የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች የሚዘጋጁ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ተጠቃሽ ናቸው። ታዳጊዎችን ለማበረታታትና ብቃት ያላቸውን ወጣት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር ወይም ከዋናው ቡድን ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆን እ.አ.አ ከ2002 ጀምሮ ከ19 ዓመት በታች የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ቻምፒዮናን አስጀመረ።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር እ.አ.አ ከ2006 ጀምሮ በየእድሜ ደረጃው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች እንዲካሄዱ ሲያደርግ፤ በቀጣዩ ውድድር ደግሞ ስያሜውን የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በሚል ተክቶታል።
ውድድሩ በየዓመቱ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት እያደገና እየተለመደ በመሄድ አገራት ወጣት ቡድናቸውን የሚያፎካክሩበት ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ሆኗል። በሴቶች እግር ኳስ ውጤታማ የሆነችው አሜሪካ በዚህ የእድሜ እርከን በሚካሄደው ውድድር ቡድኗ በተመሳሳይ የላቀ ውጤት ያለው ሲሆን፤ ሶስት ጊዜ ቻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። አውሮፓዊቷ ጀርመንም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫን ለሶስት ጊዜያት በማንሳት ከአሜሪካ በእኩል ደረጃ ተቀምጣለች።
ውድድሩ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 መካሄድ ቢኖርበትም በወቅቱ በነበረው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙ የግድ ነበር። በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆች ዓመት ደግሞ በቅንጅት ለማዘጋጀት አቅደው በነበሩት ኮስታሪካ እና ፓናማ ቫይረሱ በማየሉ ምክንያት ወደ ቀጣዩ ዓመት ሊተላለፍ ችሏል።
በዚህም መሰረት ውድድሩ ከወራት በኋላ የሚካሄድ ቢሆንም ፓናማ ከአስተናጋጅነት ራሷን በማግለሏ ኮስታሪካ የምታሰናዳው ይሆናል። በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን የተለያዩ አገራት ቡድኖቻቸውን በማጣሪያ ጨዋታዎች እያሳተፉ ሲሆን፤ አፍሪካም በውድድሩ በሁለት ቡድኖች ለመወከል የማጣሪ ፉክክሮችን የምታከናውን ይሆናል።
አፍሪካን በዚህ ታላቅ መድረክ ከሚወክሉ ሁለት አገራት መካከል አንዷ ለመሆንም ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ባወጣው መርሐ ግብር መሰረት የማጣሪያ ጨዋታዋን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
በቅርቡ በሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር የዋንጫ ባለቤት የሆነውና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የተሻለ ብቃት እንዳለው ያስመሰከረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከርዋንዳ ጋር ማድረጉ የሚታወስ ነው። በኪጋሊ እና ባህርዳር በተደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታም በአጠቃላይ 8 ለምንም በሆነ ውጤት ነበር ያሸነፈው።
ሁለተኛውን ጨዋታም ከቦትስዋና ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር በመጪው የፈረንጆቹ ወር መጀመሪያ የሚያደርግ ይሆናል። ለዚህም ጨዋታ ዝግጅት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤልም ለ22 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ቡድኑ በአዲስ አበባ የካፍ የእግር ኳስ ልህቀት ማዕከል መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅቱን የሚቀጥልም ይሆናል።
ተጫዋቾቹ ከተለያዩ ክለቦች የአሰልጣኙን ጥሪ ተቀብለው የተሰባሰቡ ሲሆን፤ የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ሰባት ተጫዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚው ነው። መዓድን ሳህሉ፣ ነጻነት ጸጋዬ፣ ገነት ኃይሉ፣ ቤተልሄም በቀለ፣ እጸገነት ግርማ፣ አይናለም አደራ እና መሳይ ተመስገን ደግሞ ጦሩ ያስመረጣቸው ተጫዋቾች ናቸው።
ድሬዳዋ እግር ኳስ ክለብ ብርቄ አማረ እና ቤተልሄም ታምሩን ሲያስመርጥ፤ አዳማ ደግሞ እየሩሳሌም ሎራቶ እና ናርዶስ ጌትነት ተመርጠውለታል። ከሃዋሳ ከተማ ቱሪስት ግርማ እና ረድኤት አስረሳኸኝ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ኚቦኝ የን፣ መስከረም ኢሳያስ እንዲሁም ገነት ኤርሚያስ በብሔራዊ ቡድኑ የተካተቱ ተጫዋቾቹ ሆነዋል።
በሴቶች እግር ኳስ የተሻለ የሚባለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብዙአየሁ ታደሰ፣ ዮርዳኖስ ሙአዝ እና አረጋሽ ካልሳ ተመርጠውለታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ንግስት አስረስ፣ ባህርዳር ከተማ ባንቺአየው ደመላሽ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አርያት ኦዶንግ የተባሉ ተጫዋቾቻቸው በብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ የተደረገላቸው መሆናቸውን የፌዴሬሽኑ በመረጃው አመላክቷል።
ቦትስዋና አንጎላን በደርሶ መልስ ጨዋታ 8ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ ውጤት ያለው ቡድን መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተዋቀረው በቅርቡ አስደናቂ በሆነ ብቃት ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫን ባነሱት ተጫዋቾች ነው።
ይህም ቡድኑ ከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝ ያመላከተ ከመሆኑ ባሻገር ጠንካራ ተፎካካሪና ለአሸናፊነት እንዲጠበቅ አድርጎታል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋው ዋንጫው አስራ ስምንት ግቦችን አስቆጥሮ ሶስት ግቦች ብቻ ሲቆጠሩበት የውድድሩን አዘጋጅ ዩጋንዳን በመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ለ ዜሮ ከመመራት ተነስቶ ከእረፍት መልስ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ዋንጫ ማንሳቱ አይዘነጋም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2014