የኢትዮጵያ ሕዝቦች አሸባሪውን ሕወሓት አንቅረው የተፉት ዛሬ አይደለም፤ ቆይተዋል። ለዚህም እንደ መርግ በከበደው የ27 ዓመታት አገዛዝ ዘመኑ እንኳን ተኝተውለት አድረው አያውቁም።
ዙርያውን ከብበው ሲያሽቃብጡለት ከነበሩት የጥቅም ተጋሪዎቹ ውጪ ያለው ሰፊው ሕዝብ የእንግልት፣ የእሥር፣ የስደት፣ የሰቆቃ ኑሮ፣ ግፋም ሲል የሕይወት መስዕዋትነት እየከፈለ ከጫንቃው ላይ እንዲወርድለት ሲታገለው ኖሯል። ጠቢቡ ሠለሞን ‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው›› እንዳለው ይሄ ሁሉም የሕዝቦች አቅም ተደማምሮም መጨረሻ ላይ ገዝግዞና ገፍቶ ጥሎታል። ይህም ሆኖ ግን ቡድኑ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አክ ! እንትፍ ! ብሎ አንቅሮ የተፋው መሆኑን ለማመን አልፈቀደም ።
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገርና ዓለም ያለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አደባባ ወጥቶ ቡድኑን በማውገዝ እያሰማ ያለው ድምጽ ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ ያመላከተ ነው ። ለዕውነት ያደሩ የውጭው ዓለም አንዳንድ ጋዜጠኞችና ሰዎችም ድምጹን ተጋርተውታል። ከሕዝቡ ጎን ቆመው አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል። ህዝቡ በሰልፎቹ ጭቆናህ፣ ኢ-ሰብዓዊነትህ በቅቶናል፤ አንተን ከጫንቃችን ለማውረድ ብዙ መስዕዋትነቶችን ከፍለናል፤ አሁንም እየከፈልን ነው፤ አርፈህ ተቀመጥ ብለውታል።
አገራችንን ከሚበትን ሉዓላዊነቷን ከሚገዳደር ኢትዮጵያን አፈራርሶ አገረ ትግራይን የመገንባት የዕብደት ቅዠትህ ታቀብ ሲልም አስጠንቅቆታል። በአንተ ለሚነዱትና ቅኝ ለመግዛት ተመኝተው ላልተሣካላቸው የውጭ ኃይሎችም ዲሽቃና መድፍ ፊት ቆመን በመስዋዕዋት ለነፃነት መውደቃችንን አስታውሳቸው፤ በባርነት መኖር የአባቶቻችን ታሪክ እንዳልሆነ ንገራቸው።
ዛሬም አገራችንን ለመጠበቅ እንደምንወድቅና መስዕዋትነት እንደምንከፍል አስረዳቸው የሚል የአሸናፊነት ድምጹን አሰምቶታል። አገር ለመሸጥ ቀብድ የበላው አሸባሪው ህውሓት ግን አሁንም በጄ አላለም።
የኢትዮጵያውያኖች ድምጽ የአገሪቱን አደባባይ በሞላበት ሁኔታ በውድህ ባይሆን በጠመንጃ መልሼ በግድ አስተዳድርሃለሁ በሚል በውጭ ኃይሎች እየታገዘ፣ የዜጎች ሕይወት እያጠፋና እያፈናቀለ ይገኛል። ቡድኑ ተሸንፎ እየሸሸ ባለበት ሁኔታም በእልህና ቁጭት ያለ የሌለ ንብረት እያወደመ ነው የሚገኘው።
ቡድኑ በመላው ሕዝባችን የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ዓመታቱን በእኩይ ተግባር ድርጊቱ ተጠምዶ ቆይቶባቸዋል። ‹‹እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል›› አለች አሉ እንደተባለችው አህያ አገሪቱን እኔ ካልገዛሁ፣ የበትረ ሥልጣኑን መዘውር እኔ ብቻዬን እንደፈለግኩ ካልዘወርኩት ምን ሊረባኝ በማለት ብዙ ዳቦ ተቆረሰ ጨዋታው ፈረሰ ዓይነት የቤት፤ እቤት የልጆች ጨዋታ ዓይነት ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።
ሕግ አርቅቆ፤ መመሪያ አውጥቶ እሱ ራሱ መተካካት ብሎ የዘረጋውን አሠራር መሠረት ያደረጉ ትግበራዎችን አጣጥሏል ፤ በግልጽ ተቃውሟል፤ በተጻረረ መንገድ በመቆም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩን ተፈታትኗል። ለዚህም ለሕግ ባለመገዛት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ክልላዊ አድርጎ ያረፈበት ማሣያ ይሆናል።
የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሉ የመደበውን በጀት ጥርግ አድርጎ እየበላ ከብዙ አገራዊ አጀንዳዎች ራሱን ማግለሉን ሲያውጅ ከርሟል። በዚሁ በጀት በሚተዳደር የክልሉ የመረጃ ማሰራጫ በመጠቀም ለአገሪቱ ሕግና ራሱ ላረቀቀው እንዲሁም ፉከራና ቀረርቶውን በኩራት ሲያሰማበት ለኖረው ሕገ መንግሥት እንኳን አልገዛም ብሎ እያከናወናቸው የነበሩ ሕገወጥ ሥራዎቹን ለፍፏል።
በዚሁ ዘዴ በመጠቀምም የገዛ ቁንጮ አመራሮቹ በተቀመጠ አሰራር እንደ እሬት እየመረራቸው ይሁንታቸውን ሰጥተዋቸው ጭምር ወደ መንበረ ሥልጣኑ የመጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድንና የለውጥ ኃይሉን የሚያብጠለጥሉ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትም ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ነበር። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መቐለ በሚገኘው የሠሜኑ ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በግላጭ ጥቃት በመፈጸም አገሩን በይፋ ክዶና፤ በአገሩ ላይም ወረራ መፈጸሙን አረጋግጧል።
የራሱ ድርጊት ለራሱ ‹‹ለቀባሪው አረዱት›› ዓይነት ተረት ካልሆነበት በስተቀር ሕዝብ ይሄን ሁሉ ሥራውን ያውቃል። ‹‹ከኔ በላይ አገር መሪ ፣ ከኔ በላይ አልሚ፣ ከኔ በላይ ለሕዝብ አሳቢ የለም›› ሲል የኖረው አሸባሪው ሕወሓት ይሄ መርሁ ‹‹ከኔ በላይ ብሄር›› በሚል ከመንደር አልፎ እስከ ቡና መጠጫ በመውረድ በጠበበ ግላዊ ፍልስፍና ተውጦ የሕዝቡን ጥቅም ሲበዘብዝ መኖሩና አገሪቱን ማራቆቱም ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ አይደለም። አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው ።
የሠሜኑ ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አሀዱ በማለት ወረራውን የከፈተው ብዝበዛውን አጠናክሮ ለመቀጠል መሆኑም በአማራ ክልል ላይ ይልቁንም በሠሜን ወሎ ዞን የፈጸመው፣ እንኳን እሱ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ፋሽሽት እንኳን ያልፈጸመው የጭካኔ ጥግ የታየበት ተግባርና ዘረፋ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እንደ ውዳሴ ማርያም ሌት ከቀን ቆሜለታለሁ እያለ በመደጋገም በስሙ ሲነግድበት የኖረውን አርሶና አርብቶ አደር ከብት አርዶ በልቷል ፣በጥይት ደብድቦ ገድሏል ።
ጎተራውን እስከ ቦሀቃ ሊጥ ዘልቆ ገልብጧል። ከአርሶና አርብቶ አደሩ ባላነሰ ቆሜላቸዋለሁ ብሎ እንዲሁ በስማቸው በመነገድ ከአገር እስከ ውጭ የዘለቀ እርዳታ ሲሰበስባቸው የኑሩትን ሴቶች ደፍሯል፤ አዋርዶና አሳፍሯል። አሰልፎም ለአዋራጅና ለደፋሪም ሰጥቷል። ለ27 ዓመታት ቆሜልሃለሁና የአንተ ነኝ ብሎ ሲነግድበት በኖረው በሰፊው የትግራይ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ የጥፋት ተግባራትን ፈጽሟል። የትላንቱ ሳይበቃው ዛሬም እወክልሃለሁ በማለት በደምና በሥጋ ሰንሰለት ከተጋመዱ ወገኖቹ እያቆራረጠው ይገኛል።
ይህ የአገርን አንድነት ስጋት ውስጥ የመክተት የቀደመ እኩይ ዓላማው አንድ አካል ነው። ይህም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ እውነታውን በሰከነ መንፈስ ሲረዳው ነገና ከነገወዲያ ጥርጉም አልባ መሆኑ የማይቀር ነው። በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ብሄርን መሰረት ባደረገው ቡድን የመተካቱ የአሜሪካ ሩጫም ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል ዓይነት እሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል ።
ቡድኑ አሁን ላይ በጠመንጃ አፈሙዝ እንዳሻው ሲፈርድና ሲቀድበት ወደነበረው መንበረ መንግሥቱ የመመለስ ተስፋው ጥቁር ታሪክ በሚሆን ደረጃ እያበቃለት ነው ። ይኸው ነው በቃ ! እንደ አገር የሚጠብቀን ብሩህ ተስፋችን ከመቼውን ጊዜ ይልቅ ወደ እኛ እየቀረበን ነው። በምዕራባውያኑ ድጋፍ የተቋቋመ ጉልበቱም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና በኢትዮጵያውያን ሕዝቦች የተባበረ ብርቱ ክንድ ደክሟል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኀዳር 28 / 2014