በዓለም ብሎም በሀገራችን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነት እየተስፋፋ መጥቷል። ማህበራዊ ሚዲያ ከሌሎቹ የመገናኛ ብዙኋን በፈጠነ መንገድ መረጃን ለመቀባበል የሚጠቅም እንደመሆኑ ለበጎ አላማ ማዋል ከተቻለ በቀላሉ የጊዜ የጉልበትና የገንዘብ ወጪዎችን የሚቀንስም ነው።
በተጨማሪ የእውቀት ሽግግር ለማድረግም ሁነኛ መንገድ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ይህ የማህበራዊ ሚዲያ በጎ ጎን እንደተጠበቀ ሆኖ በአግባቡና በሃላፊነት ካልተጠቀምንበት ደግሞ ሊያስከትል የሚችለውን ውድመትና ሽብር እኛ ኢትዮጵያውያን ያሳለፍናቸውን ጥቂት አመታት በመመልከት ቀዳሚ ምስክሮች መሆን እንችላለን።
እኛም ለዛሬ የአዲስ ዘመን ሀገርኛ አምድ እንግዳ አድርገን የምናቀርብላችሁ ማህበራዊ ሚዲያ ያሰባሰባቸውና እሱኑ በመጠቀም የበጎ አድራጎት ተግባራትን እየከወኑ ለችግር የተዳረጉ ወገኖቻቸውን በመታደግ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን እንቅስቃሴ ነው።
ወይዘሪት ፀሀይ እሸቱ በህክምና ስራ ላይ የተሰማራች ስትሆን የሂሳብ ባለሙያም ናት። በአሁኑ ወቅትም በቅንነት በጎ ፈቃደኞች ስብስብ ውስጥ አባል በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።
እኛም ፀሀይ ቅንነት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስብስብ እንዴት ወደ በጎ አድራጎት ስራው ሊገባ እንደቻለና በአሁኑ ወቅትም እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን አስመልክተን ላቀረብንላት ጥያቄ የሰጠችንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ስብስቡ የተመሰረተው በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በቴሌግራም እየተገናኙ በሚወያዩ ወጣቶች ነው።
በዚህ ፕሮግራም የቴሌግራም ግሩፕ ላይ ይሳተፉ የነበሩት አባላት ቁጥርም ሀያ ሺ የሚደርስ ነበር። አባላቱ ቅዳሜ ቅዳሜ ይቀርብ በነበረ የፍቅር ፕሮግራምና ሌሎች የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክርና የሚያወያይም ነው። በሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም ማጠናቀቂያ የክረመት ወቅት ግን አባላቱ ግንኙነታቸውና ትውውቃቸው እየተጠናከረ በመምጣቱ አዲስ ሀሳብ በማቅረብ ለምን የተቸገሩ ተማሪዎች የደብተርና ሌሎች የትምህርት ግብአት የሚውሉ ቁሳቁስ አንረዳም የሚል ሀሳብ ያነሳሉ። በሀሳባቸው ተስማምተውም የመጀመሪያውን ድጋፍ በዛው ወቅት በማድረግ ዛሬ ድረስ የዘለቀውን ስራቸውን ለመጀመር ይበቃሉ።
ከዚያ በኋላ ደግሞ በሬዲዮ ፕሮግራሙ ላይ እየተወያዩ በአዘጋጆቹ በኩል እንደ መቄዶንያ፣ ጌርጌሴኖን ላሉ የበጎ አድራጎት ማህበራት ድጋፍ ማድረግ ይቀጥላሉ። ይህም ሆኖ የስብስቡ አባላት ቁጥር በጣም ብዙ ስለነበር ስራቸውን በተመቻቻና ባሰቡት መልኩ ለማስኬድ አስቸጋሪ እየሆነባቸው ይመጣል። በመሆኑም የበለጠ የሚቀራረቡት ልጆች ራሳቸውን በማሰባሰብ የሚያደርጉትንም ድጋፍ በቋሚነት ለማድረግ በሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም ህዳር ሀያ አንድ ቀን ከስምምነት ይደርሳሉ።
በዚህም መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በዛው ቀን ህዳር 21/2012 ዓ.ም ፍቅር ለአረጋውያን የሚባልና ጎጃም በረንዳ አካባቢ ወደሚሰራ አንድ የበጎ አድራጎት ማህበር ያቀናሉ። እዛም ሄደው በጎዳና የነበሩትን ችግርተኞች በማንሳት ገላቸውን በማጠብ እንዲሁም ወንዶቹን ጸጉራቸውን በማስተካከል፣ ሴቶቹንም ሹሩባ በመስራት ያሰባሰቡትን ልብስ ለተደጋፊዎች አልብሰው ይመለሳሉ።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እስካሁንም የዘለቀውንና ብዙዎችን የታደጉበትን ለህክምና ባለሙያዎች የሁልጊዜ ጥያቄ የሚሆነውን የደም ልገሳ መርሃ ግብር ማከናወን ይጀምራሉ። ይህ የደም ልገሳ ፕሮግራም በቋሚነት በየሶስት ወሩ የሚደረግ ሲሆን እስካሁንም ቀጥሎ ለስምንት ያህል ዙር አባላቱ የደም ልገሳ መርሃግብር አካሂደዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ አለምን ያናወጠው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በተከሰተበት ወቅትም የንጽህና መጠበቂያዎችን፤ አልባሳትና ምግቦችን በማሰባሰብ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ማህበራት ውስጥ እየኖሩ ላሉ ድጋፍ ለሚሹ ወገኞች አበርክተዋል።
ወጣቶቹ የቁሳቁስ ድጋፎችን ከማድረግ ማህበራዊ ሚዲያን ለኢትዮጵያዊነት ያዋሉ ወጣቶች ባለፈ የተለያዩ በዓላትን ለምሳሌ የገና፣ የፋሲካንና የረመዳን ጨምሮ በተስፋ ቻይልድ ሁድ የካንሰር ህሙማን ህጻናት መንከባከቢያ ማእከል፤ እንዲሁም የመውሊድና የዘመን መለወጫ በአልን በዘውዲቱ መሸሻ የህጻናት ማሳደጊያ ማእከልና በሰሊሆም የአይምሮ ህሙማን መንከባከቢያ ማዕከል በመገኘት ወገኖቻቸው የቤተሰብ ስሜት እንዲፈጠርባቸው “ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር መቀበል” የሚል መርህ ይዘው በዓላቱን አብረው አሳልፈዋል።
በተጨማሪም ሌሎች በጎ አድራጎት ተቋማትን ለምሳሌ ያህል ሙዳይ በጎ አድራጎት፣ ጌርጌሴኖን የአይምሮ ህሙማን መንከባከቢያ፣ ስለ እናት በጎ አድራጎት እና የመሳሰሉት ተቋማት የሚያስፈልጋቸውንና የጎደለባቸውን በመጠየቅ የአቅማቸውን ድጋፍ በአይነት እንዲሁም በጉልበት ሲደርጉላቸው ቆይተዋል አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሁኔታ እያሉ የበጎ አድራጎት ስራቸውን የተመለከቱ ሰዎች ጥቆማ መሰረት ሁለት ጧሪ ደጋፊ የሌላቸውን ልበ ብርሃን የሆኑ እናቶች ያገኛሉ።
እነዚህ እናቶች ከአመታት በፊት የልማት ተነሺ በመሆን ከተነሱበት የቀበሌ ቤት መንግስት ሰጥቷቸው በጀሞ አንድ አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ያሉበት ቦታ ሄደው ሲያዩዋቸው ሁለቱም እናቶች ከባድ ህይወት የሚመሩ እና የእነሱን ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።
ሁለቱም እናቶች ማየት የተሳናቸው ነበሩ። ከጎናቸው ሆኖ የሚደግፋቸው ባለመኖሩም የእለት ጉርሳቸውንም የሚያገኙት ቤተክርስቲያን አካባቢ በመሄድ በልመና መጽዋች ከሚቸራቸው ብቻ ነበር። ሁለቱም እናቶች ልጆች ያላቸው ቢሆንም ልጆቹ የእነሱ ምራት ሁነው ስላደጉ የትምህርት እድልም ስላላገኙ ተወዳድሮ ስራ ለመስራት እና እራሳቸውንም ሆነ እናቶቻቸውን ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በዚሁ መሰረት የቅንነት በጎ ፈቃጀኞች አባላት ለእነዚህ እናቶች ቢያንስ የተወሰነ ቀዳዳቸውን ለመሸፈን ወርሃዊ መዋጮ በመሰብሰብ ወርሃዊ የአስቤዛ ድጋፍ ለማድረግ ይወስናሉ።
በዚህም መሰረት ይህን ተግባር በየወሩ የቤተሰብ ጥየቃ በሚል መርሀግብር በመከወን ከአንድ ዓመት በላይ ለእነዚህ እናቶች በአቅማቸው ድጋፍ አድርገዋል በማድረግም ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት እነዚህ እናቶች ልመናውን አቁመው በየወሩ በቋሚነት በሚደረግላቸው ድጋፍ እየኖሩ ይገኛሉ።
ከወርሃዊ አስቤዛው በተጨማሪ በተለያየ መልኩ ለእናቶቹ ድጋፍ ያረጋሉ ለምሳሌ ያህል ለቤቱ የሚያስፈልጉ እቃዎችን ማሟላት ቤቱን ማደስ (ቀለም ቅብ) የመሳሰሉትን አቅም በፈቀደ እንዲሟላላቸው ማድረግ ችለዋል። አባላቱም ሀያ ዘጠኝ ሴትና ሰላሳ ወንድ ሲሆኑ እነዚህ እናቶች እየተደገፉ ያሉትም በወሩ የተማሪና የሰራተኛ በሚል ተለይቶ ከእነዚሁ አባላት በቋሚነት ከሚሰበሰበው ነው።
ይህም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ ነገር ሲያስፈልግ እና ከቤተሰብ ጥየቃው መርሃግብሩ ተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ የሚሳተፉባቸው በጎ ተግባራት ይውል ዘንድ ከመደበኛው መዋጮ በተጨማሪ ሁሉም ኪሳቸውን በመዳበስ ያላቸውን አውጥተው የሚጠበቅባቸውን ያደርጋሉ። እነዚህ አረጋውያን እድሚያቸው በሰባዎቹ አጋማሽ ሲሆን በሚከተሉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት መሰረት ንስሃ የመግባት እና ስጋ ወ ደሙ ለመቀበል እንዲችሉ በእነዚህ በጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ሀይማኖታዊ ስርዓቱ የሚጠይቀውን ነገር አሟልተው ለዚህ ክብር እንዲበቁም አድርገዋል።
ጤናቸውን በመጠበቅም ረገድ በመንግስት በኩል የነጻ ህክምና አገልግሎት የሚያገኙ ቢሆንም በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ወይዘሪት ፀሀይ ነግራናለች። ለወደፊትም ልጆቻቸው የተሻለ እራሳቸውንም እናቶቻቸውንም ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ስራ እንዲጀምሩ ድጋፍ አድርገው እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ መርዳት እና ለሌሎች ተጨማሪ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ለመድረስ እቅድ አላቸው።
በሌላ በኩል በቋሚነት ድጋፍ ከሚያረጉላቸው እናቶች በተጨማሪ የእነሱ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እስካሁን በነበራቸዉ ቆይታ የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ ቆይተዋል። አብዛኛዎቹ አባላት የራሳቸው ስራ ያላቸው እና በትምህርት እና ስራ ላይ ያሉ በመሆናቸው ካላቸው የተጣበበ ጊዜ አንፃር ገቢ ለማሰባሰብ የሚያውሉት ጊዜ የሌላቸውም በመሆኑም እንደ አመራጭ ያደረጉት የኦንላይን ትኬት ሽያጭ ማከናወንን ነው። ይህን የኦን ላይን የሞባይል ትኬት ሽያጭ እያከናወኑ ያሉትም ለአባላቱ ብቻ ሳይሆን አላማውን ለሚያውቁ ሌሎች ግለሰቦችም ነው።
እነዚህ ፈቃደኛ በጎ አድራጊዎችም አንዳንድ ጊዜ ከትኬት ሽያጩም ባለፈ የተለያዩ የአይነት እና የሀሳብ ድጋፎችንም አቅማቸው በፈቀደ እያደረጉ ይገኛል። የተለያዩ የእነሱን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በተለያዩ ሰዎች ጥቆማ ወደ እነሱ ቢመጣም ካላቸው አቅም አንፃር ተደራሽነታቸው የተገደበ ሆኖ ቆይታል። ሆኖም በሚደርሳቸው ጥቆማም ሆነ እነሱም ከሚመለከቱት ተደራሽነታቸውን ማስፋት መቻል እንዳለባቸው ያምናሉ።
ነገር ግን በዚህ አካሄድ ሁሉንም ለመከወን የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው ወደ ህጋዊ መንገድ በመመዝገብ እና የአባላታቸውን ቁጥር በመጨመር ተደራሽነታቸውን የማስፋት ፍላጎት እና እቅድ ያላቸው ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም ወደ ተግባር እንደሚገቡ ገልጸዋል። ይህ ሲሳካ ተደራሽነታቸውን አስፍተው ለተለያዩ ድጋፋቸውን ለሚሹ ወገኞች የመድረስ እና ትልቅ የበጎ አድራጎት ማዕከል በማቋቋም ሰፋ ያሉ ስራዎችን የመስራት እና በበጎነት ምሳሌ በመሆን የራሳቸውን አሻራ የማስቀመጥ ህልም አላቸው።
ስብስቡ የሚገናኝባቸው በቴሌግራም ቻናል ሲሆን አንድ ሺ እና ከዛያ በላይ ተከታታይ እና አባላት ከሀገር ውስጥና ከውጪ ያለው ነው። በሀገር ውስጥ ካሉት ሰፋ ያሉት አባላት ቁጥር የሚይዘው ከአዲስ አበባ ሲሆን ከአዳማና ከቢሾፍቱ፣ ባህርዳር እና ከሌሎች የሀገሪቷ ክፍልም የሚገኙ አባላት አላቸው።
ከበጎ ስራው በተጓዳኝ ቤተሰባዊነቱን እና ለማጠናከር በየቀኑ ማታ ማታ የሚያቀርቧቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች የታሪክ፣ የጥያቄ እና መልስ፣ የጤና ነክ ጉዳዮች፤ እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉና ሌሎችም በማህበሩ አባላት እንደየእውቀታቸው የሚቀርቡበት ፕሮግራም ያለ ሲሆን በየቀኑም በእነዚህ ፕሮግራሞች በቴሌግራም የመወያያ ግሩፓቸው አማካኝነት ይማማራሉ፤ ይወያያሉ።
ይህ ስብስብ ከተመሰረተ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ ሁለት አመት ሞልቶታል። የፊታችን እሁድ ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ ይህንን በማስመልከት በአባላቶች እና ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች ያሰባሰቡትን ድጋፍ በመያዝ የሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን በዘውዲቱ መሸሻ የህፃናት መንከባከቢያ ማዕከል በመገኘት በማዕከሉ ከሚገኙ ህፃናት ጋር ለማክበር ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
የእነዚህ ወጣቶች ስብስብ ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል። የመጀመሪያው እያንዳንዱ ሰው ማህበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም ህዝብን ከህዝብ ሊያራርቅ ግጭት ለመፍጠር ሳይሆን ለበጎ አላማ ሊሆን እንደሚገባ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ እያንዳንዱ ሰው በጎ ነገር ለመስራት ውስጡ ካሰበ ትንሽም ይሁን ትልቅ ሊያደርገው የሚችለው ነገር መኖሩን ነው። በርካታ ሰዎችም ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱም አቅሙም ኖሮት አጋጣሚውን ያላገኘው የትም ሳይሄድ የማህበራዊ የትሰስር ገጾችን በመጠቀም መደገፍ ይችላል።
በኢትዮጵያ ብዙ እርዳታ የሚሹ ወገኖች እንዲሁም ብዙ መርዳት መደገፍ የሚፈልጉ እና የሚችሉ ዜጎችም አሉ የምትለው ፀሀይ ማህበራዊ የትስስር ገጾችን በመጠቀም እነዚህን ማገናኘት እንደሚገባም ታሳስባለች።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኀዳር 24 / 2014