አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር እቅዱን 81 በመቶ ማከናወኑን አስታወቀ። የመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ ታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መስሪያ ቤቱ የአገልግሎት አድማሱን ይበልጥ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ተደራሽነት በሰፈነበት ሁኔታ እቅዱን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ባለፉት ስድስ ወራትም በተለያዩ ዘርፎች ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት በተሻለ ደረጃ በማከናወን የእቅዱን 81 በመቶ መፈጸም ችሏል፡፡
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ያስቀመጠውን እቅድ ለመፈጸም በሚያደርገው ጥረት ያጋጠሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በመቋቋምና መፍትሄ በመስጠት እቅዱን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የሰራተኞች የአገልጋይነት መንፈስ አለመኖር፣ የመሳሪያዎች ስርቆት፣ የመልካም አስተዳደር ግድፈቶች፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ፣ የሃይል ብክነት፣ የቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር ለተቋሙ ስራ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡
ሆኖም እነዚህን ተቋቁሞ በማለፍ በስድስት ወሩ የ81 በመቶ አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡ ከ97 በመቶ በላይ አፈፃፀም የተመዘገበባቸው ዘርፎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ተቋሙ ከገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም አኳያ በስፋት የሄደ ሲሆን፤ በኢነርጂ ሽያጭ አሰባሰብ የ92 ነጥብ 2 በመቶ፣ በውዝፍ ሂሳብ አሰባሰብ የ76 ነጥብ 27 በመቶ፣ በቆጣሪ ሂሳብ አሰባሰብ የ80 ነጥብ 82 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል፡፡
የካፒታል ፕሮጀክት እቅድ አፈፃፀሙም 75 በመቶ ሆኗል። አቶ መላኩ እንዳብራሩት፤ የስምንት ከተሞች የሥርጭት መልሶ ግንባታ አቅም ማሳደግ ፕሮጀክ ግማሽ አመት አፈፃፀምን 8 ነጥብ 69 በመቶ ለማከናወን ታቅዶ 5 ነጥብ27 በመቶ ያህሉን በማከናወን የ60 ነጥብ 64 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
አጠቃላይ የፕሮጀክቶች የፊዚካል ስራዎች አፈጻጸምም የ97 ነጥብ 55 በመቶ ሆኗል። በተመሳሳይ፣ በግማሽ አመቱ 90 ሺ 71 አዲስ ሃይል ፈላጊ ደንበኞች ሃይል እንዲያገኙ ማድረግ፤ 109ሺ360 አዲስ ቆጣሪ ማሰራጨት፣ 58ሺ 677 ኪሎ ሜትር ኤ.ሲ ገመድ ማቅረብ መቻሉን የገለፁት አቶ መላኩ፤ ክንውኑ በ2010 ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 955ሺ 818 ኪሎ ሜትር ጋር ሲነፃፀር የ99 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል።
ለረጅም ዘመናት የተቋሙ ከፍተኛ ችግር ሆኖ የቆየውን የሃይል ብክነት ለመቀነስ በመሰራቱም በ41ሺ 59 ቆጣሪዎች ላይ አጠቃላይ ምርመራ በማካሄድ 100 ነጥብ 15 ሚሊዮን ብር፤ እንዲሁም 159ሺ 827 ነጥብ 21 ሜጋ ዋት ሀወር (MWhr) ኢነርጂ ማዳን መቻሉንም ገልፀዋል።
በተቋሙ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ለማህበራዊ ተቋማት፣ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለግል መኖሪያ ቤቶችና ለመሳሰሉት ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚህም 589 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ማስፋፊያ፣ 1ሺ 554 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር መልሶ ግንባታ፣ 25ሺ 537 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ጥገና፣ ለ61 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል ማዳረስ፣ 11ሺ 88 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ለገጠር ከተሞችና መንደሮች መካከለኛ ቮልቴጅ መስመር ግንባታ፣ እንዲሁም ለ 675 ነጥብ 92 ኪሎ ሜትር የገጠር ከተሞችና መንደሮች መካከለኛ ቮልቴጅ መስመር ግንባታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ 100 የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ እቅድ አውጥቶ ለተግባሩ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም ከንግድ ባንክ የተፈቀደው ብድር ከተለቀቀ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በግርማ መንግስቴ