ያሳለፍነው ሳምንት የእግር ኳሱ ዓለም ከክለብ እግር ኳስ ፉክክሮች ወጥቶ በብሔራዊ ቡድኖች የ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ስራ በዝቶበት ሰንብቷል። አምስት አገራት ብቻ ለዓለም ዋንጫ በሚያልፉበት የአፍሪካ አገራት የማጣሪያ ፉክክር ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ የማጣሪያ ጨዋታ የሚያልፉት አስር ምርጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚለዩባቸው በርካታ ጨዋታዎች ተጠባቂ ነበሩ። በተለይም ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሰባት የተደለደሉት ደቡብ አፍሪካና ጋና ከአስሩ ምርጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን ያደረጉት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ወሳኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አጓጊ ነበር።
ደቡብ አፍሪካ እስከ መጨረሻው የምድብ ጨዋታ በአስራ ሶስት ነጥብ እየመራች በአስር ነጥብ ከምትከተላት ጋና ጋር ከትናንት በስቲያ በኬፕ ኮስት ያደረገችው ጨዋታ ከምድቡ የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ወሳኝ ነበር። ደቡብ አፍሪካ ከምድቡ ለማለፍ የተሻለ እድል ያላት አገር ብትሆንም በጥቁር ከዋክብቱ ሜዳ የአቻ ውጤት እንኳን ማሳካት ባለመቻሏ በእኩል አስራ ሶስት ነጥብ በአንድ ግብ ተበልጣ አሳዛኝ ተሸናፊ ሆናለች። ባፋና ባፋናዎቹ በምድባቸው የመጀመሪያውን ሽንፈት በጋና አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ብቸኛዋን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አንድሬ አየው ያስቆጠራት ግብና ፍጹም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ አሁንም አከራካሪ ነው። ደቡብ አፍሪካ እኤአ በ2010 ካሰናዳችው የዓለም ዋንጫ ወዲህ ወደ ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ለመመለስ በጥሩ መንገድ ተጉዛ መጨረሻዋ ሳያምር ቀርቷል። ጥቁር ከዋክብቱ በአንጻሩ ባለፈው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ
መሳተፍ ባይችሉም ወደ ኳታር ለማቅናትና ለአራተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የመቶ ሰማንያ ደቂቃ ፍልሚያ ቀርቷቸዋል። በዚሁ ምድብ ቀድመው ከማጣሪያ ፉክክሩ ውጪ መሆናቸውን ያረጋገጡት ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ በሀራሬ ያደረጉት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ አቡበከር ናስር በመጨረሻ ሰዓት ያስቆጠራት ግብ ዋልያዎቹን ከሽንፈት ታድጋለች።
ዲሞክራቲክ ኮንጎ በዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከምድብ አስር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የቻለች አገር ሆናለች። ይህም እኤአ ከ1974 ወዲህ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመመለስ ከምርጥ አስር የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች አንዷ አድርጓታል። ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአስራ አንድ ነጥቦች ምድቡን ቀዳሚ ሆና ያጠናቀቀችው ቤኒንን ሁለት ለዜሮ ረታ ሲሆን የዓለም ዋንጫ ላይ ደርሳ የማታውቀው ተሸናፊዋ አገር ቤኒን በአንድ ነጥብ ልዩነት በሚያስቆጭ ሁኔታ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳታልፍ ቀርታለች።
በምድብ ስምንት ሴኔጋል ገና በጊዜ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የቻለች አገር ብትሆንም የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ በሜዳዋ ኮንጎን ሁለት ለዜሮ መርታት ችላለች። ሴኔጋል አስራ ስድስት ነጥብ ይዛ ከምድቧ በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ ከተፎካካሪዎቿ ቶጎና ናሚቢያ በአስራ አንድ ነጥብ ሰፊ ልዩነት ነው።
በምድብ አምስት ማሊ ዩጋንዳን በገለልተኛ ሜዳ ሞሮኮ አጋዲር ላይ አንድ ለዜሮ በማሸነፍ በአስራ ስድስት ነጥብ ከምርጡ አስር የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች አንዷ መሆኗን አረጋግጣለች። በምድብ ስምንት ሞሮኮ አንድ ጨዋታ እየቀራት በአስራ አምስት ነጥብ ከአስሩ ምርጥ ብሔራዊ ቡድኖች መካተት የቻለች ሲሆን፣ በተመሳሳይ በምድብ ስድስት አንድ ጨዋታ የሚቀራት ግብጽ በአስራ አንድ ነጥብ ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች።
ስድስት አገራት ከአስሩ ምርጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ መሆናቸው ከትናንት በስቲያ ቢያረጋግጡም ቀሪዎቹ አራት አገራት ዛሬ የሚለዩበት ወሳኝ ፍልሚያ አጓጊ ነው። በተለይም እነዚህ አገራት በየምድባቸው ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸውና የእግር ኳስ ደረጃቸውም ብዙ ልዩነት የማይታይበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዛሬውን ፍልሚያ እጅግ ወሳኝ አድርጎታል።
በምድብ አንድ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ አስራ ሶስት ነጥብ ይዛ ምድቡን ብትመራም በሁለት ነጥብ ዝቅ ብላ የምትከተላት ቡርኪናፋሶ ጠንካራ የእግር ኳስአገር በመሆኗ የዛሬውን ወሳኝ ፍልሚያ ተጠባቂ አድርጎታል። አልጄሪያ አስሩን ምርጥ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ለመቀላቀል ዛሬ በሜዳዋ ከምታደርገው ጨዋታ የአቻ ውጤት ብቻ በቂዋ ነው።
በምድብ ሁለት አስር አስር ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ የሚበላለጡት ቱኒዚያና ኢኳቶሪያል ጊኒ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በምድቡ የሚገኙ አገራትን የሚገጥሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ቱኒዚያ ዛምቢያን ስታስተናግድ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሜዳዋ ውጪ ሞሪታኒያን የምትገጥምበት የዛሬ ምሽት ጨዋታ ከአስሩ ምርጥ ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ የሚለይበት ይሆናል። በምድብ ሶስት አስራ ሁለት ነጥብ የያዘችው ናይጄሪያና በሁለት ነጥብ አንሳ የምትከተላት ኬፕቨርዴ በአረንጓዴ ንስሮቹ ሜዳ የሚያደርጉት ፍልሚያ የምድቡን አላፊ አገር የሚወስን ይሆናል።
በአፍሪካ እግር ኳስ ቁንጮ ከሚባሉት አገራት መካከል የሚጠቀሱት ኮትዲቯርና ካሜሩን ያለፉት አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አሸናፊ ብቻ ሳይሆኑ ተመጣጣኝ የእግር ኳስ ደረጃ ያላቸው አገራት ናቸው። ሁለቱ አገራት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያውም በምድብ አራት በአንድ ነጥብ ልዩነት ተናንቀዋል። በአስራ ሶስት ነጥብ የምትመራው ኮትዲቯር ብትሆንም ዛሬ ከሜዳዋ ውጪ የማይበገሩት አንበሶችን የምትገጥምበት ወሳኝ ጨዋታ የምድቡን አላፊ አገር የሚወስንና እንደ ፍጻሜ ጨዋታ የሚቆጠር ጭምር ነው። ይህ ጨዋታ የፊታችን ጥር ካሜሩን ከምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ወዲህ በአፍሪካ ከፍጻሜ በፊት የሚከናወን የፍጻሜ ጨዋታ የሚል ስያሜ ቢሰጠው አልተጋነነም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014