ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና ፈተና በድል ለመወጣት ያስችላት ዘንድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ወደ ግንባር ማቀናታቸው ይታወቃል:: ይህንንም ተከትሎ ኦሊምፒክን ጨምሮ በታላላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ኢትዮጵያን ያኮሩ እንደ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ፈይሳ ሌሊሳ፣ ማርቆስ ገነቲና ፋንቱ ሚጌሶ የመሳሰሉ በርካታ እንቁ አትሌቶች ወደ ግንባር በማቅናት ጭምር በሠላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግርም ጊዜ ለአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ እንደሚዋደቁ አረጋግጠዋል::
አገርን ከገጠማት የሕልውና አደጋ ለማዳን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዳር እስከዳር በተነቃነቀበት በዚህ ወቅት የስፖርቱ ቤተሰብ ለአገሩ አለኝታ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል:: አትሌቶች ግንባር ድረስ እየዘመቱ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የእግር ኳስ ቤተሰቡም ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆኑን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አረጋግጧል:: ከትናንት በስቲያም የስፖርቱ ዘርፍ አመራሮችና ሠራተኞች ወደ ግንባር መዝመትን ጨምሮ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን እንደገለጹ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾችም ለመከላከያ ሠራዊት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመስጠት ቃል በመግባት የአገር አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ከትናንት በስቲያ ፕሪምየር ሊጉ እየተካሄደባት በምትገኘዋ ሐዋሳ ከተማ ከ16ቱም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሂደትዙሪያ ውይይት አድርገዋል:: ከውይይቱም በኋላ የክለብ አመራሮች ወደ ተጫዋቾች ይህንን ተልዕኮ በመያዝ ሄደው አነጋግረዋል:: ተጫዋቾችና የክለብ አመራሮችም ‹‹እንኳን እግር ኳስ መጫወት በሠላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው አገር ስትኖር ነው›› በማለት የአንድ ወር ደመወዛቸውን አገርን ከመፍረስ ለመታደግ በዱር በገደሉ የሕይወት መስዋትነትን እየከፈለ ላለው ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባታቸው ታውቋል::
ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት ተጫዋቾች መካከል በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተለያዩ ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙ የውጭ አገር በተለይም አፍሪካውያን
ተጫዋቾች ይገኙበታል:: አፍሪካውያኑ ተጨዋቾች ‹‹ይህ እኛንም ይመለከታል በማለት›› ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸው ታውቋል:: ይህ የገንዘብ ድጋፍም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ታውቋል። የክለቦቹ አመራሮችም ይህ ድጋፍ በደጋፊ ማህበራትም በኩል ተጠናክሮ በደም ልገሳ ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል።
የእግር ኳሱ ቤተሰብ ለመከላከያ ሠራዊት በተለያየ አይነት ድጋፍ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያ አይደለም:: ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመወዛቸውንና የደም ልገሳ ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባታቸው ይታወሳል::
በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ የቆየ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ በቀጣይም ድጋፋቸውን በማጠናከር በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በደም ልገሳ ጭምር በመደገፍ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቋል::
ባለፈው መስከረም ወር ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማድረግ በታሰበው ‹‹እግር ኳሳችን ለሰላማችን›› የተሰኘ መርሃ ግብር በታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና በመከላከያ አመራሮች መካከል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የእግር ኳስ ውድድር መካሄዱ ይታወሳል:: ከውድድሩ ጎን ለጎን በወቅቱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች መካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ አባል ክለቦች 8 ሚሊየን ብር ለአገር መከላከያ ድጋፍ መስጠታቸው አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹም ለአገር መከላከያ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለፅ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የዚምባቡዌ አቻቸውን ባህርዳር ላይ አንድ ለባዶ በረቱበት ማግስት የደም ልገሳ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንትም በከፍተኛ ሊግ የ2014 የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አሊሚራህ ሙሐመድ ባደረጉት ንግግር ‹‹በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፌዴሬሽናችን ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውንና የደም ልገሳ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባታቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ። የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም ከውድድሩ ባሻገር በድጋፉ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናችሁን ማረጋገጥ እንዳለባችሁ ላሳስብ እፈልጋለሁ›› በማለት ተናግረዋል። አቶ አሊሚራህ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ቤቱ ተወያይቶበትም የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ አባላት ሀሳቡን በመደገፍ ከተወያዩበት በኋላ ውሳኔያቸውን በቅርቡ በፌዴሬሽኑ በኩል እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 /2014