እንደ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ አሁን ያለው የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን እ.አ.አ በ2050 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። የህዝብ ቁጥር መጨመር ማለት የምግብ ፍላጎት ይጨምራል ማለት ነው። የዓለም የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ቢሆንም ለግብርና የሚውሉ መሬቶች በፈጣን የከተሞች መስፋፋት ምክንያት እየቀነሱ ይገኛሉ። እ.ኤ.አ. በ2050 ዓለምን ለመመገብ በፋኦ ትንበያ መሰረት የዓለም የምግብ ምርት በ2007 ከነበረበት በ70 በመቶ መጨመር እንዳለበት ይገምታል። በሌላ አገላለጽ የአለም አቀፍ የእህል ምርት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ቶን ወደ 3 ቢሊዮን ቶን ማደግ አለበት።
ከሚታረስ መሬት እጥረት እና ምርታማነት መቀነሰ እንዲሁም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ማሻቀብ ጋር ተያይዞ በዓለማችን ሊፈጠር ያለውን የምግብ እጥረት ስጋት ለመቀልበስ የግብርና ምርታማነትን ከፍ የሚያደርጉ ስጋቱን ለመቀነስ ቴክኖሎጂ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚተዳደር ሽቅብ እርሻን (Vertical Farming) አስተዋውቋል። አናሊቲክስ ኢንሳይት እንዳተተው ይህ የእርሻ ዘዴ ሕንጻዎች ውስጥ እና ጣራ ላይ እንዲሁም በሌሎች አመቺ አነስተኛ የቤት እና የውጭ ስፍራዎች ወደላይ በሚደረደሩ መሰደሪያዎች አማካኝነት ዕፅዋትን የማብቀያ መንገድ ነው።
ይህ ዘዴ በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር በሆነ ከባቢ ውስጥ እንደመከናወኑ የዕፅዋቱን የእድገት ሂደት ለመከታተል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በአጋዥነት ይጠቀማል። ለዕፅዋቱ ግብዓት የሆኑ እንደ አፈር እና ማዳበሪያ የመሳሰሉትን ለመመጠን፣ የሙቀት መጠንን ለመከታተል፣ ተባዮችን ለመቆጣጠር፣ ዕፅዋቱን እና ከባቢውን የተመለከተ ዳታን ለማጠናቀር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ እንደሚውል አናሊቲክስ ኢንሳይት በዘገባው አትቷል።
ማሽን ለርኒንግን በመጠቀም የአፈሩን ምርታማነት እና የእርጥበት ይዘቱን ለመከታተል እንዲሁም ወቅቱን እና የዕፅዋቱን ሁኔታ ያገናዘበ የብርሀን ምጣኔ ሳይቋረጥ ለማቅረብ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተመራጭ መሆኑንም ነው የተዘገበው።
በተለይም ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ የማይፈልጉ ሰብሎችን መሬት ላይ ከማልማት ይልቅ በሽቅብ እርሻ ማልማት የተሻለ አማራጭ ነው የሚለው የአናሊቲካ ኢንሳይት ዘገባ፤ ሽቅብ እርሻ የውሃ አጠቃቀምን ከመቀነሱም ባሻገር “በሃይድሮፖኒካል” (ውሃ ውስጥ ለሰብል ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በመጨመር ያለ አፈር) ከፍተኛ ምርት ለማግኘት እያስቻለ ነው። ከዚህም በላይ ሽቅብ እርሻ ከፍተኛ ምርት እያስገኘ ነው። በተለምዷዊ እርሻ ከአንድ ካሬ ሜትር ከሚገኘው በላይ በሽቅብ እርሻ ከአንድ ካሬ ሜትር እየተገኘ ነው። ይህ የምርት ዘዴ የምግብ እጥረት ስጋት ለመቋቋም፣ ሊታረስ የሚችል መሬት እጦት እና ብሎም የአለም አቀፍ ረሃብን ለመቀነስ ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ነው ዘገባው ያመላከተው።
እንደ ዘገባው፤በዚህ ዘመን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ገበሬዎች ጤናማ ሰብሎችን እንዲያመርቱ፣ ተባዮችን መቆጣጠር እንድችሉ፣ የአፈር እና የሙቀት ሁኔታዎችን በኢንተርኔት ዳሳሾች መከታተል እንዲችሉ፣ ለገበሬዎች መረጃን በማደራጀት በጠቅላላው የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ከግብርና ጋር የተገናኙ ተግባራትን ለማመቻቸት እየረዳቸው ነው። በተለይም በሽቅብ እርሻ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለከፍተኛ ምርት እና ለተሻለ ውጤታማነት ጥልቅ አንድምታ ይኖረዋል።
ዘገባው እንደ ማሳያ ያነሳው በሳን ፍራንሲስኮ የተመሰረተ አግቴክ ጅምር የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሽቅብ እርሻ ነው። ይህ ኩባንያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሮቦቶችን በመቅጠር በተለምዶ ለእርሻ ከሚያስፈልገው 95 በመቶ ያነሰ ውሃ እና 99 በመቶ ያነሰ መሬት እየተጠቀመ ምርትና ምርትማነትን እንዲሁም የምርት ጥራት በየጊዜው እያሻሻለ ነው። ኩባንያው ይህንን ሊያሳካ የቻለው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ተመርኩዞ የሙቀት፣ የእርጥበት መጠን እና ጋዞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ በየጊዜ ያለማቋረጥ ራሱን እያሻሻለ በፍጥነት እና የተሻሉ ሰብሎችን እንዴት ማሳደግ እንደሚችል ራሱን የሚላምድ ነው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ብርሃን አመንጪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች እንደ የፀሐይ ብርሃን ሆነው እንዲያገለግሉ በማድረግ ነው። ይህም ማለት ሰብሉ በቀን 24 ሰዓት በሳምንት ሰባት ቀን ሁል ጊዜ በቋሚነት እንዲያድግ እና በእንፋሎት መልክ የሚወጣ ውሃ እንዳይባክን እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ያስችላል። በተጨማሪም ሰማያዊ፣ ቀይ፣ ነጭ ብርሃኖችን በማመጣጠን ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ሰብሎቹ በከፍተኛ ፍጥነት የማሳደግ አቅም አለው። በዚህም መሰረት በ0 ነጥብ 4 ሄክታር ቦታ ላይ በተለምዶ ከሚመረተው በ400 እጥፍ የሚበልጥ ምርት መመረቱንም ዘገባው አመላክቷል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014