እያንዳንዱ ሰው አንዳች የተለየ ተሰጥኦና ልዩ ልዩ የፈጠራ ችሎታ እንዳለው ይታመናል። ይሁንና ብዙዎች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ጸጋ ሳይረዱት ቀርተው አልያም መንገድ አጥተው ሲባክኑ ይስተዋላል። አንዳንዶች ደግሞ ገና በጠዋቱ መክሊታቸውን የሚያሳይ የጠራ መንገድ ያጋጥማቸውና ለነብሳቸው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ‹‹መክሊቴን አገኘሁ›› ሲሉም ይደመጣሉ ። በርካቶች ግን ከነብሳቸው ጥሪ ውጭ በሆነው መንገድ በድካም ጉዞ ሲዝሉ ይስተዋላል።
በዛሬው የስኬት አምዳችንም የነብስ ጥሪዋን አግኝታ በሕይወቷ እጅግ የሚያስደስታትን ሥራ በመሥራት ውጤታማ ስለሆነች ባለሙያ የሥራ እንቅስቃሴና የሕይወት ተሞክሮ ልናስቃኛችሁ ወደናል። እንግዳችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ወላጅ አባቷ ምክንያት እንደሆኗትና ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ስትናገር ‹‹አባቴ የሚሠራውን ሥራ ዕለት ዕለት መመልከትና መሞከር መቻሌ ተሰጥኦና ፍላጎቴን በቀላሉ መረዳት እንድችልና ውጤታማ እንድሆን አስችሎኛል›› ትላለች።
በልብስ ስፌት ሙያ ከሚተዳደሩት ወላጅ አባቷ የተገኘችው የዕለቱ እንግዳችን የሽርሽር ኢትዮጵያ መስራችና ባለቤት ሂሩት ዘለቀ ናት። የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን አምርታ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ሂሩት ትውልድና ዕድገቷ አዲስ አበባ ከተማ ነው። በትምህርት ደረጃዋም ከተግባረዕድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በዲፕሎማ ተመርቃለች። በልጅነት ዕድሜዋ ወላጅ አባቷ የወንዶች ሙሉ ልብስ ሲሰፉ እየተመለከተች አድጋለች። ከመመልከት ባለፈም ከአባቷ ሥር ሥር እየሄደች የወዳደቁ ጨርቆችን በመሰብሰብ ቆራርጣ ትሰፋ ነበር። በዚህ ጊዜም ዝንባሌዋ እንደሆነ የተረዱት አባቷ የፈለገችውን ሁሉ በነጻነት እንድትሰራ ፈቃድ ይሰጧት እንደነበር ታስታውሳለች።
ከትምህርት ጊዜ ውጭ በነበራት ትርፍ ሰዓት ሁሉ በስፌት ሥራው ወላጅ አባቷን ለማገዝ የምትታትረው ሂሩት፤ ከሌሎች ወንድም እህቶቿ ይበልጥ ለሙያው ትኩረት ትሰጥ ነበር። በመሆኑም ሙያውን ይበልጥ ማዳበር በመቻሏ ለራሷና ለእህቶቿ የተለያዩ አልባሳትን መስፋት ጀመረች። በዚህ ጊዜ ከእሷ በላይ ለፋሽን ዲዛይን ሥራ ቅርብ መሆኗን የተረዱት ወላጅ አባቷ የዲዛይን ትምህርት ቤት ገብታ እንድትማር አድርገዋል።
መደበኛ ትምህርቷን እንደጨረሰችም ዲዛይን ትምህርት ቤት ገብታ ትምህርቷን ተከታትላለች። ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት የኖረ ሙያ በመሆኑም በቀላሉ መላመድና አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ቻለች። በዚህ ጊዜ ታድያ መምህሯ እጅግ ይደሰቱባት እንደነበር የምታስታውሰው ሂሩት፤ በአንድ ዓመት የትምህርት ጊዜ ውስጥ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቀች ። ዕውቀት ችሎታዋን ያደነቁት መምህሯም በተመረቀች ማግስት በትምህርት ቤት ውስጥ የዲዛይን ትምህርት እንድታስተምር ጥያቄ ያቀረቡላታል። ነገር ግን በወቅቱ የማስተማር ፍላጎት አልነበራትምና ጥያቄያቸውን አልተቀበለችም።
ምንጊዜም ቢሆን ተሽሎ መገኘት ዋጋ አለውና ሌላ ዕድል ጠራት ። በዘርፉ ተሰማርተው መሥራት የሚፈልጉ ኮሪያውያን ወደ ኢትዮጵያ መጡ ። ኮሪያኖቹ በዲዛይን ሥራ የተሻለ ዕውቀትና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ሲፈልጉ ሂሩትን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችም ከኮሪያኖች ጋር የመሥራት ዕድል አጋጠማቸው ። ይህ አጋጣሚ ለሂሩት ትልቅ ዕድል ሆኖ በርካታ ልምዶችን መቅሰም ችላለች። ከልብስ ዲዛይን በተጨማሪ ጫማን ጨምሮ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት የሚያስችል ሥልጠናዎችን አገኘች።
ካገኘችው ዕውቀት በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ደንበኞችን የመተዋወቅና ልምድ የመለዋወጥ ዕድል አጋጥሟታል። በአምስት ዓመት የጊዜ ቆይታዋም ወደ ድርጅቱ ከሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች የተለያዩ ልምዶችን በመቅሰም ክህሎቷን ማዳበር ችላለች ። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ በመሆናቸውም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ናቸው። በዚህ አጋጣሚ የውጭው ዓለም ምን እንደሚፈልግና በምን ያህል ጥራት ተመርቶ ለገበያ መቅረብ እንዳለበት የማወቅ አጋጣሚ ተፈጠረላት። በመሆኑም ሥራውን ይበልጥ እየወደደችውና ውጤታማ እየሆነች መጣች።
ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላም ተፈላጊነቷ ጨምሮ በኢትዮጵያ ፋሽን ሾው ማሳየት ከፈለጉ ጃፓኖች ጋር አብሮ የመሥራት ዕድል አጋጠማት። አብረዋቸው መሥራት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን ሲመርጡም ሂሩት ቀልባቸውን ከገዙ ባለሙያዎች አንዷ በመሆን ተመራጭ ሆነች። በወቅቱ ለቁጥር የበዙ ሥራዎችን ከጃፓኖች በመቀበል የተለያዩ ዲዛይኖችን ሰርታለች። ሥራውን ከልብ በመነጨ ስሜት ወዳው መሥራት በመቻሏ ብዙ ዕውቀት ያገኘችበት ሲሆን፤ የጠበቀችውን ያህል ክፍያ ግን አላገኘችም። ይሁንና በወቅቱ ከፍተኛ ግምት ሰጥታ በጉጉት የምትጠብቀው የሥራውን ውጤት እንጂ ገንዘቡን አልነበረምና አልተከፋችም።
እንዲህ እንዲህ እያለች ከውጭ አገር ዜጎች ጋር በመሥራትና ሥልጠና በመውሰድ በርካታ ዕውቀት የቀሰመችው ሂሩት፤ አንድ ማሽን በመኖሪያ ቤቷ በማስቀመጥ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን በግሏ ማምረት ጀመረች። ያመረተቻቸውን ምርቶችም በተለያዩ ባዛሮች ላይ የማቅረብ ዕድል ስታገኝ ደንበኞቿም የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ሆኑ። በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም የኢትዮጵያን የቆዳ ውጤቶች በተለይም የበግ ቆዳ ለስላሳና ጠንካራ በመሆኑ ከበግ ቆዳ የሚሰሩ አልባሳትን ይመርጣሉ።
ከተለያዩ ባዛሮች ላይ ያገኘቻቸው ደንበኞች የሰጧትን ትዕዛዝ በመቀበል ሌሊቱን ጨምራ በማምረት ደንበኞቿ ባሉበት ቦታ ሁሉ ታደርሳለች። ምክንያቱም ደንበኞቿ እሷ ጋር መድረስ አይችሉምና በኤምባሲ፣ ባረፉበት ሆቴልና በሚሰሩበት መስሪያ ቤቶች ሁሉ በመሄድ ያመረተችውን ምርት ተዘዋውራ ታስረክባለች። ተጨማሪ ትዕዛዝም ትቀበላለች። በዚህ ጊዜ ሥራው እየሰፋ ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ ብቻዋን የምትዘልቀው እንዳልሆነ ተረዳች። አንድ ሁለት እያለችም ሠራተኞችን መቅጠርና ከቤት ወጣ በማለት የማምረቻና የመሸጫ ቦታ መከራየት የግድ ሆነባት።
ለዓመታት ልምድና ዕውቀትን እየሸመተች በቆየችበት የዲዛይንና የቆዳ ውጤቶች ሥራ ሽርሽር ኢትዮጵያ በሚል የንግድ ስያሜ የግል ድርጅቷን በ2000 ዓ.ም ያቋቋመችው ሂሩት፤ የድርጅቷን ስያሜ ሽርሸር ያለችበት ምክንያትም በመኖሪያ ቤቷ የምታመርተውን ምርት ደንበኞቿ ባሉበት ቦታ ሁሉ ተዘዋውራ የምታደርስ በመሆኑ ነበር። በከፍተኛ ፍላጎትና ድካም የምትሰራው ሂሩት፤ ሽርሽር ኢትዮጵያን በአምስት ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ነገር ግን በከፍተኛ ጉጉትና በጥልቅ ዕውቀት ሥራውን ጀመረች።
ወደ ሥራው በገባችበት ወቅት በዘርፉ ውጤታማ እንደምትሆን ሙሉ ዕምነት የነበራት በመሆኑ መነሻ ካፒታሏ አላሳሰባትምና ፒያሳ ላይ መሸጫ ሱቅ ተከራየች። በዚህ ጊዜ ምርቶቿን ተዘዋውራ ታስረክብ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ ደንበኞቿ በመሸጫ ሱቅ እየመጡ መውሰድ እንዲችሉ በማድረጓም ደንበኞቿ ከትዕዛዛቸው ውጭ የሆኑና የወደዱትን ምርቶች በመግዛታቸው ሌላ የገበያ ዕድል ተፈጠረላት። በተደጋጋሚ የውጭ አገር ዜጋ የተመለከተው አከራይም የቤት ኪራይ ዋጋውን ስላስወደደባት ይሄንኑ ያህል የቤት ኪራይ ከፍላ የተሻለ ባለችው ቦታ ላይ ለመስራት ወደ ቦሌ አካባቢ አቀናች።
ወደ ቦሌ ያቀናችው ሂሩት፤ ለደንበኞቿ ይበልጥ ቅርብ በመሆኗ ሌሎች ደንበኞችም ተጨማምረው ተጠቃሚነቷ ገዘፈ። በዚህ ጊዜ በቤቷ ውስጥ ከማምረት በተጨማሪ የማምረቻ ሱቅም እዛው ቦሌ በመከራየት በስፋት ማምረት ጀመረች። በዚህ ጊዜ ቀድማ በሥራ አጋጣሚ ያወቀቻት ጃፓናዊት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በመምጣቷ በጋራ የመሥራትና ምርቶቿን ወደ ውጭ አገር የመላክ እድል አገኘች።
እንዲህ እንዲህ እያለ የደራው ገበያ ሰፊ የማምረቻ ቦታ እንዲኖራት ሆነና ሙሉ ግቢ ተከራይታ በማምረት ለውጭ ገበያ ታቀርብ ጀመር። በወቅቱ ዩኒዶ የተባለ የውጭ ድርጅት በቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪ ባለሙያዎችን በማደራጀት ጎሮ አካባቢ የማምረቻ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓል። በመሆኑም ሂሩት ሽርሽር ኢትዮጵያ በተሰኘው ድርጅቷ ስም 80 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የማምረቻ ቦታ ያገኘች ሲሆን ሌሎቹም እንደ ዕድላቸው ሰፋፊ ቦታዎችን አግኝተው በአንድ አካባቢ ማምረት ጀመሩ።
‹‹እኛ አምራቾቹ ተደራጅተን በአንድ አካባቢ ማምረት መቻላችን ከፍተኛ ዕገዛ አድርጎልናል›› የምትለው ሂሩት፤ ለአብነትም በርካታ ትዕዛዞች ቢመጡ በጋራ መስራት፣ ልምድ መለዋወጥና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በጋራ ማቅረብና ሌሎችም ጥቅሞችን አግኝተናል። ድርጅቱ ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ባዛሮች ላይ መሳተፍ የሚቻልበትን ዕድል በማመቻቸት ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁና እንዲሸጡ አድርጓል። ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቀው የግለሰብ ቤት ኪራይ ውጭ በመሆን የማምረቻ ቦታ ማግኘት መቻሏ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ ያደረጋት መሆኑን ትናገራለች።
ሂሩት ከምታመርታቸው የቆዳ ውጤቶች መካከል ቦርሳ፣ ጃኬት፣ ቀበቶ፣ ዋሌቶች፣ የተለያዩ የስጦታ ዕቃዎችና ሌሎችም ይገኙበታል። 30 ለሚደርሱ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለች ሲሆን በተለያየ ጊዜም በኮንትራት ቀጥራ የምታሰራቸው ሠራተኞች አሏት። 15 የሚደርሱ መሥሪያ ማሽኖች ያሏት ሲሆን ምርቶቿንም በአብዛኛው ጃፓን፣ አሜሪካና ሱዲን ትልካለች። በዚህም የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማስገባት አበርክቶዋ የጎላ ነው።
የውጭ አገር ዜጎች የቆዳ ውጤቶችን አብዝተው ይፈልጋሉ የምትለው ሂሩት፤ በተለይም ከኢትዮጵያ በግና ፍየል ቆዳ የሚሰሩ አልባሳት በውጭው ዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊ ናቸው። ለዚህም ጥራታቸው ከሌሎች አገራት የተለየ በመሆኑ ነው። ይሁንና ከቆዳው ውጭ ያሉ አክሰሰሪዎች ማለትም ቁልፍ፣ ዚፕና መሰል ግብዓቶች ጥራት ያላቸውን መጠቀም ካልተቻለ በምርቱ ላይ ትልቅ ችግር የሚገጥም በመሆኑም ዚፕና ቁልፍ መጠቀም የማያስችል ዲዛይኖችን በመሥራት በዚፕ ምክንያት የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ እንደምትሞክርም ታስረዳለች።
‹‹የኤክስፖርት ምርት ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል›› የምትለው ሂሩት ጥራት ያላቸውን ግብዓቶች ከመጠቀም ጀምሮ ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች በማሳተፍና ሥልጠና በመስጠት ውብና ማራኪ የሆኑ የቆዳ ውጤቶችን ኤክስፖርት እንደምታደርግ ትናገራለች። ይሁንና ኤክስፖርት ላይ ጥቂት ስህተት ከባድ ኪሳራ ውስጥ ይከታል። ለአብነትም ቡኒ ቀለም አዘው ትንሽ ነጣ ካለ አይሆንም። ስለዚህ በከፍተኛ ጥንቃቄ ውስጥ ሆኖ በመሥራት ውጤታማ መሆን ይቻላል ትላለች።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ባዛሮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ያገኘች ሂሩት፤ ከዚህ ቀደም ፓሪስና ስፔን አቅንታ ምርቶቿን የመሸጥ እና ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ አጋጣሚም አግኝታለች። ባገኘችው አጋጣሚም በርካታ ደንበኞችን ለመሳብ ችላለች። ትዕዛዞችን ተቀብላ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን አምርታ ልካለች። በቅርቡም መሰል የውጭ አገር ባዛሮች ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ዓለም አቀፍ ሥጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድማ ከስፔን አገር በርካታ ትዕዛዞችን ተቀብላ እንደነበር ያስታወሰችው ሂሩት፤ በወቅቱ የቆዳ ውጤቶች የሆኑ የተለያዩ ምርቶች ተዘጋጅተው ወደ ስፔን አገር ለመላክ በዝግጅት ላይ እንዳለች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቶ ምርቶቹን ለመላክ አልቻለችም ነበር። ይህም በሥራዋ ከገጠሟት መሰናክሎች መካከል አንዱ እንደሆነ ትናገራለች።
ይሁን እንጂ ምርቶቹን አንድ ሁለት እያለች በአገር ውስጥ መሸጥ ችላለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያለውን የፋሽንና የቀለም ፍላጎት በመረዳት ለአብነትም የበጋ እና ክረምት ቀለሞችን በመለየት እንደየ አገራቱ ፍላጎት ወቅቱን የጠበቀ ምርት ወደ ውጭው ዓለም ይዛ ለመቅረብ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
የሕይወት አጋጣሚዎቿን ከውስጥ ፍላጎቷ ጋር በማቀናጀት ወደ ተግባር የቀየረችው ሂሩት፤ አጠቃላይ ካፒታሏ ስድስት ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በቀጣይም የቆዳ ውጤቶችን በኢንዱስትሪ ፓርክ ደረጃ በርካታ ማሽኖችን በማስገባት በስፋት ለማምረትና ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ አላት። በስፋት በምታመርተው ምርትም አገሯን የማስተዋወቅና ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ያላትን ምኞት ገልጻለች። ‹‹ሰዎች ደስ የሚላቸውንና ውስጣቸው ያለውን ፍላጎት ለማወቅና ለመረዳት ተስፋ ሳይቆርጡ ቢሞክሩ መልካም ነው›› የምትለው ሂሩት፤ በተለይም ወጣቶች ፍላጎታቸውን ማወቅ ከቻሉ ውጤታማ ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም፤ የትኛውም እንቅፋት ጉዟቸውን አያሰናክለውም በማለት ለወጣቶች ባስተላለፈችው መልዕክት አበቃን!
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014