ኢትዮጵያ የራሷን ሥርዓተ መንግሥት ቀርጻ አገር መሥርታና አገር ሆና እየኖረች በነበረችበት ጊዜ ዛሬ አገር ከመሆን አልፈው ከእኛ በላይ ላሳር በሚል አላዋቂ የጎረምሳ ትዕቢትና እንስሳዊ የጡንቻ ትምክህት የዓለም አገራትን አገር ሆኖ የመኖር ነፃነት እያጨለሙ የሚገኙት አሜሪካና ምዕራባውያን እንኳን አገርና መንግሥት ሊመሠርቱ አገር የሚለው ቃል ራሱ ገና በቋንቋቸው ውስጥ አልተፈጠረም ነበር።
ያኔ እነርሱ እንኳንስ ተመሳሳይ ሥነ ልቦናዊ ውቅር የጋራ ማንነት ያለው ሕዝብ በቋሚነት የሚኖርበት፣ በማንኛውም ጊዜ ማንም ጣልቃ ሊገባበት የማይችል ተለይቶ የሚታወቅ ሉዓላዊ ሥነ ምድራዊ ክልል ያለው አገርና መንግሥት ሊመሠርቱ እንደ እንስሳት በየመንጋቸው ተሰማርተው፤ እግራቸው ወደመራቸው ሁሉ እየተጓዙ በየሄዱበት የሚኖሩ ትንንሽ ከርታታ ጋርዮሻዊ ጎሳዎች ነበሩ።
የኢትዮጵያና የምዕራባውያን የአገርነትና የመንግሥትነት ታሪክ በእጅጉ የተራራቀ ነው። በዚህ ጽሑፍ አውድ «አገር» ስንል አሜሪካና ምዕራባውያኑ አገር ከሆኑ ወዲህ ያለውን ጊዜ ብቻ ማለታችን እንደሆነ ልብ ይባልልን። አሁን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በዋነኝነት ይዘነው ለተነሳነው ርእሰ ጉዳያችን አጉልቶ መመልከቻ የንጉሥ ሰገነት ሆኖ ያገለግለን ዘንድ የአገራችንንና የምዕራባውያንን የእርስ በእርስ ግንኙነት ወደኋላ መለስ ብለን በወፍ በረር ለማስታወስ እንሞክራለን።
የምዕራባውያኑና የእኛ ግንኙነት ታሪክ እንዲህ ነው። እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በታሪክ ጸሐፊዎች፣ በጠቢባንና አሳቢዎች ዘንድ በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በቀር በመንግሥታት ደረጃ ብዙም አንተዋወቅም ነበር። እግዜር ይመስገን፤ እነርሱም አያውቁንም እኛም አናውቃቸውም ነበር።
ከአስራ ስድስተኛው መቶ አጋማሽ በኋላ ግን ስለ ኢትዮጵያ ዝና አብዝቶ ይሰማ የነበረው የወቅቱ የአውሮፓ ኃያል መንግሥት ፖርቹጋል ጋር መጀመሪያ በራሱ ፍላጎት (ጥቅም) ቀጥሎ ልክ እንደዛሬው ኢትዮጵያ ከውስጥ በተፈጠረባት የሕልውና ጦርነት ምክንያት በእኛ ፍላጎትና ግብዣ በጥቂቱም ቢሆን ግንኙነት ተጀመረ። በቀሪው የአፍሪካ ክፍል ግን ከአስራ ስድስተኛው መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ለሦስት ክፍለ ዘመናት የዘለቀና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በኃይል ከቀያቸው እየተፈናቀሉ በገፍ ወደ አሜሪካና ካሪቢያን የተጋዙበት የባሪያ ንግድ በዚሁ በፖርቹጋል መንግሥት አጋፋሪነት በምዕራባውያን እየተካሄደ ነበር። በዚህም ለሕይወት እጅግ አደገኛ በሆኑ ሃሩራማ በረሃዎች ላይ በከባድ የጉልበት ሥራዎች ላይ በግዳጅ እንዲሰማሩ እየተደረጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በአሰቃቂ ሁኔታ በውሃ ጥም፣ በረሃብና በበሽታ እንዲያልቁ ተደርገዋል።
ምዕራባውያኑ ደግሞ የአፍሪካውያኑን ጉልበት በመጠቀም አዲስ በቆረቆሯቸው የአሜሪካና የካሪቢያን አገራት ይዞታዎቻቸው ሰፋፊ የጥጥና የሸንኮራ እርሻዎችን እያረሱ፤ በአፍሪካውያን ላብ ከላብ አደርነት ተላቀው ልፋት የሌለው የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ ችለዋል።
በአፍሪካውያን አቅም ከባሪያ ንግድ በኋላ አፍሪካን በኃይል አንበርክከው በቅኝ የሚገዙበትንም አቅም ገንብተዋል። ምዕራባውያኑ በባሪያ ንግድ አማካኝነት የአፍሪካውያኑን ጉልበት በመጠቀም ለሦስት ምዕተ ዓመታት ያካበቱትን ሀብት በመጠቀም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ከፈጠሩና በካፒታልና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ አገራዊ አቅም ከገነቡ በኋላ በአልማዝና በወርቅ የተሞላው ድንግሉ የአፍሪካ ምድርና ገና ያልተነካው ዕምቁ የአፍሪካ ሀብት ይበልጥ እያጓጓቸው፤ ለአፍሪካ ያላቸው ፍላጎት እጅጉን እያየለ ሄዷል። በመሆኑም ሕዝቧን በቋሚነት በቅኝ ለመግዛትና በተደራጀ መንገድ ሀብቷን ለመበዝበዝ አፍሪካን ለመቀራመት በእኛ አቆጣጠር በ1876 ዓ.ም በርሊን ላይ በይፋ ጉባኤ ጠርተው መክረዋል፤ አፍሪካን ከፋፍሎና ተከፋፍሎ ለመግዛት የሚያስችላቸውን የስምምነት ውሳኔም አሳልፈዋል።
ምዕራባውያኑ አህጉራችንን ለመውረር እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ከፖርቹጋል በቀር አንድም ሌላ የአውሮፓ አገር አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ ፍላጎት አልነበረውም። ከሌላው የአፍሪካ ክፍል ጋርም ቢሆን ከላይ በጠቀስነው መንገድ በተካሄደው የባሪያ ንግድ አማካኝነት ያደርጉት ከነበረው መደበኛ ያልሆነ አነስተኛ ግንኙነት በቀር አስከ አስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ድረስ ምዕራባውያኑ ከአፍሪካውያን ጋር በመንግሥታት ደረጃ የሚደረግ ይኽ ነው የሚባል መደበኛ ግንኙነት አልነበራቸውም።
በርሊን ላይ ተቀምጠው አፍሪካን ለመቀራመት በወሰኑት ውሳኔ መሠረትም ሳይውሉ ሳያድሩ በፍጥነት ወደ ውቧ የጥቁር ምድር ገብተው ምዕራባውያኑ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች ሕዝቦቿን በግፍ በቅኝ ግዛት መግዛት፣ ሀብቷን በገፍ መበዝበዝ ጀመሩ። ከአሥራ ሁለት ዓመት ባልበለጠ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ ዘጠና በመቶ የሚደርሰውን የአፍሪካ አህጉር በቁጥጥራቸው ሥር ማዋል ቻሉ። በበርሊኑ አፍሪካን ተከፋፍሎና ከፋፍሎ የመግዛት
ኢምፔሪያሊስቶች ስምምነት እጣ ወጥቶለት ኢትዮጵያን ለመግዛት ተስማምቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄድ የተወሰነለት (የተወሰነበት ሆነ እንጂ በኋላ) ጣሊያን ነበር። እንግዲህ ምዕራባውያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የአፍሪካ ክፍል በኃይል ተቆጣጥረው ሕዝቦቿን በጭካኔ እያሰቃዩ በነበሩበት ወቅት በዚያ ሁሉ ፈጣን ግስጋሴያቸው መሃል በ1888 ዓ.ም «የነጭ የበላይነት» የተባለው የዚህ ሰብዓዊ ተውሳክ ተሸካሚ ከነበሩ እብሪተኞች መካከል አንዱ የነበረው የጣሊያን ቅኝ ገዥ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ የመጣው።
አገሪቱን በኃይሉ አንበርክኮ ሕዝቦቿን በባርነት ለመግዛት ከጥቁር ሕዝብ አገር አንዷ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የመጣው ምዕራባዊ ቅኝ ገዥ ኃይል 1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ባደረገው የግፍና የወረራ ጦርነት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ አሳፋሪ ሽንፈት ተሸነፈ።
እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ሕዝብ «ምንጊዜም የበላይ ነን» ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸነፈ። በዚህም ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ድል በእኛ በኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ተጻፈ! ከራሱ ውጪ ሰውን እንደ ሰው የማይቆጥረው ዓለሙን ሲያምሰው የነበረው መድኃኒት የለሹ የነጭ የበላይነት ክፉ የሰውነት በሽታም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር መድኃኒቱ ተገኘለት!።
የነጭ ወራሪንና የነጭ የበላይነት ወረርሽኝን ያስቆመው ማርከሻው መድኃኒት ስምም«ኢትዮጵያዊነት» የሚባል መሆኑን የዓለም ሕዝብ ሁሉ አወቀ። በዚህም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው የሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር ለተገኙ ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የነፃነት መታገያ አርማ፣ የድል አቅጣጫ ጠቋሚ፣ የአሸናፊነት ቋሚ ምልክት ሆነ! በአንጻሩ ከእኔ በላይ ላሳር ይል በነበረው ምዕራባዊ ኢምፔሪያሊስት የቅኝ ገዥ ኃይል ዘንድ ደግሞ ሽንፈቱ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ። የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝብ፤ በአጠቃላይ ለሰው ዘር ሁሉ የፍትሐዊነት፣ የእኩልነትና የነፃነት ምልክት የመሆኑን ያህል፤ በሰው ልጆች እኩልነት ለማያምነው «የበላይ ነን» ለሚለው የምዕራባውያን እብሪተኛ ኃይል የሽንፈትና የውርደት ተምሳሌት ሆነ። በሕልውናው ላይም ከፍተኛ ስጋት ፈጠረበት።
ይህም «ስልጡንና» ኃያል ነኝ ብሎ የሚያስበውን የምዕራባዊውን እብሪተኛ ኃይል ሳይወድ በግድ ኢትዮጵያን እንዲያውቅ፣ ከማወቅ አልፎም እንዲያከብራት፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የእርስ በእርስ ግንኙነት ግብዣ እንዲያቀርብላት አስገደደው። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የውስጡን በውስጡ ይዞ፣ የሽንፈትና የውርደት ስሜቱን ዋጥ አድርጎ እና ችሎ ዲፕሎማሲን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር መደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነትና «ወዳጅነት» ለመፍጠር ተሽቀዳደመ።
ከሁሉ ቀድሞ በአዲስ አበባ ኤምባሲውን በመክፈት የመጀመሪያውን የ «ወዳጅነት»ግብዣ ያቀረበውም ተሸናፊው የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ራሱ የጣሊያን መንግሥት ሆነ። ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን… ሁሉም ምዕራባውያን ወደሚንቁትና በቅኝ እየገዙት ወደነበሩት የአፍሪካ ምድር እየመጡ ከጥቁሯ አፍሪካዊት እመቤት ከኢትዮጵያ ጋር የአቻ ለአቻ ግንኙነት ለመመሥረት ደጅ ጥናቱን ተያይዘዋል።
ሁሉም ከኢትዮጵያ ጋር የሚፈልጉትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና «ወዳጅነት» መሠረቱ። ከወዳጅነት አልፈውም ኢትዮጵያን «ለማገዝ» እና ወደ «ዕድገት» ጎዳና እንድታመራ በማሰብ የዲሞክራሲና የልማት «አጋር» ሆኑ። እነሆ በዚህ መንገድ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጀመረውን ግንኙነት ታሪክ በእነርሱ ለመቀየር የሽንፈታቸውና የውርደታቸው ምክንያት በሆነችው በጣሊያን መሪነት በ1928 ዓ.ም በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ወረራ እስከፈጸሙበት ጊዜ ድረስ ለሚቀጥሉት አራት አሥርት ዓመታት ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ «ጽኑ ወዳጅ» ሆነው ቆይተዋል።
ሽንፈታቸውን ለመበቀልና ውርደታቸውን ለመመለስ በድጋሚ የግፍ ወረራ በማካሄድ ብዙ ሞት፣ ስቃይ፣ ጥፋትና ውድመት ቢያደርሱብንም በጀግኖች አባቶቻችን ጽኑ ትግልና አስደናቂ መስዋዕትነት አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ተሸንፈው ወጥተዋል።
አፍሪካን በቋሚነት በቅኝ ለመግዛትና ሀብቷን ለመበዝበዝ ብሎም የአፍሪካውያንን ባህል፣ ታሪክና ማንነት አጥፍተው የራሳቸውን ለመጫን የታተሩት ምዕራባውያን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በአፍሪካ ምድር እንደልባቸው እየፈነጩ የፈለጉትን ቢያደርጉም ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ከተሸነፉ በኋላ ግን ኢትዮጵያን በጦርነት ማሸነፍ እንደማይቻል ተስፋ ቆርጠው ለመቀመጥ ተገደዋል።
ራሱ የ “ABYSSINIA: The Powder Bar[1]rel; A Book on The most Burning Question of the Day” መጽሐፍ ደራሲ፣ ባሮን ሮማን ፕሮችስካ፤ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያን በቀጥታ ጦርነት ገጥሞ ማሸነፍ የማይቻል መሆኑን አስታውቋል። ኢትዮጵያን ማሸነፍ የሚቻልበት ሌላ መንገድ ይኖር እንደሆነ ለአርባ ዓመታት ጥናት አደረጉ።
ከላይ የጠቀስነው የሮማን ፕሮችስካ መጽሐፍም የዚህ ጥናታቸው ውጤት ነው። ከጦርነት ሌላ ኢትዮጵያን ማሸነፍ የሚቻልበት መንገድ መኖሩን ለማወቅ ድፍን አርባ ዓመታትን የፈጀውና በመጽሐፍ መልክ የቀረበው የጥናቱ ዋነኛ ምክረ ሃሳብ በአንድ አረፍተ ነገር ተጠቃሎ ቢገለጽ የሚያስተላልፈው መልዕክትም የሚከተለውን ነው። «መቼም ቢሆን ኢትዮጵያን በቀጥታ ጦርነት ገጥሞ ማሸነፍ አይቻልም። ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ማሸነፍ ከፈለጋችሁ ማሸነፍ የምትችሉት በቀጥታ ጦርነት በመግጠም ሳይሆን ቀጥተኛ ያልሆነ ሌላ የእጅ አዙር ዘዴን በመጠቀም ነው። እርሱም ኢትዮጵያውያንን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት… ከፋፍላችሁ በማለያየትና በማዳከም በዚህም አንድ ሆነው እንዳይቆሙና እርስ በእርስ እንዲጠፋፉ በማድረግ ነው» የሚል ነው።
በዚህ ምክረ ሃሳብ መሠረትም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ ይዛ ከጀግኖች አባቶቻችን ኢትዮጵያውያን ጋር እየተዋጋች አምስቱንም ዓመታት ሙሉ በጦርነት ውስጥ ሆና ስትቆይ በጦርነት፣ በችግር ውስጥም ሆና ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የአስተዳደር ሥርዓት ቀርጻ እንደምንም ተቸግራም ቢሆን ከፋፋዩን ሥርዓት በኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ሞክራለች።
በመጨረሻም በጀግኖች አርበኞች እናቶቻችንና አባቶቻችን አይበገሬ ኢትዮጵያዊ ክንድ ተሸንፋ ከአገራችን ስትወጣ፤ በራሳችን ፍልስፍና ተመርታ፣ የከፋፋይ ሥርዓቷ አስቀጣይ፣ የጥፋት አጀንዳዋ አስፈጻሚ የሆኑ፣ በኢትዮጵያዊነት አስተሳስሮ አንድ አድርጎ የሚያኖረንን የአገራቸውን የአንድነት ሰርዶ የሚበሉ ከሃዲ የአገር ቤት ሆዳም በሬዎችን ተክታብን ሄደች/ተክተውብን ሄዱ። እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምዕራባውያኑ፤ በተለይም እንግሊዝ ጣሊያንን ተክተው ሊያስተዳድሩን ሞከሩ፣ ግን አልተቻለም። ቀጥለውም እንግሊዞች የጣሊያንና የምዕራባውያኑ «ኢትዮጵያን ከፋፍለህ፣ አዳክመህ አጥፋ ፖሊሲና ሌጋሲ አስቀጣይ» የሆኑ የትግራይ ባንዳዎችን ፈጥረው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ረጅም መንገድ ተጉዘዋል። በዚህም አገርና ሕዝብ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል።
ያለፉትን ሃያ ሰባት ዓመታትን ደግሞ እነዚህን የጥፋት ዓላማ ተሸካሚ ፈረሶቻቸውን ጭራሽ መንግሥት አድርገው ሾመው የነፃነት ምልክት የሆነችውን፣ ለበላይነት አስተሳሰባቸውና ዓለምን በኃይል አንበርክኮ በእጅ አዙር የመግዛት ሰይጣናዊ አላማቸው ሁሌም አጥብቀው የሚፈሯትን አገር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የቻሉትን ያህል ሞክረዋል። እነሆ አሁንም እነርሱ የፈጠሩት የጥፋት ተውሳክ ተሸካሚው አሸባሪው ሕወሓት ራሳቸው ምዕራባውያን እንኳን ያልቻሉትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ ለመግባት ምሎ ከእነርሱ ተባብሮ እየወጋን ይገኛል።
ዋናው የኢትዮጵያ ጠላት ከውስጥ ሆኖ ዘወትር ለምዕራባውያኑ የጥፋት እሾክ የሚያስወጋን ከውስጥ የበቀለው እርጉሙ እሾክ ሕወሓት በመሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምዕራባውያኑ ጫና እንድትላቀቅ፤ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ሁሌም ከፍ ብላ በክብር እንድትኖር ከፈለግን ጋላቢውን ሳይሆን መጀመሪያ ማጥፋት ያለብን ተጋላቢውን ነው። ያኔ ጋላቢው በራሱ ጊዜ ይጠፋል፤ ኢትዮጵያም በነፃነትና በክብር ከፍብላ ትቆማለች!::
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ኀዳር 28 / 2014