የቀን ፀሐይ ግለት፣የሌሊቱም ቁር ሳይበግራቸው ባዶ እግራቸውን በጫካና በጎዳና ላይ የሩጫ ልምምዳቸውን የሚሠሩ፣ የእግራቸው መቁሰልና መድማት የማያቆማቸው፣ ከህመማቸው በቅጡ ሳያገግሙ ለአገራቸው ሰንደቅዓላማ ክብር እስከመጨረሻ የሚፋለሙ፣ ህመማቸውን ‹‹ዋጥ አርገው›› ውድድራቸውን በድል በመወጣት ለክብሯ ምንጊዜም ዘብ የሚቆሙላት አትሌቶች አገር ኢትዮጵያ ትሰኛለች፡፡
ነጭ ላባቸውን በማፍሰስ ብቻም ሳይሆን ወድቀው እየተነሱ፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ለአገራቸው ክብር ቅድሚያ ሰጥተው ለባንዲራዋ የሚሮጡትላት የስፖርቱ ዓለም ጀግኖች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንቁ አትሌቶች የሚባሉትም ውድድሮችን በማሸነፍ ብቻ አይደለም፡፡
አገራቸው በፈለገቻቸው ጊዜ ሁሉ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በማበርከት አለኝታነታቸውን በተግባር ለማስመስከር የሚቀድማቸው የለም፡፡ ዛሬም እነዚህ እንቁዎች አገራቸው የሕልውና ፈተና በገጠማት ጊዜ ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ውድ ህይወታቸውን ለመስጠት እንደማይሰስቱ፣ ከአገራቸው የሚቀድም ሌላ ጉዳይ ሊኖራቸው እንደማይችል በተግባር አሳይተዋል፡፡
በዓለም ህዝብ ፊት በኦሊምፒክ አደባባይ ኢትዮጵያ እውቅና እና ክብርን እንድትቀዳጅ ካደረጓት ስፖርቶች መካከል የአትሌቲክስ ስፖርት ቀዳሚውን ስፍራ መያዙ ይታወቃል፡፡ ታዲያ በዚህ ስፖርት ለሃገር ከተመዘገቡ ድሎች መካከል በኦሊምፒክ ሁለት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ፤ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ አምስት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ13 ሜዳሊያዎች በሦስት አትሌቶች ብቻ ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ጀግኖች ደግሞ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ገዛኸኝ አበራ እና ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡
የአትሌቲክስ ስፖርት ፈርጥ እና በስፖርቱ የብቃት መለኪያ ሚዛን የሆኑት እነዚህ አትሌቶች አሁን ደግሞ ለሃገራቸው ክብር ዳግም በጦር ግንባር ተሰልፈዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር ማቅናታቸውንና አገራቸውን የሚወዱ ሁሉ ‹‹በግንባር እንገናኝ›› ያሉትንም ጥሪ እንቁዎቹ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተቀብለዋል፡፡ በሰላማዊው የፍልሚያ አውድ ድልና አሸናፊነት መለያቸው ነውና የአገራቸውን ሕልውና ፈተና ለሆነው አንገብጋቢ ጉዳይ እንቁዎቹ አትሌቶች ህይወታቸውን ሳይሳሱ ለመስጠት ወደጦር ግንባር ተጉዘዋል፡፡
ለሃገር ተቆርቋሪውና በየትኛውም ጉዳይ ቀዳሚ ተሰላፊ የሆነው አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘውን ወቅታዊውን ሁኔታ እንዳላየ ማለፍ አላስቻለውም፡፡ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ከቀያቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቹ በገንዘብና በቁሳቁስ ሲደግፍ የቆየው ጀግናው አትሌት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ በመቀበል ከመከላከያው ጎን በግንባር ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ካረጋገጠ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በኦሊምፒክ የሁለት ወርቅ፣ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ፣ በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች፣ ዋንጫዎችና ዘርፈ ብዙ ክብሮች ባለቤት የሆነው ኃይሌ፤ ሃገር በፈለገችው ጊዜ ሁሉ ለመዝመት ፈቃደኛ መሆኑንም በማሳወቅ በዓለም መገናኛ ብዙሃን ጭምር መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ጀግናው አትሌት ኃይሌ ቀደምቶቹን ተከትሎ ወደ ስፖርቱ ሲገባ፤ እርሱን የተመለከቱ በርካቶች ፈለጉን ተከትለው ለሃገር ክብር ተሰልፈዋል፡፡ ዛሬም እንደትላንቱ ለሃገር ክብር የሚሮጡ ሳይሆን ለህልውናዋ በግንባር የሚዘምቱ መሆናቸውን እንዲሁም ደጀንነታቸውን ያረጋገጡትም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የሲድኒ ኦሊምፒክና የኤድመንተን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ገዛኸኝ አበራም ሃገራዊ ጥሪውን ተቀብሎ ሌላኛውን የኦሊምፒክ ጀግና ተቀላቅሏል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ በኦሊምፒክ ሃገሩን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ያደረገውና በዴጉ የዓለም ቻምፒዮናም የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀው ወጣቱና ከለውጡ በፊትም የነበረውን ጨቋኝ ስርዓት በአደባባይ ሲቃወም የነበረው ደፋሩ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳም ሃገራዊ ጥሪውን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
ሃገር እንደ ሃገር የመቀጠል ዕድሏ አደጋ ላይ ሲወድቅ ያስከበረቻቸውን ኢትዮጵያን አክብረው በጦር ሜዳ ከከተቱ አትሌቶች መካከል አንዱ ኮማንደር ማርቆስ ገነቲ ነው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች ውጤታማ መሆን የቻለውና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው አትሌት ማርቆስ እንደ ጓደኞቹ ሁሉ በግንባር ለመገኘት ወስኖ ተነስቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሚታወቁበት ረጅም ርቀት ሳይሆን በአጭር ርቀት ውጤታማ የሆነችው አትሌት ፋንቱ ሜጌሶም ለሃገሯ አስፈላጊ በሆነችበት ዘርፍ ሁሉ አለኝታ ከሆኑት መካከል እንደሆነች በቃሏ አረጋግጣለች፡፡
አትሌቶቹ በግንባር ተገኝተውም ለሃገራቸው ሰላም እየተዋደቀ የሚገኘውን ሠራዊት አበረታተዋል፡፡ አትሌቶቹ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታም፤ በዓለም መድረክ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርገው ያውለበልቡላትን ኢትዮጵያን ጁንታው ፈጽሞ እንደማያፈርሳትና ምን ጊዜም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ወራሪውን ኃይል እንደሚፋለሙ ገልጸዋል፡፡ ሃገር ማዳን ለመከላከያ ሠራዊት ብቻ የሚሰጥ ኃላፊነት ባለመሆኑ በየሥራ መስኩ ያሉ ሌሎች ዕውቅ ኢትዮጵያዊያንም ወደ ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አትሌቶቹ ሠራዊቱ እያሳየ ያለውን ጀብድ አድንቀው፤ ሠራዊቱን ተቀላቅለው አሸባሪውንና ወራሪውን ቡድን ለመፋለም ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014