የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ለ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድለው ስድስት ጨዋታዎችን አከናውነው ጨርሰዋል። ዋልያዎቹ ገና በጊዜ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፉክክሩ ቢሰናበቱም በስድስቱ ጨዋታዎች ያሳዩት አቅም አበረታች መሆኑን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ሃሳብ እየሰነዘሩ ይገኛሉ።
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ውጤታማ ለመሆን እየተጓዘበት ያለው ሂደት አመርቂ ነው ለማለትም ይቻላል። ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪ ጨዋታዎቹ በአብዛኛው በውጤት ረገድ ስኬታማ ባይሆንም ከዚህ ቀደም እንደነበረው በደመነፍስ ከመጫወት ወጥቶ በሚታይና የራሱ መገለጫ ሊሆን በሚችል አጨዋዎት መታየቱ እንዲሁም ቡድኑን ለመገንባትና ለዘላቂ ውጤታማነት እየተሰራ ያለ መሆኑን ፍንጭ ሰጥቷል። ከዚህ መልካም ጅማሬው እንዳይንሸራተትም አሰልጣኙንም ሆነ ተጫዋቾችን ማድነቅ፣ ማበረታታትና ማገዝ ያስፈልጋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቀድሞውን አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ የጀመሩትን የቡድን ግንባታ በማስቀጠል ያደረጉት ጥረትና የታየው ተስፋ የቡድኑን አጨዋወት ቢቻል ወደ ወረቀት አውርዶ፣ ታርሞና ተስተካክሎ የአገሪቱ የእግር ኳስ የአጨዋወት ፍልስፍና ቢሆን መልካም ውጤት እንደሚያስገኝ የበርካቶች እምነት ነው። አንድ አሰልጣኝ የጨዋታ ሃሳብ ካለው የቡድኑ ነፍስና ስጋ ሜዳ ላይ ይታያል። እንዴት ማጥቃትና መከላከል እንዳሰበ በግልፅ ይስተዋላል። በሀሳቡ ውስጥ ብዙ መማማሪያ የታክቲክ ሀሳቦችም ይኖሩታል። የአሰልጣኝ ውበቱ ቡድንም በስድስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሊጎለብቱ የሚችሉ በርካታ የታክቲክ ሃሳቦች እንደነበሩት ማስተዋል ይቻላል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአብዛኞቹ ጨዋታዎች ሲከላከል 4-1-4-1 መሃል ሜዳ ላይ ሆኖ ነው። ይህ በዘፈቀደ የሚመጣ ሳይሆን ስራ ይፈልጋል። ቡድኑ ብዙ ጊዜ 4-5-1 ወይም 4-1-4-1ና 5-4-1 ይጠቀማል። ከኋላ ጀምሮ በመጫዎት የሰው ለሰው ጫና ሲገጥመው ይህንን ለመፍታት በግራና ቀኝ መስመር ተከላካዮቹ አግድም ኳሶችን እና አንዳንዴም ለአጥቂ ረዥም ኳስ በመጣል ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግም ተስተውሏል።
በአንድ በኩል በቁጥር በዝቶ በመጫዎት፣ በሌላኛው በኩል ነፃ ሰው ለማግኘት የሚያደርገው ጥረትም እንደ ሃሳብ አስደናቂ ነው። አንድ ለአንድ ተከላካዮች ከተቃራኒ ቡድን ጋር ሲገናኙ ያለባቸው ክፍተት ግን ሳይጠቀስ የሚያልፍ አይደለም። በግብ ጠባቂ በኩል ቡድኑ ያለበትን ክፍተት ማንሳት ነገር መደጋገም ይሆናል።
እያጠቁ በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው ጥር የአፍሪካ ዋንጫ መጠንቀቅና ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው ክፍተት መሆኑን መጠቆም ያስፈልጋል። ቡድኑ ኳስ ይዞ ወደ ተጋጣሚ ቀጠና ዘልቆ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክር ኳሱ በተጋጣሚ ቢከሽፍበት፣ ለመልሶ ማጥቃት የተዘጋጁትን የተጋጣሚ ተጨዋቾች መከላከል ያስፈልጋል። ያለበለዚያ አደጋው የከፋ ይሆናል። ይህም ባለፈው የጋና ጨዋታ በተደጋጋሚ ታይቷል። ተጋጣሚ ኳሱን ወደ ግራ ወይንም ወደ ቀኝ የሚያንሸራሽረው ነፃ ተጨዋች ለማግኘት ስለሆነ፣ በቡድን እንደ አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ መፍትሄ ነው፣ የበለጠ ስራም ይፈልጋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቆመ ኳስ የሚቆጠርበት ግብ በበርካታ አጋጣሚዎች ዋጋ ሲያስከፍሉት ማየት የተለመደ ነው። የማዕዘን ምት በውስጥና በውጭ እግር ሊመታ ይችላል። የማዕዘን ምት ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ግብ ሊቀየር ይችላል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሁንም ከቆመ ኳስ በተለይም የማዕዘን ምትን መከላከል ላይ መስራት ይጠበቅበታል።
የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና የውበቱ አባተ ብሄራዊ ቡድን ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫዎት ሀሳብ የተሻለ ነገር አሳይቷል። ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫዎት እድሎችን ፈጥሮ፣ ግቦችን በማስቆጠር ማሸነፍ የኢትዮዽያ የእግር ኳስ የተሻለው ሀሳብ እንደሆንም ጥሩ ምስክር መሆን ችለዋል። ለአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ መግባት እንደሚቻልም ተስፋ ሰጥቷል። እንደ አገር የምንጫወተውን የእግር ኳስ ሀሳብ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ተርጉሞና ተንትኖ የሚያስቀምጥ የአገሪቱ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ቢኖርና የተጀመረውን መሰረት ማጠናከር ይቻላል።
ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት አገር አንድም ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ አለመኖሩ ቡድኑን በበለጠ ለማጠናከር እንቅፋት ነው። ስቴድየሞች ሲገነቡ ለፖለቲካዊ ጉዳዮች መሰብሰቢያ፣ ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማሳለፊያና መሰል ጉዳዮች ታስበው መሆን የለበትም። በዚህ ላይ ክለቦች የሚታወቅ የእግር ኳስ ሀሳብ የሌላቸው መሆኑ እንደ መሰረታዊ ትልቅ ችግር ማንሳት ይችላል። ሀሳብ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘፈቀደ አጨዋወታቸው እንኳን የራሳቸው ስታዲየም የላቸውም።
ከክለቦች ባሻገር ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋርም ቢሆን፣ በሊጋችን ውስጥ ግልፅ ሀሳብ ያላቸው አሰልጣኞች አለመኖራቸው ለብሄራዊ ቡድኑ ማነቆ ነው። አሁን ካሉት አሰልጣኞች እንኳን ቢቆጠሩ ከሶስት አይበልጡም። ይህ ማለት ተጨዋቾቹን ለብሄራዊ ቡድን የሚያበቃ ባለሙያ የለም ማለት ነው። እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እንኳን የተጀመረ ነገር የለም።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተና አብርሃም መብራቱ ያሳዩን ጭላንጭል ከአሰልጣኞቹ የራሳቸው ችሎታ እንጅ ሌሎች ምንም አስተዋፅኦ አላደረጉም። ይህን የታየ የተስፋ ጭላንጭል ወደ ተሻለ የብርሃን ጮራ ለማሸጋገር አሰልጣኞችን ማሰልጠን ያስፈልጋል። ከመሸፋፈን መማማር ቢቀድም ጥሩ ነው። ብሄራዊ ቡድን የሁሉም አሰልጣኞች አስተዋፅኦ ነውና። በአንድና ሁለት አሰልጣኞች ብቻ ለውጥ አይመጣም። ከዚህ በላይ ውጤት ሊመጣ የሚችለው እንደ አገር ከተሰራ ብቻ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014