ሁሌም በዘመን መሀል በጊዜ ተዳፍነው የማይጠፉ፣ በአድማስ የማይከለሉ፣ በድንበር ሳይታጠሩ ፀንቶ የሚቆዩ ድንቅ ክስተቶች ይፈጠራሉ። ሰበብ አልባ ክስተት የለምና ሁሉም የምክንያት ውጤት ስሌት ናቸው። ሁሉምም የራሳቸው መሆኛ ጊዜ አላቸው።
አንዳንዴ ደጋግመው ቢከሰቱ ደስ የሚሉ ውብ ክስተቶች አሉ። የትናንት ናቸው ተብለው ሲታለፉ የሚከብዱ ሁሌም የሚናፈቁ የክስተት ትእይንቶችም አሉ። ከሰሞኑ ‹‹no more ወይም‹‹በቃን›› በሚል በመላው ዓለም በመካሄድ ላይ የሚገኘው የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ ድምጸቱንና ድምቀቱ ከዚያም በላይ አላማውን ላስተዋለ ሰው ምናለ ደጋግሞ ቢከሰቱ ማለቱ አይቀርም።
ኢትዮጵያዊነት እንደ ዓድዋ ተራሮች ፅኑ፣ እንደ ድሉ አንፀባራቂ ሰንደቅ ሆኖ በታየባቸው በእነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ኢትዮጵያዊነት በአገራት አደባባዮች ደምቆና ገዝፎ ታይቷል።
የማንነትና የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ፍቺው ቅኔና ወርቁ ነፃነት መሆኑ የአደባባይ እውነታ ሆኗል። ኢትዮጵያውያን አብረው ሲተሙ ከውብም በላይ አስፈሪ መሆናቸው፤ የችግሮቻችው ግዝፈትም በአብሮነታቸው ቦታ እንደሌለው፣ ኃይላቸው ከአብሮነታችን የሚመነጭ ጥንካሬአቸው እንደሆነ ተረጋግጧል።
በሰልፎቹ ኢትዮጵያውያን ተንበርክኮ ከመኖር ሞትን ተቀብለው ቀና እንዳሉ በክብር መሞትን የሚመርጡ ስለ ነፃነታቸው ቀናኢ የሆኑ ሕዝቦች መሆናቸውን አስመስክረዋል። እንደ ሴረኛውና ሸራቢው፣ እንደ ሟርተኛውና ፈራጁ ኢትዮጵያ ከውጭም ከውስጥም ፈተና ሲበዛ የምትደክም፣ ሕዝቦቿም የሚንበረከኩ እንዳልሆኑም በዓለም አደባባይ ታላቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይ የሴራው ተዋናይ በሆኑ አገራት ሜዳ ተገኝተው በግልፅ ቋንቋ፤ ‹‹አንድ ነን! ሉዓላዊ ነን! ማደግ መብታችን ነው! ከመንገዳችን ውጡልን!፤ አገሬን አትንኩ!፣ ከአገሬ ላይ የክፋት ዓይኖቻችሁን ንቀሉ!፣ መሰሪ እጆቻችሁን አንሱ እምብኝ ለቅኝ ግዛት!፣ እምብኝ ለሴራ፣ እምብኝ ለሐሰት፣ እምብኝ ለጣልቃ ገብነት፣ እምቢ ለአገሬ!» የሚሉ መልዕክቶቻችን ደምቀውና ጎልተው ተደምጠዋል። ሰልፈኖችም የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ፅኑ ፍላጎት ምን እንደሆነ ከፍ ባለ ድምጽ መስማት ለሚፈልገው፤ ለማፈይልገውም አሰምተዋል።
‹‹no more ወይንም ‹‹በቃን” በተሰኘው አገራዊ ንቅናቄና የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ውሸት ደጋፊዎች ቢኖሯትም የእውነትን ያህል አቅም እንደሌላት በተጨባጭ ታይቶበታል። እውነት የቀበራትን ፈንቅላና የጋረዳትን መጋረጃ ገላልጣ አደባባይ ላይ ጎልታ ቆማለች።
ሀቅ ሲኖርህ በፍርሀት ሳይሆን በኩራት እንደምትራመድ ተመስክሮበታል። ውሸትና ውሸታሞች ሲርበደበዱ፣ እውነትን የተደገፉ በልበ ሙሉነት ቆመውበታል። የኢትዮጵያውያን የእውነት ጎርፍ የዓለምን ውሸት በሙሉ ጠራርጎታል። ኢትዮጵያውያን የያዙት እውነት በሐሰተኛ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙፆን ቢዘገብ ባይዘገብ በክብር መዝገብ ላይ በደማቁ ታትሟል።
በእርግጥም ኢትዮጵያ የውስጥ ተላላኪዎችና የውጭ ሴረኞች በደገሱት የጥፋት ድግስ በሸረቡት ሴራ ተጠልፋ የምትንኮታኮት ሳትሆን ሞተው ሊያኖሯት በቆረጡ እልፍ ልጆቿ ወደቀች ሲሏት ቀና ቀጥ የምትል እና ፍሬ ምታፈራ፤ ጠፋች ተበተነች ሲሉ ከአለት የጠነከረ አንድነት የምትገነባና የምታፀና ነፃ የነበረች፣ ነፃ የሆነች፣ ነፃ ሆና ታፍራና ተከብራ የምትኖር አገር ነች።
ወትሮም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ይራብ ይጠማል እንጂ በነፃነቱ አይደራደርም። የነፃነት ትርጉም ስለሚገባው ለነፃነት መስዋትነት ይከፍላል። ለነፃነቱ ራሱ ዘብ ይቆማል። የሌሎችን ነፃነት አክብሮ የራሱንም ያስጠብቃል። ነፃነቱን የሚገዳደሩትን ለመፋለም ለነገ የሚለው ቀን የለውም።
በዚህ ሰልፍ ላይም የኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር ሁሌ እንደጋለ ሳይቀዘቅዝ የሚኖር ፍም እሳት እንደሆነ፣ ኢትዮጵያውያንም አገራቸውን የነኩባቸው ዕለት ትንታግና አይነኬ አራስ ነብር እንደሚመስሉ፣ በአገራቸው ለመጣ ሞትን እንደ ሠርግ እንደሚቆጥሩት አስመስክረውበታል።
ለመላው ዓለም በዚህ መልኩ ድምጻችንን ማሰማታችን እጅግ ጠቃሚ ነው:: በአሁኑ ወቅትም እውነትን ለመካድና ላለመስማት ከማሉት ውጪ ድምፃችን ሰሚ እያገኘ መሆኑን እየተመለከትን እንገኛለን። በ# NO MORE ሃሽታግ ዘመቻ ምክንያትም የኢትዮጵያ የነፃነት ትግል የአፍሪካ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝቡና ለነፃነት የሚታገሉን ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅትም ከግለሰብ እስከ አገርም የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፉ ቁጥራቸው ከዕለት ዕለት እየጨመረ መጥቷል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት የ #በቃ ንቅናቄን መቀላቀላቸውም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
ከረፈደ አገር ከፈረሰች በኋላ ብንጮህ፣ ብናብድ ምንም ፋይዳ የለውም። የሰሞኑ ሰልፍ በየሳምንቱ መደጋገምም አለበት። ወያኔዎች አገር ካላፈረስን ብለው በየቀኑ በውጭ አገር ጎዳናዎች ሲንደባለሉ፣ እኛ አገር ለማቆየት ከዚህም በላይ ብንጮህ ያንስብናል!።
ያለንበት የፈተና ወቅት መሰል አበርክቶ እና የተልዕኮ መጋራት ይፈልጋል። ሁሉም በዚህ አዲስ ታሪክ ጅማሪ ውስጥ የሚጠበቅበትን ብቻ እንደዜጋ ማበርከት ከቻለ ወደ አሰብንበት የታሪክ ከፍታ መድረሳችን ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት ጥቂት ጠብታ ማዋጣት ከቻልን የጎደለውን ፈጣሪ ይሞላዋል። ይህ ደግሞ የሃይማኖታዊ አስተምሯችን እውነታ ነው። እንደ አቅማችን የሚገባንን መስዋዕትነት በመክፈል ለአገራችን ሕያውነት ባለውለታዎች ነን።
የጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል በሁለንተናዊ ድል ለማጠናቀቅ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን «ሊነጋ ሲል ያለው ጨለማ ድቅድቅ እንደሆነ » ያለንበትም የትግል ምዕራፍ እንዲሁ ነው።
በርግጥ ጣፋጩን ስኬት የሚያጣጥሙ የሚጀምሩ ሳይሆኑ የሚጨርሱ ናቸው። መጀመርም ይልቅ መጨረስ ትጋት ይጠይቃል። በመጀመራችን ብቻ ሳይሆን ስለመጨረሳችንም እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ኢትዮጵያን የማስከበሩ ተጋድሎ በፍፃሜ እንጂ በጅማሬ ብቻ አይመጣም።
ውጤቶች በውጣ ውረዶች የተሞሉ በርካታ ሒደቶች አሏቸው። ፈለግንም አልፈለግንም በወቅታዊው ፈተና መፈተናችን አይቀርም። በምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም የሚበጀንን ለይተን መንገዱን በጽናት ስለጀመርን በጽናት መጨረስ በሚያስችል ማንነት እራሳችንን ማጠንከር ያስፈልገናል።
በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም የምንፈተነው በአቅማችን ነው። ፈተናዎቻችን ሊያጠነክሩን የመጡ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው። ከፈተናችን መጠንከር ይልቅ የሽንፈታችን ምንጭ የሚሆነው የእምነታችን መላላት ነው። የእምነታችን ጥንካሬ የአሸናፊነታችን መሠረት ነው። ብንወድቅ እንነሳለን፤ ብንሞት በሞታችን ህያው የሆነ እልፍ ትውልድ እንፈጥራለን፤ እየተተካካን አገራችንን እንደ አገር እናስቀጥላለን።
በያንዳንዷ እርምጃችን አገራችንንና የአገራችንን ክብር እናስቀጥላለን። መራመዳችን ለምንፈልገው ነገር ቅርብ ያደርገናልና ተራምደን ለመድረስ እንጂ ቆመን ለማልቀስ እጅ አንስጥ። በማይቆም ጥረት ውስጥ ስንኖር ደግሞ ለማይቀር ድል እንታጫለን።
‹‹What Goes Around Comes Around›› እንደሚባለው፣ የምናጭደውም ከዘራነው ውጪ አይሆንም። ሽንፈታችን የሚፀናው ፍልሚያውን ለማቆም ስንወስንና ስንቆም ነው። ድላችን የትግላችን ፍሬ ነው። ስኬታችንም የፅናታችን ውጤት ነው። በፅናታችን ከፀናን ድል በእጃችን ነው። ፈተናዎች ያንገዳግዱን ይሆናል እንጂ አይጥሉንም። ባለመሰልቸት ከታገልን የፈለግነውን ከማግኘት የሚያቆመን ኃይል አይኖርም! ።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2014