በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት 2022 የዓለም ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ለ14ኛ ጊዜ በዱባይ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ በዚህ ሻምፒዮና ላይ አፍሪካ በሁለቱም ጾታ አንድ አንድ ተወካዮችን የምታሳትፍ ሲሆን፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በመጪው ጥር ወር የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል፡፡ ‹‹አፍሮ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና›› በሚል የሚካሄደው አህጉር አቀፉ የማጣሪያ ሻምፒዮናም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚደረግ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄደውን ውድድር በብቃት ለማስተናገድም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አሳውቋል። ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው አህጉር አቀፉ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ከጥር 15-21/2014 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፤ ውድድሩን ለማስተናገድ ከሚደረገው በመሰናዶ ባሻገር ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን ውጤታማ እንዲሆንም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በዚህም በሻምፒዮናው የሚሳተፋ ቡድን አባላት ስኬታማነት አቅም እንዲሆን የመወዳደሪያ ዊልቸር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ድጋፉ ከተለያዩ አካላት የተበረከተ ሲሆን፤ የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ በአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት 19 ዊልቸር እና የ250 ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል። የኢትዮጵያ ፖራሊምፒክ ኮሚቴም ለብሔራዊ ቡድኑ የትጥቅ ድጋፍ አበርክቷል።
አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅቱን በማስመልከትም የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጎጆ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዚህም ውድድሩን በብቃት ለማስተናገድ እና ተፎካካሪ ለመሆን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ተናግረዋል። ውድድሩ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት መካሄዱም አገሪቷ አሁን ያለችበትን አስቸጋሪ ወቅት በማለፍና ሰላም መሆኗን ለመላው ዓለም የምታሳይበት እንዲሁም መልካም ገጽታዋን የምትገነባበት መድረክ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሩን ለማስተናገድ እድል ማግኘቷ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። ‹‹ምንም እንኳ አገሪቷ በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ብትገኝም፤ ሁሉም በየዘርፋ የአገርን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን በሚደረገው ውድድር የኢትዮጵያን አሸናፊነት እና አገር ወዳድነት መንፈስ በመላበስ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ለማድረግ ከወዲሁ በአካል፣ በአዕምሮ እና በስነልቦና ዝግጅት ሊደረግ ይገባል›› ማለታቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር መረጃ አመልክቷል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ለውድድሩ መሳካት መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት ብሄራዊ ቡድኖች በሴት 12 እንዲሁም በወንድ 12 ተጫዋቾች ተመርጠው ስልጠና ጀምረዋል፡፡ በሻምፒዮናው ላይም ሰባት የአፍሪካ አገራት ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን እንደሚያሳትፉም ታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014