የ2014 ዓ.ም ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን የውድድሩ የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተከናውኗል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚመሩ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የከፍተኛ ሊግ ውድድር የ2014 ዓ.ም የዕጣ ማውጣት ስነ ሥርዓትና የውድድር ደንብ ማጽደቅ ከትናንት በስቲያ ካሳንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል።
ሃያ ሦስት ክለቦች በቀጣዩ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመሳተፍ በሚፋለሙበት የከፍተኛ ሊግ የዘንድሮ ዓመት ውድድር ክለቦቹ በሦስት ምድብ ተከፍለው ይፎካከራሉ። በዚህም ስምንት ክለቦች በሚፋለሙበት ምድብ አንድ ገላን ከተማ፣ አምቦ ከተማ፣ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ሻሸመኔ ከተማ፣ሀላባ ከተማ፣ጌዲዮ ዲላ፣ባቱ ከተማ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተደለደሉ ሲሆን ጨዋታዎቹም በሀድያ ሆሳዕና ሜዳ ላይ የሚከናወኑ ይሆናል።
በተመሳሳይ ስምንት ክለቦች በሚፋለሙበት ምድብ ሁለት ሲልጤ ወራቤ፣ለገጣፎ ከተማ፣ቡታጅራ ከተማ፣ከፋ ቡና፣ ቤንች ማጂ፣ ቡራዩ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ሰንዳፋ ከተማ የተደለደሉ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹ በሐዋሳ ሜዳ የሚከናወኑ ይሆናል። ሰባት ክለቦች የሚፋለሙበት ምድብ ሦስት ጨዋታዎች በጅማ ሜዳ እንደሚስተናገዱ የተገለጸ ሲሆን፣ የውድድር መርሃግብሩ በደብዳቤ እንደሚገለጽ የውድድር ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ወርቁ ገልፀዋል ። በዚህ ምድብ ሀምበርቾ፣ፌዴራል ፖሊስ፣የኢትዮጵያ መድን፣ ነቀምት ከተማ፣ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣የካ ክፍለ ከተማና ደቡብ ፖሊስ መደልደላቸው ታውቋል።
በእጣ ማውጣት ስነስርአቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አሊሚራህ ሙሐመድ ባደረጉት ንግግር ‹‹በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፌዴሬሽናችን ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመዛቸውንና የደም ልገሳ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባታቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ ።
የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም ከውድድሩ ባሻገር በድጋፉ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናችሁን ማረጋገጥ እንዳለባችሁ ላሳስብ እፈልጋለሁ››በማለት ተናግረዋል። አቶ አሊሚራህ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ቤቱ ተወያይቶበት የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ አባላት ሀሳቡን በመደገፍ ከተወያዩበት በኋላ ውሳኔያቸውን በቅርቡ በፌዴሬሽኑ በኩል እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል።
በሦስት ምድብ ተከፍሎ በሦስት ክልሎች የተካሄደው የ2013 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድር አፈፃፀም፣ የዳኞች ፣ የዲስፕሊንና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ሪፖርት እንዲሁም የ2014 ዓ.ም የውድድር ደንብ ቀርቦ ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የውድድር ደንቡን አፅድቀዋል።
በተጨማሪም የከፍተኛ ሊግ ውድድርን በሚገባ ለማስተዋወቅና የስፖንሰር ሽፕ ገቢ ለማግኘት እንዲሁም የሊጉን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ እንዲረዳ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀው የከፍተኛ ሊግ የውድድር ሎጎ (ዓርማ) ለተሳታፊ ክለቦች ቀርቦ ሀሳቡን በመደገፍ የማዳበሪያ ሃሳቦች የተሰጡበት ሲሆን፣ ተጨማሪ ሃሳቦችን በቀጣይ ቀናት በፌዴሬሽኑ በኩል እንዲልኩና ማሻሻያ ተደርጎበት በስራ አስፈፃሚ እንደሚፀድቅ ተገልጿል።
በመጨረሻም ለ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች የውድድርና የመወዳደሪያ ሜዳዎች የዕጣ ማውጣት ፕሮግራም ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ በፈፀሙ 23 ክለብ ተወካዮች ተከናውኗል ።
በዕለቱ የእጣ ማውጣት መርሃግብር ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አሊሚራህ ሙሐመድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ፣ የቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ፣ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቋሚ ኮሚቴዎችና የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለብ ተወካዮች፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተገኝተዋል ።
በዛሬው እለትም ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ የ2014 ዓ.ም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነሥርዓት የሚያካሂድ ሲሆን ፣ ነገ በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ የአንደኛ ሊግ ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነሥርዓት እንደሚከናወን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014