• የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክን መረቁ
• በጋሞ አባቶች ተመረቁ
• የሃገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማሙ
አዲስ አበባ፡ -የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክን መረቁ። አርባ ምንጭን ጎብኝተዋል፣የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ተስማምተዋል። ሁለቱ መሪዎች ትናንት የመረቁት የኢንዱስትሪ ፓርክ በ75 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን 8 ሼዶች እንዳሉትም ተነግሯል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ በ75 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን ግንባታውም በ2009 ዓ.ም መጀመሩ ተጠቅሷል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል። በተመሳሳይ ሁለቱ ከትናንት በስቲያ አርባ ምንጭ ከተማ ሲገቡ የጋሞ አባቶች እና ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። የጋሞ ዞንአባቶች ሁለቱንም መሪዎች የመረቁ ሲሆን የሰላም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የጋሞ ባሕል መግለጫ የሆኑ ስጦታዎችን ማበርከታቸውንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከትናንት በስቲያ በስካይ ላይት ሆቴል ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን ሁሉ አቀፍ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተስማምተዋል። በድንበር አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፤ ለሰላምና ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ቅድሚያ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ በአዲሱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው የሞያሌን አካባቢን የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንዲሰሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው አገሮቹ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ያላቸውን ምቹ ሁኔታ አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ ባለፈው አንድ አመት በአገሪቱ እየመጣ ያለው ሰላም እና የኢኮኖሚ መነቃቃት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እየሳበ ይገኛል። በመሆኑም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረሙ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር የበለጠ በማጠናከር የኢኮኖሚ አቅምን ማሳደግ ላይ ያለመ ነው።
የሁለቱ አገራት የጠበቀ ወዳጅነትም ለአገራቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አይነተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ ወዳጅነታቸውም የሁለቱ አገራት ህዝቦችንም ተጠቃሚ ያደርጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ በመጠቆም፤ በአገራቱ ድንበር ላይ የሚገነባው የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የንግድ ቀጣና በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኬንያውያን ኢንቨስተሮች በሀይል አቅርቦት፣ በአቬሽን፣ በተቀነባበረ የግብርና ምርቶች፣ በጨርቃጨርቅና መሰል ዘርፎች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመራር አገሪቱን በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ እንደሚገኝ የጠቆሙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፤ እየጠነከረ ያለውን የሁለቱ አገራትን ግንኙነት በመጠቀም አዲስ የስራ እና የኢንቨስትመንት ጥምረት በመፍጠር የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ለሁለቱም አገራት የንግድ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
አገራቱ ካላቸው ሰፊ ንግድ እና ኢንቨስትመንት አንጻር እየተከናወነ ያለው ንግድ እና ኢንቨስትመንት የለም በሚያስችል ደረጃ ላይ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በአገራቱ ያሉ ባለሀብቶች በተለያዩ መሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንትን በመጨመር ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ማጠንከር እንደሚገባ ገልጸዋል። የሁለቱን አገራት ጥቅም ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ሆነው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል በድንበር አካባቢ ለሚከሰቱ የሰላም መደፍረስ እልባት የሚሰጥ የሰላም ኮሚቴ ይቋቋማል።
የሰላም ኮሚቴው የሚመለከተው የመንግስት ተቋማትን፣ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሁለቱም አገራት አስተዳደሮችን እንዲሁም ከሁለቱም አገራት የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችን የሚይዝ እንደሚሆን ተነግሯል። 32ተኛው የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የድንበር ኮሚሽን በአዳማ ለሶስት ቀናት ባደረገው ስብሰባ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ መምከሩ ይታወሳል። በተጨማሪም የጋራ ድንበር ኮሚሽኑን ህገ ወጥ የሰዎች እና የመሳሪያ ዝውውር ለመግታት በሚያስችሉ ስትራቴጂዊ ጉዳዮች ፣ በትምህርት እና ጤና እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ዙሪያ መክሯል። የኢትዮ ኬንያ ድንበር ኮሚሽን በቀጣናው አንጋፋው የድንበር ኮሚሽን እንደሆነ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በአብርሃም ተወልደ