‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘንህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልምርህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።›› በአድዋ ዘመቻ ወቅት ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ የክተት አዋጅ ባስነገሩበት ወቅት ያስተላለፉት መልዕክት ነበር።
ዛሬም ታሪክ ተደገመና እነሆ የእናት ጡት ነካሾች ለ30 ዓመታት የበዘበዟትን አገር የቁም ስቃዩን ያበዙበትን ሕዝብ መካስ ስለ በደላቸው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው ጥቅማችን ቀረ ሌብነት ሊቆም ነው ብለው አገርን ለጦርነት ሕዝብን ለእልቂት ዳረጉ። ይህንን ተከትሎም በብዙ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ሲጠብቃቸው የነበረው መንግሥት ጦሩን አዝምቶ አደብ እያስገዛቸው ቢሆንም አገሬን ቆሜ ለቀማኛ አልሰጥም ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር አቅንተው የህልውና ትግሉን እንደሚመሩት አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮም ወደ ግንባር አቅንተው የህልውናውን ትግል እንደሚመሩት ታውቋል። ይህም ታሪክ እራሱን ይደገም ዘንድ ያስገደደም ሆኗል። ሕዝባቸውንም ተከተለኝ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። ይህ ውሳኔ ትልቅ ነው። ታሪካዊም ነው። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ብሎም እንደ አገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነታቸው አዲስ አበባ ቤተመንግሥትና ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ቁጭ ብለው በመገናኛ ቴክኖሎጂ ብቻ በመታገዝ ጦርነቱን መምራት ቢችሉም አርዓያነት ላለው ተግባር በአካል ግንባር ተገኝተው፣ ባሩድ እየሸተታቸው፣ እንደወታደሩ ስቃጥላና ኮቾሮ እየተመገቡ፣ ከኮዳ ውሃ እየተጎነጩ ትግሉን ለመምራት መወሰናቸውን አሳውቀዋል።
ይህ ውሳኔም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ጽኑ የአገር ፍቅር፣ የመሪ ልዕልና ያሳየ በመሆኑ ስማቸውና ታሪካቸው ከታላላቆቹ የኢትዮጵያ መሪዎች አጠገብ በወርቃማ ብዕር የሚከተብ ይሆናል።
የብልጽግና አመራሮችም የሊቀመንበራቸውን ፈለግ ተከትለው በረሃ ሊወርዱ፣ ግንባር ዘልቀው የሕወሓትን ወረራ ሊቀለብሱ በጋራ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል። የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የቀድሞ ሰራዊት የጦር ጄኔራሎች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና አገር ወዳድ ዜጎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሆን ጠላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድርጊቱ ለመግታት ወደግንባር እንደሚሄዱም እያሳወቁ ነው። ይህ ተግባር ወቅቱን የሚመጥን እርምጃ እንደሆነም ብዙዎች ይናገራሉ። አሁን ጦሩ ከቷል። አመራሩ በቦታው ላይ ይገኛል። እንግዲህ የሚቀጥሉት ቀናት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ናቸው።
በአንጻሩ ደግሞ በችርቻሮና ቅንጥብጣቢ ድሎች ሲቦርቅ ሲፎክር ለያዥ ለገላጋይ ሲያስቸግር የከረመው የሕወሓቶች መንደር ደረት ለመድቃት፣ ሙሾ ለማውረድ ይዘጋጅ ዘንድም ጊዜው ደርሷል። የፈረንጆቹን ጎዳናዎች በመንከባለልና በመንደባለል ሲያጨናንቅ የሰነበተው የሕወሓት የዲያስፖራ ደጋፊም እንደተለመደው ጸጉራቸውን እየነጩ፣ ነጠላቸውን ዘቅዝቀው እሪታቸውን ለማቅለጥ ከወዲሁ ልምምድ መጀመር ግድ ይላ ቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩና የፓርቲያቸው አመራሮች ውሳኔ ከፍተኛ የሞራል ግንባታ ለሕዝባችን የሚያጎናጽፍ፣ የጠላትን ሰፈር በፍርሃት የሚያርድ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። በሕወሓት የእብደት ጦርነት ስሜቱ የተጎዳው ኢትዮጵያዊ የሚካስበት ወቅት ከደጃፋችን ተጠግቷል። ለ46 ዓመታት በሕወሓት የዘረኝነት ጦስ የተነቃነቀው የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ይቆም ዘንድ ቀኑ ተቃርቧል። መሪ ክተት ብሎ ከቤት መቅረት ኢትዮጵያዊነት አይደለም። “ማርያምን አልምርህም፣ ከተህ ጠብቀኝ፣” እንዳሉት አጼ ምኒሊክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም ኢትዮጵያውያን ተከተሉኝና አብረን አገር እናድን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያን ደግሞ ምላሽ መስጠት ያውቁበታል። ታሪካቸውን ሊደግሙ እነሆ ከዳር እስከዳር ተነስተዋል። ምናልባት ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ አንዳንድ አላዋቂዎች እንደሚሉት በአንድ ሌሊት በስሜት ተነሳስቶ የተወሰነ አይደለም። እንደውም የጦር ሜዳ ሕይወትና ትግል ትናንት ወጣትነታቸውን ያሳለፉበት ዛሬም አገሪቱን እናምሳት ካሉት ጋር እየታገሉና እየተፋለሙ የቆዩበት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ታሪክን የደገመ ኢትዮጵያን ከባንዳ እጅ ለማላቀቅ የተሄደበት ድንቅና ሕዝብ ሊከተለው የሚገባ ውሳኔ መሆኑን ደግሞ የታሪክ መምህሩ አቶ ተስፋዬ አለማየሁ ይናገራሉ። እኛም እንዲህ ያለው ውሳኔ ታሪካዊ ዳራው ምን ይመስላል ስንል ጥያቄዎችን ሰንዝረናል።
አዲስ ዘመን፦ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደጦር ግንባር ዘምተዋልና ይህ ምን ማለት ነው ?
አቶ ተስፋዬ፦ አሁን ባለው የመሪነት ትርጉም የአንድ አገር መሪ አገሩ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከዜጎቹ ጋር ሆኖ ወደጦር ግንባር መዝመቱ እጅግ የሚገርም ከመሆኑም በላይ እንድ መሪ ትልቅ የሚያደርገው ብሎም ከቀደሙት አባቶቹ ጋር በታሪክ እንዲወሳ የሚያደርግ ከዛ ባለፈ ደግሞ ግንባር ላይ ያለውን ሠራዊት በማበረታታት ድል የእኛ እንዲሆን የሚያስችል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ባለው የመሪነት ትርጉም የአንድ አገር መሪ ማለት ሰርቶ የሚያሰራ በምሳሌ የሚያስረዳ መንገድ እያሳየ የሚመራ ማለት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ያደረጉት ነገርና የወሰኑት ውሳኔ የመሪን ግንባር ቀደምነትና ምሳሌነት የሚያጎላ ታሪካዊ ስራ ነው።
ኢትዮጵያ ከብዙ ዓመታት በፊት የነበሯት ታላላቅ መሪዎችም በየትኛውም የጦር ግንባር ላይ በመሳተፍ ብዙ ጀብዶችን አስመዝግብዋል። በመሆኑም አመራር ማለት ከላይ ቁጭ ብሎ የገዢነት ስሜቱን እያንጸባረቀ መኖር ሳይሆን ብዙ መሪዎችን ማፍራት መቻል ማለት ነው። እሳቸውም ብዙ መሪዎችን ለማፍራት ግንባር ድረስ መሄዳቸው የመሪነት ተምሳሌት ያደርጋቸዋል።
የእኛ የቀደመ ታሪክ እኮ የሚያስረዳው ይህንኑ ነው፤ መሪዎቻችን ሠርተው የሚያሠሩ ተዋግተው ውጊያ ምን እንደሆነ ለሕዝባቸው የሚያሳዩ ነበሩ ፤አሁንም በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ መሪ ማግኘታችን በዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምሳሌ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ አንጻር በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ እርግጠኛ ነኝ አብዛኛው ዜጋ ወደጦር ግንባር ለመሄድ እንደተነሳሳ እኔ በበኩሌ ለመሄድ ቆርጬ ተነስቻለሁ።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ በታሪካችን ቀጥታ ጦር ግንባር ላይ በመሄድ ፊት ለፊት ጠላት የገጠሙ በርካታ መሪዎች አሉን ፤ ነገር ግን በዚህ ዘመናዊነት በተላበሰ የመሪነት ወቅት የዶክተር ዐቢይን ውሳኔ እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አቶ ተስፋዬ፦ የአጼ ቴዎድሮስን፣ የአጼ ምኒሊክን፣ የአጼ ዮሐንስንና የሌሎቹንም ታላላቅ መሪዎቻችንን ፈለግ የተከተለ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። በሌላ በኩል ደግሞ መሪዎች ሆነው የአገራችን ህልውና ከሚደፈር እንሞታለን ብለው የወደቁት እነ ደጃዝማች ኡመር ሰመተር፣ አቡነ ጴጥሮስን ስንመለከት ስለ አገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት ሲሉ ወድቀዋል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ሆኗል። ይህንን እንከተላለን እያልን ነበር የኖርነው። ነገር ግን እነዚህ የጁንታ አመራሮች አገር በመሩበት ጊዜ እንኳን ታሪክ ሊሰሩ አገርን ሊያሻግሩ ተጠምደው የነበሩት ሌብነት ላይ ነበር። ይህ እኩይ ተግባራቸው ፍርድ አደባባይ የሚያቆማቸው ቢሆንም እንኳን የለውጡ አመራር እንዲሁም ሕዝቡ ይቅርታ አድርጎላቸው ነበር። ነገር ግን እኛ ካልመራን አገር ትፍረስ ብለው የተነሱት በዚህ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ በድምጹ የመረጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መላው ሕዝቤን ወክዬ ጦር ሜዳ ድረስ እሄዳለሁ ማለታቸው ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነታቸውን፣ ቆራጥነታቸውንና ጀግንነታቸውን የሚገልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የአሁኑን የህልውና ጦርነት ከአድዋ ጋር የሚያመሳስሉት አሉ፤ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደግሞ ጦርነቱ አፍሪካዊ ይዘት ይዟል የሚል ነውና ይህንን ከታሪክ አንጻር እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ተስፋዬ፦ አዎ ይህንንም ሆነ የቀድሞውን ጦርነት ቢያመሳስሉት የሚገርም አይሆንም። ምክንያቱም ሁሉም ለነጻነት የተደረጉና እየተደረጉ ያሉ ትግሎች በመሆናቸው። በነገራችን ላይ በአድዋ ጦርነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከልጅ እስከ አዋቂ ወጥቶ ጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት የቀጣው እምቢ ለነጻነቴ ለሉዓላዊነቴ ብሎ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙ የአፍሪካ አገሮች እንዲህም ይቻላል እንዴ? ነጭ በጥቁር ይረታል እንዴ? ብለው ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸውም ወቅት ነው። በወቅቱ እኮ ሁላችንም የአምላክ ፍጡሮች የሰው ዘር ብንሆንም በቆዳ ቀለማችን መለያየት ብቻ ብዙ ነገሮች ደርሰውብናል፤ አፍሪካውያን እንደማያስቡ እውቀት እንደሌላቸው ተመራምረው ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የፈለጉበት እንደማይደርሱ አድርገው ሲቀርጹት የነበረውን ነገር አክሽፎባቸዋል። በአራቱም ማዕዘን መጥተው ወረውን ሊያንበረክኩን ቢያስቡም እንደማይችሉ አሳይተናቸዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ዓርማ በቅኝ አገዛዝ ውስጥ ለነበሩትም ተምሳሌት ሆናቸዋል። ይህንን ከታሪክ አንጻር ስናየው ሁኔታው እየተለዋወጠ መጥቶብን ነው እንጂ ደጋግመን ያልተሸነፍን ጀግንነታችንን ዓለም የሚያውቀው ሉዓላዊነታችንንም ጠብቀንና አስጠብቀን የኖርን ነን።
ይህንን ደግሞ አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት አድርገው ከመውሰዳቸውም በላይ ከነጻነታቸው በኋላ የኖሯቸውን ሰንደቅ አላማዎችን እንኳን ሁኔታው ቢለያይም አረንጓዴ። ቢጫና ቀይ የሌለበት የለም። ዘንድሮም የገባንበት ጦርነት ተመሳሳይ ነው፤ ምናልባት የውጭ ወራሪ ኃይል መጥቶ አለመውረሩ ነው እንጂ ባንዳዎችና ከሃዲዎች የውጭ ጠላቶቻችንን አስተባብረው ነው የተነሱብን፤ ነገር ግን የቀደመውን የጀግንነት ታሪካችንን የሚደግም ስራ ከመሪያችን ጀምሮ በመላው ሕዝብ እየተሰራ ነው።
ዛሬ ላይ አሜሪካና አውሮፓ እያደረሱብን ያለው ተጽዕኖ እኮ በተዘዋዋሪ በቅኝ እንግዛችሁ ለእኛ ታዘዙ ነው፤ ሌላ ምንም ነገር የለውም። እኛ ደግሞ በለመድነው የድል አድራጊነት የነጻነት ፋና ወጊነታችን አማካይነት እምቢ ለነጻነቴ ብለናል ፤ ይህ ደግሞ አሁንም የአፍሪካ አገሮች አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ መሪዎቻቸው ከአሜሪካና አውሮፓ ጋር ያላቸውን የጥቅምም ይሁን የሌላ ልዩነት እንዲረዱና ራሳችንን መቻል እንችላለን ወደሚል አቋም ላይ እንዲደርሱ ያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሜሪካን እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የአሸባሪውን በሕወሓት እድሜ ለማርዘም የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል። በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካን ኢትዮጵያውያን እንዲሸበሩ የሚያደርጉ የተለያዩ ሙከራዎችንም እያደረገች ነውና እንደው ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ተስፋዬ፦ አሜሪካን እኮ መንግስታዊ አሸባሪ ተቋም ነው። ከዴሞክራሲና ከሕዝብ ፍላጎት አንጻር ሳየው መንግስት ነውም ብዬ ለመጥራት እቸገራለሁ። አሜሪካ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ እየገባች እኔ ካላማሰልኩ አሸባሪ እደግፋለሁ፣ እንድትፈራርሱ እረዳለሁ፣ እያለች ነው። በተግባርም በብዙ አገሮች ላይ እያሳየች ያለው ይህንኑ ነው። ስለዚህ እኔ አሜሪካንን አሸባሪ መንግሥት ነው ብዬ ነው ልጠራ የምችለው።
በመሆኑም እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ወደጎን በመተው ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ አንድነታቸውን ማጠናከር አልደፈር ባይነታቸውን በተግባር ማሳየት የእናት አባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውም ማስመስከርና ባሉበት ዘመን የማይጠፋ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ መስራት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ከቻልን እንደ ቀደመው ጊዜ ዛሬ ላይ ፈርተው አልያም የራሳቸው ጥቅም በልጦባቸው ከአሜሪካን ጎን ቆመው የሚያዩን ሁሉ ይፈልጉናል ያከብሩናል። ነገር ግን የአሜሪካንን ጫና ፈርተን ወደኋላ ያልን ለታ የማንወጣው ባርነት ውስጥ እንገባለን። እኛ ብቻ ሳንሆን ደግሞ መላው አፍሪካን በማስገባት ታሪካችንን እናጠፋለን።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በግንባር ሄጄ ውጊያውን እመራለሁ፣ እሳተፋለሁ፤ እናንተም ኢትዮጵያውያን ተከተሉኝ ማለታቸው በሕዝቡ ዘንድ ምን ይፈጥራል ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እኮ ይህንን ጦርነት ለመምራት ግንባር ድረስ መሄድ አይጠበቅባቸውም ነበር። ቢሯቸው ቁጭ ብለው በቴክኖሎጂ ሁሉንም ማድረግ፣ ማዘዝ፣ መከታተል፣ መምራት ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን እርሳቸው እንደ ቀደሙት ታላላቅ መሪዎች ሁሉ አገር ወዳድ ቆራጥና ጀግና በመሆናቸው ግንባር ድረስ ሄደው ወታደሩ የበላውን በልተው። ውሃቸውን በኮዳ ተጎንጭተው። ባሩድ ሸቷቸው። እንቅልፍ አጥተው ለመምራት ነው የወሰኑት፤ ይህ እጅግ በጣም ትልቅ ውሳኔ ከመሆኑም በላይ ለኢትዮጵያውያንም ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው። ከምሳሌነቱም በላይ ኢትዮጵያውያን በተግባር የአገር ፍቅራቸውን ጀግንነታቸውን እንዲያሳዩ የሚያስችል እድልም ነው።
የአገር መሪ ሆኖ ለሕዝቤ ምሳሌ ልሁን ማለት እጅግ የላቀ ክብር የሚያሰጥ የጀግንነት ተግባር ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያውያንን ቆራጥነት ያሳየ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ የተፈተነችበት ወቅት መቼ ነበር እንዴትስ አለፈችው?
አቶ ተስፋዬ፦ አዎ ጣሊያን ሲወረን ከፍተኛ የሆነ ችግር ፈተና ነበር፤ ታሪክም ይህንን ያስረዳል፤ ነገር ግን ለችግር እጅ የማይሰጡት ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውንና የደረሰባቸውን ሁሉ ቻል አድርገው ጣሊያንን ቀጥቅጠውና የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ አድርገው አሳፍረው ከአገራቸው ምድር ጠራርገው አስወጥተዋል። ኢትዮጵያ ይህ ብቻ ሳይሆን በዘመነ መሳፍንቱ የሥልጣን ጊዜ ከባድ ፈተናዎችን አሳልፋለች። ሕዝብ በአገሩ ላይ ነፍጠኛ ጭሰኛ እየተባለ ብዙ ችግር ይደርስበት ነበር። በወቅቱም ይህ ዘመን የታሪክ ጸሐፍት እንደጻፉት ኢትዮጵያን በሃብት በተለያዩ ነገሮች ያወደማት ወደኋላ ያስቀራት መሆኑን ያትታሉ። እንደውም አሁን ላለንበት ችግር የደረስነውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹም አሉ። ነገር ግን በአገር ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ላይ አተኩረው ሕዝቡን ቢያሰቃዩትም የውጭ ወራሪ በመጣባቸው ጊዜ የራሳቸውን ችግር ቁጭ አድርገው በአንድነት ይዘምቱ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የአሁኑ ግን ከውስጥ የበቀለ ከሃዲ ባንዳ የእናት ጡት ነካሽ አሸባሪ ነው የተፈጠረብን በመሰረቱ ይህ ኃይል እንደ ወንዶቹ ፊት ለፊት አይታኮስም እየተሽሎከሎከ ሕጻናትን እያሰማራ የተለያዩ ጥፋቶችን ነው የሚያደርሰው። ይህ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ድባቅ መምታት አልቻሉም። አሁን ላይ ግን በትምህርቱም በቴክኖሎጂውም ታግዘን ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ይኖርብናል። ይህ ወቅት ከዘመነ መሳፍንቱ ጊዜ ጋርም ይመሳሰላል ፤ ምክንያቱ ደግሞ በዘመነ መሳፍንት ጊዜም ቢሆን ስልጣንን ለብቻዬ ካልያዝኩ አርፌ አልቀመጥም ከሚለው ጋር ነው ችግሩ። አሁንም ለ30 ዓመት አፈር ያስበላት አገርን አሁንም ይዤ ካልሞትኩ አገር አፈርሳለሁ ከሚል ራስ ወዳድ ጋር ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ያንን ዘመን በአንድነቷ እንደተወጣችውና እንዳለፈችው ሁሉ አሁንም ይህንን ጊዜ ታልፈዋለች፤ ትወጣዋለች።
አንድነቱና ልዩነቱ ይህ ነው። ከዚህ በመነሳትም ሕዝቡ ትልቅ ትምህርት ወስዶ በአገሩ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ፈተና ከዚህ ቀደምም ማለፏን የሚያሳዩ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥና በመረዳት አንድነቱን አጠናክሮ ከችግሯ ያወጣት ዘንድ እጠይቃለሁ።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው ቡድን ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ወደሥልጣን ሲመጣ የተጠቀመበት መንገድና አሁን አገር ለማፍረስ እየሄደበት ያለው አካሄድ ተመሳሳይ እንደሆነ ይነሳልና እርስዎ ይህንን ነገር እንዴት ያነጻጽሩታል?
አቶ ተስፋዬ፦ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲነሱ በሐሰትና በራስ ወዳድነት የተመሰረቱ ቡድኖች ናቸው። የትግራይ ነጻ አውጪ ብለው ራሳቸውን ሰየሙ እንጂ በተበደለው ሕዝብም ነገዱበት እውነትን ይዘው ተፋልመው አይደለም እዚህ የደረሱት። ይህ ደግሞ ታሪክም የሚያውቀው ሐቅ ነው።
እነሱ ማለት እኮ ያኔም ቢሆን ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ በረሃብ እየጨረሱ ረሃብን የጦር ስልት አድርገው የነበሩ ናቸው። አሁንም ከ30 ዓመት በኋላ ሕዝብን ወደ ጦርነት እያስገቡ በስንት ድካም የተገነባን ከተማ እያፈረሱ፤ ሰዎች ንብረታቸው እየተቀማ ነው ያለው። ጅራፍ እራሱ ገርፎ እንደሚባለው ሁሉ እነሱ ከጀሌዎቻቸው ጋር ሆነው በሚሰሩት ጥፋት የኢትዮጵያ መንግሥትን ተወቃሽ ለማድረግም ይጥራሉ፤ በእርግጥ እነሱ የትጥቅ ትግል በሚሉት ወቅትም ሲያደርጉ የነበረው ይህንን ነው። በመሆኑም ሴረኝነታቸው የታወቀ አብሯቸው የኖረ ነው።
አንድ መምህር እንዳሉት “ ሕወሓት ማለት እንደ አውሬ የመጣ። እንደ አውሬ ያሸነፈ። በዛው በመጣበት አኳያ ተመልሶ እንደ አውሬ የሄደ። አሁንም ደግሞ አብሮት የኖረው አውሬነቱ ተነስቶበት ጸብ ጭሮ እየተዋጋ ያሉ ነው”። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በተለይም ለእኔ ኢትዮጵያዊነታቸውንም ትግራዋይነታቸውንም እጠራጠራለሁ፤ በዚህች በተባረከች ምድር ላይ ስለመብቀላቸውም ጥያቄ አለኝ። በታሪክም እንደነሱ ያለ መሰሪ በዝባዥ ሙሰኛ አገራቸውንን ሕዝባቸውን የማይወዱ አካላት የሉም።
አዲስ ዘመን፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከተሉኝ አገርን ከባንዳ እጅ ፈልቅቀን እናውጣ በማለት ጦር ሜዳ ከተዋል፤ እንደው እዚህ ላይ የሕዝቡ ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፦ መሪው ለአገሬ ክብር ለሕዝቤ በሰላም ወጥቶ መግባት ስል እሰዋለሁ ብሎ ጦር ግንባር ሲሄድ ሕዝቡ ደግም በየአንዳንዷ ደቂቃና ሰከንድ ጥያቄ ይቅረብለትም አይቅረብለትም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት። በየቦታውም ይህንን የሚያስተባብሩ አካላት ኖረው የአገር ፍቅር ያላቸው ወገኖች የሚያደርጉትን ዝግጅት በማጠናከር ወደአስፈላጊው ቦታ እንዲዘምቱ ማድረግ ይገባል። እዚህ ላይ ግን ሕዝቡ ጦር ሜዳ በመሄድ ብቻ ሳይሆን አጋርነቱን ማሳየት ያለበት በተሰማራበነት የሥራ መስክ ሁሉ ተጨማሪ ከብክነት የጸዱ ሰዓታትን ጨምሮ በመስራት ማሳየት ምሳሌ መሆን አለበት። በመሆኑም በዲፕሎማሲው በሕክምናው በአገልግሎት አሰጣጡ በመምህርነት በተማሪነት እየተጋ አገርን ማዳን የየራስን አሻራ ማኖር ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ የግለሰቦች አልያም የመሪዎች ብቻ አይደለችም ፤ የሁሉም ዜጋ ናት ብሎ የሚያምን ሁሉ አገሩን ላለማስደፈር በተጠንቀቅ መቆም አለበት። አስፈላጊም ከሆነ ለመስዋዕትነት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ፦ እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014