ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደ አገር የተለያዩ ዘርፎች ላይ በተቋም ደረጃ የተለያዩ ሪፎርሞች፣ ተቋማዊ መዋቅሮችና ለውጦች ሲካሄዱ በበርካታ አጋጣሚዎች አንድ ጊዜ በሚኒስትር ደረጃ ሌላ ጊዜም በኮሚሽን ደረጃ ከሌሎች ዘርፎች ጋር እንዲጣመር እየተደረገ ጭምር እዚህም እዚያም የሚንከላወሰው የስፖርቱ ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆኖ ይጠቀሳል። ይህም የአገሪቱ ስፖርት ወደ ፊት ከመጓዝና ከመመንደግ ይልቅ ወደ ኋላ ለመጓዙ አንዱ ምክንያት ተደርጎ በተደጋጋሚ ይነሳል።
በእርግጥ የኢትዮጵያ ስፖርት ከመዋቅርና አደረጃጀት ይልቅ በእድገቱ ላይ እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት መካድ አይቻልም። ከስፖርቱ ይልቅ ስፖርቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካና ስፖርቱን በሚመሩ የተለያዩ አካላትና ግለሰቦች መካከል ያለው መጠላለፍና ሴራ ጎልቶ በሚታይባት አገር በርካታ አስተዛዛቢ ጉዳዮች በየጊዜው ይስተዋላሉ። በቅርቡ በተጠናቀቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንኳን ከስፖርቱ ይልቅ ስፖርቱ ውስጥ የነበረው ፖለቲካ ሚዛን ደፍቶ የታየበት አጋጣሚ የሚዘነጋ አይደለም። በበርካታ አጋጣሚዎችም መሬት ወርዶ ከሚታየው የአገሪቱ ስፖርት ይልቅ ስፖርቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካና ስፖርቱን በሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች መካከል ያለው ሽኩቻ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሲሆን ማየት ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።
ይህም የኢትዮጵያን ስፖርት ክፉኛ ከጎዱት ምክንያቶች ሚዛን እንደሚደፋ ብዙ ማሳያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። የኢትዮጵያን ስፖርት ለዘመናት ከያዘው ማነቆ ፈልቅቆ ለማውጣትና ወደ ፊት ለማራመድም በቅድሚያ ይህን ችግር መቅረፍ አስፈላጊ ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው።
በቅርቡ በተዋቀረው መንግሥት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማዋቀር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት ከተቋቋሙት የመንግሥት ተቋማት አንዱ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲያከናውናቸው ከተሰጡት 18 ሥልጣን እና ተግባራት መካከል 10ሩ ስፖርቱ በአገራችን እንዲስፋፋ እና ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባው የሚያመላክቱ ናቸው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች ዙሪያ ግልፅነት በመፍጠር እና በትብብር ወደ ውጤት ለመቀየር ከክልልና ከተማ አስተዳደር የባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ከአገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና አመራሮች ጋር ከቀናት በፊት በአዳማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩም ከስፖርት ፖለቲካ በመውጣት እና የአገራችንን ጥቅም በማስቀደም ለስፖርቱ ውጤታማነት በመቀራረብ መስራት እንደ ሚያስፈልግ ተጠቁሟል። መድረኩን ያጠቃለሉት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በአሁኑ ሰዓት የአገራችን ስፖርት ውጤታማነት እየቀነሰ መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመፍታት አገራዊ ስፖርት ሪፎርሙን ጨምሮ ሌሎች የተጠኑ ሰነዶችን ወደ መሬት ማውረድ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተለይም ከስፖርት ፖለቲካ እና ከመሳሳብ በመውጣት፤ የአገራችንን ጥቅም በማስቀደም ለስፖርቱ ውጤታማነት ተባብረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ስፖርት ዋነኛ ማነቆ የሆነው ጉዳይ ላይ አጽዕኖት ሰጥተው አብራርተዋል። ‹‹ስፖርት የሰላም መሣሪያ ነው ፤ ስፖርት ለማህበረሰብ ልማት እና ለአገር ብልፅግና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበን በትብብርና በቅንጅት በመስራት ስፖርቱን መለወጥ ይገባል›› ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።
መድረኩ ለሁለት ቀናት የቆየ ሲሆን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተሰጡ ተግባርና ኃላፊነቶች፣ በቀጣይ በመቶ ቀናት በሚከናወኑ ተግባራት እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በሚኖረው ዕቅድ ትስስርና ግንኙነት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ የክልልና ከተማ አስተዳደር የባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የአገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት አመራሮች፣ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የኪነጥበብና ሥነጥበብ የፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሂዲም በመድረኩ ተገኝተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014