አዲስ አበባ፡- የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በምዕራባውያኑ የተከፈተባትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከመመከት ባለፈ የውጭውን ማኅበረሰብ ሥነልቦና መግዛት የሚያስችል አቅም ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ -ተግባቦት ትምህርት ክፍል ትናንት ‹‹ የቀውስ ወቅት እና የዲፕሎማሲ አዘጋገብ›› በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በምዕራባውያኑ የተከፈተባትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በመከላከል ረገድ አንጻራዊ የሆነ ለውጥ አሳይተዋል።ይሁንና ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀና የውጭውን ማኅበረሰብ ቀልብ በመግዛት ብሎም እውነታውን ያገናዘበ አጀንዳ ከመፍጠር አኳያ ፊት መሪ መሆን አልቻሉም።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የሚዲያ ባለሙያ ሙሐመድ አል አሩሲ በመድረኩ የውይይት መነሻ ሃሳብ ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አንጋፋና ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት ቢኖሯትም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሥራዎችን ከመሥራት ረገድ እምብዛም ጎልተው አይታዩም።በተለይም አገሪቱ አሁን ከገጠማት የውስጥና የውጭ ጫናን የሚመጥን የሚዲያ ሥራ መሥራት ላይ ብዙ ይቀሯቸዋል፡፡
‹‹ አብዛኞቹ ሚዲያዎቻችን የውጭ ኃይሎች በየቀኑ የሚነዙትን የሃሰት ዜና እና ፕሮፖጋንዳ በመመከት ሥራ ላይ የተጠመዱ ናቸው›› ያሉት አቶ ሙሐመድ፤ ይህም በመሆኑ የውጭ ኃይሎች የሚፈልጉትን አጀንዳ መልሶ በማስተጋባት የበለጠ ተጽእኖዎችን እንዲያሳርፉ እድል የፈጠሩላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በአንጻሩ ምዕራባውያኑም ሆነ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎች ሊቢያና ሶሪያ ላይ ሲፈጽሙ እንደነበሩት ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሃሰት ዘመቻቸው ለመቆጣጠርና የሥነልቦና ቀውስ ለመፍጠር ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የግብፅ መንግሥታት የአባይ ወንዝ ከግብፅ እንደሚነሳና ኢትዮጵያ የግብፆችን ውሃ እየገደበች ስለመሆኑ ሕዝባቸውን ማሳመን የቻሉት በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት ነው።በሕዝባቸው ላይ በሃሰት ተመስርተው የሠሩት የፕሮፖጋንዳና የሌሎችንም ድጋፍ ለማግኘት አስችሏቸዋል።
በተመሳሳይ ምእራባውያኑ በሚዲያዎቻቸው እያደረጉት ያሉት ተጽዕኖ ኢትዮጵያን የአጀንዳቸው አስፈጻሚ ከማድረግ ባለፈ የገዛ ታሪኳን በሃሰት እስከመገንባት የደረሰ አካሄድ የተከተለ ነው፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅና የሥነልቦና የበላይነት የሚያላብስ ሰፊ ሥራ መሥራት መቻል እንደሚገባቸው አቶ ሙሐመድ ተናግረዋል።በተለይም የኢትዮጵያን እውነታ በማሳየት ለምዕራባውያን አዲስ አጀንዳ መፍጠር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የቀውስ ወቅት ዘገባን በሚመለከት በመድረኩ የውይይት ሃሳብ ያቀረቡት የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ጌታቸው ንጋቱ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት ባልተናነሰ በምዕራባውያኑ የሚደረግባት የፕሮፖጋዳ ዘመቻ በሕዝቦቿ ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና እያሳደረ ይገኛል።በተለይም በሃሰተኛ ዜናዎችና መረጃዎች በሕዝቡ ላይ እየፈጠሩ ያሉት ውዥንብር ጉዳቱ በቀላሉ የሚተመን አይደለም፡፡
‹‹ በአገራችን ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንደሚባለው ሁሉ በሃሰተኛ ወሬዎች የሚደረጉብን ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ሳይቀር ጥርጣሬ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ምዕራባውያኑ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተሰደዱ ዜጎችን እንደ ጥሩ እድል በመጠቀም የሚያስተላልፉት የሃሰት ዜና በእርዳታ ስም ንግድ እስከ መነገድ የሚደርስበት ነባራዊ ሁኔታ መታየቱን አስረድተዋል፡፡ ከጦርነቱ የሚያገኙትን ትርፍ ለማስቀጠል ሲሉ ብቻ እውነታውን አንሻፎ በማቅረብ የዓለም ማኅበረሰብ ሥነልቦና መግዛት እንደቻሉ ተናግረዋል።
ለዚህም አሜሪካኖቹ በሱማሊያ፤ በሊቢያና በሶሪያ ያደረሱትን የቁስና የሥነ ልቦና ጥፋት አብነት አድርገው ጠቅሰዋል።‹‹ አገሪቱን ከመውረራቸው በፊት ያስተላለፏቸው የሃሰት ዘገባዎች ለወረራቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሏል›› ብለዋል። የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች የፖለቲከኞቻቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም ሲሉ በስሩ ተከታታይ በሃሰት ዘገባ እውነታው እንዲደበቅና ብዙኃኑን የእነሱ ዓላማ አስፈፃሚ እስከማድረግ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ በመገንዘብ ወቅቱን የሚመጥኑ ዘገባዎችን ሊሠሩ እንደሚገባ፤ ብሎም የሕዝቡን ሥነ ልቦና መገንባት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመከላከልና እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት ከተለመደው የዲፕሎማሲ ሥራ ባሻገር ለዲጂታል ዲፕሎማሲ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።በተለይም ከዲያስፖራው ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ያለው ተግባር ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና በማህበራዊ ሚዲያው የሚደረገው ይህ የዲፕሎማሲ ሥራ በሚስጥር የሚሰሩ ሥራዎችን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ከመሆኑና በተቃራኒ ጎን ለተሰለፉ ኃይሎች እድል የሚሰጥ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ የዓለምን ማኅበረሰብ መድረስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።በተለይም ይህ የመገናኛ አውታር ለአሸባሪዎች መፈልፈያ እየሆነ በመምጣቱ በዲጂታል የሚሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ ይህንን ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ልኬ ሞላ በበኩላቸው፤ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ዩኒቨርሲቲው ከተሰጡት ተልዕኮዎች ዋነኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ መድረኩ አገሪቱ ዲፕሎማሲውና በሚዲያው የሚታዩ ድክመቶችን ነቅሶ ከማውጣት ባለፈ የመፍትሔ ሃሳቦችንም ለማመንጨት እድል የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። እውቀት መር መረጃ በመስጠት በዘፈቀደ የሚመራውን የሚዲያዎችን አሠራር በመቃኘት ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሕዝቡንም ግንዛቤ በማሳደግ ከውጭው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኀዳር 28 / 2014