ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች 12 የሚሆኑ ደረጃ አንድ ስታዲየሞች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚህ ስቴድየሞች ግንባታ እስከአሁን የተጠናቀቀው መዋቅራቸው ብቻ መሆኑን ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አብዛኛዎቹ ስታዲየሞች ከስማቸው ቀጥሎ ዓለም አቀፍ የሚል መለያ ያላቸው ይሁኑ እንጂ ተገንብተው መጠናቀቅ ተስኗቸው ባሉበት ሁኔታ ዓመታትን ለመቁጠር ተገደዋል። በመንግሥት በኩልም፤ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው ስታዲየሞች የግንባታ ጊዜ ሲራዘም ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርጉ በመሆናቸው በአፋጣኝ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንደገቡ የሚያደርግ አሠራር አልተበጀም፡፡
በቢሊየን የሚቆጠር የአገር ሀብት ፈሶባቸው እየተገነቡ የሚገኙት ስቴድየሞች ግንባታቸው ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ በጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ኢትዮጵያ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በተለይም የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ለማድረግ ለሌሎች አገራት ሜዳ ተጨማሪ ገንዘብ መክፈሏ የግድ ሆኗል። በመሆኑም ስታዲየሞች በዕቅዳቸው መሰረት ላለመጠናቀቃቸው ክልሎች ከሚያነሱት የበጀት እጥረት እንቅፋት ከመሆኑ ባለፈ ለዘርፉ ማነቆ ሆኖ የቆየው ችግር ለበርካቶች ግልጽ አይደለም፡፡
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አሥመራ ግዛው፤ ለረጅም ጊዜ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሚመለከት ሊፈታ ያልቻለውና ስር የሰደደው መሰረታዊ ችግር የህግ ማዕቀፎች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ተናቦ በቅንጅት በመሥራት በኩልም ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
ክልሎች ስታዲየምና ሌሎች የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ሲያደርጉ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት መንገድ ከዚህ ቀደም አልነበረም፡፡ ይህ ይሆን ዘንድም የስፖርት ማዘውተሪያ ከጥናት ጀምሮ ተገንብተው እስኪጠናቀቁ ድረስ ክትትል በማድረግ ዕውቅና የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አገራዊ ደረጃ (ስታንዳርድ) የሚሰጥበት ደንብ ሊኖር እንደሚገባ አቶ አሥመራ አስተያየታቸው ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ደረጃ ይሰጥ የነበረው በልማዳዊ አሠራር እንጂ የህግ ማእቀፍ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በግንባታ ላይ ያሉትንም ይሁን ወደፊት የሚገነቡ ማዘውተሪያዎችን በሚመለከት ከመነሻው ጀምሮ በሥራ ላይ እያሉ በክትትል መስፈርቶችን አሟልተዋል በሚል የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ መመሪያ ተዘጋጅቷል።
ከዚህ ቀደም በአንድ ክልል ስታዲየም ግንባታ ላይ እያለ የፌዴራሉ መንግሥት በጎደሉ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብቶ መሟላት አለበት የሚለውን ጉዳይ እንዲሟላ ማስገደድ አይችልም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግንባታው የሚከናወነው በክልሉ መንግሥት ውሳኔና በራሱ በጀት በመሆኑ ነው፡፡
ይህንን የሚመለከት አዋጅ ቢኖርም ለማስተግበር የሚያስችል መመሪያ አለመኖሩ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህል በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ጥናት የተደረገበትን የሐረር ስታዲየምን ያነሳሉ፡፡ ይኸውም ስታዲየሙ ጥሩ ዲዛይን ያለው ቢሆንም በግንባታ ወቅት ግን በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህንንም የክልሉ ስፖርት ቢሮ፣ ግንባታውን የሚፈጽመው ተቋራጭ፣ አማካሪው እንዲሁም ሌሎች አካላት በተገኙበት ክፍተቱን በተመለከተ መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ኃላፊነት አልነበረውም፡፡
ከስታዲየም ግንባታ ባለፈ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሚመለከት እንደየደረጃው ከቀበሌ ጀምሮ ሊኖሩ የሚገባቸው በመጠን ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ በመስፈርቱ መሰረት ማሟላት ያልቻሉትን ማስገደድም ሆነ ዕርምጃ መውሰድ አይቻልም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በየክልሉ የሚገኙ አመራሮች በየጊዜው የሚቀያየሩ በመሆቸው በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እስኪጨብጡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በአንጻራዊነት ከሌሎች ክልሎች ይልቅ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂ ባይሆንም በማዘውተሪያዎች ግንባታ እንዲሁም የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል በሌሎች ክልሎች የነበሩትን የማዘውተሪያ ስፍራዎች ጭምር ነጥቆ ለሌላ አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል።
ይህም የህግ ማዕቀፍ አለመኖር እና ግንዛቤው እስከታችኛው እርከን ድረስ አለመውረድ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ሌላው ችግር የክልሎች ነው፤ ከዚህ ቀደም እንደታየው በሌላ ክልል ስታዲየም ስለተገነባ ከበጀታቸው ጋር ሳያጣጥሙ በሞራል ግንባታ መጀመር ይታይ ነበር። ግንባታው ታምኖበትና በአቅም ልክ እንዲካሄድም ከክልል መንግሥታት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግና ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ በመሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀጣይ የቤት ሥራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ፡፡
ከላይ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ማሠሪያ የሚሆነው የህግ ማዕቀፎችን በመመሪያዎች መደገፍ ነው፡፡ በዚህም ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅዶ ሰፊ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡ ነገር ግን የተዘጋጁ መመሪያዎችን አጽድቆ ወደ ሥራ መግባት ካልተቻለ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠል የግድ እንደሚሆን ስጋታቸውን ያንጸባርቃሉ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014