ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረወሰኖች በሁለቱም ጾታ እየተሰበረባት የምትገኘው የቫሌንሲያ ከተማ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን የማራቶን ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ታስተናግዳለች። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው የዘንድሮው የቫሌንሲያ ማራቶን ለመወዳደር የርቀቱ ፈርጦች የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ከወዲሁ እንደሚሳተፉ እያሳወቁ ነው። ከማራቶን በተጨማሪ ከረጅም ርቀት ውድድሮች ወጥተው በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ፉክክር ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ በርካታ አትሌቶች በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ይህም እንደ ግማሽ ማራቶን ቫሌንሲያ በሙሉ ማራቶንም የዓለም ክብረወሰን የምታስተናግድበት እድል እንዲኖራት አድርጓል።
የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና የሶስት ጊዜ አሸናፊው ኬንያዊ አትሌት ጂኦፍሪ ኮምዎረር በዘንድሮው የቫሌንሲያ ማራቶን እንደሚፎካከሩ ስማቸው ይፋ ከተደረገ አትሌቶች መካከል በጉልህ የሚጠቀስ ነው። ከግማሽ ማራቶን ስኬቶቹ በተጨማሪ የሁለት የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮኑ ኮምዎረር በማራቶን ያለውን 2:06:12 ሰዓት በቫሌንሲያ ለማሻሻል ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ኮምዎረር ይህን ፈጣን ሰዓት እኤአ 2012 ላይ በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠበት ወቅት ካስመዘገበ ወዲህ በኒውዮርክ ማራቶን ሁለት ጊዜ ማሸነፍ የቻለ ነው፤ አትሌቱ በጉዳት ምክንያት በቶኪዮ ኦሊምፒክ መሳተፍ እንዳልቻለ ይታወቃል። ቫሌንሲያ ማራቶን ላይ ግን የተሻለና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደተዘጋጀ ታውቋል።
ሌላኛው ኬንያዊ ላውረንስ ቺሮኖ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ አትሌት ነው፤ አትሌቱ 2019 ላይ በቦስተን ማራቶን 2:03:04 ያስመዘገበው ሰዓት በቫሌንሲያው ፉክክር ፈጣኑ አትሌት አድርጎታል። ይህም የአሸናፊነት ግምት ከተቸራቸው አትሌቶች ግንባር ቀደሙ ያደርገዋል።
ኬንያውያኑ አትሌቶች ባላቸው ስኬትና ፈጣን ሰዓት መሠረት ቫሌንሲያ ላይ የተሻለ ትኩረት ቢሰጣቸውም የዘወትር ተቀናቃኛቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። በተለይም የ2019 የዱባይ ማራቶንን ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ሄርጳሳ ነጋሳ እንዲሁም አትሌት ክንዴ አጥናው በዚህ ፉክክር ውስጥ የተካተቱና ማራቶንን ከ2:04 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የቻሉ መሆናቸው ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ማሳያ ሆኗል።
ባለፉት ዓመታት በረጅም ርቀት ጠንካራ ተፎካካሪነቱን ያስመሰከረው አትሌት አንዱአምላክ በልሁ በቫሌንሲያ ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዱ ነው። በ2019 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አንዱአምላክ በ2020 የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናም ተመሳሳይ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል።
አንዱአምላክ ቫሌንሲያ ላይ የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር ለማድረግ ተዘጋጅቷል፤ ይህ የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት አትሌት በ10ሺ ሜትር 26:53:15 እንዲሁም በግማሽ ማራቶን 58:54 የሆነ የራሱ ፈጣን ሰዓት አለው። ይህም ሰዓቱ በአማካይ ሲሰላ ቫሌንሲያ ላይ በማራቶን ፈጣኑ አትሌት ያደርገዋል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ማራቶንን ከ2:20 በታች መሮጥ የቻለ አትሌት ባይሳተፍም ለተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ ከተጠቀሰው ሰዓት የተሻለ ሊመዘገብ እንደሚችል አዘጋጆቹ ተስፋ አድርገዋል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉተኒ ሾኔ ባለፈው የዱባይ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ 2:20:11 ያስመዘገበች አትሌት በመሆኗ ዘንድሮ ቫሌንሲያ ላይ የተሻለ ሰዓት ያስመዘግባሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች ቀዳሚ ናት። በ2019 የአምስተርዳም ማራቶን 2:20:48 ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አዝመራ ገብሩም ከሁለት ሳምንት በኋላ ቫሌንሲያ ላይ የተሻለ ፈጣን ሰዓት ያስመዘግባሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አትሌቶች ዋነኛዋ ሆናለች።
የ2018 ፕራግ ማራቶን ቻምፒዮኗ ኬንያዊት አትሌት ቦርኒስ ቺፕኪሩይ፣ የዩጋንዳ የርቀቱ ክብረወሰን ባለቤት ጁሊየት ቼክዌል እንዲሁም የሶስት ጊዜ የሮም ማራቶን አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ራህማ ቱሳ በቫሌንሲያው ፉክክር ከተካተቱ ጠንካራ አትሌቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014