ዓለም ላይ በአስተሳሰቡ እንደ በረታ ማህበረሰብ ስልጡን አለ ብዬ አላስብም። የአብዛኞቹ አገራት የስልጣኔ ምንጭ አስተሳሰብ ነው። በአስተሳሰቡ የበረታ ማህበረሰብ ድሀ ሆኖ አያውቅም።
ይሄን እውነት ወደ አገራችን ስናመጣው አስደንጋጭ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱም በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ማህበረሰብ ስለሌለን ነው። የሕወሓት የስልጣን ዘመን ከሀሳብ ይልቅ ኃይል፣ ከመነጋገር ይልቅ መገፋፋት ያየሉበት ጊዜ ነበር። ውሸትና የፈጠራ ወሬዎች ታሪክና ሰውነትን የመረዙበት የባለጊዜዎች ድራማ ነበር።
ኢትዮጵያን የሳሉ እጆች በታሪክ ተመስጋኝ የሆኑትን ያክል ተወቃሽ የሚሆኑበትም እድል አለ። ዘመነ ሕወሓት የኢትዮጵያዊነት የዝቅታ ጥግ ነው። ዛሬም ድረስ ከፍ ያላልነው በዚህ ከሀዲ ቡድን በተኳሉ የግፍ እጆች አማካኝነት ነው። አገር በሀሳብ ስትመራና በሀይል ስትመራ አንድ አይነት አይደለም።
ሀገር በሀሳብ ስትመራ ምክንያታዊ ትውልድን ነው እየፈጠረች የምትሄደው። አገር በሀሳብ ስትመራ ሚዛናዊና አመክንዮአዊ ነፍስና ስጋ ነው የሚፈጠረው። አገር በሀይል ስትመራ ግን ልክ እንደ አሁኑ እኔና እናተ እኔነትን የምናራምድ ራስ ተኮር እሳቤን እናዳብራለን። ራስ ተኮር እሳቤ ደግሞ ሀገር ከማፈራረስ በስተቀር የሚያመጣው ትርፍ የለም።
አሸባሪው ሕወሓት አሁን ላይ እኔነትን በተላበሱ አማፂያን ሀገር እያወደመ ያለው በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ስላለፈ ነው። አገራችን መልካችን ናት። የኢትዮጵያዊነት ቅይጥ መልካችን፣ ቅይጥ ማንነታችን ሀገር በሚሏት ግኡዝ እውነት ውስጥ የቆመ ነው። አንድ ሰው ሀገሩን ሲወድና ራሱን ሲወድ የተለያየ ነው።
ሀገሩን የሚወድ ሰው ሌላውንም የመውደድ ሀይል በውስጡ አለው። ራሱን የሚወድ ሰው ግን ሁልጊዜም የራሱ ነው። ሁሉንም ነገር ከራስ ጥቅም ጋር ብቻ በማገናኘት የሚኖር ነው። ራስን ብቻ በመውደድ ውስጥአገር የለችም። እኛና ሌላው ሰው ያለው አገርን በመውደድ ውስጥ ነው። ራስን ብቻ መውደድ ጎደሎነት ነው። የኢትዮጵያዊነትን ጸዐዳ መልክ የሚያሳድፍ ሰይጣናዊ መንፈስ ነው።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ አሸባሪው ሕወሓት ነው። የቡድኑ መልክ የኔነት መልክ ነው። ከትላንት እስከ ዛሬ የኖረው አገሩን ሳይሆን ራሱን በመውደድ ነበር። ህዝቡን ሳይሆን ራሱን በመጥቀም ነበር። አገር መውደድ መነሻውም መድረሻውም ህዝብ ነው። ራስን መውደድ ግን በተቃራኒው የሀገርንና የህዝብን ጥቅም ለራስ ማዋል ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት የፖለቲካ አካሄድ አገርና ህዝብ የሌሉበት የኔነት ቀመር ነው። በዚህ የፖለቲካ ርእዮት ሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ተጠቀመች? ህዝባችንስ ምን አገኘ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ ያለፈው ስርዐት አገር በመውደድ ሳይሆን ራስን በመውደድ፣ አገር በማገልገል ሳይሆን ራስን በማገልገል ላይ የቆመ ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያን እንሳል ስል የተነሳሁትም ለዚህ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ማንነት ያስፈልጋታል።
ከትላንት የተሻለ፣ ከአምናው የላቀ ሁለንተናዊ መታደስ ግድ ይላታል። ወቅቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እየተንጸባረቀ ያለበት ሰሞን ላይ ነን። ለኢትዮጵያ መነሳት የለውጡን መንግስት ተስፋ ያደረጉ ብዙዎች ናቸው።
በዚህ የተስፋ ሀዲድ ላይ ሀገራችንን ከትላንት አላቀን ወደ አዲስ ነገ ለመውሰድ ደግሞ እኛ እናስፈልጋለን። ካለ እኔና እናንተ አዲስ መንግስትና አዲስ አስተሳሰብ አዲስ ሀገርም የለም። አዲስነት ያለው በእኔና በእናንተ ለውጥ ውስጥ ነው። እኔና እናንተ እስካልተለወጥን ድረስ የሚለወጥ ሀገርና ህዝብ አይኖርም።
የለውጡ መንግስት ራዕይና ተልዕኮ እውነት የሚሆነው እንኳን አስቀድመን እኛ ስንለወጥ ነው። ማንኛውም ነገር በእኛ በኩል ወደ ሀገርና ወደ ትውልዱ የሚንጸባረቅ ነው። ማንኛውም ነገር እኔና እናንተን መሰረት ያደረገ ነው።
ባለን በሚኖረን እውቀትና ክህሎት አገራችንን እናገልግል። ሕወሓት አገር ለማበላሸት ከእውነት ይልቅ ውሸትን ነበር የተጠቀመው። ከሀዲዎቹ ትላንትናና ከዛ በፊት ባለው የስልጣን ዘመናቸው ራሳችንም ሆነ ለሌሎች እንዳንጠቅም አድርገው በአጉል አስተሳሰብ የዘረኝነትን ቀንበር አሸክመውን ነበር። ከእውነት ይልቅ ውሸት እየፈጠሩ ኢትዮጵያዊነትን ሲያቆሽሹ ነበር። እኛ በተራችን በእውነትና በሀቅ ሀገራችንን ለመሳል
እንነሳ። ለሚመጣው ትውልድ የምናስረክባትን መልካም ኢትዮጵያ እንፍጠር እላለው። እያንዳንዳችን ለሕወሓት የማትመችን ኢትዮጵያ የመፍጠር የቤት ስራ አለብን፣ ለጠላቶቿ የማትንበረከክን አገር የመፍጠር የቤት ስራ። እያንዳንዳችን ሀላፊነት አለብን፤ አዲስ ሀገርና አዲስ ትውልድ የመፍጠር ሀላፊነት። በሀሳባችን ኢትዮጵያን እንሳል። በእውቀታችን ህዝባችንን እናገልግል። የአሁኗ ኢትዮጵያ በሕወሓት ውሸት፣ በሕወሓት ጭካኔ፣ በሕወሓት የፖለቲካ አስተሳሰብ የተፈጠረች ናት።
ከዚህ የተሳሰተ መስመር ወጥተን ወደ ላቀ ህዝባዊ እሳቤ እንሸጋገር። በጋራ ሀሳብ፣ በጋራ እውነት፣ በጋራ ጥበብ የተሳለች ሀገር ታስፈልገናለች ይቺ አገር ደግሞ በእኔና በእናንተ ውስጥ ነው ያለችው። እንሳላት። አሁን ላይ ብዙ ነገራችን እየተበላሸ የመጣው ራሳችንን ብቻ በመውደዳችን ነው።
ባለፉት የፖለቲካ ስርዐቶች ውስጥ የተማርናቸው እኩይ ትምህርቶች አገር የሚያስወድዱ ሳይሆን ራስን የሚያስወድዱ ነበሩ። ህዝብ የሚጠቅሙ ሳይሆኑ ግለሰብን የሚጠቅሙ ነበሩ። አሁን ላይ እነዛ ትምህርቶች ፍሬ አፍርተው በሁሉ ነገሩ የተበላሸነውን እኔና እናንተን ፈጠሩ። ይሄ የአሸባሪው ሕወሓት የሀያ ሰባት ዓመታት የፖለቲካ ቁማር ነው። ዛሬ ላይ ላለችው ኢትዮጵያ ከትላንቱ የላቀ እሳቤ ያስፈልጋታል። በዚህ ገናና እሳቤ ተራምደን የሁላችንንም የጋራ ሀገር እንሳል እላለው።
አገር እኔና እናንተ ነን። ሀገር የእኔና የእናንተ የመጪውም ትውልድ የአንድነት ነጸብራቅ ናት። እንሳላት። የአሁኗ ኢትዮጵያ ራስ ወዳዱ የሕወሓት ቡድን ለራሱ ብቻ እንድትመቸው አድርጎ የፈጠራት ናት። የአሁኑ እኔና እናንተ በሕወሓት የፖለቲካ ጭቅቅት የቆሸሽን ነን። ንሰሀ ያስፈልገናል። የሀሳብ ንሰሀ። እውነት ያስፈልገናል አገር፤ የማፍቀር እውነት። ሀሳብ ያስፈልገናል፤ አሸናፊ ሀሳብ።
ጠንካራ አገርና ትውልድ የሚገነባው በጠንካራ ሀሳብ ነው። የትላንት አዳፋ ታሪካችንን ትተን በአዲስ ሀሳብ መቆም ኢትዮጵያን ለመሳል ትክክለኛ ነገር ነው እላለው። አሁን ላይ ለአገራችን ምን እንደሚያስፈልጋት በደንብ እናውቃለን። በልማት ጎዳና ላይ ነን። በለውጥና በተሀድሶ መስመር ላይ ነን።
ለጋራ ጥቅም በጋር እየተጋን ያለንበት ሰሞን ላይ ነን። የኢትዮጵያ የምንጊዜም ጠላት የሆነውን ሕወሓትና አስተሳሰቡን እየታገልን ያለንበትም ውቅት ነው። እስቲ ከዚህ ሁሉ በኋላ የምትፈጠረውን ኢትዮጵያ አስቧት። ከዚህ ሁሉ ትግል፣ ከዚህ ሁሉ ተጋድሎ በኋላ የሚፈጠረውን አዲስ ትውልድ አስቡት።
ከፊት ለፊታችን ትንሳኤ አለን። ከፊት ለፊታችን ንጋት አለን። በዚህ እውነት ውስጥ መኖር ነው የሚያስፈልገን። በዚህ አገራዊ ስሜት ውስጥ አብሮ መሆን፣ አብሮ መቆም ነው ዋጋ ያለው። አብሮ መሆን ለየትኛውም ነገር ዋጋ ያለው ነገር ነው። ከውስጥም ሆነ ከውጪ ለሚነሱ የሉአላዊነት ችግሮች አንድነት ዋስትና ነው። የጥንት አባቶቻችን አገር ጠብቀው ያቆዩልን በአንድነት ጥበብ ነው።
እኛም አሁን ላይ ላለው ሀገራዊ ተግዳሮቶቻችን አንድነት ያስፈልገናል። የጠላቶቻችንን ሴራና ተንኮል ልንወጣ የምንችለው በተባበረ ክንዳችን ብቻ ነው። ሕወሓት አሜሪካንንና መሰል ሸረኛ ቡድኖችን ይዞ ቡራከረዩ እያለ ነው እኛ ደግሞ በአንድነትና በህብረት በመቆም የአባቶቻችንን ታሪክ መድገም ይኖርብናል። ዓለም ላይ በአንድነት እንደቆመ ህዝብ ለጠላቶቹ አስፈሪ ነገር አለ ብዬ አላስብም።
ጠላቶቻችን የሚደፍሩን መለያየታችንን አይተው ነው። በአድዋ የታየው የአንድነት መንፈስ በህዳሴ ግድባችን ላይ ታይቷል። አሁንም አገር ለማፍረስ በተነሳው የሕወሓት ቡድን ላይ ሊደገም ይገባል እላለው። ይሄ ሁሉ አገር ለመሳል፣ ትውልድ ለመፍጠር እየሄድንበት ያለውን መንገድ ያሳያል ባይ ነኝ። ከዚህ በኋላም ባሉት የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ላይም በቻልነው ሁሉ ኢትዮጵያን ለመሳል መበርታት ይጠበቅብናል።
ዛሬ ላይ ልንሄድባቸው የምንናፍቃቸው ዓለም ላይ ያሉ ድንቅ አገራት በዜጎቻቸው የተሳሉ ናቸው። መጀመሪያ ክፉዎች ከጫኑብን የእኔነት አስተሳሰብ እንውጣ። መጀመሪያ ለጥቂቶች የፖለቲካ ትርፍ ከተተበተበብን የውሸት ትርክት እንጽዳ። መጀመሪያ አገርና ህዝብ ምን እንደሆኑ እንወቅ። መጀመሪያ እኛ ለአገራችን፣ ሀገራችንም ለእኛ ምን ማለት እንደሆንን እንመርምር።
እኛ የምንኖረው አገራችን ስትኖር ነው። ያለ ሀራችን የእኛ መኖር ምንም ነው። ሀገራችን ሰላም ሆና እንድትኖር እኛ ዜጎቿ ሰላም ያለው አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። በእውቀታችንና በሙያችንም ሀገራችንን ማገልገል የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። በእውቀታችሁ ለአገራችሁ ካልታመናችሁ አገራችሁን መሳል አትችሉም። በስልጣናችሁ ሀገራችሁን መጥቀም ካልቻላችሁ ትውልድ መፍጠር አትችሉም።
ለምንም ነገር ተጠያቂ እኛ ነን። ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ተጠያቂው ሕወሓት ነው። እኛ ደግሞ ለነገው ትውልድ ዛሬ ሀገራችንን አድምቀን መሳል ይኖርብናል። እጃችሁ ላይ ያለው ምን አይነት ጥበብ ነው? ልባችሁ ውስጥ፣ አእምሯችሁ ውስጥ ያለው ሀሳብ ምን አይነት ነው? ሀገር የምትሳለው በዚህ ነው። በዘመነ አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን ነበር። ለዚህ ደግሞ አንድ መዐት አሁናዊና ትላንታዊ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በሕወሓት ድሮነት ውስጥ አገርና ህዝብ አልነበሩም ተገቢው ክብርና ዋጋም አልተሰጣቸውም ነበር። የዛሬ ሰንካላ ርምጃችን የትላንት የፖለቲካ ስርዐት የፈጠረው ስለመሆኑ እኔም እናንተም የምንስማማበት ጉዳይ ነው። በእያንዳንዳችን ትላንትና ውስጥ በሕወሓት የፖለቲካ ሴራ ያደፈ ሰውነት አለ።
በእያንዳንዳችን አምና ውስጥ በከሀዲያን የተሰወረ እውነት አለ። ይሄ ሰውነት መጽዳት አለበት። ይሄ እውነት መገለጥ አለበት። በጥቂት ራስ ወዳድ ቡድኖች የተከናነብነውን የውሸት ጭንብል አውልቀን እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት መልበስ አለብን። ኢትዮጵያን ለመሳል የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሄ ነው። አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ስም አሜሪካና መሰል አገራትን ሲጠቅምና ሲያገለግል የኖረ ነበር።
የአሁኑ የአሜሪካ ጩኽት የቡድኑን የትላንት የፖለቲካ ቀመር በደንብ የሚያሳይ ነው። ከጠላት ሀገራት ጋር አገርና ትውልድ የሚጎዱ በርካታ ሴራዎችን ሲያሴር እንደነበር በዚህና በዚያ መገንዘብ ይቻላል። ያለፉት የሕወሓት የስልጣን ዘመናት ራስን ብቻ የመጥቀምና የማገልገል አስተሳሰብ የተስተናገደበት ዘመን ነበር።
ባህልና ታሪክ፣ ሰውነትና ሉአላዊነት ዋጋ ያጡበት የኔነት መንፈስ የሞላበት ነበር። ህዝብ የሌለበት፣ ትውልድ የመከነበት አረመኔ አስተሳሰብ የተዋቀረበት የአማጺያን ስብስብ ገኖ የወጣበት ነበር። አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያዋረደና ያጠለሸ ከመሆኑም ባለፈ የአገሬን የሉአላዊነት አጥር የነቀነቀ ታሪካዊ ጠላት ነው።
ከድሀ ጉያ በቅሎ፣ በድሀ ርስት በልጽጎ ተመልሶ አገር የጎዳ ባንዳ ነው። አገራችን ከሌላት ላይ ሰጥታ አስተምራ፣ ከሌላት ላይ ቆርሳ ቀን አውጥታ ዛሬ ባከበረችው ወሮ በላ ልጇ እየተዋረደች ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬም ድረስ ከለቅሶዋ አላባራችም። ሕወሓት ለሀገራችን መከራ ሆኖ ለህዝባችን ስቃይ ሆኖ በትውልድ ነፍስ ላይ ክህደትን አትሟል። አገር መልካም ሀሳብ ያስፈልጋታል።
ሀገር ቀና ልብ ግድ ይላታል። ያለ መልካም ሀሳብና ያለ ቀና ልብ አገርና ህዝብ ምንም ናቸው። በመልካም ሀሳባችን ኢትዮጵያን መሳል እንችላለን። በቀና ልባችን ትውልድ መፍጠር ይቻለናል። ዛሬ አገራችን እየጠበቀችን ነው። ልንደርስላት ይገባል። እኛ ደግሞ ሀገራችንን ለመሳል በቂዎች ነን። አሸባሪው ሕወሓት እንደ ትላንቱ ዛሬም አልተማረም በሀሳብ ልናሸንፈው ይገባል።
በአንድነት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት ልንፋለመው ይገባል። የሕወሓት ከሀዲ ቡድን ጫካ የገባው አገራዊ መነቃቃት አስፈርቶት ነው። በነጋ ቁጥር ጨለምተኞች መግቢያ ያጣሉ። ህዝብ ተስፋ ባገኘ ቁጥር ጨካኞች እየተሸነፉ ይመጣሉ። ሀገር በእውነት ስትቆም ሀሰተኞች ይወድቃሉ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይሄ ነው። በብርሀናችን ሕወሓትን እያሸነፍንው ነው። በእውነታችን፣ በአንድነታችን፣ በመነቃቃት መንፈሳችን እኩይ ተግባሩን ታሪክ እያደረግንው ነው። አገራችንን እንሳል። አገር መሳል ሀገር ከማፍቀር ይጀምራል። አገር መሳል ለወገን በጎ ከማሰብ ይነሳል። ጠላቶቻችንን በመፋለም፣ የእውነትን መንገድ በመሻት ይጀምራል።
ባለን እውቀት፣ ባለን መክሊት ሁላችንም ሀገራችንን ለመሳል መታጠቅ ይኖርብናል። ከለውጡ መንግስት ጎን በመቆም በሀሳብ ነጋችንን እንሳል። አሁን ላይ እንደፈለግን የምንሆነው አገር ስላለን ነው። ሀገር የማንነት መገለጫ አውድ ናት። ሕወሓት ካለበሳት ጥቁር ማቅ ወደ ሚደነቅ የብርሀን ዘውድ ልናሸጋግራት ግድ ይለናል። የአገራችን ትንሳኤ እኛ ነን ለሀገራችንም የአዲስነትን ጸዐዳ ኩታ ልናለብሳት ይገባል። አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014