ዓለም እና አህጉር አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሃገራዊ ውድድሮች ዘለግ ላሉ ዓመታት በብቸኝነት ይስተናገዱ የነበሩት በአዲስ አበባ ስታዲየም መሆኑ ይታወቃል:: ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ባለፈ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ሌሎች ሁነቶችንም ለማስተናገድ ተመራጭ ስፍራ ሆኖ ቆይቷል:: ይሁንና በጊዜ ብዛት በማርጀቱና ሜዳውና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ክፍሎቹ ዘመኑን የሚመጥኑ ባለመሆናቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ እገዳ ካስተላለፈባቸው ስታዲየሞች መካከል አንዱ ሆኗል::
ይህንን ተከትሎም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስታዲየሙ የካፍን መስፈርት ባሟላ እንዲሁም በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ እድሳት እንዲያገኝ አድርጓል:: ከወራት በፊት እድሳቱ የተጀመረው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍ በተሰጠው አስተያየት መሰረት በዋናነት ለመስራት የታቀደው የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍሎችን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ክፍሎች መሆኑን በሚኒስቴሩ የፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው ይገልጻሉ:: በካፍ ግብረመልስ የመልበሻ ክፍሎች ብዛታቸውም ሆነ ስፋታቸው በቂ አለመሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በአራት ክፍሎች የመከፋፈል ስራው ተጠናቋል:: ቀሪዎቹ ስራዎችም የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን ለመስራት እንዲሁም አስፈላጊውን የመልበሻ ክፍል ቁሳቁስ መግጠም ነው:: በተመሳሳይ የዳኞች ማረፊያ፣ የህክምና እንዲሁም የስፖርት አበረታች ንጥረ ነገሮች መመርመሪያ ክፍሎች ግንባታም መጠናቀቁን ያመላክታሉ::
በክረምቱ ምክንያት በሚፈለገው ልክ መስራት ያልተቻለው የሜዳው ስራም የክረምቱን ማብቃቱን ተከትሎ ወደ ቁፋሮ የተገባ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም ተጠናቆ የመጀመሪያ ደረጃ ስራው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል:: በቀጣይም የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ዝርጋታና ሌሎች ቀሪ ስራዎች በሶስት ወር ውስጥ ተጠናቆ የሳር ተከላው ይጀመራል::
ስራውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለመስራት ታቅዶ ከወራት በፊት ወደ ተግባር ሲገባ አሁን ላይ አጠቃላይ ስራው 40 ከመቶ ላይ መድረሱንም ዳይሬክተሩ ያረጋግጣሉ:: በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥም ከ80 በመቶ በላይ የሆነ አፈጻጸም ሊመዘገብ እንደሚችልና በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሙሉ ለሙሉ የአንጋፋው ስታዲየም እድሳት ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ይገባል የሚል እምነታቸውንም አንጸባርቀዋል::
የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ስፖርታዊ ውድድሮችንም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን ለማስተናገድ ተመራጭ ከሆኑት ከተሞች መካከል አንዷናት:: ይሁንና ስሟን የሚመጥኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው ምክንያት አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማሰናዳት እድሎችን ማግኘት አልቻለችም::
ያገኘቻቸውን እድሎችም በዚሁ ምክንያት መነጠቋ የሚታወስ ነው:: በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ግዙፍና ዘመናዊ ብሄራዊ ስታዲየም እያስገነባ ይገኛል:: ይሁንና እንደሚጠበቀው ስታዲየሙ በአፋጣኝ አለመጠናቀቁ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ቅሬታን የሚያስነሳ ነው::
ዳይሬክተሩ ይህንን በሚመለከትም፤ የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ውል የተፈረመው በ2008 ዓ.ም ቢሆንም እስካሁን ድረስ አለመጠናቀቁን በመመልከት የስፖርት ቤተሰቡ እንደ ጉድለት ያነሳዋል:: ይሁን እንጂ አስቀድሞ በታሰበው ጊዜ መሰረት ላለመሄዱ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ዙር ለመግባት ሲወጡ የቆዩት ዓለም አቀፍ ጨረታዎች በበቂ ሁኔታ ተጫራቾች ባለመገኘታቸው ለሁለት ዓመታት መቆየት የግድ ብሎ ነበር:: በመሆኑም ህብረተሰቡ በሚሰማው ስጋት ልክ ግንባታው የተጓተተ አለመሆኑን ያስረዳሉ:: ለማሳያ ያህልም ሜዳው ከመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ሳር በማልበስ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚቻል ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ:: ይሁን እንጂ ጣራው በሚተከልበት ወቅት ሊበላሽ ይችላል በሚል ስጋት ለማራዘም እንዳስፈለገም ያስረዳሉ::
በአሁኑ ወቅትም በዋናው ስታዲየም ዙሪያ የሚገነቡት 20 የሚሆኑ ሜዳዎች አብዛኛው ስራቸው ተጠናቆ የማጠቃለያ ብቻ ይቀራል:: የጣራ ተሸካሚ ቋሚዎች ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የሚቀሩት ስራዎች በወራቶች ውስጥ ሊጠናቀቁ የሚችሉ ጥቂት ስራዎች ናቸው:: ከዚህ በኋላ የሚጀመሩት ትልልቅ ስራዎችም፣ የጣሪያ እና የቴክኖሎጂ ገጠማ ስራዎች ሲሆኑ በዚህ ረገድ ሊኖር የሚችለው ውስንነት እቃዎችን ለማስገባት አስፈላጊ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ነው:: ለዚህ ይረዳ ዘንድም የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እየተተገበረ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ እንደሚመዘገብ ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2014