ኢትዮጵያ በእግር ኳስ እምቅ አቅም ያላቸው በርካታ ታዳጊዎች ያሉባት አገር ብትሆንም እንዳለመታደል ሆኖ ታዳጊዎቿን ከለጋ እድሜያቸው አንስቶ ዓለም በደረሰበት የእግር ኳስ ሳይንስና ስልጠና ኮትኩቶ ለትልቅ ደረጃ የሚያበቃ የእግር ኳስ አካዳሚ ሊኖራት አልቻለም። መንግሥት ይህን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ቢከፍትም በእግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አይደሉም።
እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩትም እስካሁን በሚፈለገው ደረጃ ታዳጊዎችን ከስር ጀምሮ ኮትኩተው በማውጣት ለትልልቅ ደረጃ በማድረስና የአገሪቱን እግር በሚለውጥ መልኩ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። ክለቦችም ቢሆኑ በቅርቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ቢሾፍቱ ላይ ከገነባው ዘመናዊ አካዳሚ በስተቀር ሌሎቹ አካዳሚዎችን ገንብተው ታዳጊዎችን በማፍራት ረገድ ይህ ነው የሚባል አቅም እንደሌላቸው ይታወቃል። በዚህም በርካታ ታዳጊዎች አቅሙ እያላቸውና ራሳቸውን ለእግር ኳስ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው እድሉን ባለማግኘት የመጫወቻ እድሜያቸው ያልፋል።
ይህን የአካዳሚ ችግር ለመፍታት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ታዳጊዎችን ሰብስበው በማሰልጠን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጥረት የራሱ ውስንነቶች ያሉበት ከመሆኑ በተጨማሪ ታዳጊዎቹን የሚያሰለጥኑት በክፍያ መሆኑ በርካታ ታዳጊዎች የኳስ እምቅ አቅም ይዘው የገንዘብ አቅም በማጣት ባክነው ይቀራሉ። ይህም ኢትዮጵያ በታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ጭምር መጫወት የሚችሉና ብሔራዊ ቡድናቸውንም እንደ ዓለም ዋንጫ ባሉ ታላላቅ መድረኮች ማብቃት የሚችሉ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች እያላት ዓለም አሁን የደረሰበት የእግር ኳስ አካዳሚ ባለመኖሩ ሕልማቸው እውን ሳይሆን ይቀራል።
መቀመጫውን በጀርመን አገር ያደረገው ስሪ ፖይንትስ የተሰኘ ድርጅት ግን ይህን የኢትዮጵያ ታዳጊዎች የዘወትር ህልም እውን ለማድረግ መላ ይዞ መምጣቱን አሳውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ከድርጅቱ ጋር በተለያዩ የዕድሜ ክልል ወጣቶችን በእግር ኳስ በማሰልጠን ለብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ለአውሮፓ ክለቦች ገበያ ለማብቃት በማሰብ የወጣቶች ብሔራዊ አካዳሚ በቋሚነት ለመገንባት ሰሞኑን ይፋዊ ስምምነት አድርጓል። በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ዋና ጸሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም የስሪ ፖይንት ናሽናል አካዳሚ ፕሮጀክት መስራቹ አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤልና ወላጅ አባቱ አቶ ሳሙኤል ባአምና እንዲሁም ወላጅ እናቱ ተገኝተዋል።
ከፊርማ ሥነሥርዓቱ በፊት አቶ ኢሳያስ ጅራ ‹‹የፌዴሽኑ የረጅም ጊዜ ሕልም አሁን እውን ሆኗል›› በማለት ስለ ፕሮጀክቱ አብራርተዋል። የአካዳሚ ግንባታውን ውጪ በተመለከተ በአጠቃላይ ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን ብር እንደሚሸፍን ጠቅሰውም የግንባታውን ወጪ በተመለከተ አራት አራት ሚሊዮን ብር ሁለቱም አካላት ለማዋጣት መስማማታቸውን ተናግረዋል። የተጫዋቾች የዝውውር ፖሊሲን በተመለከተ ታዳጊዎች በአካዳሚው ስኬታማ መሆን ከቻሉና ለአውሮፓ ክለቦች የመጫወት ዕድል ከተፈጠረ ከሚገኘው የዝውውር ገንዘብ ፌዴሬሽኑ 40 በመቶ እንዲሁም ስሪ ፖይንትስ 60 በመቶ እንደሚወስዱ የጠቀሱት አቶ ኢሳያስ፣ አካዳሚውን በቅርቡ ለመገንባት ጨረታዎች ይፋ ሆነው ሥራው ለመጀመር መታቀዱን ገልጸዋል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ተጫውቶ ስኬታማ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት ለጀርመኑ ክለብ ሄርታ ቢኤስሲ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው የትውልደ ኢትዮጵያዊው ዴቪ ሴልኬ ወላጅ አባትና የስሪ ፖይንትስ አካዳሚ መስራች አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል፣ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓላማ አብራርቷል። የፊርማ ሥነሥርዓቱ ከመካሄዱ በፊትም የአካዳሚው ዲዛይን ለዕይታ በቅቷል።
‹‹ዓላማችን እንደ የልጅ ልጄ ዴቪ ሴልኬ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችን ለአውሮፓ ክለቦች ማፍራት ነው›› በማለት ለመገናኛ ብዙኃን የገለጹት አቶ ሳሙኤል እግር ኳስ በቤተሰባቸው ውስጥ እንደሚወደድና አራቱም ወንድ ልጆቻቸው ኳስ ከልጅነታቸው ጀምሮ በጀርመን አገር አካዳሚዎች ይጫወቱ ስለነበረ ከኳስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል። ‹‹አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው ኳስ ሜዳ ላይ ነው። እና ሁሌም እመኝ የነበረው የታዳጊዎች አካዳሚ በአገሬ ቢኖር ብዬ ነው›› ይላሉ።
‹‹የልጅ ልጄ ዴቪ ሴልኬ መነሻው ከልጅነቱ ጀምሮ ከአካዳሚ ሆኖ በቡንደስሊጋ ስኬታማ በመሆን ከሚሊዮን ዩሮ በላይ ዝውውር ማግኘት እንዲችል መሠረቱ የወጣቶች አካዳሚ ነው፣ ስለዚህ ምኞቴ የነበረው አገሬ ላይ ምን አለ እንደዚህ አይነት አካዳሚ ቢኖር የሚል ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ይህን ለማሳካት ኢትዮጵያ መጥተናል። ምንም እንኳን ኑሯችን ጀርመን ቢሆንም ይህን ፕሮጀክት ለማሳካት ኢትዮጵያ ለመኖር አስበናል›› ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፣ የአካዳሚው ዓላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ በ15፣ 17ና 20 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለብሔራዊ ቡድን፤ አልፎም ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ገበያ ለማብቃት በማሰብ የወጣቶች ብሔራዊ አካዳሚ መገንባት ነው። ይህ አካዳሚ በርካታ ሚሊዮን ብር የሚወጣበት ሲሆን የሚገነባው የካፍ አካዳሚ በሚገኝበት አያት አካባቢ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ቦታው ለጨረታ ቀርቦም ሥራዎቹ ይጀምራሉ። የአካዳሚው ግንባታ በሁለትና በሦስት ወራት እንደሚጠናቀቅም ተስፋ አላቸው። ተጫዋቾችን ከየክፍለ አገሩ በመመልመል ወደ አዲስ አበባ የማምጣቱ ሂደት ሊፈትን ቢችልም ይህን ለማሳካት ከውጭ አገር የሚመጡ መልማዮች ተዘጋጅተዋል። በተጨማሪም በአገር ውስጥ ካሉት ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት የታሰበው ዓላማ ይሳካል የሚል እምነት አላቸው።
‹‹ፕሮፌሽናል የሆኑና በዚህ ሙያ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ይዘን በቅንጅት ነው የምንሰራው ። ሁሉንም ነገር ዘመናዊ በሆነና በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት ተቀናጅተናል። ቀጣዩ ጉዞ ንድፈ ሐሳቡን ወደ ተግባር መለወጥ ነው›› በማለትም አቶ ሳሙኤል ከኢትዮ ኪክኦፍ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014