ወይዘሮዋ የጅብ ድምጽ በሰሙ ቁጥር ልባቸው ይረበሻል። ሰውነታቸው ይርዳል። ሀሳባቸው እየተበተነ ዕንባ በአይናቸው ይሞላል። ድምጹ ሲደጋገም ይይዙት ይጨብጡት ያጣሉ። ይህ ድምጽ ለእሳቸው የተለየ ትርጉም አለው። ከማይሸሹት እውነት፣ ከማይተውት ሀቅ ያደርሳቸዋል።
ይህ ስሜት የወይዘሮዋ ብቻ አይደለም። የጅቡ ጉዳይ የመላው ቤተሰብ ችግር ነው። ሲጨላልም፣ ሲመሽና ሲነጋ ሁሉም በድምጹ ይረበሻሉ። ህጻናት ጭምር እንደ እናታቸው ይርበተበታሉ። ድምጹ እስኪርቅ፣ ዝምታ እስኪሆን ይጨነቃሉ። ተመልሶ አፉን ሲከፍት ደግሞ እንደ ወይዘሮዋ ይይዙት ይጨብጡት ያጣሉ።
አብሮ አደጎቹ
በከምባታ ጠምባሮ ዞን ቀዲዳ ጋሚላ ወረዳ ጆሬ ቀበሌ ውስጥ ነው። በዚህ ቀበሌ ጨቤ የተባለ ገጠር ይገኛል። በስፍራው በርካታ የአካባቢው ልጆች ህጻንነታቸውን በቡረቃ አሳልፈዋል። መክሊት ማሩና ዴቦ ማሴቦም የአካባቢው ፍሬዎች ናቸው። ሁለቱም ተወልደው ያደጉት በጆሬ ቀበሌ ጨቤ አካባቢ ነው። መክሊት ና ዴቦ በልጅነት ዕድሜቸው ቤተሰቦቻቸውን አገልግለዋል። ከብት አግደው፣ ውሃ ቀድተዋል። ከቤት ገብተው የታዘዙትን ከውነዋል።
ሁለቱ ታዳጊዎች በዕድሜ ከፍ ሲሉ አልተለያዩም። በወላጆቻቸው ይሁንታ ትምህርት ቤት ገብተው የቀለም ሀሁን ቆጠሩ። ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው እጅ ለእጅ ተያይዘው ወጥቶ መግባት ልምዳቸው ሆነ። አብሮ አደግነታቸው፣ በተለየ ያስተሳስባቸው ጀመር። ቅርበታቸውን ባልንጀራ መሆናቸውን ብዙዎች አወቁ።
ዴቦ ለመክሊት በእጅጉ ያስባል። እሷም ብትሆን ለእሱ ያላት ስሜት ከሌሎች ይለያል። ቤተሰቦቻቸው የሁለቱን መቀራረብ አይጠሉትም። ከልጅነታቸው አብሯቸው የዘለቀውን አንድነት ይወዱታል። የጨቤ ጎጥ ነዋሪም የልጆቹ ጓደኝነት አስጨንቆት አያውቅም። ቅርበታቸውን በበጎ ተርጉሞ ተቀብሎታል።
አሁን ሁለቱ ልጆች በእድሜ ጎልብተው፤ በዕውቀት ዳብረዋል። በትምህርት ዓለም የዘለቁበት ቆይታ ፍላጎታቸውን እያጣመረ ነው። ሁለቱም በቤተክርስቲያን ውለው መንፈሳዊ ትምህርትን ይቀስማሉ። እንዲህ መሆኑ ለቤተሰቦቻቸው ደስታን አጎናጽፏል። ወጣትነታቸውን ለዕምነታቸው ሰጥተው ለአምልኮ ማደራቸው አስከብሯቸዋል።
የዴቦ ፍላጎት በመንፈሳዊ መዘሙር ላይ ነው። ዘወትር ሙዚቃ መሳሪያዎችን እየተጫወተ በዝማሬ ያገለግላል። መክሊት ሁሌም ከአጠገቡ አትጠፋም። የሚዘምረውን እየተቀበለች፣ አብራው ታዜማለች። ሁለቱም በመንፈሳዊ ህይወታቸው በርትተው ዘለቁ። ዝማሬን ከአምልኮ አጣምረው በሰዎች ፊት ሞገስ አገኙ።
ዴቦ ከነመክሊት ቤት ጠፍቶ አያውቅም። ወንድሞቿ ጓደኞቹ ናቸው። በእናት አባቷ መወደዱ ቤተኝነቱን አጠናክሯል። ጠዋት ማታ በሚያዘወትረው ቤት እንግድነት አይሰማውም። አብሮ መብላት መጠጣቱ እንደልጅ አስቆጥሮት ባዕድነቱን ረስቷል።
የመክሊትና የዴቦ ወላጆች እንደልጆቻቸው ይቀራረባሉ። በሰፈርና በአምልኮ ስፍራዎች ሳይቀር በአንድ ይታያሉ። ይህ ጥምረት ሁለቱን ቤተሰብ አዛምዶ አብሮነትን አጠንክሯል። ወዳጅነታቸውን አጎልብቶ አንድነታቸውን አሳይቷል።
ሁለቱ ወጣቶች ዕድሜአቸው ሲጨምር ፍላጎታቸው ከወትሮው ተለየ። ዴቦ መክሊትን በስስት ዓይን ያስተውላት ጀመር። መክሊትም ለእሱ ያላት ስሜት እንደፊቱ አልሆነም። በሁለቱም ልቦና ወንድም እህት ይሉት እውነት ይሰረዝ፣ ይረሳ ያዘ። በተገናኙ ቁጥር ውስጣቸውን የፍቅር ስሜት ያግለው ጀመር።
የሁለቱ ወጣቶች ቤተሰብ አዲሱን ስሜት አልተረዳም። ወጣቶቹ በእነሱ ፊት ዓይን አይስቡም። ከቀደመው የተለየ ድርጊት የላቸውም። እንደፊቱ ሆነው ጊዜውን ይገፋሉ። እንደተለመደው ከአምልኮ ደርሰው ይመለሳሉ። ሰው ባላያቸው ጊዜ ድብቁ ፍቅራቸው ይወጣል። በናፍቆት፣ በሰስት ይተያያሉ። ከአካባቢ ርቀው ናፍቆት ስሜታቸውን ይወጣሉ።
የመክሊትና የዴቦ ትምህርት አልተቋረጠም። እሱ ዘጠነኛ እሷ ስምንተኛ ክፍል ደርሰዋል። ትምህርቱ ከፍቅራቸው ጎን በእኩል ይራመዳል። አንዳንዴ ወጣቶቹ አረፍ ብለው ስለወደፊቱ ያወጋሉ። ትምህርታቸውን ሲጨርሱ፣ ጋብቻን ያስባሉ፤ ልጅ ወልዶ መሳምን፣ ቁምነገር ማድረስን ይመኛሉ። በሁለቱም ልብ የተጸነሰው ፍቅር ነፍስ ዘርቶ ዕድሜው ጨመረ። ድብቁ ግንኙነት ከማንም ዓይንና ጆሮ አልደረሰም።
ሶስት ዓመታት የዘለቀው ፍቅር አሁንም በድብቅ ቀጥሏል። ዴቦ ከነመክሊት ቤት ሲመጣ ይጠነቀቃል። ከፍቅረኛው የተለየ ጨዋታ የለውም። እንደወትሮው ቆይቶ፣ ቁምነገር አውርቶ ይወጣል። የመክሊት ቤተሰቦች ዴቦን አስተናግደው፣ መልካም ሀሳቡን ተቀብለው ይሸኙታል።
ዴቦና መክሊት የጀመሩት የፍቅር ግንኙነት ከመሳሳም አልፏል። ሁለቱም ይህ ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን ያውቁታል። የወደፊቱ ዓላማና ዕቅዳቸው በዚህ ጉዳይ አብዝተው እንዲጨነቁ አልፈቀደም። አንድ ቀን በጋብቻ ተሳስረው ትዳር መያዛቸው አይቀሬ ነው። በዚህ ቀን ድብቁ ፍቅራቸው ገሀድ ሆኖ ቃልኪዳን ያስራሉ። ልጆች ወልደው ይስማሉ ።
ቅያሜ…
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መክሊትና ዴቦ መሀል ቅያሜ ገብቷል። ቀናት ያስቆጠረው ኩርፊያ በእርቅ አልተፈታም። ሁለቱም ሲተያዩ ፊታቸውን ያዞራሉ። ደፍሮ የሚያወራ ጨክኖ ጨዋታ የሚጀምር የለም። በሚገናኙበት የአምልኮ ቦታ የግላቸውን አገልግለው በዝምታ ይለያያሉ።
ዴቦ በኳየር ዝማሬ መሀል መክሊትን አሻግሮ ያያታል። መክሊትም በርቀት እያስተዋለች ፣ በዓይኖቿ የሚያቀራርብ፣ አልተገኘም። ሁለቱም በዝምታ ፣ በቅያሜ ዘልቀዋል።ኩርፊያው ቀናትን አልፎ ሁለት ወራትን ተሻግሯል።
መክሊት አሁን ጤና እየተሰማት አይደለም። መፍዘዝ፣ መጨናነቅ ጀምራለች። ሁሌም ማለዳ የሚታይባት ያልተለመደ ምልክት ይደጋግማት ይዟል። የበላችው አይረጋም፣ ዕንቅልፍ፣ ዕንቅልፍ ይላታል። ዝምታ ለቅሶና ሀዘን እየዞራት ነው። ወጣቷ የውስጧን ስሜት ማወቅ አልቸገራትም። ከዚህ ቀድሞ በእንዲህ አይነቱ ስሜት ባታልፍም እንድትጠራጠር ሆናለች። አዎ መክሊት ነፍሰጡር ናት፤ አርግዛለች።
ተማሪዋ መክሊት ይህን ለማረጋገጥ ሀኪም ዘንድ ቀረበች። የፈራችው አልቀረም። አስቀድማ የጠረጠረችው እርግዝና ዕውን ሆኗል። ቁርጡን ስታውቅ ጭንቀት ያዛት። ጠዋት ማታ በትካዜ አንገቷን ደፋች። በቅርብ የምታዋየው ሚስጥረኛ ባልንጀራ የላትም።
ከዴቦ ጋር ያላት ድብቅ ግንኙነት ማንም ጆሮ አልደረሰም። መክሊት በእጅጉ ከፋት፣ ደግማ ደጋግማ እያለቀሰች አዘነች። ይህን ስሜቷን እንደያዘች ለዴቦ አዋየችው። ዴቦ ፈጽሞ በእርግዝናው እንደማይሆን ገልጾ ጽንሱን ማስወረድ ግድ እንደሆነ ነገራት። እንዲህ መሆኑ በሁለቱ ልቦና ቅያሜ ፈጥሮ ቆየ።
ዴቦና መክሊት ሁሌም ከቤተክርስቲያኑ አምልኮ ይተያያሉ። እንደፊቱ ተገናኝተው፣ አያወሩም። እንደቀድሞው የራሳቸው ጊዜ የላቸውም። አሁንም በኩርፊያና ቅያሜ ዘልቀዋል። ቆይታው ሲጠናቀቅ ስርዓቱ ሲያበቃ ወደጉዳያቸው ይሄዳሉ። ይህ ጊዜ ለመክሊት ጭንቀት፣ ለዴቦ ማምለጫ ሆኗል።
መክሊት ሰሞኑን የሰማችው አዲስ ወሬ ከጭንቀቷ ተዳምሮ እየረበሻት ነው። ዴቦ ከሌላ ሴት ጋር ፍቅር ጀምሯል መባሉ አስደንግጧታል። ጉዳዩን ደጋግማ ስታስበው ተስፋ ትቆርጣለች። ቀን ይጨልምባታል። በፍርሀት ትርዳለች። ቤተሰቦቿን እያሰበች በእሷ ያላቸውን ዕምነትና ኩራት ትስለዋለች። የሆነው ሁሉ ያሸብራታል።
መለስ ብላ ከራሷ ስታወጋ አብረው የገቡት ቃል፣ የያዙት ዕቅድ ገዝፎ ይታያታል። ይሄኔ ዴቦ በእሷ እንደማይወሰልት፣ ፈጽሞ እንደማይክዳት ታምናለች። እንደገና መለስ ብላ ራሷን በማሳመን ትጽናናለች። ዴቦን ‹‹አናግሪው ፣በግልጽ አዋይው›› የሚል ቃል ሹክ ይላታል። ይህን ለማድረግ ትወስናለች።
አንድ ቀን መክሊት ለዴቦ ስልክ ደወለች። ዴቦ የእሷ ቁጥር መሆኑን ሲያውቅ አልዘጋወም። ስልኳን አንስቶ የምትለውን ጠበቀ። መክሊት ኩርፊያዋን ትታ ቅያሜዋን ረስታ ልታናግረው እንደምትሻ ነገረችው። ያለችውን አድምጦ በቀጠሮ ተለያዩ።
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም
ሁለቱ ወጣቶች በቀጠሮው ቀን ከተባባሉበት ስፍራ ተገናኙ። አካባቢው ጫካ የበዛበት፣ ቁጥቋጦ የወረሰው ሰዋራ ነው። ቦታው በሚስጥር ተገናኝቶ የልብን ለማውጋት ያግዛል። እነሱም ቢሆኑ ለዓመታት ከሌሎች ርቀው በድብቅ መሽገውበታል። ፍቅራቸውን፣ ናፍቆታቸውን ተወጥተውበታል።
ዛሬ ግን ይህን ለማድረግ አልተገናኙም። ኩርፊያና ቅያሜ በወረሰው ስሜት ጠልቀዋል። ከሰላምታ በኋላ ከአንድ ቦታ አረፍ ብለው ንግግር ጀመሩ። ዴቦ ጽንሱን እንዳስወረደችው እርግጠኛ ሆኗል። መክሊት በዝግታ ጨዋታውን ጀመረች። አሁንም እርግዝናው እንዳለና የታሰበውን መፈጸም እንዳልቻለች ነገረችው።
ዴቦ በንዴት ጋየ፣ በብስጭት ፊቱ ተቀየረ። እሷ የምትለውን ጨርሶ መስማት አልፈለገም። እየተናደደ፣ እየበሸቀ ፈጣን ምላሹን ሰጣት። በአስቸኳይ ጽንሱን እንድታስወርደው አስጠነቀቃት። መክሊት ይህን ስታውቅ በድንጋጤ ደርቃ ቀረች። ምላሹ አሁንም እንዲህ ይሆናል ብላ አልጠበቀችም። ውሳኔውን አልገመተችም።
ዴቦ የአካባቢውን ባህል የቤተሰብን ተጽዕኖ እያሰበ የተረገዘው ፈጽሞ መወለድ እንደሌለበት ወሰኗል። ውሳኔውን ለመተግበርም ይበጃሉ ወዳላቸው ሀኪም ቤቶች መክሊትን ሲያመላልስ ቆይቷል። የዛኔ እንዳልተሳካ ቢያውቅም እሷ እንደምትጨርሰው ተማምኖ ነበር።
ውሎ አድሮ የእርግዝናው ሚስጥር ከአንዳንዶች ጆሮ ደረሰ። ወሬው በዚህ ብቻ አልቆመም። ከሚያገለግሉበት ቤተክርስቲያን፣ ከጓደኞቻቸውና ከሌሎችም ተዳረሰ። ጥቂት ቆይቶም ቤተሰብ ጉዳዩን ሰማው።
መክሊት ይህን ሁሉ ጫና የምትሸከመው አልሆነም። አርቃ ስታሰበው በቤተክርስቲያን፣ በወላጆቿና በአካባቢው ሰዎች እንደምትጠላ ገባት። አሁን ከእሷ ብዙ ለሚጠብቁ ምላሽ የላትም። በድርጊቷ፣ በእሷ ላይ በሆነው ሁሉ አፍራለች። እናም ዴቦን በዛን ቀን ከአካባቢው፣ ተያይዘው እንዲጠፉ በመራር ለቅሶ ለመነችው፣ ተማጸነችው።
ዴቦ የመክሊትን ጉዳይ መቀበል አልቻለም። ሀሳቧን በሀሳቡ ተቃወመ። ደጋግሞም ጽንሱን እንድታስወርድ አሳሰባት፣ አስጠነቀቃት። ሁለቱ በተቃርኖ ሆነው ተሟገቱ። ጭቅጭቃቸው አየለ። ከመግባባት አልደረሱም። ጥቂት ቆይቶ ዴቦ ሌላ ሀሳብ አቀረበ። ተያይዘው ወደእሷ ቤተሰቦች እንዲሄዱና ጉዳዩን በግልጽ እንዲያስረዱ ጠየቃት።
መክሊት አሁንም ባመጣው ዕቅድ አልተስማማችም። ንግግሩ አላሳመናትም። ስሜቷን የተረዳው ዴቦ አሁን የሚገኝበትን አዲስ ህይወት አሰበው። ሌላ ፍቅረኛ ይዟል። በፍጹም ከእሷ መለየትን አይሻም። በመክሊት ሰበብ ጅምር ፍቅሩ እንዲገታ፣ አዲስ ህይወቱ እንዲደናቀፍ አይፈልግም።
መላልሶ በጉዳዩ አሰበበት። በአይምሮው የመጣው እውነት ሚዛን እየደፋ ነው። ዞር ብሎ መክሊትን አስተዋላት። አንገቷን ደፍታለች። በአቋሟ እንደጸናች መሆኑ ገባው። ንዴቱ አገረሸበት፣ እልህ፣ ብሽቀት ያዘው።
ጥርሱን እንደነከሰ ከጀርባው የሻጠውን ስለት አወጣ። አልመለሰውም። አጥብቆ እንደያዘው በጉሮሮዋ መሀል አሳረፈው። ክፉኛ የተወጋችው መክሊት ድርጊቱን መቋቋም አልቻለችም። ከእጁ ተንሸራታ ከመሬት ወደቀች። ዴቦ መለስ ብሎ አላያትም። በደም እንደተነከረች ከጫካው፣ ከጉድባው ትቷት ከስፍራው ተሰወረ ።
ሰዓቱ ገፍቷል፣ ምሽቱ በርትቷል። መክሊት ከትምህርት ቤት በሰዓቱ አልገባችም። እንዲህ መሆኑ የተለመደ አይደለም። እናት፣ አባት መላው ቤተሰብ ጭንቅ ይዞታል፡፤ ሁሉም በር በሩን እያዩ፣ መምጣቷን ይናፍቃሉ። ኮሽታ፣ ኮቴ ያዳምጣሉ። መክሊት አልመጣችም። ያለ ዕንቅልፍ ያፈጠጠው ቤተሰብ ሰላም አላገኘም። ሌሊቱ ተጋምሶ ውድቅት ሆነ። አዲስ ነገር ሳይሆን ወፎች ተንጫጩ።
በማግስቱ – የፖሊስ ምርመራ
ለከምባታ ጠንባሮ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት በማለዳው የደረሰው ጥቆማ የፖሊስ አባላትን ትኩረት ስቧል። ጠቋሚዎቹ አየን ያሉትን ጉዳይ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሀይል አስፈልጎም አንድ ቡድን ወደስፍራው ተንቀሳቅሷል። ቡድኑ በጠቋሚዎች እየተመራ ከጫካው ሲደርስ ያየውን ማመን አልቻለም። በጅብ ተበልቶ በየቦታው የተበተነ የሰው አካል ይመለከታል። ጠጋ ብሎ ሁኔታውን ሲያስተውል ጉዳዩ የሴት አካል መሆኑን ያረጋግጣል። በስፍራው በደም ተነክሮ የተቀዳደደ ልብስ፣ የሴት ጫማ የራስ ቅልና የእጅ ሞባይል ወድቋል።
ቡድኑ መረጃዎቹን በጥንቃቄ ይዞ የሟች ቤተሰብን ማፈላለግ ሲጀምር የመክሊት አባት ልጃቸው ከቤት እንደወጣች አለመመለሷን ለፖሊስ ቀርበው ያስረዳሉ። ፖሊስ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ሟች የእሳቸው ልጅ ስለመሆኗ ያረጋግጣል።
ድርጊቱን የሰማው የአካባቢው ነዋሪ የሆነውን ማመን አልቻለም። ለመክሊት አሰቃቂ ሞት ተጠያቂው ዴቦ መሆኑ እንደታወቀ የቤተሰቡ ሀዘን በረታ። ዴቦ ማሴቦ ለነመክሊት ቤተሰብ የልጅ ያህል ነበር። ከመክሊት ጋር አፈር ፈጭተው፣ ውሃ ተራጭተው በአንድ አድገዋል፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ትምህርት ቤት ሄደዋል። ሁለቱም በሚያገለግሉት ቤተክርስቲያን ጥሩ ዘማሪዎች ነበሩ። ወላጆቻቸው ዓመታትን በፍቅር፣በመተሳሰብ ዘልቀዋል።
ተወዳጇ፣ ልበቀናዋ፣ ዓመለ ሸጋዋ መክሊት በአብሮ አደግ ጓደኛዋ ይህ አይነቱ ግፍ ይፈጸምባታል ብሎ ያሰበ አልነበረም። የወላጅ እናቷ ስሜት ደግሞ ከብዙዎች በእጅጉ ይለያል። ሲመሽ ሲነጋ ጭንቀታቸው ይበረታል። ጅብ ሲጮህ… የሚገቡበት ያጣሉ። ብርክ ይይዛቸዋል።
ጅብ ሲጮህ… ይንቀጠቀጣሉ፣ አምርረው ያለቅሳሉ። ድምጹን ሲሰሙ ‹‹ልጄን የበላብኝ ይህ ይሆን? ›› ይላሉ። ዝም ሲል ሌላ ያለ ይመስላቸዋል። አዕምሯቸው ይሄኛው ነው›› ሲላቸው። በፍርሀት ይርዳሉ። ሀዘናቸው ይበረታል። ትኩስ ዕንባቸው ይወርዳል። ጭንቀታቸው ለቤቱ ህጻናት ጭምር ከተጋባ ቆይቷል። ጅብ ሲጮህ… የመላው ቤተሰብ ስሜት ይቀየራል።
ውሳኔ…
ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የከምባታ ጠምባሮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍቅረኛውን ሕይወት በግፍ ነጥቆ አካሏን በጅብ ባስበላው ተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ በአስረጂነት የቀረቡ ማስረጃዎችን ትክክለኛነት መርምሮም ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል። በዕለቱ በሰጠው ብይንም ወንጀለኛው ዴቦ ማሴቦ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ወስኗል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014