በተለያዩ ዓለማት በሚገኙ ታላላቅ ክለቦች፣ የእግር ኳስ አካዳሚዎችና ማሰልጠኛ ማእከሎች በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በእግር ኳስ ዙሪያ ይገኛሉ። እነዚህን ተጫዋቾች ከያሉበት መልምሎ በየደረጃው ለሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወቱ ማድረግ የስፖርት ቤተሰቡ የሁልጊዜም ጥያቄና ምኞት ነው።
ይህን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ ተጫዋች ዴቪድ በሻህ አሁን በጀርመን አገር እየሰራ ከሚገኘው የተጫዋቾች ወኪልነት ሥራው ጎን ለጎን በራሱ ተነሳሽነት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ከያሉበት ዓለም በማፈላለግ፣ አድራሻቸውን በመያዝና ግንኙነቶችን በመፍጠር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ፍቃደኝነታቸውን እያረጋገጠ ይፋ ሲያደረግ ቆይቷል።
የዴቪድ በሻህ ጥረት በቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ይሁን በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በተለይም ፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ ጅራና ዋና ጸሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኖች የሚካተቱበትን መንገድ ለማመቻቸት ትልቅ ተነሳሽነት በማሳየትና የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ አበረታች ሥራዎችን ሲሰሩ ነበር። የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድናቸው ለማካተት ፍላጎት ማሳየት የጀመሩት ኢትዮጵያ ባለፈው ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድርን ባዘጋጀችበት ወቅት ነው።
ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ለማሰለፍ ትልቁ እንቅፋት የሆነው ኢትዮጵያ የጥምር ዜግነትን የማትፈቅድ አገር መሆኗ ቢሆንም ፊፋ ለመሰል ችግሮች መፍትሄ እንዲሆን የስፖርት ፓስፖርትን መላ መዘየዱ ይታወቃል። በዚህም ተጫዋቾች ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ ለትውልድ አገራቸው የሚጫወቱበት እድል ተፈጥሯል። ይህን እድል ለመጠቀም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የጀመሩት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ግን እስካሁን ፍሬ አፍርቶ አልታየም። እንዲያውም ጉዳዩ በጅምር እንደቀረና እንደ አጀማመሩ መዝለቅ ሳይችል በችልታ እየታየ እንደሆነ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ብሔራዊ ቡድኑን በተመለከተ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድናቸው የማካተት ጉዳይ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ካሉ አሰልጣኙ አሁንም በራቸው ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል። “በሬ ክፍት ነው፣ በዚህ ጉዳይ የሕጋዊነት ጥያቄ መነሳቱም አይቀርም፣ መንግሥት ይፈቅዳል ወይ? ተጫዋቹስ ለኛ ለመጫወት የያዘውን የጀርመንና የእንግሊዝ ፓስፖርት ቀዶ ለመምጣት ይፈቅዳል ወይ?፣ የሚለው ጥያቄ ራሱ ምላሽ ያስፈልገዋል” በማለት አሰልጣኙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አሰልጣኙ ይህን ይበሉ እንጂ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ ለመጫወት የግድ የያዙትን የሌላ አገር ፓስፖርት መቅደድ እንደማይጠበቅባቸው ፊፉ የስፖርት ፖስፖርትን አሰራር ማምጣቱ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ችግር አለ ተብሎ አይታሰብም። ምናልባትም ችግሩ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተያያዘ ከሆነም አሰራሮችን ፈትሾ እድሉን መጠቀም እንደሚያስፈልግ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው።
ምናልባትም ኢትዮጵያ በቀጣዩ ጥር በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነ ለመቅረብ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በመጠቀም በቀሪዎቹ ጊዜዎች እድሎችን ማመቻቸት ቡድኑ ያለበትን በርካታ ክፍተቶች ሊደፍን እንደሚችል ይታመናል። ለዚህም አሰልጣኝ ውበቱ አሁንም ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በራቸውን ክፍት ማድረጋቸው የሚበረታታ ነው። አሰልጣኙ በመግለጫቸው “በአሰልጣኝነት ታሪኬ ክለብ ስቀይር አንዱን አፍርሼ ሌላውን የገነባሁበት ታሪክ የለኝም” ያሉ ሲሆን ባለፉት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጋና ጋር ካደረጉት ጨዋታ በላይ በዚምባቡዌው ጨዋታ ቡድናቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተለይ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ኳሷን በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በማድረግ የመጫወት ዕድል መፍጠራቸውን በማስታወስ፣ ይሄም ለውጥ እንደሆነ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ‹‹ለአፍሪካ ዋንጫው ሊጉ የሚዘጋልንና የመዘጋጃ ቀን የሚሰጠን ወደ 12 ቀን ቢሆን ነው፣ ጊዜው ቢያጥርም ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት በምንፈልገው ደረጃ ለመዘጋጀት እንሞክራለን፣ ከውድድሩ በፊትም ወደ 3 የሚጠጉ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግም አቅደናል›› ሲሉ ተናግረዋል።
ስለ ቡድኑ ጨዋታ እቅድ የተጠየቁት አሰልጣኙ ‹‹ይሄ የጨዋታ መንገድ የብሄራዊ ቡድኑ መገለጫ ነው ተብሎ የተቀመጠ የጨዋታ ሞዴል የለንም፣ ስመጣም አላገኘሁም ስንመጣም የጨዋታ ሞዴል እንዲኖረው እንሰራለን ያልኩት ለዚህ ነው፣ ከዚያ ውጪ በኃላፊነት ላይ የነበሩ አሰልጣኞቹ ጨዋታ ሞዴል አልነበራቸውም አላልኩም፣ ይሄ መስተካከል አለበት›› ሲሉም በአጽንኦት አሳስበዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014