ከኢትዮጵያና ከእውነት አምላክ ጋር ተገደን የገባንበት ጦርነት ሙሉ በሙሉ በእኛ አሸናፊነት በቅርብ ይጠናቀቃል። የድህረ ጦርነቱ ዳፋ ግን ላልተወሰነ ጊዜ አብሮን ይኖራል ። የፍትሕ ሚኒስቴር የሽብር ቡድን ደቡብ ወሎን የኦሮሞ ብሔረሰብ እና የሰሜን ሸዋ ዞኖችን በወረራ ከመያዙ በፊት ይፋ ያደረገው ቅድመ ምርመራ ውጤት ይፋ እንደሆነው ሕወሓት ወሯቸው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ብቻ 483 ሰዎች በግፍ ተገድለዋል ፤ 163 ሰዎች አካል ጉዳተኛ ሆነዋል ፤ 109 ሕጻናትን ልጃገረዶችንና ሴቶችን ለመግለጽ በሚከብድ ሁኔታ በቡድን አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል።
እነዚህ ዞኖች ከወራሪው ነጻ ሲሆኑ የተፈጸመው ህልቆ መሳፍርት ከዚህ የከፋና በብዙ እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን በአንጾኪያ ገምዛና በጋሸና ይህ ጥሎት የሚሄድ ጠባሳ በቀላሉ አይድንም። እንግዲህ ቁስሉ እስኪጠግግ፣ ሰንበሩ እስኪጠፋ፣ የአእምሮና የስነ ልቦናው ቅሪቱ እስኪወገድ ድረስ ሕማማቱ አብሮን ይባጃል ።
አረመኔውና ግፈኛው ሕወሓት በማይካድራ በጭና በደብረ ታቦር በአጋምሳ በውጫሌ በጋሊኮማ በንፋስ መውጫ እና በወረራቸው አካባቢዎች በሙሉ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ለማየት የሚዘገንኑ ዘግናኝ ግፎችና ስቃዮች ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን ለስነ ልቦና እና የአዕምሮ ሕመም ተዳርገዋል።
አራትና አምስት ልጆቹን ከእነ ባለቤቱ ያጣ፤ እናትና አባታቸውን በግፍ የተነጠቁ ብላቴናዎች፤ የክህነት ሚስቱ የተነጠቀ የሃይማኖት አባት፤ የተደፈሩ ልጃገረዶችና ሴቶች፤ እንደ ልጆቹ የሚያያቸው እንስሳት በጥይት የተደበደቡበት ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው ክህደትና ጭፍጨፋ ሲፈጸም የተመለከቱ የሠራዊቱ አባላት ፤ ወዘተረፈ ከደረሰባቸው የቅስምና የልብ ስብራት ለማገገም ዓመታት ይወስድባቸዋል ።
ለዛውም የሕክምና የስነ ልቦና ምክርና መልሶ የማቋቋም ሥራው በተጠና አግባብ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን ከተፈጸመ። አበክሮ የተሰበረን መንፈስና ልብ ስለመጠገን ፤ እንዲሁም በአሸባሪው ሕወሓት አስገድዶ ማጥመቅ (ኢንዶክትሬሽን) በተሳሳተ ትርክት እና በማስፈራራት የሸፈተን ልብ ስለመማረክም አበክሮ ማቀድና መስራት የጦርነቱ አካል ነው ።
አሸባሪውና ከሀዲው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ይዞ ለመጥፋት ታጥቆ እየማሰነ ነው። ትግራይን ሴቶችና ጨቅላዎች ብቻ የሚባዝኑበት የመናፍስት ክልል ሊያደርገው ቆርጦ ተነስቷል። እያደረገውም ነው። መጀመሪያ ወጣቱን በመቀጠል ሕጻናትን ከዚያ አረጋውያንንና አካል ጉዳኞችን በጦርነት እየማገደ እየጨረሳቸው ነው።
በእብሪትና በማንአለብኝነት እያስገደደና እያታለለ ትግራዋይን በሕዝባዊ ማዕበል በየግንባሩ እየማገደ እያስፈጃቸው ነው። በደቡብ ጎንደር በሰሜን ጎንደር በዋግ ኽምራ በሰሜን ወሎ በደቡብ ወሎ በተለይ በኩታበር በቦሩ ሜዳ በሐይቅ በጭፍራ በአፋር ትግራዋይ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው።
ሕወሓት ካፈርሁ አይመልሰኝ ብሎና ተስፋ ቆርጦ ትግራዋይን ይዞ እየሞተ ነው ። ከዚህ የከፋና የባሰ ምን ይመጣል በሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ጣዕረ ሞት ላይ ሆኖ እንኳ ትግራይን የወላድ መካን እያደረጋት ነው ።
በ17 አመቱ ጦርነት 60ሺህ ልጆቹን በመነጠቁ ጧሪና ቀባሪ ማጣቱ ሳያንስ ዛሬ የተረፉ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ትርጉም ለሌለው ጦርነቱ ተማግደው ሲያልቁ ዛሬ ተረኛው እሱ ሆኗል። አሸባሪውና ከሀዲው ሕወሓት የእሱን ተስፋ መቁረጥ ወደ ሕዝቡ በማጋባት ስለነገ ሕይወቱና ኑሮው
ተስፋ እንዲቆርጥና እንዳይጨነቅ በማድረግ ፤ ከአማራ ከኤርትራ ከአፋርና ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ተቆራርጦ ከጎኑ እንዲሰለፍ እያደረገ ይገኛል ። ሆኖም የተረፈውን ትግራዋይ ከሕወሓት መንጋጋ ለመታደግ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠላትነት እንደማያየው ለማረጋገጥና የሕወሓትን ሰንኮፍ ለመንቀል የትግራዋይን ልብ ስለመማረክ አበክሮ ማሰብና መሥራት ይጠይቃል።
የጸረ ሽብር ትግሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የትግራዋይን ልብ በመማረክ ሲታጀብ ነውና ።የጸረ ሽብር ትግል በአውደ ወጊያ በሚቀዳጁት ድል ብቻ አይረጋገጥም ። የአሸባሪው ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሆነውን ሕዝብ ልቦና እና አመለካከት ከወዲሁ መማረክ ግድ ይላል። አሸባሪውን ከሕዝብ የመነጠል የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል ።
አሜሪካ ለ20 አመታት ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገፍግፋ በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ሰውታና አካል ጉዳተኛ አድርጋ በባዶ እጇ አጨብጭባ ተሸንፋና ተዋርዳ የወጣችው የአፍጋኒስታውያንን ልቦና ማሸነፍ ባለመቻሏ ነው ። የግንባሩን አውደ ውጊያማ ከ20 አመት በፊት ታሊባንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ አሸንፋ ነበር። በኢራቅ በሶሪያ በሶማሊያ በየመን በሊቢያ በናይጀሪያ በማሊ በሞዛምቢክ ወዘተረፈ አሸባሪዎችን በቀላሉ ማሸነፍ ያልተቻለው ለዚህ በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com ነው። አሸባሪዎችን በጦርነት ለማንበርከክ ከሚደረገው ፍልሚያ ባልተናነሰ ርዕዮተ ዓላማቸውን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ከሚጠቀሙበትና በአካልም በስነ ልቦናም ካገቱት ሕዝብ ማውጣትና ማጽዳት ይጠይቃል ።
በአሸባሪው ሕወሓት ላይ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ የተቀዳጀነውን አንጸባራቂና በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተዋጀውን ድል ማጽናት ያልቻልነው የትግራዋይን ልቦና በቅጡ ባለመማረካችን ነው። አሁንም የማይቀረውን ወታደራዊ ድል ለማጽናትና ለማዝለቅ ከወዲሁ የትግራዋይን ልብ በማሸነፍ ልናጅበው ይገባል። ይበል የሚያሰኙ ሕዝባዊ ውይይቶችና ሌሎች ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ከሸኔ ከጉሙዝ ታጣቂዎችና ከሌሎች አሸባሪዎችና ሽፍቶች ጋር የምናደርገውን ትግልም እንደዚሁ። በውል ባንገነዘበውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያውያንን በተለይ ደግሞ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ ብዙ ጥረዋል። ሩቅ መንገድ ተጉዘዋል። ዋጋም ከፍለዋል። ለሰላም ካላቸው ቁርጠኝነትና ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በውትድርና ሕይወታቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት፤ ጓደኞቻቸውንና ወንድማቸውን ስለነጠቃቸው፤ ጦርነት የአገርን ኢኮኖሚ ምን ያህል እምሽክ ድቅቅ እንደሚያደርግና እንደሚያወድም አበክረው ስለተገነዘቡና፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ይበቃዋል በሚል ጽኑ እምነትና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች የድሀን ልጅ የእሳት ራት ያደርጋሉ እንጂ እነሱ አይዋጉም በማለት ለትግራይም ሆነ ለሌሎች ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ እስከ መጨረሻው ሰዓት ሆደ ሰፊነትንና ትዕግስትን መርጠዋል ። አበው ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንዲሉ በከሀዲውና የእናት ጡት ነካሹ በሆነው ትህነግ መከላከያችን፣ ሉዓላዊነታችን፣ አገራችንና ሕዝባችን ለሰላም በታመኑ ከጀርባ ተወጉ።
ባጎረሱ ጣታቸውን ተነከሱ። አሸባሪው ሕወሓት በእብሪት በጫረው እሳት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፋ ፤ አካል ጎደለ ፤ የአገር ኢኮኖሚ ክፉኛ ደማ ፤ የሽብር ኃይሉ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማቶች መልሶ ለመጠገን ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆነ። በወረራው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዕለታዊ እርዳታ ለማቅረብ ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጭ ተደርጓል። ልብ አርጉ ይህ ወታደራዊውን ወጭ አይጨምርም። ጥገና ሲያካሒዱ የነበሩ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በግፍ ተገደሉ ። ይህ የትግራዋይን ልብ የማሸነፍ ጥረት አካል ነበር ። መንግስት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀውም ለዚሁ ሰናይ አላማ ነበር ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ከጠብመንጃ አዙሪት ለማውጣትና ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች ያልሄዱበትን የሆደ ሰፊነትና ቁጭ ብሎ የመነጋገር አዲስ መንገድ በመምረጣቸው በልኩ እውቅና ሊሰጣቸውና አብዛኛው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ሲገባ መንግሥታቸው በልፍስፍስነት ከመወቀሱ ባሻገር ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ደጋፊያቸውና ተከታያቸው ብዥታና ድንጋሬ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የትግራዋይን ልብ ለመማረክ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ግንዛቤ አልተያዘም። ይሁንና የእፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24ቱን ታላቅ ክህደት ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የአገር ሕልውናን ለማስቀጠል ያሳዩት ቁርጠኝነት እና ሠራዊቱ ከተፈጸመበት ታሪክና ትውልድ ይቅር ከማይለው ክህደት በኋላ ሞራሉና ወኔው አንሰራርቶ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ እጅን በአፍ የሚያስጭን አንጸባራቂ ድል በማስመዝገቡ አገራዊ ሞራሉ እንዲያንሰራራ አድርጓል ። እፉኝቱ ትህነግ ይታበይበትና ይመካበት የነበረውን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ በሶስት ሳምንታት ውስጥ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓም መቐሌ ሊገባ ችሏል ። ለዛውም እጅ የመስጫ የመጨረሻ ቀነ ገደቡን ጨምሮ ስድስቱ ቀናት ሳይታከሉ ።
ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓም መንግስት ለሰብዓዊነት ሲል ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም አፋርንና አማራን በመውረር ሸዋ ድረስ የነበረው ወራሪው እንደ ታች አምናው አሁንም እየተገረፈና እንደ ቅጠል እየረገፈ እግሬ አውጭኝ እያለ ነው ።ያለፈውን ስህተት ላለመድገም ከስህተታችን ተምረን ወታደራዊ ድሉን በፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ድል ልናጅበው ይገባል።
የእነ ባቲ ኮምቦልቻ ደሴና ሌሎች ከተሞች ከወራሪው ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባለፈው ማክሰኞ እንዳሳሰበው ድሉን መያዝ ማጽናትና መጨመር ግድ ይላል። እንደ መውጫ አሸባሪው ሕወሓት እንደ ሰብዓዊ ጋሻና እንደ መደበቂያ የሚጠቀምበትን የትግራዋይ ልብና አመለካከት ማሸነፍ ሳይቻል ወታደራዊ ድሉ ሙሉኡ አይሆንም።
በጦር ሜዳ የሚገኘው ወታደራዊ ድል የትግራዋይን ልብና አመለካከት በማሸነፍ ካልታጀበ የአሸባሪው ሕወሓት መደምሰስ ብቻ ድሉን ዘላቂና አስተማማኝ አያደርገውም። የኢፌዴሪ መንግሥት ከጦርነቱ ባልተናነሰ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ የተግባቦት ስልት ነድፎ ሌት ተቀን መሥራት አለበት።
ደጀኑን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ለማነቃነቅ እና የአሸባሪው ሕወሓትን ጭካኔና አገር የማፍረስ ደባ ለማጋለጥ እየሰራው ባለ ልክ የትግራይ ሕዝብን ለመማረክም በአግባቡ መንቀሳቀስ አለበት ። ለ50 ዓመታት ያህል እንደ መዥገር ደሙን ከሚመጠው፤ የወላድ መካን ካደረገው፤ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ በአፈናና ጭቆና ባሪያ ካደረገው፤ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ደም እያቃባው ካለ ፤ በስሙ እየማለና እየተገዘተ የቡድናዊ ጥቅም ማሳደጃ ካደረገው ፤ ወዘተረፈ ይልቅ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት በፍቅር በሰላም በነጻነትና በአንድነት የመበልጸግ አቅምና ተስፋ እንዳለው፤ ለአሸባሪው ሕወሓት ግለኛ ጥቅም ሲባል ልጆቹ ከጉያው እየተነጠቁ ለጦርነት እንደማይማገዱ፤ የትግራዋይ እጣ ፈንታ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመስዋዕትነት የተሳሰረና የተገመደ መሆኑን ደጋግሞና በጥበብ አዋዝቶ በመግለጽ ልቡንና አመለካከቱን ማሸነፍ አለበት።
በስሙ እየማለና እየተገዘተ ለ27 ዓመታት አገርንና ሕዝብን በጠራራ በአደባባይ እየዘረፈ ራሱን ሲያበለጽግ እሱን ከድህነት አረንቋ ከሴፍቲነትና ከተረጅነት ነጻ እንዳላወጣው ፤ አንድ ጊዜ ዐቢይ ሊያንበረክክህ ነው ሌላ ጊዜ አማራ ሊያጠፋህ ነው እያለ፤ በተሳሳተ ትርክትና ቁጭት ሲያታግለውና ሲማግደው የኖረው ፤ ከተደቀነብህ አደጋ የምታደግህ እኔ ብቻ ነኝ የሚለው ለግል ጥቅሙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን ደጋግሞ ማጋለጥ ያስፈልጋል። የትግራይ ሕዝብ መጻኢ እድል ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በደም የተሳሰረ ነው !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 30/2014