አገርን ለመደገፍ የተለያየ መንገድን መከተል ግድ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ ሠላማዊ ሰልፍ ነው፤ ይህም ሁለት መስመሮችን ይይዛል። የመጀመሪያው ጠላትን በተቃውሞ ማውገዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው በመኖርና በመተግበር ለአገር መቆምን ማሳየት ነው። ዛሬ ደግሞ ይህ ነገር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጊዜ እንደሆነ በደንብ ይታመናል። ሰዎችም ከውጪም ከውስጥም የሚነሳውን የጥላቻ ስብከት ለመቃወም በየፊናቸው የወጡት ለዚህ ነው።
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የዓለምን ሁለንተናዊ ሠላም እና እድገትን ለማረጋገጥ በሚል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ህብረቶች ተቋቁመዋል። የዓለም ማህበር ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን የእነዚህ ህብረቶች መስራች የሆኑ አገራት ሳይቀር የሠላም ጠንቅ ሆነው ሲንቀሳቀሱ የመታየታቸው እውነታ ነው።
አብዛኞቹ የሰው ልጅ ሠላምና ደህንነት ሳይሆን አገራዊ ጥቅማቸውን በማስቀደም በአገራት የውስጥ ጉዳዮች ሳይቀር ጣልቃ በመግባት ግጭት አባባሽ ናቸው። ለዚህም አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ታላላቅ አገራት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ሰብዓዊ መብትና በሌሎችም ትርጉም አልባ ምክንያቶች የአገራትን ሠላምና መረጋጋት ሲያፋልሱ ይስተዋላሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። አገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ብዙም ሰላም ያልሰጣቸው እነዚህ አገራት፤ ከአሸባሪው ሕወሓት የጥፋት መንገድን ጋር ተቆራኝተዋል። በመደገፍም የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት ፤ ከዛም ባለፈ ሕልውናዋን ስጋት ውስጥ በሚጨምር የተናበበ የጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገኛሉም።
አገራቱ በተለይም አሜሪካ የአገር ነቀርሳ የሆነውን የአሸባሪው ሕወሓት ተፈጥሯዊ ሞት ለመቀልበስ በብዙ መልኩ ከቡድኑ ጋር ሰልፈኛ ሆናለች። የቡድኑን የሽብር ተግባሮች እንዳላየ ከማየት ጀምሮ በመንግሥት ላይ ያልተገቡ ጫናዎችና ማስፈራሪያዎች እስከ ማሰማት ድረስ የሚደርሱ ተግባራትን ታከናውናለች።
መንግሥት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን በአሸባሪው ቡድን ላይ ሲወስድ ከፍ ባሉ ጩኸቶች ዓለም አቀፍ መድረኮችን ማጣበብ፤ ቡድኑ ስኬታማ የሆነ ሲመስላት ደግሞ ዝምታን በመምረጥ ግልጽ የሆነ ድጋፏን ለአሸባሪው ቡድን በመስጠት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ የሽብር ተግባር ጋር ያላትን አጋርነት ታሳያለች።
ከዚህም ባለፈ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር አሸባሪውን ሕወሓት ለማትረፍ በተመሳሳይ መንገድ ከተቋቋመበት መርህ ወጥቶ ለቡድኑ ወገንተኛ የሆኑ ተግባራትን ሲያከናውን ይታያል። በግጭት አካባቢዎች ዙሪያ የተዛቡ መረጃዎችን ከመልቀቅ ባለፈ በተቋሙ ሠራተኞች በኩል ለቡድኑ የተለያየ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ በብዙ መረጃ ተጋልጧል።
አሸባሪው ቡድን በአፋር እና በአማራ ሕዝቦች ላይ የእብሪት ወረራ ፈጽሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ ችግርና መፈናቀል በትግራይ ክልል ብቻ እንዳለ አድርጎ በማየት ተገቢውን እርዳታ ለተጎጂ ዜጎች ለማቅረብ ዳተኛ ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ከዚህ ዳተኛነቱ አልወጣም። በተለይ አሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ከአሸባሪው ሕወሓት ጎን ሆነው ስለ ሠላምና የሕዝብ ደህንነት የሚያወሩት ወሬ በብዙ መልኩ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ነው። ይህ ደግሞ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣሊያንን ከማውገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረውን ያልተገባ ተጽዕኖ ያስታውሰናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ወራሪን ያሳፈርነው በማህበራዊ እሴቶቻችን በተገነባ አንድነት እና ከዚህ በሚመነጭ የአትንኩኝና አይበገሪነት መንፈስ ነው። ይህ መንፈስ ዛሬም በዚህም ትውልድ ውስጥ ህያው ነው።
ዓለም ገና ሳይሰለጥን እኛ ወደ ላይ ከፍ እንበል ስንል ከአንድ ድንጋይ አክሱምን ያነጽን፤ ሲያሻን ከዓለም በተቃራኒው ከላይ ወደታች የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የፈለፈልን እንደሆንንም ታሪካችን በተጨባጭ ምስክር ነው። ሰለጠንን ያሉ እንደቅርጫ እጣ ተጣጥለው ዓለምን ለመቆጣጠር በየፊናቸው ሲሰማሩ እኛ ለማንም አንገታችንን ያልደፋን መሆናችንን መገንዘብ ይቻላል። አሁንም አንደፋም ቀና እንዳልን እንቀጥላለን። ሰሞኑን በመላው አገሪቱ ሕዝባችን በሠላማዊ ሰልፎቹ እያረጋገጠ ያለው ይህንኑ ነው።
አውሮፓውያን በየዘመኑ ማንነታችን የሚበርዙ የተለያዩ የሴራ ተግባራትን አድርገዋል፤ አሁንም እያደረጉ ነው። መጀመሪያ መልካም መስለው መርዛማ ሴራቸውን በዜጎቻችን ላይ ይረጫሉ። ያ ካልተሳካላቸው ከውስጥ ጠላትን ማስነሳት ላይ ያተኩራሉ። ይህ ሳይሆንላቸው ከቀረ ደግሞ ባንዳዎችን ሰብስበው ስልጣን ይሰጡና በእኛና በእኛ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጪ ይሆናሉ። ባለፉት 27 ዓመታት ሲያደርጉትም የነበረው ይህንኑ ነበር። የአሸባሪው ሕወሓት የሥልጣን ዓመታት ለእነርሱ ምቹ ነበርናም ምንም ሳይሉ እንዲቆዩ ሆነዋል። አሁን ግን እኛ ለራሳችን ወሳኝ ነን ሲባሉ በትራቸውን አነሱ።
አሁን የቀደመ ሥራቸውን ማስቀጠል አትችሉም፤ እጣ ፋንታችንን የምንወስነው እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም ስንላቸውም በሰብዓዊ መብት እና በእርዳታ ስም የተለያዩ ሴራዎችን እየጎነጎኑብንም ይገኛሉ። በዓለም አቀፍ መድረኮችና በሚዲያዎቻቸው ጭምር ዘመቻ ከፈቱብን። ለወትሮው የሕጻናት መብት ይከበር እያሉ የሚጮሁ፣ ከእኛ በላይ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ላሳር የሚሉ ነበሩ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃኖች። ነገር ግን በአማራ እና በአፋር ክልል የሕጻናት እና የእናቶች ደም በሽብርተኛ ቡድኑ እንደጎርፍ ሲፈስ ዝምታን መረጡ።
አገርና ሕዝብን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥትና የመከላከያ ሠራዊቱ ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ተልዕኮዋቸውን ከማጠልሸት ጀምሮ ለአሸባሪው ወታደራዊ ድጋፎችን እስከመስጠት የደረሰ ጣልቃ ገብነት ፈጸሙ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከራሱ በላይ ሆኖ ለመታየት የማያደርጉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ አሁን መላው ሕዝባችን ከትናንት ታሪኩ ብዙ ተምሯል። ከራሱ በላይ ስለራሱ የሚያስብለት እንደሌለ በተጨባጭ ተረድቷል። የዘገየ ቢመስልም በቁጥርም በአይነትም መብዛቱ ውበት እንደሆነ ገብቶታል።
አንተ ተቃዋሚ እኔ ደጋፊ እያለ እርስ በርስ ከመጠላለፍም እየወጣ ይገኛል። መደጋገፉ አገር እንደሚያሻግርና ከችግር እንደሚታደግም ተገንዝቧል። ለችግሮቹ መፍትሄው እሱ ራሱ እንደሆነ ነጋሪ በማያስፈልገው ደረጃ አውቋል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ሰሞኑን በየአቅጣጫው እየተደረገ ያለው የተቃውሞ ሰልፍና ዘመቻውን የመቀላቀል ሥራ ነው።
ለምዕራባውያን የከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት የ27 ዓመታቱ የአሸባሪው ሕወሓት አገዛዝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በኢትዮጵያ ውስጥ የልዩነት ፍሬም አፍርቷል። በዚህም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ሴራው በለውጡ አማካኝነት ሊከሽፍ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ጫካ በመግባት ኢትዮጵያን ዳግመኛ የማፍረስ አላማ ተጀምሯል። ይህም አጋጣሚ የመጠበቅ የምዕራባዊያኑ እኩይ ሴራ እንደሆነ ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ተገንዝበውታል። በአሁኑ ወቅት የምዕራቡ ዓለም በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ እያሳየ ያለው ከፍ ያለ ጣልቃ ገብነትንም በደንብ ነቅቶበታል። በዚህም በሚችሉትን ሁሉ አገር በማፍረስ እኩይ ተግባር ላይ ላለመሳተፍ ወስኖ አገሩን እየጠበቀ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የገባችበት ጦርነት ፈልጋው ሳይሆን ተገዳ እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ቡድኑ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን በሠላማዊ መንገድ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ እንዲሰራ በብዙ መንገድ ተለምኗል። መንግሥት ለጀመረው የልማት እና የብልጽግና ጎዳና እንቅፋት እንዳይሆንም ተማጽኖ ጭምር ተደርጎለት እንደነበረ ይታወሳል። ነገር ግን ቡድኑ ከተዛባ የኃይል አሰላለፍ ስሌት ባለፈ እብሪት እና ከምዕራባውያኑ እያገኘ ባለው አይዞህ ባይነት አገርና ሕዝብን ስጋት ውስጥ በሚጨምር የሽብር ተግባር ውስጥ ተዘፍቋል። ለሕዝባችን ፈተና ሆኗልም።
አሁን ያለው የሕዝቡ ፈተና እና ትግል በታሪኩ ተሻግሮ ከመጣቸው የሚያንስ እንጂ የሚበልጥ ባለመሆኑ አሸናፊነቱ አያጠያይቅም። ይህ ፈተና እልህ አስጨራሽ ቢመስልም ሕዝቡ በጽናት የሚሻገርበት፤ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር አቅም የሚፈጥርበት እድልን የሚያገኝበት እንደሚሆን ይታመናል። ይህም እውን ሆኖ በቅርብ እናየዋለን። ድል ኢትዮጵያዊያና ለሕዝቦቿ!
መንበረ ልዑል
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014