል።
ዛሬ ዛሬም በተለይ አሜሪካ በጎረቤት አገር የተጠላውን፣ የአጎራባች ክልል ሕዝቦችን በመጨፍጨፍና ግፍ በመፈጸም አውሬነቱን ያስመሰከረውንና በመላ ኢትዮጵያውያን ተነቁሮ የተተፋውን የአሸባሪውን ሕወሓት አጽም በውሸት መረጃና ፕሮፖጋንዳ ሥጋ አልብሰውና አግዝፈው በማሳየት በሌለ አቅሙ እንዲፈራ ለማድረግ ተግተው እየሰሩ ነው።
በእነዚሁ ኃይላት የሚዘወሩትን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ ሲ.ኤን.ኤን ኦስሼትድ ፕሬስ ወዘተ. አሸባሪው ኃይል ያልተጎናጸፈውን ድል የተጎናጸፈ በማስመሰል ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ ነው የሚል የሐሰት ትርክታቸውን ማሰራጨት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ሆኗል። ከዚህም ባለፈና እጅግ በወረደ መልኩ የአሜሪካ ኤምባሲ እየደጋገመ በሚያወጣቸው ግራ የተጋቡ ሽብር የሚፈጥሩ መግለጫዎች አገር ልትፈርስ የደረሰች በማስመሰል የእነሱን ጨምሮ የሌሎች አገር ዜጎች አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ እየወተወቱ ይገኛሉ። መሬት ላይ ያለው እውነታ አየሩን ከተቆጣጠረው የእነሱ የውሸት መረጃ ተቃራኒ መሆኑን በመረዳት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ ባለመውጣት ላሳዩት ምላሽም ብድር ሁሉ እናቀርባለን፤ ከጅቡቲ የሚወረወር ወታደራዊ ኃይል እንልካለን እስከሚል ቅዠታዊ መግለጫ እስከ ማውጣት አድርሷቸዋል።
ይሁንና ይኸ የሐሰት መረጃቸውና ሊፈጥሩት የሚሞክሩት የሽብር ወሬ እንደደርግ ዘመን መሪ አገርን ለቆ እንዲወጣ ሕዝብም በሽብር ወሬ ተፈትቶ ጭቆናን ዳግም እንዲቀበል ለማድረግ አልቻለም። ይልቁኑ ወሬያቸው በአዲሱ ዘመን እየተለቀቀ ያለ አሮጌ ወሬ መሆኑን በመረዳት ትርፉ ትዝብት መሆኑን ብቻ አረጋገጠ እንጂ።
ኸርማን ኮኸን እና ፌልትማን እንደ ተልዕኮ አስፈፃሚ ልብ ብሎ ላየውና ከላይ እንደተብራራው በሰብዓዊ መብት ስም ክስ እየፈጠሩ የመንግሥትን ሥም ካጠለሹና ተላላኪያቸውን በተለያየ ሁኔታዎች ከደገፉ፤ በሚዲያ ዘመቻቸው ሽብር ከፈጠሩና ሕዝብን በወሬ ከፈቱ በኋላ ይህን አድርገውም መንግሥትን ካዳከሙ ወይም ያዳከሙ ከመሰላቸው በኋላ ድርድር በሚል ሽፋን ተላላኪና አሻንጉሊት መንግሥት የማስቀመጥ ሥራቸውን በተግባር ላይ ያውላሉ።
ይህንንም የሚያስፈጽሙት ባረጀ እና ባፈጀ አሮጌ ዘዴያቸው ስለመሆኑ የ1983ቱን ኸርማን ኮኸን ከ2014ቱ ፌልትማን ጋር በማነፃፀር በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ለማንም ግልጽ እንደሆነው በአሜሪካና በምዕራባውያን ቀጥተኛ ድጋፍ ፋፍቶ የጎለመሰውንና የሸበተውን ሕወሓት መራሽ ኃይል በተላላኪ መንግሥትነት ለማስቀመጥ በስመ ድርድር የተሠራውን ሴራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ታትሮ ያስተገበረው የቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣን ኸርማን ኮኸን ነበር።
ይህ ሰው ሕወሓትና የደርግ መንግሥትን በጀርመንና ጣሊያን ያደረጉትን የማደራደር ሥራ ከመምራቱም በላይ በአሜሪካ ላይ የተደረገውን እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ በሚል ሴራዊ ምክንያት ሕወሓትን ለአራት ኪሎ የመንግሥትነት መንበር ያበቃ ነው።
እዚህም ላይ የሚደንቀው ነገር ዘመኑንና ሁኔታውን በቅጡ ለመረዳት ያልፈቀደችው አሜሪካ አሁንም በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግሥት የማስቀመጥ ተልዕኮዬን ያስፈጽማል በሚል ዕሳቤ በጉዳይ አስፈፃሚነት ፌልትማንን ሾማለች።
ይኸ ግለሰብም ዓይኑን በጨው አጥቦ ከተራ ሽፍታነት ያልዘለለ አቅም ላለው አሸባሪው ሕወሓት ግዘፍ ነስቶ አሁንም ኢትዮጵያን ከሚያክል ትልቅ አገርና ከፍተኛ ሕዝብ ተቀባይነት ያገኘውን መንግሥት ከተራ ሽፍታ ጋር ለማደራደር ላይ ታች እያለ ይገኛል። ይህም እንዲህ ከላይ እንደጠስቅናቸው ጉዳዮች አሮጌ ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ለማስቀመጥ የተሞከረበት አሮጌ አቀራረብ መሆኑ ግልጽ ነው።
ረሃብን ለርካሽ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ ታሪክ ራሱን የደገመበት ሌላኛው የአሜሪካና የሸሪኮቿ ተላላኪ መንግሥት የማስቀመጥ አካሄድ ረሀብን ለርካሽ ፖለቲካ ማስፈፀሚያነት ማዋል ነው። ለዚህም የ1977ቱን ድርቅና አሁንም ሕዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው ብለው የሚደሰኩሩበትን ሁኔታ በመመልከት ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ማድረግ ይቻላል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ታዋቂ ግለሰቦች እንዳስታወቁት አሜሪካና ምዕራባውያን በስመ ርዳታ የ1977ቱን ድርቅ አሸባሪውን ሕወሓትን ለማጠናከርና ለመደገፍ ተጠቅመውበታል።
በድርቅ ለተጎዱ ሕዝቦች ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ በሚል የዳቦ ሥምም ለሕውሓት የጦር መሳሪያና ሌሎች ድጋፎች በሰፊው ሲያቀርቡ እንደነበር ታሪክ በትዝብት ሰንዶ ያስቀመጠው እውነት ነው። ከዚህም አልፎ አሸባሪው ሕወሓት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለእርዳታ የመጣን ስንዴ በሱዳን በአደባባይ እየሸጠ መሣሪያ ሲሸምት ምዕራባውያኑ እያዩ እንዳላየ ያለፉበት አስከፊ አሳዛኝ እውነት ነው።
ምን ይሉኝን የማያውቁት እነዚሁ አገራት ዛሬም አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ በሚል ብሂል ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል ረሃብን ለርካሽ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ማስፈፀሚያ ሊጠቀሙበት ሲውተረተሩ እየተስተዋለ ነው።
አሁን እየተጠቀሙበት ባለው አሮጌ ስሌት አስገራሚው ነገር የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡበትን ወደብ እስከመምረጥ የደረሰ ዓይን አውጣነት የታየበት መሆኑ ነው። ለዚህም የሱዳን ድንበር ካልተከፈተ ሲሉ ደጋግመው የጠየቁበትን ሁኔታ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ይሁንና ያረጀ ተንኮልና ሴራቸውን አስቀድሞ የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥትም ለሰብዓዊ መብት አቅርቦት አመቺ ሁኔታዎች በማሟላት የተደበቀ ሴራቸውን ማክሸፍ ችሏል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የምዕራባውያኑ ፍላጎት ለተቸገረ ሕዝብ ርዳታ ማቅረብ አለመሆኑን የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ለርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ከተሰማሩ 1200 መኪኖች ውስጥ 240 ብቻው ተመልሰው ሌሎቹ በዚያው ቀርተው ለሕወሓት የሽብር ጦር ግልጋሎት ቢውሉም እስካሁን አካፋን አካፋ ብሎ የፈረጀና ያወገዘ አንድም ምዕራባዊ አገር አለመታየቱ ነው። “ይህ የአሁኑ አካሄዳቸው ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጋር ሲነጻጸርም ተመሳሳይ ነገር ነው ያለው።
በደርግ ዘመንም የአሁኑ አሸባሪው ሕወሓት እንዲገባ የተደረገው በዚሁ መንገድ ነው።በተለይ የእርዳታ ፖለቲካው ዋናው መንገድ ነው።ዩኤስኤይድ የተባለው ድርጅት የእርዳታ ድርጅት አይደለም።በመጀመሪያ ሲቋቋም እርዳታ መስጠት ሳይሆን ጄነራል ማርሻል የሚባል አሜሪካዊው ሰው ነው ሐሳቡን ያመጣው።አገራትን ለመቆጣጠር በስመ እርዳታ ድርጅት እናቋቁምና የምንፈልገውን አገር እንቆጣጠር በሚል ነው ድርጅቱ የተቋቋመው፤ እስከዛሬም የቀጠለው ሂደት ያው ነው።
ድርጅቱ የእርዳታ ድርጅት አይነት ባህሪም የለውም።የድርጅቱ ኃላፊ የተባለችው ሳማንታ ፓወርም በፖለቲካው ውስጥ ገብታ ብዙ ስትል እንደነበር የሚታወስ ነው” ዶክተር ሳምሶን መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር እንደ ማጠቃለያ የመጀመሪያና በታሪኳ ልዩ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሚያስደንቅ ሕዝባዊ ተሳትፎና ጽናት ባካሄደች፣ ሠፊ ሕዝባዊ ተቀባይነትና ድጋፍ ያለው መንግስት ባለቤት በሆነች ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ብዙ ርቀት በተጓዘችና ከምንም በላይ ለሉዓላዊነታቸው ልዩ ቦታ የሚሰጡ ሕዝቦች ባለቤት የሆነችውን የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ በምንም መልኩ ሊመሳሰል ከማይችለው የደርግ መንግሥት ጋር በማመሳሰል ባረጀና ባፈጀ ዘዴና ሴራ ያንኑ ውጤት ድጋሚ ለማምጣት በአሜሪካና ምዕራባውያን ሸሪኮቿ እየተደረገ ያለው ጥረት በታሪክ መዝገብ ተከትቦ የሚኖር የወረደ ተግባር ስለመሆኑ ጥርጥር አይኖርም።
ርዳታን ከነጻነት ጋር ፈጽሞ ከማያወዳድሩት ኢትዮጵያውያንና የነጻነት ቀንዲል የሆኑ ሕዝቦች ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ያውም በአሮጌና የአራዳ ልጆች “የተበላ” በሚሉት ዘዴ እጅ ለመጠምዘዝ መሞከርም ትዝብት ላይ ይጥል ይሆን እንጂ ጠብ የሚል አንዳችም ፋይዳ እንደማይኖረው መረዳቱ ተገቢም አትራፊም ይሆናል።
ፍቃዱ ከተማ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1/2014