ፈረንሳይ አዘጋጅ በነበረችበት እአአ የ2003ቱ የፊፋ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አፍሪካዊቷ አገር ካሜሩን ከኮሎምቢያ ጋር ባደረገችው ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቦችን ልብ ያደማ አንድ አሳዛኝ ክስተት ታየ። በጨዋታው 72ኛ ደቂቃ የማንቺስተር ሲቲው ኮከብ ማርክ ቪቨን ፎይ መሃል ሜዳ ላይ በድንገት ተዝለፍልፎ ወደቀ። በህክምና እርዳታ ሊነቃ ባለመቻሉም ለተጨማሪ ህክምና ከሜዳ ወጣ። ነገር ግን ካሜሩናዊው ተጫዋች ራሱን ስቶም በህይወት መቆየት የቻለው ለ45 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። የሞቱ ዜና ሲሰማም በመላው ዓለም የሚገኙ የስፖርት ቤተሰቦችን በእጅጉ ያሳዘነ እንዲሁም የሞቱ ምክንያት የሆነው ከልብ ጋር የተያያዘ ህመም አሳሳቢነትም መነጋገሪያ ሆነ።
ይህ 18 ዓመት የሆነው ታሪክ በብዙዎች ዘንድ የሚታወስና ለአብነት ያህል ተነሳ እንጂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አሁንም ድረስ በድንገት ሕይወታቸውን እስከማጣት ከሚያደርሳቸው የጤና እክል መካከል ቀዳሚው የልብ ህመም ሆኗል። በሜዳ ላይ ተዝለፍልፈው በመውደቅ ህክምና ያስፈለጋቸው፣ ከወደቁበት ዳግም ያልተነሱ እንዲሁም በዚሁ ምክንያት የእግር ኳስ ሕይወታቸውን ለማቆም የተገደዱ ተጫዋቾች ቁጥር ቀላል የሚባልም አይደለም። አርጀንቲናዊው ኮከብ ሰርጂዮ አጉዌሮ ከማንቺስተር ሲቲ ወደ ባርሴሎና ባቀና በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጨዋታ ሊያቆም እንደሚችል ከሰሞኑ ተሰምቷል። የ33 ዓመቱ ተጫዋች በራሱ ላይ ያስተዋለውን የጤና ሁኔታ መለወጥ ሃኪም ዘንድ እንዲቀርብ ሲያደርገው የልብ ህመም ተጠቂ መሆኑ ተደርሶበታል። በዚህም ምክንያት ከእግር ኳስ ሕይወት መሰናበቱ በብዙዎች ዘንድ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
የልብ ህመም በእግር ኳስ ተጫዋቾች ዘንድ መከሰቱ የተለመደ ሲሆን፤ ክርስቲያን ኤሪክሰን በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ላይ በሜዳ ላይ ራሱን ስቶ መውደቁ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የኢንተር ሚላን የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ዴንማርካዊ በወቅቱ በልብ ህመም ምክንያት ሆስፒታል እስኪደርስ ድረስ መተንፈስ አቁሞም ነበር። የቀድሞ የስፔን እንዲሁም የሪያል ማድሪዱ ስመ ጥር ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ራሱን ከእግር ኳስ ያራቀውም በተመሳሳይ ችግር ነበር። ግብ ጠባቂው እአአ በ2019 ጓንት መስቀሉን ያሳወቀው የልብ ህመም ተጠቂ መሆኑን ካወቀ ከአንድ ዓመት በኋላም ነው። በእንግሊዝ ሊግ አንድ ተሳታፊ የሆነው ክለብ ቦልተን ዋንደረርስ የቀድሞ ተጫዋች ፋብሪክ ሙምባ ጫማ ለመስቀል የተገደደበት ምክንያትም ይኸው የልብ ህመም ነው። ተጫዋቹ በኤፍኤ ካፕ ጨዋታ ላይ ሳለ አቅሉን ስቶ የወደቀ ሲሆን እድለኛ ሆኖ ህይወቱ ሊተርፍ የቻለው ልቡ ለ78 ደቂቃ መምታት ካቆመ በኋላ ነው።
በስፖርተኞች ላይ የሚታይ የልብ ህመም አብዛኛውን ጊዜ አስቀድሞ የማይታወቅና በድንገት የልብ ደም መርጨት ማቆም ነው። ይህ ዓይነቱ ክስተት በልምምድም ሆነ በውድድር ወቅት ሊያጋጥም የሚችል ሲሆን፤ ወጣትና ታዳጊ ስፖርተኞችን ጭምር ለከፋ ጉዳት እንዲሁም ሕይወትን እስከመቅጠፍ የሚደርስም ነው። የልብ ህመም ሁሌም በተጫዋቾች ዘንድ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ተከትሎም የዓለም እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው (ፊፋ)፤ የእግር ኳስ ቡድኖች ለተጫዋቾቻቸው ሁሌም የጤና ሁኔታ ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲሁም በየቡድኑ ቋሚ ባለሙያዎችና ምርመራዎች እንዲኖሩ ያስገነዝባል።
ለድንገተኛ ሞት ከሚያጋልጡት ምክንያቶች መካከል አንዱ የልብ ጡንቻዎች ማበጥ ሲሆን፤ ከጡንቻ አፈጣጠር ጋር ተያይዞም የደም ፍሰት ሊገታና ለሞት ሊዳርግ ይችላል። የልብ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አኒል ማልሆትራ ከተለያዩ የእግር ኳስ ማሕበራት በተውጣጡ 11 ሺ ወጣት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ጥናት አድርገዋል። በዚህም መሰረት 42 የሚሆኑት ድንገተኛ ሞት ሊያስከትል በሚችል የልብ ህመም የተጠቁ መሆናቸውን ደርሰውበታል። ከ42ቱ መካከል 30 የሚሆኑት በቀዶ ጥገና እንዲሁም ሌሎች ህክምናዎችን በመከታተል ወደ እግር ኳስ መመለስ የሚችሉ ሲሆን፤ 12ቱ ግን እግር ኳስን እርግፍ አድርገው መተው እንደሚገባቸው ተነግሯቸዋል።
ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ፈተና እሆነ የመጣው ከልብ ጋር የተያዘ ችግር ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በተለያዩ የዓለማችን ኳስ ተጫዋቾች ላይ ተደጋግሞ ታይቷል። በነዚህ ወራት በእግር ኳሱ ዓለም በአጠቃላይ ከልብ ጋር በተያያዘ ሃያ ሦስት ተጫዋቾች ሜዳ ላይና ከሜዳ ውጪ ችግር የገጠማቸው ሲሆን ሦስቱ ሕይወታቸው እንዳለፈ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም የችግሩ አሳሳቢነት ልብ አልተባለም እንጂ የከፋ መሆኑን የሚጠቁም ሆኗል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014