ተግባራት፣ በመም ሩጫ፣ በአገር አቋራጭ፣ በጎዳና ላይ ሩጫዎች እንዲሁም በዕርምጃ ውድድሮች በዓመቱ ድንቅ ብቃት ያሳዩ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ አወዳዳሪነት ይሸለማሉ፡፡
እአአ 1988 የተጀመረው ይህ ሽልማት ሳይቋረጥ በየዓመቱ ሲካሄድ፤ ከአትሌቶች በተጓዳኝ ተስፋ ያለው ወጣት አትሌት፣ አሰልጣኝ፣ ፌዴሬሽን እንዲሁም የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎችንም በተለያየ ዘርፍ ይሸልማል፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት ታላቅ በሆነው በዚህ ሽልማት ላይም ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በወንዶች ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ቀዳሚው አትሌት ሲሆን፤ የረጅም ርቀት ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ እአአ 2004 እና 2005 በተከታታይ አሸናፊ ነበር።
በሴቶች አትሌት መሰረት ደፋር እአአ 2007 ስትሸለም፤ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያናም በተከታታይ ዓመት አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ እአአ 2012 በተጀመረው ምርጥ ተስፋ ያለው ወጣት አትሌት ዘርፍም አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከሁለት ዓመት በፊት አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ይሁንና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክስ የምትታወቀው ኢትዮጵያ አትሌቶቿን ከአሸናፊነት ብቻም ሳይሆን ለሽልማት በዕጩነት ከሚቀርቡት አትሌቶች የስም ዝርዝሮች ውስጥ መካተት አልቻለችም፡፡ ትናንት በተካሄደው የ2021 የምርጥ አትሌቶች ሽልማት ላይም ተስፋ የተጣለበት ምርጥ ወጣት አትሌት ዕጩ ውስጥ የተካተቱት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሸላሚ ለመሆን አልቻሉም፡፡
በምርጥ ተስፋ ያላው ወጣት አትሌት ዘርፍ ከዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካተታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁንና የዘርፉ አሸናፊዎች በሴቶች አሜሪካዊቷ የቶኪዮ ኦሊምፒክ 800 ሜትር አሸናፊ አቲንግ ሙ እንዲሁም በወንዶች በአጭር ርቀት ሩጫ ዩሴን ቦልትን እንደሚተካ የሚነገርለት አሜሪካዊ ኤሪዮን ኒተን ኦሊምፒክ ልዩነት የፈጠረበት የምርጥ ተስፈኛ አትሌቶች ሽልማት አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
በዘርፉ በዕጩነት የቀረበችው ኢትዮጵያዊት አትሌት የ19 ዓመቷ ዘርፌ ወንድማገኝ በወጣትነቷ አገሯን በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የወከለች አትሌት ናት፡፡ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪዋ አትሌት እአአ 2019 በዶሃ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በብሄራዊ ቡድኑ ተካታለች፡፡
በቶኪዮ ኦሊምፒክም በምትታወቅበት ርቀት አገሯን በመወከል እስከ ፍጻሜ መድረስ የቻለች ተስፈኛ ወጣት አትሌት ናት፡፡ በኦሊምፒክ ማግስት በኬንያዋ ናይሮቢ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ላይም ተካፍላ በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን ስትበቃ፤ በርቀቱ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ባለክብረወሰን ለመሆንም ችላለች፡፡
በወንዶች በኩል ደግሞ ዕጩ የነበረው ታደሰ ወርቁ የ18 ዓመት ወጣት አትሌት ሲሆን፤ በወጣት ብሄራዊ ቡድን ደረጃም ጥሩ ብቃት እንዳለው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እያሳየ ይገኛል፡፡ ታደሰ በናይሮቢው ቻምፒዮና በሁለት ርቀቶች ተካፍሎ በ3ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
እአአ 2019 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር የብር ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ፤ በአገር ውስጥ በተሳተፈባቸው ውድድሮችም የተሻለ ውጤትና ፈጣን ሰዓት ያለው ተስፈኛ አትሌትም ነው፡፡ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ምርጫ እንደ ትልቅ መስፈርት የሚታየው አትሌቱ በዓመቱ ያሳየው አቋም ሲሆን፤ ዓመታዊ ውድድሮችም ለዚህ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ አትሌቶች በዕጩነት ከቀረቡ በኋላ የስፖርት ቤተሰቡን ጨምሮ በተለያዩ ባለሙያዎች በሚሰጥ ድምፅ ለአሸናፊነት የሚበቁ በመሆኑ በዘንድሮው ውድድር ኦሊምፒክ ከሚዳኙባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ በዕድሜ ገደብ እንዲሁም ተስፈኛ አትሌቶች በሚል በሚካሄዱት ምርጫዎች ትልልቅ ቻምፒዮናዎች ዋነኛው መስፈርት ባይሆኑም በአትሌቶች መካከል ግን ልዩነትን የመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳላቸው በዚህ ውድድር (በተለይም በሴቶች ዘርፍ) ታይቷል፡፡ ብዙዎች ለማሳካት ረጅም ጊዜ የሚፈጅባቸውና ከባድ ሥራንም የሚጠይቀው በብሄራዊ ቡድን አገርን በኦሊምፒክና ዓለም ቻምፒዮና መወከል ነው፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዘርፌ ገና በወጣትነቷ በስፖርቱ ዓለም ታላላቅ በሚባሉት መድረኮች ተሳታፊ መሆን ችላለች፡፡ አሁን ካለችበት ደረጃ መድረሷ እንዲሁም የምታስመዘግባቸው ውጤቶች በእርግጥም ጥንካሬዋን እንዲሁም ለወደፊት የሚኖራትን ተስፋ የሚገልጽ መሆኑ አሸናፊ የመሆን ዕድሏን እንደሚያሰፋው ይገመት ነበር። ይሁንና በዕጩነት ከቀረቡት ተፎካካሪዎች በተለይም አሸናፊዋ አትሌት በኦሊምፒክ ከመሳተፍም ባለፈ የላቀ ውጤት ያላት መሆኑ ሽልማቱን ለማሸነፏ ምክንያት ሆኗል።
በወንዶች በኩል አብዛኛዎቹ ዕጩዎች የተመረጡት በናይሮቢው ውድድር ባሳዩት ምርጥ ብቃት ሲሆን፤ እንደ ታደሰ ሁሉ በቻምፒዮናው ድርብ ድል ያስመዘገቡም ናቸው፡፡ ነገር ግን አሜሪካዊው ኒተን በወጣቶች ቻምፒዮና ባለ ክብረወሰን በሆነበት 200 ሜትር በኦሊምፒክም አገሩን ወክሎ በመወዳደር አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ በሽልማቱ ዕጩዎች መካከል ልዩነት እንዲፈጥር አድርጓል። ከአምስቱ የምርጥ ተስፈኛ አትሌት ዕጩዎች መካከል ብቸኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ መሆኑ ለአሸናፊነቱ ከፍተኛ ድርሻ እንዳስገኘለት አያጠራጥርም፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኀዳር 24 / 2014