ከወር በፊት በዩጋንዳ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የመካከለኛና ምሥራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በማንሳት በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ትልቅ ድል ያሳኩት የሉሲዎቹ ተተኪዎች ከጣፋጩ ድላቸው ማግስት ወደ ሌላ የስኬት ጉዞ አማትረዋል።
ይህም በ2022 በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ማጣሪያ ተሳታፊ ለመሆን የሚያደርጉት ጉዞ ነው።
ከሴካፋ ድላቸው ማግስትም ሦስተኛውን ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ጨርሰው ከትናንት በስቲያ ወደ ተጋጣሚያቸው አገር ቦትስዋና አቅንተዋል።
‹‹ተጫዋቾቼ መቶ በመቶ ከሴካፋ ድል ደስታ ወጥተው ለዓለም ዋንጫው ዝግጁ ሆነዋል›› በማለት ወደ ቦትስዋና ከማቅናታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ የተናገሩት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል፣ የሜዳ ችግር እንደፈተናቸው ገልጸዋል።
‹‹በቀን ሁለቴ ለመሥራት የነበረን ሃሳብ በብሄራዊ አካዳሚ ያለው ሜዳ ምቹ ባለመሆኑ በይበልጥ በአካል ብቃት ላይ አተኩረን ስንሠራ ቆይተናል፣ ነገር ግን በ35 ሜዳ የምንችለውን ጥሩ ልምምድ እንድሠራ ያደረገን እንደ አገር አይቶ የረዳንና ሜዳውን የፈቀድልንን ዘላለም በቀለን እናመሰግናለን፣ በምቹ ሜዳ ልምምዳችንን ሠርተን ዛሬ ጨርሰናል›› ሲሉም ቡድኑ ባለፉት ሳምንታታ በዝግጅት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ተናግረዋል።
ቡድኑ ለተወሰነ ጊዜ መበተኑን በተመለከተ አሰልጣኙ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱም ‹‹ተጫዋቾቹ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ እንደመቆየታቸው ጫና ውስጥ ስለነበሩ የተወሰነ ቀን ማረፋቸው የግድ ነው፣ የተወሰነ የሴካፋ ቻምፒዮኖች የዓለም ዋንጫ ጉዞ ነገ ይጀምራል ጊዜ ዕረፍትም በማግኘታቸው ተስማምቻለሁ፣ መሆን ያለበት ነው የሆነው፣ አሁን ግን ለቀጣዩ ጨዋታ መቶ በመቶ ከሴካፋ ድል ደስታ ወጥተው ለዓለም ዋንጫው ማጣርያ ዝግጁ ሆነዋል›› ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፣ ቡድኑ የሴካፋ ዋንጫ በመውሰዱ የጎደለው ነገር የለም ማለት አይቻልም። ቡድኑ ጠንካራም ደካማም ጎን የነበረው በመሆኑ ጉድለቶቹን ለማስተካከል ጥረት እንዳደረጉ አሰልጣኝ ፍሬው ተናግረዋል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነገ የሚገጥሙት የቦትስዋና ቡድንን ያለፉ ጨዋታዎች በመመልከት የተወሰኑ ቪዲዮችን ለማየት ጥረት እንደተደረገ የገለጹት አሰልጣኙ፣ የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት ተረድቶ ለነገው ጨዋታ የመዘጋጀት ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
የወዳጅነት ጨዋታንም በማድረግ ለነገው ፍልሚያ የሚችሉትን ሁሉ ዝግጅት እንዳደረጉ አብራርተዋል። በሴካፋው ዋንጫ አስደናቂ ጨዋታና በርካታ ግቦችን በተጋጣሚዎቻቸው መረብ ላይ ማሳረፍ የቻሉት የ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋኝጫ ማጣሪያ የበቁት በዘንድሮው የሴካፋ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፈው በአምስት ጨዋታዎች አንድም ሳይሸነፉ ለቻምፒዮንነት ክብር በመብቃት ነው።
በሴካፋው ውድድር በአጠቃላይ አስራ ስምንት ግቦችን አስቆጥረው ሦስት ግብ ብቻ አስተናግደዋል። ይህም ብሔራዊ ቡድኑን በቀጣይ በሚያደርገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከጠንካራ ተፎካካሪነት ባለፈ በውጤት የታጀበ ረጅም ጉዞ እንደሚያደርግ ግምት አሰጥቶታል።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን ሁለተኛው ዙር ላይ የተቀላቀሉት የሉሲዎቹ ተተኪዎች ርዋንዳን በሜዳዋና ከሜዳዋ ውጪ በተመሳሳይ አራት ለዜሮ በድምሩ ስምንት ለዜሮ በመርታት ለነገው ሦስተኛ ዙር ማጣሪያ መድረሳቸው ይታወቃል።
በዚህ ዙር ቦትስዋናን በደርሶ መልስ ጨዋታ አጠቃላይ ውጤት ማሸነፍ ከቻሉ ከታንዛኒያና ቡሩንዲ አሸናፊ ጋር በአራተኛው ዙር ማጣሪያ የሚገናኙ ይሆናል። የሉሲዎቹ ተተኪዎች ቻምፒዮን በሆኑበት የዘንድሮ የሴካፋ ዋንጫ ታንዛኒያን ሁለት ለአንድ፣ ቡሩንዲን አንድ ለዜሮ መርታታቸው አይዘነጋም።
የአፍሪካ አገራት የዓለም የሴቶች ከሃያ ዓመት በታች ማጣሪያ ጨዋታ በሦስተኛው ዙር አስራ ስድስት አገራት በደርሶ መልስ ጨዋታ የሚፋለሙ ሲሆን፤ ከእያንዳንዱ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን ወደ አራተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ያልፋል።
በአራተኛው የማጣሪያ ውድድርም ስምንት አገራት በደርሶ መልስ ሁለት ጨዋታዎች ተለይተው ለመጨረሻውና አምስተኛው ዙር ማጣሪያ ጨዋታ አራት ቡድኖች የሚለዩ ይሆናል። በመጨረሻም አራቱ ቡድኖች በሁለት ጨዋታዎች ተፋልመው ሁለቱ አሸናፊ አገራት ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014