የመጨረሻ ክፍል
ኢትዮጵያ በአትሌቲከስ ውድድሮች ያልረገጠችበት የአለም ክፍል የለም። በአለም አቀፍ ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃም አትሌቲክሳችን ይታወቃል። ይህን ያህል የሚታወቀውን አትሌቲክሳችንን ግን ከማን ጋር ብናነጻጽረው ነው ተገቢ ሊሆን የሚችለው። ልናነጻጽር የሚገባው ከምራባውያን አገራት ጋር ሳይሆን ከጎረቤት ኬንያ ጋር መሆን አለበት። እንደ እድል ሆኖ ኬንያ አጠገባችን ትገኛለች። በአቅምም እንዲሁም በኑሮ ደረጃ እምብዛም አንለያይም፡ ስለሆነም ለንጽጽር ይመቻል።
በእያንዳንዱ አህጉራዊ አትሌቲክስ ውድድር እያንዳንዱ አገር ያገኛቸው የሜዳሊያ ብዛቶች ተደምሮ ደረጃ ይወጣለታል። የኢትዮጵያ ደረጃ 1 ጊዜ 3ኛ፡ 5 ጊዜ 4ኛ፡ 2ጊዜ 5ኛ፡ 3 ጊዜ 6ኛ፡ 1 ጊዜ 7ኛ እንዲሁም ሁለት ጊዜ 8ኛ እና 9ኛ ስትሆን፣ አንድ አንድ ጊዜ 11ኛ፡15ኛ እና 16ኛ ሆና ጨርሳለች።
ጎረቤታችን ኬንያ 4ጊዜ 1ኛ፡ 7ጊዜ 2ኛ እና 3ኛ፡ 1ጊዜ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃ ደርሳለች። ኬንያ ከ21 ውድድር 18ጊዜ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በታች አልወረደችም።
አገራችን ጎረቤታችንን በደረጃ ሰንጠረዥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የበለጠቻት። እኛ 3ኛ ስንወጣ ኬኒያ 4ኛ ሆና ጨርሳለች፤ ይህም አዲስ አበባ በተደረገው 16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና ነው። በእውነት ከሆነ የደረጃ ልዩነታችን ጎልቶ ይታያል። ለማስረዳት ያህል አትሌቲክሳችንን ከእግር ኳስ ደረጃ አወጣጥ ጋር ስናነጻጽረው ኬንያ ፕሪሚየር ሊግ ስትወዳደር ኢትዮጵያ ደግሞ ከሱፐር ሊጉ ወርዳ ብሔራዊ ሊግ ትጨወታለች ማለት ነው። ያገራችንን አትሌቲክስ መለወጥ ከፈለግን ጎረቤት ኬንያን እንደ ግብ አስቀምጠን ብንቀሳቀስ ትልቅ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን።
የሴቶች አትሌቲክስ በአንፃሩ ከወንዶች የበለጠ ተሻሽሏል የዛሬ 50 ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሲጀመር በውስን ሜዳ ተግባራት ብቻ ነበር ውድድሮቹ የተካሄዱት (100- 200- 400ሜ -አሎሎ- ዲስከስ- ጦር ውርወራ- ከፍታ እና ርዝመት ዝላይ)። ባሁኑ ጊዜ የውድድር ወሰኑን አስፍተው 100-400 ሜ መሰናክል- ሱሉስ ዝላይ ተጨምረዋል።
ሴት አትሌቶቻችን በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በመካከለኛ እና በረጅም ሩጫ ከጅምሩ መሳተፋቸው ይታወቃል፤ ሆኖም በአጭር ሩጫ፣ ዝላይ እና ውርወራ እኤአ በ 2006 ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉራዊ ውድድር መሳተፍ የጀመሩት። (ቀደም ብሎ በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአገራችን አቆጣጠር በ1962 እና 1963 ለመጀመሪያ ጊዜ በናይሮቢ እና ቀጥሎም በሉሳካ ሴት አትሌቶቻችን ተሳትፈዋል)።
የመጀመሪያዎቹን ውጤቶች ከዛሬው ጋር ስናነፃፅር ከፍተኛ ልዩነት ይታያል። ወንዶች አትሌቶቻችን ያላሳኩትን ሴት አትሌቶቻችን በአንፃሩ አሳክተዋል። ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ አንዴ በርዝመት ዝላይ (6.23ሜ) ሌላ ጊዜ ደግሞ በከፍታ ዝላይ (1.80ሜ) ውጤታማ ሆነዋል።
የዛሬዎቹ ውጤቶች ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከተመዘገቡት ውጤቶች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ለውጥ እና መሻሻል ያሳያሉ። በ100ሜ ከ13.2 ሴ ወደ 11.8 ሴ፣ በ200ሜ ከ27.8 ሴ ወደ 24.06 ሴ ወርዷል፡ በ400ሜ ከ1ደቂቃ 02.10 ሴ ወደ 53.18 ሴ ዝቅ ብሏል። በርዝመት ዝላይ ከ 4.40ሜ ወደ 6.23ሜ ተሻሽሏል። በከፍታ ዝላይ ከ1.15 ወደ 1.80ሜ አድጓል። በአሎሎ ውርወራ ከ7.40 ሜ ወደ 13.28 ተሻግሯል። በዲስከስ ውርወራ ከ21.28 ወደ 39.17 ተሻሽሏል። በጦር ውርወራ ከ24.88 ሜ ወደ 43.96 ሜ ተሻግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴት አትሌቶቻችን ብዙ ለውጥ ቢያሳዩም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎቻችን በመጀመሪያው ዙር ይወድቃሉ። የመጀመሪያውን ማጣሪያ ካለፉ ደግሞ ልክ እንደ ወንድ ተወዳዳሪዎቻችን የግማሽ ፍጻሜ በርን ማለፍ ተስኗቸዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ስትራቴጂ ይቀይስበአሁኑ ወቅት የኢንተርናሽናል አማተር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተወሰኑ የሜዳ ተግባራት መሰረዝ ጀምሯል፣ በተለይ ረጅም ሩጫዎችን አካሄዱ። እኛ እና ኬንያን በግልፅ የሚጎዳ ነው። ከዚህ ድርጅት ከንቱ ሙግት ከመጀመር ይልቁኑ አዲስ ስትራቴጂ ቀይሶ የተለያዩ የሜዳ ተግባራት ውጤት አሻሽሎ መጓዝ ትክክለኛ አካሄድ ይመስለኛል። ጎረቤታችን ኬንያ አካሄዷን ከቀየረች ሰንበት ብላለች፤ ያልታሰበ እና ያልተጠበቀ ውጤት በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ እንዲሁም በኦሊምፒክ መድረክ ማስመዝገብ ጀምራለች።
የአገራችን አትሌቲክስ ለመቀየር በተለይ የአሰልጣኞችን ብቃት ማሳደግ፣ ከባህላዊ ልምምድ እንዲላቀቁ ትልቅ ጥረት ማድረግ፣ ጥንካሬን ልምምድ በዐይነ ቁራኛ ማየት እንዲያቆሙ ማስተማር፣ በየልምምድ ቦታዎች በቀላል ወጪ የጥንካሬ መሳሪያዎች ሰርቶ ማቅረብ፣ የአሰልጣኞች ደረጃ አወጣጥን በአዲስ አዘጋጅቶ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በመጀመሪያ በእያንዳንዱ የሜዳ ተግባር ሚኒማ ለማሟላት የሚቀረውን ደረጃ ለይቶ ማወቅ፣ ቀጥሎም ግማሽ ፍፃሜ ደርሶ ፍፃሜ ለማለፍ የሚጎድለውን ልምምድ ቀይሶ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
በብሔር ብሔረሰቦች የተገነባችው አገራችን ለሁሉም የአትሌቲክስ ሜዳ ተግባራት የሚስማሙ አትሌቶች መልምሎ ማፍራት አያቅጣትም። የውድድር ቁጥር በጣም ከማነሱ የተነሳ አትሌቶች ጎጂ የሆነ ረጅም እረፍት ይወስዳሉ። አንድ ቀን አልያም ቢበዛ ሁለት ቀን የሚውል ውድድር ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የውርወራ ዋንጫ፣ የዝላይ ዋንጫ፣ የአጭር ርቀት ሩጫ ዋንጫ፣ በታላላቅ የመንግሥት ባለስልጣን ስም ለምሳሌ የፕሬዚዳንት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር፣ የከንቲባው ዋንጫ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር የወዳጅነት ውድድር ቢዘጋጅ መልካም ይሆናል።
ለመደምደም
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የአስተሳሰብ፣ የልምምድ፡ የአደረጃጀት ለውጥ ማምጣት አለበት። ብዙ ጉልበት በከንቱ እየባከነ ማየት ያሳዝናል፤ ያስቆጫል። የአገሪቱ የወጣቶች ድርሻ ሲታይ በትክክል ከተሰራበት ትልቅ ተስፋ እንደሚያመጣ ምንም ጥርጣሬ የለውም። የወርቅ ማእድን ቁጭ ብሎ እየጠበቀን ነው። ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ይህን እምቅ ሀብት ቆፍረው እንዲያወጡ ይጠበቃል።
ፈረንሳዮች ማስተዳደር አስቀድሞ መተንበይ/ማቀድ ነው ይላሉ። ስለሆነም የአገራችን የስፖርት ኃላፊዎች እና ባለስልጣን የችግሩን ጥልቀት እና ስፋት አይተው አስተሳሰባቸውን ለውጠው በአዲስ አመለካከት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። የአገራችን ሕዝብ ለስፖርት ያለው ፍቅር የሚያስደንቅ ነው። ተስፋውን ላለማስቆረጥ ተጠንቅቆ መስራት ያስፈልጋል።
ዶ/ር ኤልያስ አቡሻክር
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014