በስፖርት ታሪክ ለውጥና እድገት የታየበት ጊዜ እአአ በ1980ዎቹ መሆኑን የታሪክ ማህደሮች ያስነብባሉ፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት በዚሁ ወቅት የተሻሉ እንቅስቃሴዎች የታዩ ሲሆን፤ እአአ 1983 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መካሄድ ጀመረ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በተካሄደው ኦሊምፒክ ደግሞ በበርካታ ስፖርቶች ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ፈቃድ አገኙ፡፡ ሴቶች የሚሮጡባቸው ርቀቶች ከ1ሺ500 ሜትር እንዳያልፍም ተደርጎ ነበር፡፡ ታዲያ በእነዚህ ገደቦች ውስጥ ተሳትፋ ውጤታማ የሆነች፤ በኋላም ለሴቶች ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጥረት ያደረገች አንዲት ሴት በታሪክ ትነሳለች፡፡
ይህቺ ሴት ግሬቴ አንደርሰን የምትሰኝ ሲሆን እአአ በ1953 በኦስሎ ከተማ ነው የተወለደችው፡፡ የልጅነት ጊዜዋን ከሁለት ታላላቅ ወንድሞቿ ጋር በማሳለፏ ምክንያትም ነገረ ስራዋ ሁሉ የወንዶችን ይመስል ነበር። በጨዋታ ወቅት ወንድሞቿ አባረው የማይዟት ፈጣን ስትሆን፤ እያደገች ስትሄድ የሩጫ ዝንባሌ እንዳላት ተረዳች፡፡ በመሆኑም በሜዳ ተግባር አሊያም በመም ሩጫ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ለቤተሰቦቿ አሳወቀች፤ ነገር ግን ያገኘችው ምላሽ ‹‹አይሆንም›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ሳትገደብም በ13 ዓመቷ የአትሌቲክስ ክለብን ተቀላቀለች፤ ከአራት ዓመታት በኋላም በሃገር አቀፍ ውድድሮች መሳተፍ ቻለች፡፡ በወቅቱም ቤተሰቦቿ ችሎታዋን በመቀበል ድጋፍ ማድረግና ማበረታታት ጀመሩ፡፡
በሙኒክና ሞንትሪያል ኦሊምፒኮችም ሃገሯ ኖርዌይን በመወከል በ800 ሜትር እና በ1ሺ500 ሜትር ርቀቶች ተወዳዳሪ ነበረች፡፡ በወቅቱ ሩጫ እንደ ስራ ባለመታየቱ አብዛኛዎቹ አትሌቶች በመደበኛነት ሌሎች ስራዎች ላይ ማተኮራቸው ውጤታማነታቸው ላይ ችግር ያስከትል ነበር፡፡ እርሷ ግን ጃክ ዌይትዝ ከተባለው አሰልጣኟ ጋር በትዳር በመጣመሯ የተሻለ ስልጠና እና ዝግጅት እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ ይሁን እንጂ እአአ 1976 የሞንትሪያል ኦሊምፒክ ከተካፈለች በኋላ የአትሌቲክስ ስፖርት ተሳትፎዋ እንዳበቃ በይፋ አስታወቀች፡፡ ይሁንና ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ውድድር ተመልሳ በ3ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ በምትታወቅበት 1ሺ500ሜትር ደግሞ አምስተኛ ደረጃን፣ በአውሮፓ ቻምፒዮና ካገኘች በኋላ ዳግም ‹‹ውድድር በቃኝ›› ማለቷ ተሰማ፡፡
የባለቤቷ ጓደኛ የሆነ ሰው ግን በኒውዮርክ ማራቶን እንድትሳተፍ ጥሪ ባቀረበው መሰረት በብቃቷ የሚተማመነው አሰልጣኟና ማናጀሯ ጃክ በዚህ ውድድር እንድትሳተፍ ግፊት አደረገ፡፡ ሴቶች እምብዛም በማይሳተፉበት ረጅሙ ርቀት ለመሳተፍ የወሰነችው ግሬቴ የመጀመሪያ የጎዳና ላይ ውድድሯ በመሆኑ በራስ የመተማመን ስሜቷ ተሸርሽሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር የረገጠችው በርካቶችን አስከትላ በቀዳሚነት ነበር፡፡ ይህ ያልጠበቀችው ውጤታማነት ክብረወሰንን በመስበር (02፡32፡30) ጭምር የታጀበ ቢሆንም፤ ደስተኛ አልነበረችም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውድድሩ ረጅምና እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሲሆን፤ በድጋሚ ማራቶን ላለመሮጥ ለባለቤቷ በንዴት ስሜት ቃል ገብታለትም ነበር፡፡
ከድሏ በኋላ በርካታ መገናኛ ብዙሃን የፊት ገጽ እንዲሁም እንግዳ ብትሆንም ግሬቴ ግን በድጋሚ ውድድር ማቆምን እያሰበች ነበር ወደ ሃገሯ የተመለሰችው፡፡ ሴቶች ባልተለመዱበት በዚህ ውድድር ክብረወሰንም ጭምር መሻሻሉ የብዙዎችን አይን ሲገልጥ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የአትሌቲክስ አወዳዳሪ ድርጅቶች በበኩላቸው ተሳታፊ እንድትሆን ግብዣ ያደርጉላትም ነበር፡፡ ሩጫን ማቆም የምትፈልገው ግሬቴም ለስፖርቱ ያላት ፍቅር ሚዛን በመድፋቱ ከዚያን በኋላ በተካሄዱ 47 ውድድሮች ተሳትፋ በበርካቶቹ አሸናፊ ለመሆን በቃች፡፡ በኒውዮርክ ያስመዘገበችውን ሰዓትም በማሻሻል 2:27:33 ስትገባ፤ ማራቶንን ከ2ሰዓት ከ30 ደቂቃ በታች የሮጠች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት በሚል ስሟ ከክብር መዝገብ ሰፍሯል፡፡
ይህ ስኬቷም ከራሷ አልፎ በዓለም ላይ ለውጥ በማስከተሉ እአአ በ1980ዎቹ የታዩትን ስፖርታዊ እድገቶችና ለውጦች ለማምጣት በቃ፡፡ አትሌቲክስም የተጨማሪ ጊዜ ሳይሆን መደበኛ ስራ ሲሆን፤ ግሬቴ ዳግም ሃገሯን ወክላ በኦሊምፒክ መድረክ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቃች፡፡ የሴቶች አትሌቲክስ ዋስና ጠበቃ የሆነችው ግሬቴ የመጀመሪያዋ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮን ስትሆን፤ በኒውዮርክ ማራቶን ለዘጠኝ ጊዜያት አሸናፊ እንዲሁም በመላው ዓለም ላሉ ሴት አትሌቶች ተምሳሌትም ናት፡፡ በሃገሯም ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የ5ኪሎ ሜትር ውድድር በማዘጋጀት አስደናቂ ውጤት ያገኘች ሲሆን፤ ከጊዜ በኋላ በሁለቱም ጾታዎች እንዲሮጥ በማድረግ የውድድሩን ተወዳጅነት እንዲጨምር አድርጋለች፡፡ እአአ 2005 በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቷ እስካለፈበት ዕለት ድረስም ህይወቷ ከሩጫ የተነጠለ አልነበረም፡፡ ይህ አትሌቷ ለስፖርቱ ያደረገችው አስተዋጽኦም የዓለም አትሌቲክስን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ እንድትታወስና ስሟም ከመቃብር በላይ እንዲውል አድርጓታል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም