ሰዎቹ ዛሬም ቲያትሩን ከመድረኩ ላይ መጫወታቸውን አላቆሙም። እየተወኑ ነው። ድራማው ግን ያን ያህል የኢትዮጵያውያንን ቀልብ የማረከ አልሆነም። በአጠቃላይ “የተዋጣለት አይደለም” ማለት ይቻላል። ለዘመናት ይህን መሰል “ስላቃዊ አገር የማፍረስ ድራማ” ሲያከሽፍ የነበረ ማህበረሰብ በአማተር አርቲስቶች መወራጨት ልቡ ሊደነግጥለት አልቻለም።
አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የቲያትሩ ደራሲዎችና ዳይሬክተሮች የረጅም ግዜ አገር የመበተን፣ በጠራራ ፀሃይ የመዝረፍ ልምድ ያላቸው የምእራቡ ዓለም ሰዎች መሆናቸው ነው። እንዴት አልተሳካላቸውም? ምን አልባት ቀሽም አርቲስቶችን መምረጣቸው ይሆን? አይ አይ!! ነገሩ ወዲህ ነው። አገሪቷ “ኢትዮጵያ” በመሆኗ ነው። አሊያማ ዋል አደር ሳይል እንደሚደረማምሷቸው አገራት እኛም ተራው ይደርሰን ነበር። ግን አልሆነም። ወደፊትም የሚታሰብ አይደለም።
ተስፋ የማይቆርጡት “የእኩይ” አላማ ባለቤቶቹ አዳዲስ “ሴራ” እየጠመቁ የቻሉትን እየሞከሩ ነው። ዜጎቻቸውን ምንም አስጊ ሁኔታ በሌለበት እያሸበሩ ከኢትዮጵያ እንዲለቁ፣ ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ መጎትጎታቸውና ተግባር ላይ ማዋላቸው ውጤት ያመጣ የመጫወቻ ካርድ መሆን አልቻለም። ሚዲያዎቻቸው “ጉሮሯቸው እስኪነቃ” ቢጮሁም የአባቶቹን ታሪክ በመድገም ያለው የአገሬ ህዝብ “ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ” ብሎ ለሉአላዊነቱ እየተዋደቀ ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ ጭራሽ ይባስ ብለው ወረራ የመፈፀም እቅድ እንዳላቸው እየነገሩንና እያስፈራሩን ነው። ለዚህ ደግሞ መልስ አለን። “በሱማሌ ካልተቀጣችሁ ሞክራችሁ እዩት የሚል”። ይሄ ብቻ አይደለም። የዘመናት የባንዳነት ታሪክ ያላቸውን የጣት ቁስሎቹን ከአገሩ ስለማይበልጡ ቆርጦ ሊጥላቸው አንድ ሃሙስ ቀርቶታል። ለዚህ ደግሞ አንዳች ጥርጥር የለውም።
ከሁሉም በላይ እኛን እያስገረመን ያለው የኛዎቹ ጉዶች “የእናት ጡት ነካሾች” መቅበዝበዝ ሳይሆን የአሜሪካና የአንዳንድ ምእራባውያኑ ጠላቶቻችን በዙሪያቸው ለማፍራት መንቀዥቀዣቸው ነው። ለኛዎቹ ግልገል አሸባሪዎች “እዳው ገብስ ነው” …“ሂሳብ እናወራርዳለን” ሲሉ የአገር ክንድ የሆነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚጠብቁት ልጆቻችን አዋርደው ወደ መቃብር እያወረዷቸው ነው። እኛ ያልገባን አድሮ ሊያስተዛዝበን የዘመናት የአጋርነትና የወዳጅነት ታሪክ ያላቸው አገራት ክንዳችን የዛለ መስሏቸው የምንግዜም ስትራቴጂክ አጋራቸው ከሆንነው ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመቃቃር የሻቱበት ምክንያት ነው። ያገሬ ሰው ለዚህ አይነቱ “ቅሽምና” አንድ አባባል አለው “በቅሎ ገመዷን በጠሰች ቢባል፤ ተውአት ትበጥስ ለራሷ አሳጠረች” የሚል።
ይህ ሁሉ ሊሳካ ያልቻለ “ቀቢፀ መፍጨርጨር” አድርገው እንኳን የተስፋ በመቁረጥ እንቅልፍ እንዳልወሰዳቸው ስናይ ዛሬም እንገረማለን። በዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ ደግሞ አዲስ ድርሰት እያስተዋወቁን ይገኛሉ። ነገሩን አጥርቶ ለማየት ከዚህ ስክሪፕት ውስጥ ትንሽ ቀንጨብ አድርገን እናጫውታችሁ። ነገሩ ወዲህ ነው። ለዓመታት በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ “ቤንች ተሰላፊና የህውሓት የጋሪ ፈረስ” ከመሆንና በህዝብ ዘንድ በወላዋይነታቸውና በአስመሳይነታቸው ወደዳር ከመገፋት ያልዘለለ አንዳች ጠብ የሚል ቁምነገር የሌላቸው የአገር ሸክሞች ከወደ አሜሪካ ሳታየር ኮሜዲ ይዘውልን ብቅ ብለዋል። ይሄ ኮሜዲ ድራማ ባለማሳቁ ብቻ የሚያስቅ ነው።
በቀድሞው የሽብርተኛው ትህነግ ታጋይነት፣ አሁን ደግሞ ገመድ ላይ በመንጠላጠልና ዥዋዥዌ በመጫወቱ ምክንያት አቋሙ በማይታወቀው ስዬ አብርሃ መሪ ተዋናይነትና አሰባሳቢነት እየተሞከረ ያለውን ኢትዮጵያን መቅኖ የማሳጣትና የማፍረስ ሴራ ለማስቀጠል እንደ አማራጭ ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ጥሩ የመጋለብ ጫንቃ ያላቸው አቶ ልደቱ አያሌው፣ታምራት ላይኔ፣ ያሬድ ጥበቡና ሌሎችም በረዳት ተዋናይነት ተመርጠው የአሜሪካንና የምእራባውያኑን ሴራ አካል ሆነዋል።
ለድራማቸው ደግሞ “የኢትዮጵያ ህልውና ተቆርቋሪዎች” የሚል ርእስ ሰጥተውታል። በተለይ አቶ ልደቱ “ልቤ ሊፈርስ ነው” በሚል ድራማ ያለማቋረጥ አቤቱታውን አቅርቦ በህክምና ሰበብ አሜሪካ ቢሄድም ተመልሶ ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ እላይ እታች ሲል መመልከታችን አስገርሞናል። በእርግጥ ምንም ያክል ክፉ ባንሆንም ኢትዮጵያችን በእርሱ መሰል የባንዳነት ትወና ከምትፈርስ “ልቡ ቢፈርስ” ምርጫችን ነው።
የሆነው ሆኖ እነዚህ የጋሪ ፈረሶች አንድ ነገር ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። እርሱም እኛ ኢትዮጵያውያን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመመከት በምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ እንቅፋት ለመሆን በመንገዳችን ላይ የሚቆሙትን ማናቸውም ሃይላት እንደምናስወግድ ነው። ይሄን ለመገንዘብ ደግሞ እሩቅ መሄድ አያስፈልግም። በእኛ በኢትዮጵያውያን ሉአላዊ ምድር ላይ ማንነታቸውን ዘንግተው፣ አልጠግብ ብለው እየተፉ፣ በጋሪ ፈረስነታቸው ተወዳዳሪ ያጡትን ሁለት የሽብር ቡድኖች ማየት በቂ ነው።
መቅበዝበዛቸው ከምድር በታች ከመውረድ የዘለለ ያተረፈላቸው “ቤሳ ቤስቲ” የለም። ይህን ጉዳይ የታዘበው ትንግርቱ ገብረፃዲቅ በአማራ ቲቪ ላይ ብቅ ብሎ “ትህነግ የሚጠቀምባቸው ፈረሶች ቀድሞ ይጠቀምባቸው የነበሩት ናቸው። አሁንም አማራ ናቸው ብሎ ሊጠቀምባቸው የሚጎትታቸው ሆዳሞች አሉ። የትህነግ ፈረስ የሆኑ ሆዳም አማራዎችን የአማራ ህዝብ የመበቀል መብት አለው” በማለት እቅጩን ተናግሯል። እኛ ደግሞ እንዲህ እንላለን አሸባሪው ትህነግም ሆነ መሰል የኢትዮጵያ አፍራሽ የውጪ ሃይሎች የሚጋልቧቸው ግለሰቦች በጥቁር መዝገባችን ላይ ሰፍረው የሚገባቸውን ዋጋ የሚከፍሉበት ግዜ እሩቅ አይደለም።
አንድ ጀግና የጦር አበጋዝ ሚስቱንና ቤተሰቡን ተሰናብቶ ወደ ጦር ግንባር ይሄዳል። ይሄን የሰማ ጎረቤቱ ታዲያ በውሽማነት ይገባል። ይሄን ክህደት የሰማው ጀግና ታዲያ እንዲህ የሚል መልእክት ይልክለታል “እሳትን ጭድ ሆነህ ቆየው” መልዕክቱ ግልፅ ነበር። ምንም እንኳን ቤቴ ተደፈረ ብሎ ከግንባር ጥሎ አልመጣም ምክንያቱም ከቤቱ መደፈር በላይ “የአገሩ ሉአላዊነት” ተደፍሮ በግንባር በመዋደቅ ይቀድም ነበር። ይሁን እንጂ ጦርነቱን በድል አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ክብሩን የማስመለስ ዘመቻ መምጣቱ አይቀርምና “እሳትን ጭድ ሆነህ ቆየው” የሚል ቅኔ ሰደደለት።
ዛሬም የነዚህ የጋሪ ፈረሶች ተግባር ይህን ከመሰለው “የውሽማነት” ቅሌት ጋር ይመሳሰላል። ለዚህ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በዙሪያችን የከበበንን ጠላት አንበርክከን እስክንጨርስ “እሳትን ጭድ ሆናችሁ ቆዩት” የሚል መልእክት ለተጋላቢዎቹ የምንልከው። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014