የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ባለፈው ክረምት በጃፓኗ መዲና ከተካሄደ ወዲህ የአትሌቲክሱ ዓለም በዚህኛው አመት ከሚጠብቃቸው ታላላቅ ውድድሮች አንዱ የሆነው የ2022 የዳይመንድሊግ ፉክክሮች መርሃግብር ይፋ ሆኗል። በዚህም መሠረት የዓለማችን ከዋክብት አትሌቶች በተለያዩ አራት አህጉራት በአስራ አራት የዓለማችን ከተሞች በተለያዩ ርቀቶች የሚፎካከሩ ይሆናል። ከነዚህም መካከል ቻይና በሁለት የተለያዩ ከተሞች ሁለት የዳይመንድሊግ ውድድሮችን እንደምታስተናግድ ከወጣው መርሃግብር ለመረዳት ተችሏል።
በርካታ የመም እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ውድድር አትሌቶችን ከዓለም ዙሪያ በሚያፎካክረው የ2022 ዳይመንድሊግ አትሌቶች ለአንድ ቀን በሚካሄዱት አስራ ሦስት ውድድሮች ነጥብ ለመሰብሰብ ይፎካከራሉ። አስራ ሦስተኛ አመቱን የያዘው የዳይመንድሊግ ውድድር ዘንድሮ ከግንቦት አንስቶ እስከ መስከረም የሚካሄድ ይሆናል።
የመጀመሪያው ውድድር እንዳለፉት አመታት በግንቦት አጋማሽ በኳታር መዲና ዶሃ እንዲካሄድ መርሃግብር የተያዘለት ሲሆን ከስምንት ቀናት በኋላ ውድድሩ ወደ እንግሊዝ አቅንቶ በበርሚንግሃም ከተማ ይከናወናል። በተመሳሳይ ወር ግንቦት መጨረሻ ላይ ሦስተኛው ውድድር ወደ አሜሪካ አቅንቶ ዩጂን ከተማ ላይ ይካሄዳል። ይህ ውድድር የሚካሄድበት ስቴድየም የ2022 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን የሚያስተናግድ በመሆኑም የዳይመንድሊጉ ውድድር ለዓለማችን አትሌቶች የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚያደርጉትን ዝግጅት የሚፈትሹበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ በመዲናዋ ራባት አራተኛውን የዳይመንድሊግ ፉክክር ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ስታስተናግድ፣ በቀጣይ ለአንድ ወር ለሚቆይ ጊዜ አራት የዳይመንድሊግ ፉክክሮች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይካሄዳሉ። ከራባት ቀጥሎ በቅደም ተከተል የዳይመንድሊግ ፉክክሮችን የሚያስተናግዱት ከተሞችም የጣሊያኗ ሮም፣ የኖርዌይ ኦስሎ፣ የፈረንሳይ ፓሪስና የስዊድን መዲና ስቶክሆልም ይሆናሉ።
አራቱ የአውሮፓ ከተሞች ከሚያስተናግዱት ፉክክር በኋላ በሐምሌ ወር ተጠባቂው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በዩጂን ሲካሄድ ለተወሰነ ጊዜ የዳይመንድሊግ ፉክክሮች ይቋረጣሉ። ከቻምፒዮናው መልስ ግን ዳይመንድሊጉ ፉክክሮች ከ2019 ወዲህ ወደ ቻይና ተመልሰው በሐምሌ መጨረሻ ሻንጋይ ላይ ይካሄዳሉ። በቻይና የሚካሄደው ሁለተኛው የዳይመንድሊግ ፉክክርም በነሐሴ መጀመሪያ ሊካሄድ መርሃግብር ወጥቶለታል።
በዚሁ ወር በፈረንሳይ ሞናኮና በስዊዘርላንድ ሉዛን የሚካሄዱ የዳይመንድሊግ ፉክክሮች አትሌቶች ወደ መጨረሻው ፉክክር ከማቅናታቸው በፊት ነጥቦችን የሚሰበስቡበት ይሆናል። አስራ ሦስተኛው የዳይመንድሊግ ፉክክር በቤልጂየም ብራሰልስ ጳጉሜን ወር ላይ ሲከናወን በአመቱ የዳይመንድሊግ ጉዞ በቂ ነጥቦችን የሰበሰቡ አትሌቶች ለመጨረሻውና ትልቅ ነጥብ ለሚያስገኘው የሁለት ቀናት የዙሪች ዳይመንድሊግ ፉክክር የሚለዩበት ነው። ዙሪች መስከረም መጀመሪያ ላይ ለሁለት ቀናት በምታስተናግደው ፉክክርም ሰላሳ ሁለት አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች በሁለቱም ጾታ በሰበሰቡት ከፍተኛ ነጥብ መሠረት የውድድር አመቱ አጠቃላይ የዳይመንድሊግ አሸናፊ ሆነው የሚለዩ ይሆናል።
የትኛው የውድድር ዓይነት በየትኛው ከተማ እንደሚካሄድ በቀጣዩ ወር ዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚደረግ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አሁን ይፋ የተደረገው መርሃግብርና ውድድሮችን እንዲያስተናግዱ የተመረጡ ከተሞችን በተመለከተ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ ያለው የጤና ሁኔታን መሠረት አድርጎ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል አዘጋጆቹ ጠቁመዋል። ደህንነቱ የተጠበቀና ጥራት ያለው ውድድር ለማካሄድም አዘጋጆቹ ለአትሌቶችና ለተመልካቾች ደህንነት ቅድሚ እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2021