አዲስ አበባ ፡- ከ123 ዓመት በፊት በዓድዋ ጦርነት መስዋእትነት ለከፈሉ ጀግኛ አርበኞች የመታሰቢያ ሃውልት እንደሚቆም ተገለጸ።123ኛው አመት የዓድዋ ድል በዓል አዲስ አበባ በሚገኘው የሚኒልክ አደባባይ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት፣ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋእትነት ድልን አጎናጽፈውናል፤ ድል ደግሞ ከነፃነት በላይ ነው። ለዚህ ክብር ላበቁን አርበኞችና መስዋትነት ለከፈሉ ጀግኖች አባቶች አዲስ አበባ ክብራቸውን የሚመጥን ትልቅ እና ማስተማሪያ የሆነ የመታሰቢያ ሃውልት ይሰራላቸዋል።
የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ተጋድሎና መስዋትነት አገራቸውን ያስከበሩበት ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ አንፀባራቂ የሆነ ድል ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፣”የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ተጋድሎና መስዋትነት ሀገራችንን ያስከበሩበት ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ አንፀባራቂ የሆነ ድል ነው” ብለዋል።
የጥንታዊ አርበኞች ማህበር አባል አርበኛ ማሚቴ ምህረቱ በበኩላቸው፣እቴጌ ጣይቱ በዛን ወቅት ጀግና ለመሆን ቆራጥነት እንጂ ወንድ ሆኖ መፈጠር አይጠይቅም በሚለው የጀግና አባባላቸው ለአድዋ ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ሴቶች ስንቅ በማቀበል፣ወኔ በመስጠት፣ ፈሳሻ እና መድሐኒት በመያዝ የቆሰለውን በማከም ለድሉ የበኩላቸውን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ሚኒልክ አደባባይ በተከበረው በዓል የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በአብርሃም ተወልደ