የችግረኛ ልጅ ነው። ወላጆቹ እሱንና ሌሎችን ለማሳደግ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ኑሮ መላው ቤተሰብ እንደነገሩ ያድራል። ህይወት በገጠር መሆኑ ለጉሮሮ አያሳጣም። ለም መሬት ካፈራው በረከት ጎርሶ ማደር የተለመደ ነው።
የጋሞ ቤተሰቦች ይህን እውነት ለዓመታት ኖረውታል። ችግርና መከራውን ደስታና ሀዘኑን አሳምረው ያውቁታል። ጋሞ ካሱ ተወልዶ ያደገው ደቡብ ክልል ደራራ ወረዳ ነው። የጨቂላ ቀዬ ልጅነቱን እንደ እኩዮቹ እንዲቦርቅ፣ እንዲደሰት ዕድል ሰጥታዋለች። በመስክ በመንደሩ ዕድሜው የፈቀደለትን ለመሆን ያገደው አልነበረም።
ጋሞ በዕድሜው መብሰል ሲጀምር ወላጆቹ ከፍ እንዳሉት የሰፈሩ ልጆች እንዲሆንላቸው ተመኙ። ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት እንዲሄድ ዕውቀት ሸምቶ እንዲመለስ ፈለጉ። ያሰቡት አልቀረም። ጋሞ በአካባቢው ከሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ዕድልን አገኘ።
ይህኔ በእሱ ውስጥ የነገ ተስፋ የሚታያቸው እናት አባት የልባቸው ሞላ፣ የሀሳባቸው ደረሰ። ለልጃቸው እንደአቅማቸው፣ እንደ እሱ ፍላጎት እየሞሉ አገዙት። ትምህርቱ እንዳይቋረጥ፣ ከእኩዮቹ እንዳያንስ አድርገው ደገፉት። ትምህርቱን አንድ… ብሎ የጀመረው ታዳጊ በየዓመቱ ክፍሎችን እየተሻገረ ሰድስተኛ ክፍል ደረሰ።
አሁን የቤቱ አባወራ ኑሮ ይከብዳቸው ይዟል። የጎደለውን ሞልቶ ልጆች ለማሳደግ፣ ጎጆን በየመልኩ ለመደጎም አቅማቸው ተፈትኗል። ይህን የሚያውቀው ጋሞ ሁሌም ጭንቀታቸውን ይጋራል። ዛሬ እሱም እንደሳቸው የቤቱ ችግር ተካፋይ ነው። ሲኖር በልቶ ለማመስገን፣ ሲጠፋ እንደነገሩ ለማደር ሁሉን በእኩል ይጋራል።
ጋሞ ስድስተኛ ክፍልን አልፎ ሰባተኛ ሲገባ የቤተሰቡ ችግር እንደቀጠለ ነበር። አባቱ ከዕለት ጉርስ አልፎ ለእሱ የትምህርት ወጪ የሚተርፍ አቅም አልነበራቸውም። ጋሞ የኑሮው ድካም እያንገላታቸው መሆኑን ሲረዳ የትምህርቱ ጉዳይ አደጋ ላይ መሆኑን አወቀ።
ጋሞ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል። ይህ ጊዜ ለወደፊት ዓላማው መሰረት የሚጥልበት ነው። ቀጣዮቹን ዓመታት በጥንካሬ ከበረታ በትምህርቱ መልካም ፍሬን ይይዛል። ለቤተሰቦቹ ተስፋ፣ ለታናናሾቹ አርአያ ሆኖ ይዘልቃል። የወላጆቹን ድካም ይመልሳል፣ የልቡን ምኞት ይሞላል።
አሁን ጋሞ ስምንተኛን ክፍል ማጋመስ ጀምሯል። ወላጅ አባቱ ግን እንደትናንቱ አልበረቱም። ኑሮና ህይወት ከብዷቸዋል። የእጃቸው ጥሪት እንደቀድሞው አይደለም። ለቤት ለልጆቻቸው የሚሆን በቂ ገንዘብ አጥተዋል። ጠዋት ማታ የሚፈትናቸው ችግር ቀላል አልሆነም። በትካዜ ውለው ማምሸት ልምዳቸው እየሆነ ነው።
ይህ እውነት የታዳጊውን ተማሪ የህይወት መስመር ቀየረው። ጋሞ በአባቱ መቸገር ምክንያት ከትምህርት ሊታጎል ግድ አለው። ደጋግሞ የመቅረቱ ውጤት ትምህርቱን ከነአካቴው እንዲያቋርጥ ምክንያት ሆነ። ብርቱ የነበረው ልጅ ጓደኞቹን እየሸኘ ከቤት መዋል ጀመረ። የትናንቱ ተስፈኛ ተማሪ ስለ ነገ ማንነቱ ተስፋቢስ ሆነ። ጊዜያትን ያለ ቁምነገር አሳለፈ።
ከትምህርት ከተራራቀ ወዲህ የቤት ልጅ መሆን የጀመረው ጋሞ የኔ የሚለውን መተዳዳሪያ አላገኘም። ያለአንዳች ስራ አሰልቺ ወራትን ቆጠረ። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ያለምንም ለውጥ የቆይታ ጊዜው ጨመረ። ጥቂት የማይባሉ ዓመታትንም በቤቱ ተቀምጦ አሳለፈ።
ጋሞ ግራ መጋባት ላይ ደርሷል። ከትምህርት፣ ከስራ አልያም ከትዳር አልሆነም። የቤተሰብ ሸክም መሆኑ እየከበደው ነው። ይህን ጉዳይ ደጋግሞ ሲያስበው ውስጡ ለውሳኔ ይፈጥናል። መጪው ህይወት በዚህ መልክ እንዲቀጥል አይሻም። ሁሌም ‹‹ከቤትህ ውጣ፣ ከሰፈርህ ራቅ የሚል ስሜት ይፈትነዋል።
አንድ ቀን ጋሞ ሲብሰለሰልበት ከከረመው ውሳኔ ላይ ደረሰ። ሲያቅደው ለነበረው ዓላማ ቆረጠ። መዋል ማደር አልፈለገም። ጓዙን ሸከፈ፣ መንገዱን ተለመ፣ መድረሻውን ወሰነ። ጊዜው የጥቅምት ወር ነበር። የወቅቱ ብርድና ውርጭ በወጉ አያላውሰም። ጋሞ ይህ ሁሉ አላሳጨነቀውም። ከቤቱ ወጥቶ ከቀዬው ሲርቅ በእንግድነት የሚቀበሉትን የአገሩን ልጆች እያሰበ ነበር።
የጋሞ መንገድ ወደአዲስ አበባ አቀና። ከዚህ ቀድሞ እሱ ባለፈበት መስመር በርካቶች ተጉዘውበታል። የአብዛኞቹ ህይወት የሚያስከፋ አይደለም። መከራና ችግርን ተቋቁመው ካሰቡት ደርሰዋል። ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ተርፈዋል። እሱም ቢሆን ህይወቱ ከእነሱ እንደማይለይ ተማምኗል። ባልንጀሮቹን መስሎ ከአገር ያወጣውን ችግር ታግሎ ለማሸነፍ ተዘጋጅቷል።
ህይወት በአዲስ አበባ…
ጋሞና አዲስ አበባ ሲገናኙ ፈጥነው ተላመዱ። እንግድነቱን ያልጠሉት የሰፈሩ ልጆች በወጉ ተቀብለው አስተናገዱት። ዋል አደር ሲል የከተማውን ህይወት ለመደ፣ ሰርቶ በማደር እንጀራ መብላት፣ የልብን መሙላት እንደሚቻል አወቀ። ለገሀር አካባቢ መዋል ሲጀምር የቀን ስራ አላጣም። በደከመበት ልክ እያገኘ ገንዘብ መያዝን አወቀ።
የቀንስራው ውሎ ለራሱ ያህል አላሳጣውም። ከሚከፈለው ገንዘብ እየቆጠበ፣ ለምግብና ልብሱ ያተረፋል። አንዳንዴም ሌሎችን ለመምሰል በአቅሙ ለመዝናናት ይሞክራል። ለእሱ ሰርቶ ማደሩ፣ ገንዘብ መያዙ ከምንም በላይ ዋጋ አለው። የመሹዋለኪያ ሰፈርና አካባቢውን ለመልመድ ጊዜ አልፈጀበትም። ሞቅ ደመቅ ባለው ሰፈር እየሰራ በልቶ ያድራል።
ሰፈሩ በርካቶች ሮጠው የሚያድሩበት ነው። ስፍራው በብዙ አይነት ሙያዎች ከትንሽ አስከትልቅ ገቢ ይገኝበታል። ሮጠው የሚያድሩት ለጉሮሯቸው አያጡም። በዚህ አካባቢ ሰርተው ደክመው የሚኖሩ፣ ደልለው፣ ሰርቀው የሚገቡ በአንድ ይውላሉ።
ሁሉም የልፋቱን ለማግኘት፣ የኪሱን ጎዶሎ ለመሙላት ተግቶ አዳሪ ነው። አሸዋን በመኪና የሚያስጭነው፣ እንዲሸጥ፣ እንዲገዛ የሚደልለው፣ አልጋ የሚያከራየው፣ ገብቶ ተኝቶ የሚወጣው ሁሉ በአንድ መስመር ሲጋፋ ይውላል። ከገበያው፣ ከሱቁ፣ ከጉልት፣ ከሰፈሩ የሚተራመሰው መንገደኛ አስከ ምሽት አካባቢውን አድምቆት ይውላል።
ጋሞ ቀኑን ሙሉ ሲደክም ውሎ ጎኑን ለማሳረፍ ምሽቱን አልጋ ፍለጋ ይባዝናል። እስከ ዛሬ ለኔ የሚለው ማረፊያ ቤት የለውም። በወር ከፍሎ ለማደር የሚችልበት የቤት ኪራይም ምርጫው አልሆነም።
ሁሌም በጨርቆስ መንደር ጠባብ መንገዶች ተዟዙሮ ከሚያገኛቸው ደሳሳ ቤቶች በአንዱ ዕንቅልፉን ጨርሶ ይወጣል።
ጋሞ ለጎኑ ማረፊያ የሚመርጣቸውን ቤቶች ለማግኘት ተቸግሮ አያውቅም። ሁሌም በአካባቢው ቆመው ‹‹አልጋ አለ›› እያሉ የሚጣሩትን ድምጽ ተከትሎ ከአንዱ ይመሽጋል። የአልጋው ኪራይ እንደዘመነኞቹ ማፊያዎች ኪስ አይጎዳም። ለአንድ ቀን አዳር እስከ አስራ ሁለት ብር ያስከፍላል።
ወፍ ሲንጫጫ ‹‹ማቄን፣ ጨርቄን›› አይልም። ከመኝታው ፈጥኖ ይነሳል። በቀን ስራው ሮጦ የሚያገኘውን ጥቂት ገንዘብ ቋጥሮም ሆዱን ሸንግሎ ይውላል። ምሽቱን ከተለመደው መኝታ ለማሳለፍ የአልጋውን ክፍያ ማሟላት ግድ ይለዋል።እንዲህ ካልሆነ ከደሳሳ ቤቶቹ ጎስቋላ አልጋዎች ማሳለፍ፣ አይቻለውም።ሲነጋ እንደለመደው የቀን ውሎውን ሊጀምር ማልዶ ይነሳል።
አንዳንዴ ጋሞ ከቀንስራው ውሎ ከሚያገኘው ገንዘብ ለመጠጡ የሚተርፍ አያጣም። ማደሪያውን ፍለጋ ከመሄዱ በፊት ከመጠጥ ቤቶች ጎራ ብሎ እንዳሻው ይጎነጫል። ደጋግሞ ሲጠጣ ለሞቅታ ቅርብ ነው። ሂሳቡን ዘግቶ ወደማደሪያው ሲጓዝ ውስጡ ሰላም ይሉት የለውም። ትዕግስት ያጣል፣ ነገር ይሸተዋል፣ መጣላት፣ መሳደብ ያምረዋል። መደባደብ፣ መነዛነዝ ይፈልጋል። መንገዱን አልፎ ከመኝታው ከደረሰ በዕንቅልፍ ይሸነፋል። ማለዳ ዓይኑን እያሸ፣ አፉን እያዛጋ ከለመደው የእንጀራ ፍለጋ ይኳትናል።
ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም
ምሽት ሁለት ሰዓት እያለ ነው። ጋሞ ውሎውን በስራ አሳልፎ ከመጠጥ ቤት ጎራ ብሎ ቆይቷል። ሰዓቱ እገፋ ሲሄድ ወደማደሪያው ለመሄድ ተነሳ። እንደለመደው ሞቅታ ላይ ነው። ድካም የዋለበት አካሉን መጠጡ ተቆጣጥሮታል። ውስጡ ንዴትና ብስጭት ይመላለስበታል።
ከነበረበት ወጥቶ የመሹዋለኪያን አቅጣጫ ሲጀምር ከሩቅ ሶስት ሰዎችን ተመለከተ። ሶስቱም የአገሩ ልጆች፣ እንደሱ ለፍቶ አዳሪዎች ናቸው። ራት ቀማምሰው ወደማደሪያቸው እያመሩ ነው። ጋሞ ከእነሱ መሀል ያለውን መሰለን ነጥሎ አተኮረበት። ንዴቱ ጨምሯል፣ ብስጭቱ አይሏል። እየቀረባቸው ሲሄድ ስሜቱ ተቀያይሮ ነበር።
መሰለ ለጋሞ ከአገር ልጅ ባለፈ የቅርብ ጓደኛው ነው። ክፉደጉን በእኩል ተጋርተው ቀናትን ተሻግረዋል። ጋሞና መሰለ እንደተያዩ ድንገቴ ጠብ ተነሳ። ምክንያቱ ያልገባቸው ሁለቱ ለመገላገል መሀል ከመግባታቸው የመሰለን ከመሬት መውደቅ አስተዋሉ።
ጋሞ ባልንጀራውን እንዳየ በእጁ የያዘውን ኮብል ስቶን በቀኝ ጭንቅላቱ ላይ አስጠግቶ ወርውሮታል። ድንጋዩ አቅጣጫውን አልሳተም። የመሰለን አናት ክፉኛ ገመሰው። ድንጋዩና ተጎጂው እኩል መውደቃቸውን ያዩ ጓደኛሞች መሰለን ለማንሳት ተረባረቡ። በደም የተነከረው ወጣት ጉዳቱን መቋቋም አልቻለም። ምድር ሰማዩ እንደዞረበት በግንባሩ ድፍት ብሎ ወደቀ።
ሁኔታውን ያስተዋለው ጋሞ ድንጋጤ ያዘው። የጓደኛው በደም ተነክሮ መውደቅ አስደንብሮት በሩጫ ከስፍራው ተሰወረ። ሁለቱ ጓደኛሞች እየተንቀጠቀጡ ጓደኛቸውን አነሱ። ወደ ሕክምና የሚያደርሱበት የገንዘብ አቅም አልነበራቸውም። እንደምንም ደጋግፈው ከማደሪያቸው ሲያስገቡት የመሰለ ደም ያለመቋረጥ ይፈስ ነበር።
ጋሞ በጨለማው እያሳበረ ወደፊት ገሰገሰ። መንገዱ ከለመደው የመኝታ ስፍራ አልነበረም። አጎና ሲኒማ አካባቢ ሲደርስ ከአንድ የጎዳና ጥግ ጎኑን አሳረፈ። ለሊቱን ድንጋጤ እያባነነው፣ ቅዠት እያስደነበረው ያለአንዳች ዕንቅልፍ አሳለፈ። በሰራው፣ በፈጸመው ድርጊት ጥፋተኝነት እየተሰማው ነበር፡ ፡
በማግስቱ…
የመሰለ ባልንጀሮች በኮብልስቶን ጥርብ ጭንቅላቱን የተመታው ባልንጀራቸው ጉዳት የከፋ መሆኑን አውቀዋል። አሁንም ከጭንቅላቱ የሚፈሰው ትኩስ ደም የሚቆም አልሆነም። ለሊቱ እጅግ ከባድና አስጨናቂ ሆነባቸው። መሰለ ምሽቱን ለህክምና አለመድረሱ ትንፋሹን እያሳጠረው ነው።
ወጣቶቹ ወፍ ሲንጫጫ ጠብቀው አንድ ዘመዱን አገኙት። የመሰለ የቅርብ ዘመድ በሰማው እውነት ተደናግጦ ከስፍራው ደረሰ። መሰለን ሲያገኘው ተስፋ አልጣለበትም። ያለመቋረጥ በፈሰሰው ደም ክፉኛ ዝሎና ተዳክሞ ነበር።
ጋሞ ለሊቱን በጎዳና አሳልፎ በጠዋት ከስፍራው ራቀ። አሁንም የጓደኛው ሁኔታ እያሳሰበው ነው። ከሚታወቅበት አካባቢ ሳይጠጋ ወሬ ጠየቀ። ጓደኛው ባጋጠመው የከፋ ጉዳት ሆስፒታል መግባቱን ሰማ። ቀኑን ሙሉ ሲጨነቅ፣ ሲደነግጥ ዋለ። ጥፋቱ የበዛ መሆኑ ቢገባው አገሩ ተሳፍሮ መሄድን አሰበ። በእጁ በቂ ገንዘብ የለም። በቅርቡ በሦስት መቶ ሀምሳ ብር የገዛውንና ብዙ ያለበሰውን ሱሪ አስታወሰ። ሳይደክም፣ ሳይለፋ በሁለት መቶ ብር ሽጠው።
ጋሞ አሁን ለአገሩ መግቢያ መሳፈሪያ አግኝቷል። ውሎ ሳያድር ዕቅዱን ለመፈጸም ተቻኮለ። ያሰበውን ከማድረጉ በፊት ግን አስደንጋጭ ዜና ደረሰው። ከአንድ ቀን በፊት በኮብል ስቶን ጥርብ የፈነከተው ባልንጀራው መሞቱን ሰማ። ክፉኛ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ።
ጋሞ ከዚህ በኋላ መሸሸ መደበቁ እንደማይበጀው አወቀ። ጥቂት ራሱን አረጋግቶም ከራሱ መከረ። በስሜት ተነሳስቶ፣ በመጠጥ ሀይል ተገፍቶ የፈጸመው ወንጀል የቅርብ ጓደኛውን አሳጥቶታል። አሁን እጁን ለህግ ከመስጠት በቀር ምርጫ የለውም። ይህን አስቦ ከፖሊስ ጣቢያ ደረሰ። የፈጸመውን ድርጊት ተናግሮም ራሱን ለህግ አስረከበ።
የፖሊስ ምርመራ …
ከፖሊስ ጣቢያው ደርሶ እውነቱን ያስረዳውን ተጠርጣሪ ቃል የተቀበለው መርማሪው ረዳት ኢንስፔክተር ሲሳይ ተሾመ የጋሞን የህይወት ታሪክና የወንጀል ድርጊት አፈፃፀም በጥንቃቄ አሰፈረ። በዕለቱ የነበሩ እማኞችን ቃል ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር አዛምዶም በወንጀል መዝገብ ቁጥር 1592/11 ላይ መዘገበ። መረጃዎች በበቂ ደረጃ መሟላታቸውን አረጋግጦም ክስ እንዲመሰረት መዝገቡን ለዓቃቤ ህግ አሳለፈ።
ውሳኔ…
ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ጋሞ ካሱ ላይ የቀረበውን የግድያ ወንጀል አጣርቶ ከመጨረሻው ውሳኔ ደርሷል። ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው በፈጸመው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ በሰጠው ፍርድም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስር ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ወስኗል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014