• የአካባቢው ህብረተሰብ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው
ለገጣፎ:- በለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ በቤተክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በምግብ፣ እና መጠለያ እጥረት ልጆቻቸው እየተጎዱ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቀረቡ።
ወይዘሮ በላይነሽ ኤልያስን በለገጣፎ- ለገዳዲ ዳሊ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ በተጣለ ድንኳን ውስጥ ናቸው። የሁለት ዓመት ልጃቸውን አቅፈው እንባቸው በጉንጮቻቸው እያፈሰሱ ብሶታቸውን ይናገራሉ። “የት ወደቅሽ፣ ልጆችሽስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? ብሎ የጠየቀና አንድም የመንግስት አካል የለም” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ የልጆቻቸው እጣ ፋንታ ምን ላይ እንደሚወድቅ ስጋት ገብቷቸዋል።
ወይዘሮ በላይነሽ እንደገለጹት፤ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ከ150 ሰዎች ጋር ድንኳን ውስጥ ብርድ እየጠበሳቸው ለማደር ተገደዋል። የአካባቢው ህብረተሰብ ግን ከአስተዳደሩ በተለየ የሚበላውንም ሆነ የሚጠጣውን ለተፈናቃዮች እያቀረበ ይገኛል። አሁን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑንና ልጆችን ጤናም ሆነ ለወላድ እናቶች አስፈላጊው እንክብካቤ ማድረግ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሄ ያስፈልጋል።
“ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለን እስከመቼ እንቆያለን” የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ወይዘሮ በላይነሽ፤የፌዴራል መንግስት ችግራቸውን አይቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል። የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አበበ ገብረጻዲቅ ደግሞ በአረብ አገር ሰርታ ዞሮ መገቢያዬ ይሆናል ብላ ልጃቸው ቤት ብታሰራም በህገወጥነት ተፈርጆ በመፍረሱ ህመም ላይ እንደጣላቸው ተናግረዋል። አሁን በቤተክርስቲያኗ ከተጠለሉ ሳምንት እንደሆናቸው ገልጸዋል። የአካባቢው ህብረተሰብ ከአስተዳደሩ በተለየ ሰብዓዊነት የሚሰማው በመሆኑ ምግብ እና ውሃ እያቀረበላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይሁንና የመንግስት አካላት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ አለመንቀሳቀሳቸው ከቀን ወደ ቀን የተፈናቃዮችን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል። እንደ አቶ አበበ ገለጻ፤ ድጋፍ ባለመደረጉ ለህጻናት፣ እናቶችንና አረጋውያን የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ያሳያል። አንዷ ልጃቸው በአረብ አገር መከራውን ችላ ሰርታ ባገኘችው ገንዘብ የተገነባው ቤታቸው ሲፈርስ ቆመው ማየታቸው እጅጉን ሀዘን ላይ ጥሏቸዋል። የእድሩን ድንኳን ጭምር በመለገስ ለመጠለያነት ላዋለው ለአካባቢውን ማህበረሰብ ግን ምስጋና አቅርበዋል።
ከለገጣፎ- ለገዳዲ በተጨማሪ አያት ጣፎ መካነ ሕይወት መድሀኒያለም እና ቅድስተ አርሴማ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ተፈናቃዮችም ይገኛሉ። ቦታው ሜቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ፊት ለፊት ይገኛል። በማዕከሉ በአግባቡ የሚጦሩ አረጋውያንን መመልከት ሲቻል በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ደግሞ 1500 የሚደርሱ ተፈናቃዮች ምግብና ውሃ ሳያገኙ ሜዳ ላይ ይታያሉ። የዚህ አካባቢ ወይም የወረገኑ ተፈናቃዮች በወንዝ ዳር የተሰራው ቤታቸው በመፍረሱ ኑሯቸውን በቤተክርስቲያኑ ግቢ ካደረጉ ሳምንት ተቆጥሯል።
ቤተክርስቲያኗ በሰጠቻቸው ድንኳን ውስጥ ሴቶች ሲያድሩ፣ ወንዶች ደግሞ ግቢው ውስጥ ስለሚያድሩ ብርድ ላይ ናቸው ሲሉ አቶ ባደግ ተሰማ ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው በዚህኛው ጊዜያዊ መቆያ ደግሞ ልክ እንደ ለገጣፎ እና ለገዳዲዎቹ ሁሉ ምግብና ውሃ የሚያቀርብ ማህበረሰብ በብዛት የለም። በመሆኑም መንግስት ህዝቡ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። አቶ ባደግ እንደሚያስረዳው፤ ቅድሚያ ግን ስለሰብዓዊነት ማሰብ ይገባል። ተፈናቃዮቹ ምግብ አብስለው እንኳን መመገብ የሚችሉበት እቃ የላቸውም።
ከነዕቃቸው ነው ቤቱ የፈረሰው።ቤተክርስቲያኗ ባትኖር በርካቶች በአውሬ ተበልተው ይቀሩ ነበር። አሁንም በርካቶች በምግብ እጦት እና በመጠለያ እጥረት እየተሰቃዩ በመሆኑ መንግስት ድጋፍ ማድረጉን ችላ ማለት የለበትም። የብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የአደጋ ተጎጆዎችን ለመርዳት በቅድሚያ ምክንያቱ፣ ሰዎቹ ያሉበት ሁኔታ እና ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በሚሰጡት ጥቆማ መሆኑን ተናግረዋል።
ቦታው ላይ የተከሰተው ሁኔታ ምክንያት እና ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ እንዲሁም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በጽሁፍ መረጃ መላክ እንዳለባቸው አስረድተዋል። ስለዚህ ጥያቄው በቀረበ ሰዓት ድጋፍ ለመስጠት ችግር እንደማይኖር ነው የተናገሩት። ይሁንና በጉዳዩ ላይ አስመልክቶ ለኮሚሽኑ የጽሁፍ ጥያቄ ስለመቅረቡ አለማወቃቸውን ገልጸዋል። የለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር አረንጓዴ ቦታዎችን፥ የወንዝ ዳርቻዎችን፥ ከፈቃድ ውጭ የተያዙ እና ካሳ ተከፍሎባቸው ግንባታ የተካሄደባቸው ናቸው ያላቸውን ቤቶች የዛሬ ሳምንት ማፍረስ መጀመሩ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ጌትነት ተስፋማርም