ኢትዮጵያ የገባችባቸው ጦርነቶች ሁሉ የህልውና፣ የመገፋትና በባላንጣዎቿ ትንኮሳ ነው፡፡ ቅኝ ሊገዟት በሚከጅሉ ሀይሎች ። ይሁን እንጂ በዘመኗ የገጠማትን ፈተና ሁሉ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ስታልፍ ኖራለች፤ ወደፊትም ትኖራለች፡፡ በጦርነት ታሪኳ ሁሉ ሽንፈትን የማታውቀው ኢትዮጵያ ለአንድነቷና ለሉዓላዊ ክብሯ በዱር በገደሉ የሚዋደቁላት የቁርጥ ቀን ልጆቿ የሕይወት መስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በደምና በአጥንት ጸንታ የቆመች አገር ስለመሆኗም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በታሪኳ ታፍራና ተከብራ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት ሆና መቆየቷም ለዚሁ ነው፡፡
በጀግኖች ልጆቿ አጥንትና ደም መሰረቷን ያጸናች ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ዓለም መስክሯል። በደም የተጻፈ ደማቅ ታሪክም አላት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ሥሙ ከፍ ብሎ የሚነሳውን የዓድዋን ታሪክ ብቻ እንኳ ብናነሳ አባ ዳኘው ምኒልክ ፈረሳቸውን ጭነው ዘምተዋል፣ አዝምተዋል፣ ተዋግተው አዋግተዋል። እንደ ሠራዊታቸው በዱር በገደል አድረዋል፣ ተጠምተዋል፣ ተርበዋል። ባለቤታቸው ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ እምዬ ምኒልክን ሸኝተው፣ እኔ በቤተመንግሥት ልሰንብት፣ እናንተ ተዋጉ ብለው አልቀሩም። ከአገር በላይ ማንም የለምና ፈረስ ጭነው፣ ዘማች አስከትለው፣ የጦርነት ስልት ነድፈው ዘምተዋል፣ አዝምተዋል፣ አሸንፈውም ተመልሰዋል።
‹‹የአገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በጸሎትህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም ማርያምንም ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረሂሉ ድረስ ከተህ ላግኝህ፡፡ እንግዲህ ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬም አልጠራጠርም›› በማለት ክተት አውጀው የጦር መሪ ሆነው ዘምተዋል። ተዋግተው አዋግተውም በድል ተመልሰዋል፡፡ ይህ የዓድዋ ድል ትልቁ የኢትዮጵያውያን ስኬት ነው፡፡
ምኒልክ በመሩት ጦርነት ለጥቁር ሕዝቦች ምሳሌ የሆነው የዓድዋ ድል በመገኘቱ ነጮች ደንግጠው ጥቁሮች ግን ነፃ ወጥተዋል። ይህን ተከትሎም በዓለም ላይ ነጻነት ነግሷል። በአፄ ምኒልክ ያላበቃው የጦር ሜዳ ስኬት በአፄ ኃይለ ሥለስላሴም ተደግሟል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም በዘመናቸው አባ ጠቅልን ጭነው ማይጨው ድረስ ዘምተዋል። ተዋግተው አዋግተዋል። ከእነዚህ የአገር መሪዎች ብሎም የጦር መሪዎች አስቀድመው የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታትም እንዲሁ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ንግሥናቸውን ረስተዋል። ከቤተ መንግሥት ዙፋናቸውም ወርደው የጦር ተዋጊ ሆነዋል፡፡ ጠላትንም በመጣበት እግሩ እየመለሱ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር አድርገዋል፡፡
ነገሥታቱ ትዕዛዝ በመስጠት ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ ከማለት አልፈው እንዲህ ላደርግ ነውና ሕዝቤ ሆይ ተከተለኝ በማለት ክተት ያውጃሉ። ቃል ለእናት አገራቸው ይገባሉ የገቡትን ቃል ኪዳንም ይፈፅማሉ። ሕዝቡም አለን በማለት ይከተላቸዋል፡፡ ትጥቅና ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነቱን በተግባር ያሳያቸዋል፡፡ ታድያ በየዘመናቱ የተነሱት ነገሥታት ሕዝቡን ይዘው ዘምተው አዝምተዋል፣ ተዋግተው አዋግተዋል፣ ግዳይ ጥለው ኢትዮጵያን ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ አድርሰዋል።አሁን ላለው ትውልድ ከነሙሉ ክብሯኗ የጀግንነት ስሟ አስረክበዋል።
ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናትና ‹‹እኛ እያለንላት ኢትዮጵያ አትፈርስም›› የሚሉ ለቁጥር የበዙ ልጆቿ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ከነተላላኪዎቹ በቆፈረው ጉድጓድ ሊቀብረው ተነስተዋል፡፡ ቡድኑ በሥልጣን ዘመኑ የፈጸመው ግፍና በደል አልበቃ ብሎት ሕዝብ አሽቀንጥሮ ሲጥለው ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጇል፡፡የአሜሪካና የምዕራባውያኑን ተልእኮ ተቀብሎም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እያደማ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ሀይሎች የተከፈተባት ጦርነት በማንነቷ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ታድያ በማንኛውም የትግል መስመር መሪዎቿ እንዲሁም ሕዝቡ የአምላኩን ዕርዳታ ይጠይቃል፡፡ ከመጠየቅ ባለፈም ስለሚተማመን ጭምር ሠራዊቱ በጀግንነት ለአገሩ ህልውና ይፋለማል፣ ህዝብም ደጀን በመሆን አይዞህ ባይነቱን በሁሉም መስክ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚከፈት ጦርነት ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ ተሸንፈው አያውቁም።
የአድዋ ድል ከሌሎች ድሎች ሁሉ በጉልህ የሚጠቀሰው መላ ኢትዮጵያውያንን ዳር እስከ ዳር ያሳተፈ፣ ለጥቁር ሕዝቦች በመላ ዓለም ፋና ወጊ የሆነ፣ የወራሪ ኃይል አጎብዳጅና ባንዳዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ምድር ወራሪውን ድል ማድረግ በመቻሉ ነው። ዛሬም ከቀደመው የጦር ሜዳ የስኬት ታሪኳ ያልተማሩ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ሊያጠፉ ተነስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በደምና አጥንት መሰረት የተገነባች በሉዓላዊነቷ ድርድር የማታውቅ አገር ኢትዮጵያ ዛሬም እንደትናንቱ ወራሪዋን የሚያዋርድና አፈርሳታለሁ የሚሉትን አፍራሾችዋን ሊያፈርሷቸው የሚችሉ የቁርጥ ቀን ልጆች አሏትና አትፈርስም፡፡
እንደ አድዋው ጀግና እንደ አጼ ምኒልክ ፤ ለኢትዮጵያ ክብር እስከ መጨረሻው ህቅታ እንደተዋደቀው እንደ አጼ ቴዎድሮስ፤ የዚያድባሬን ጦር ለማርበድበድና የሠራዊቱን ወኔ ለማነቃቃት ግንባር ድረስ ዘምቶ ኢትዮጵያን ነጻ እንዳደረጋት እንደ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያ ጦር ሜዳ ሄዶ ከፊት የሚቆምላት ቆራጥ መሪ አላት፡፡ መሪያቸውን የሚያደምጡና የሚከተሉም ጀግና ልጆች አሏት ፡፡
ኢትዮጵያ የገጠማትን ሁለንተናዊ አደጋ ለመመከት ከፊት ቀድሞ የሚዋደቅላትን ህዝብና መሪ አጥብቃ በምትሻበት በዚህ ጊዜ የዘመኑ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መሪ የሆኑት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደ ቀደሙት ነገሥታት ሁሉ ወደ ጦር ሜዳው እዘምታለሁ፣ እዛው እንገናኝ ብለው በደምና አጥንት በተጻፈው በኢትዮጵያ ደማቅ ታሪክ ላይ ዳግም ታሪክ ለመጻፍ ከተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደማቅ ታሪክ ውስጥ የደመቀ አሻራውን ማሳረፍ የሚሻ ሁሉ ይከተለኝ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ወታደሩ የበላውን በልተው የጠጣውን ጠጥተውና በተኛበት በዱር በገደል ተኝተው ሀገራችንን ነፃ ሊያወጡ ከወሬ ባለፈ በተግባር ተንቀሳቅሰዋል። እርሳቸው ሞተው ሀገራችንን ነፃ ሊያወጡ፤ ለአፍሪካና አፍሪካውያን የነጻነት ብስራት ሊያበስሩ ቆርጠው ተነስተዋል።
ታድያ ይህ አገራዊ ጥሪ የሆነው አዋጅ የአገር ሉአላዊነትን ከማስከበር ባለፈ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ጥሪ ነውና ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሪያቸውን በመከተል አሸባሪውን የኢትዮጵያ ጠላት እስከወዲያኛው ሊያሰናብቱት ቆርጠዋል። ለጥሪውም ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ሀብት ያለው በገንዘቡ፣ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ደጀንነቱን አሳይቷል።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገጠማት ጦርነትም አገርን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል፤ የመኖርና ያለመኖር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የህልውና ጦርነቱን ተቀላቅሎ በደምና አጥንት ጸንታ የቆመችውን አገር እሱም ተገቢውንና አስፈላጊውን ዋጋ ከፍሎ ለልጅ ልጆቹ ማውረስ እንዲችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰርክ አንስተው የማይጠግቧት ኢትዮጵያ የሕይወት መስዋትነትን ለመክፈል ያላቸውን ቁርጠኝነት በተለያየ ጊዜ በሚያደርጓቸው ንግግሮች መግለጻቸው የሚታወቅ ቢሆንም ወደ ግንባር በመሄድ ጦሩን ለመምራት የወሰኑት ውሳኔ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ሆኖታል፡፡ ከሠራዊቱ ባለፈም መላው የኢትዮጵያውያንን ልብ ያሞቀና ያጀገነ ሆኗል፡፡ ዛሬም ልክ እንደጥንት አባቶቻችንና የአገር መሪዎች ሁሉ ‹‹በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም›› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የክተት ጥሪ አውጀው በአውደ ግንባሩ ጦሩን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በጦር ሜዳ ውሏቸውም ትርጉም ያለው ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
በርካታ ጦርነት የገጠማት አገር ኢትዮጵያ ድል ከመቀዳጀትና በስኬት ከማጠናቀቅ ያፈነገጠ ታሪክ የላትምና ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ድል እንደሚመለሱ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለም። ታሪኳን እያወቁ የደፈሯት ክብራቸውን የጠሉና የተዋረዱ የውስጥና የውጪ ሀይሎች ናቸው፡፡ እርግጥ ኢትዮጵያ አሁን የተደቀነባት አደጋ ከውስጥ የኢትዮጵያውያን ነቀርሳ ከሆነው የትህነግ እና ሸኔ እንዲሁም የጥቁሮች ጠላት ከሆኑት ምዕራባውያን ጋር በመሆኑ ትግሉን መራር ያደርገው ይሆናል እንጂ ጣፋጩን ፍሬ ከማየት የሚገታ ኢትዮጵያዊም ሆነ የኢትዮጵያ መሪ አይኖርም፡፡
ጦር ሜዳ ወርዶ ጦርን መምራት አገርን ከወራሪ መከላከልና ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ የቀደምት አባቶች ታሪክ ነው። ዛሬ ይሄ ታሪክ እራሱን ደግሟል፡፡ በመሆኑም ልክ እንደቀደምቶቹ ሁሉ አገረ መንግሥቱን የሚመሩት የዘመኑ መሪ ወደ ግንባር በመሄድ ጦርነቱን ለመምራት ወስነዋል፡፡ ውሳኔያቸውንም በተግባር አውለው አንድ አመት ያስቆጠረውን ጦርነት መቋጫው በቅርብ እንዲሆን በማሰብ ሁሉን ትተው ፊታቸውን ወደ ጦር ሜዳ መልሰዋል፡፡
የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት ከነበረበት የሥልጣን ማማ ቁልቁል ወርዶ እኔ እንዳሻኝ የማላደርጋት ኢትዮጵያ አትኖርም በማለት እኩይ ተግባር ፈጽሟል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከሕዝቦቿ ውስጥ መፋቅ እንደማይቻለው ሲያውቅም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንደሚወርድ በእብሪት ተናግሯል፡፡ ቡድኑ ባሴረው ሴራ ተጠልፎ መቀመቅ የወረደ ቢሆንም ቅሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ባዶ ዲስኩሩ እየታበየ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳን የውጭ ወራሪዎች ከውስጥ ተላላኪዎቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር አንድነቷን ለመናድ ሁለንተናዊ ጦርነት የከፈቱባት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአንድነት ቆመዋል፡፡ ሲኦል የምትገባ ኢትዮጵያ አትኖርም፡፡ እኛ ቆመን ኢትዮጵያ አትፈርስም እኛ ሞተን ኢትዮጵያ ትኑር ያሉትን ብቸኛ የዘመኑ መሪን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር ዘምተዋል፡፡ በዘመቻውም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ታዋቂ ሰዎች ፣ባለሀብቶች … በሁሉም ግንባሮች ተሰልፈው ሙሉ ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውንና ውድ ሕይወታቸውን በመስጠት ጭምር የህልውና ዘመቻው ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ሊያደርሱት ወጥረው ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ውጥናቸው ሰምሮ ጉዟቸው በስኬት እንዲጠናቀቅም መላው ኢትዮጵያዊ በአንድነት ቆሟል፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች በግንባር ተገኝተው የጦርነቱ ፊት አውራሪ በመሆን ህዝቡን ክተት ተከተለኝ ማለታቸው የብዙዎችን ልብ ያሞቀና ስነልቦናን የጠገነ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህም ዋና ዓላማው የሽብር ቡድኑን ዕድሜ ለማሳጠርና አገርን ከውድቀት ለማታደግ ትክክለኛው ጊዜ መሆኑን በማመን በርካታ ኢትዮጵያውያን መሪውን ሊከተል ወስኖ ከቀጠሮው ቦታ ደርሷል፡፡
ሠርቶ ማግኘት፣ ወልዶ መሳም፣ ሮጦ ማሸነፍና በዓለም አደባባይ ሰንደቅን ከፍ ማድረግ የሚቻለው አገር ሲኖር ነው ያሉት ታዋቂዎቹ፤ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ከተቀበሉት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከእነርሱም በተጨማሪ በርካቶች ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በተባባረ ክንድ መመከት የግድና ወሳኝ መሆኑን ተረድተዋል፡፡
ብዙዎች ወቅቱ ዳግም የአድዋ ድል የሚበሰርበትና ኢትዮጵያን የመታደግ በመሆኑ ሕዝቡ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ተከተለኝ የሚል መሪ ማግኘቱ ዕድለኛነቱን ያነሳሉ፡፡ ሴረኛው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን እኩይ ተግባር ለመመከትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጦር ግንባር ተገናኝተዋል።፡ ጦርነቱ የኢትዮጵያ ብቻ እንዳልሆነ የተረዱት አፍሪካውያንም ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው›› ሲሉ እውነታውን እየገለጹ አጋርነታቸውንም እያሳዩ ነው፡፡
ከሰሞኑም በቃ (#NoMore) በሚል ሃሽታግ ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ ቀንድ ዲያስፖራዎች አሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባውያን አገራት ጣልቃ ገብነታቸውን በመቃወም ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፎችን አድርገዋል፡፡ ይህም ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደተናገሩት ‹‹ጊዜው አገርን በመስዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው›› በማለት መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁትን መሪ በመከተል እያንዳንዳችን ኢትዮጵያን ለማዳን የበኩላችንን እንወጣ።የሀገርን ሉአላዊነት ማስከበር፤ ሀገርን ከመፍረስና ህዝብንም ከሞትና ስደት ማዳን ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ነው። ይሄንን በስኬታማነት እንወጣ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014