የተወለደችው ህዳር 12 ቀን 1931 ዓ.ም ነው። ከጣልያን ወራሪ ጋር ሲዋጉ ከቆዩ በኋላ ወደ ኬንያ ተሰደው ሲኖሩ ከነበሩት አርበኛ አባቷ አቶ ከበደ ወርቄና ከእናቷ ወ/ሮ ደስታ ብሩ ኬንያ ሲኦሎ በምትባል ከተማ ነበር ይህችን ዓለም የተቀላቀለችው።
አመጣጧም ያለአላማ አልነበረም። በአንድ ጎን የጥበብ ተሰጥኦን በሌላ ጎን ደግሞ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ተልዕኮን አዝላ ነው ወደዚህች ምድር የመጣችው። እስከ 4 ዓመቷ በኬንያ ከቆየች በኋላ ኢትዮጵያ ነጻ በመውጣቷ ጠለላ ከበደም ከወላጆቿ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች።
ጠለላ ከበደ በዚያን ወቅት እንደነበሩ የእድሜ እኩዮቿ በአዲስ አበባ ሰፈሯ አካባቢ በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ከየኔታ እግር ስር ተቀምጣ ፊደል ቆጥራለች:: በኋላ ዲታ ዲባ የሚባሉ ጣልያናዊ ትምህርት ቤት፤ ከዚያም ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት፤ ሃኪም ወርቅነህ የሚባል የማዘጋጃ ትምህርት ቤት፤ በመጨረሻም ሚሲዮን ላዛሪስት የአሁኑ ሴንትሜሪ ተብሎ በሚታወቀው ትምህርት ቤት እስከ አም ስተኛ ክፍል ተምራለች።
የዘፋኝነት ተሰጥኦ የነበራት ጠለላ ከበደ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትርን በ1948 ዓ/ም ገና ታዳጊ ወጣት ሳለች በመሪ ድምጻዊነት ተቀላቅላለች። በወቅቱም ጠለላ የወቅቱ አስቴር አወቀ በሚል ትጠራ ነበር ይላሉ።
ጠለላ ከድምጻዊነቷ ባለፈ በተዋናይነት፤ በተዋዛዥነት ያገለገለች ሁለገብ አርቲስትም ናት። ድምጸ መረዋዋ አርቲስት ጠለላ ከበደ ከምትታወቅበት የድምጻዊነት ጥበብ ባለፈ በቴአትሩም በኩል ውድቅት ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ ቴዎድሮስን ጨምሮ ከ30 በላይ በሚሆኑ ቴአትሮች ላይ ተሳትፋለች ። ጠለላ ከበደ በልዩ ልዩ ትዕይንተ ጥበባት ዝግጅት ዘመኑ በሚፈልገው መልኩ በተለያዩ የቅስቀሳ የኪነጥበብ ስራዎች ላይ በመሳተፍ በየክፍለሀገሩ በመዞር የኪነጥበብን እድገት ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው ማሕበረሰብ እንዲቋደስ የበኩሏን ጥረት ለማድረግ የተጋች አርቲስት መሆኗን የስራ ታሪኳ ያስረዳል።
አርቲስቷ ለ32 ዓመት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ካገለገለች በኋላ ከመስከረም 1 ቀን 1983 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ብትገለልም በሌላው የህይወቷ ገጽ ለህዝብ ኖራለች።
ጠለላ ከበደ ከወጣትነቷ ጊዜ ጀምሮ በነበራት ከፍተኛ የአገርና የሕዝብ ፍቅር ከሙያዋ ባሻገር ለዴሞክራሲ ፍትህና እኲልነት ታግላለች። በአካባቢዋ፤ በሙያ ባልደረቦቿ በጣም ተወዳጅ የነበረችው እርቲስቷ ለቆመችለት ዓላማ ወደኋላ የማትል፤ ፍትህ ሲጓደል ድምጿን ለማሰማት የማታፈገፍግ፤ አድርባይነትን በጣም የምትጠየፍና አካፋን አካፋ እያለች በቃሏ የኖረች የግንባር ስጋና እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነበረች።
“ሎሚ ተራ ተራ” የሚለውን ዘፈን ዘፈንሽ በመባል ጠለላ ከበደና ከሷ ጋር ሌሎች ስድስት የሙዚቃ ባለሙያዎች በ 1967 ዓ.ም በደርግ ካድሬዎች ለአራት ወራት ከስድስት ቀናት ለእስር ተዳርገዋል። ጦር ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ ከተፈቱ በኋላም ጠለላ ከበደ ለሁለት ዓመት ያህል ከአዲስ አበባ አካባቢ እንዳትንቀሳቀስ፤ ከናዝሬት አልፋ እንዳትሄድ፤ በግዞት እንድትቆይ ተፈርዶባታል።
በመስከረም 10 ቀን 1987 ዓ.ም ፕሮፌሰር አስራት በወያኔ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ፍትህን ለመጠየቅና ድምፃቸውን ለማሰማት በፍርድ ቤቱ አካባቢ ከነበሩት ለእስር ከተዳረጉት 1500 ሰዎች መካከል አንዷ ጠለላ ከበደ ናት። እነዚህ ሰዎች በዚያን ቀን እየተደበደቡ ሰንዳፋ ተወስደው ፀጉራቸው ተላጭቶ ታስረዋል። 1000 ሰዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርገው ሲለቀቁ ጠለላ ከበደ ከሌላ 500 ሰዎች ጋር ይቅርታ አንጠይቅም በማለታቸው ለተጨማሪ 25 ቀናት ታስረው በከፍተኛ የሕዝብ ግፊትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመፈታት በቅተዋል።
ከእስር ከተፈታች ከሶስት ወር በኋላ አማራጭ ሃይልና መላው አማራ መስቀል አደባባይ በጠራው ሰልፍ ላይም ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጋለች። በስደት ወደ ሰሜን አሜሪካ ከሄደች ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የኢሕአፓ ጠንካራ ደጋፊ በመሆን ለረጅም ዓመታት ስታገለግል እንደነበር ታሪኳ ያስረዳል።
አርቲስት ጠለላ ከበደ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ችግረኞችን በመርዳት በሚያደርጉት የገቢ ማስገኛ ድርጅት ገቢ ማስገኛ ዝግጅት እንድትሳተፍ ስትጠየቅ ጥሪውን በመቀበል በሙያዋም ሆነ በገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ሰብአዊ አገልግሎት ሰጥታለች።
ድምጻዊት ጠለላ ከበደ በአደረባት ህመም ለጥቂት ቀናት በህክምና ስትረዳ ቆይታ በተወለደች በ83 ዓመቷ በስደት ትኖርበት በነበረው ሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት በተወለደችበት ቀን ኅዳር 12 ቀን 2014 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
ኅዳር 17 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 6፡30 ጀምሮ ለረጅም ዓመታት በኪነጥበብ ዘርፍ ባገለገለችበት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የአስከሬን ስንብት የተደረገ ሲሆን በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ከቀኑ 9፡00 አስከሬኗ በክብር አርፏል።ድምጻዊት ጠለላ ከበደ 10 ልጆች 18 የልጅ ልጆች 3 የልጅ ልጅ ልጅ ያፈራች እናት ነበረች።
ጠለላን በተመለከተ ሃሳባቸውን በማሕበራዊ ሚዲያ ካጋሩት መካከል የሙዚቃ ሀያሲዋ ብሌን ዮሴፍ እንዲህ በማለት ጽፋለች፤-
“በሙዚቃ ኦርኬስትራዎች ውስጥ ሴቶችን በድምፃዊነት እንዲሁም በቲያትርም ውስጥ በተዋናይትነት እንደባለሙያ መቀጠር በማይታሠብበት ዘመን ላይ ጠለላ ከበደ በዘመናዊ ሙዚቃ ሙያ ድምፃዊነት ፣በትወናና በዳንስ ከተቀጠሩት ፈር ቀዳጅ መካከል ናት። ከ1940 ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ጠለላ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመናዊ ኦርኬስትራ ጋር የቢግ ባንድ አይነት የሙዚቃ ውህዶችን የሰማንባቸውን ፣ከባህላዊ መሳሪያ ጨዋታዎች ጋርም አገርኛ ሙዚቃዎችን አስደምጣናለች። ከምኒልክ ወስናቸው ፣ከለማ ገ/ሕይወት ጋር እንዲሁም በግሏ የሠራቻቸው የሙዚቃ አይነቶች እና የሙዚቃ ሐሳብ ልዩነቶች ይገርማሉ። አዝማሪ ጠለላ ከበደ ምንም የማይገድባት ፣ለወደደችው ጥበብ የበረታች ፣ ከቀዳሚዎቹ ፋና ወጊዎች መካከል ናት።”
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014