በፖርቹጋል ማይዴራ ደሴት ከድሃ ቤተሰቦች የተፈጠረው መልከ መልካም የእግር ኳስ ፈርጥ ከምንም ተነስቶ ዛሬ ላይ ያልተጎናጸፈው ስኬት የለም። በሀብት ይሁን በእግር ኳስ ስኬቱ ይህ ቀረህ የማይባል ደረጃ ላይ የተቀመጠው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶስ ሳንቶስ አቪየሮ ከእግር ኳስ ስኬቶቹና ከሚያስቆጥራቸው የትየለሌ ግቦች በዘለለ ለጋስነቱ ብዙ ሲነገርለት አይታይም።
የዩኒሴፍ፣ የሴቭ ዘ ቺልድረንና ዎርልድ ቪዥንን በመሳሰሉ ዓለምአቀፍ የረድኤት ተቋማት አምባሳደር ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ሮናልዶ በመገናኛ ብዙሃን ከመልካም ጎኑ ይልቅ ህጸጾቹ ጎልተው የሚነገሩበት አጋጣሚ ትንሽ አይደለም። ዓለማችን በታሪኳ ካየቻቸው ድንቅ የእግር ኳስ ፈርጦች አንዱ የሆነው ሮናልዶ ከኳስ ሕይወቱ ውጪ ብዙ ሊነገርለት የሚገባና ለብዙዎችም አርአያ የሚሆን ተግባር ይፈጽማል።
በቅርቡ በፈጸመው የረድኤት ተግባር እንኳን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለአገሩ ሶስት ሆስፒታሎች 1 ነጥብ8 ሚሊዮን ዶላር ከማበርከቱ ባሻገር በጣሊያኑ ክለብ ጁቬንቱስ እያለ ለተመሳሳይ ተግባር የሚውል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዩሮ ያህል ከደመወዙ ተቀናሽ አድርጎ ለግሷል። እኤአ በ2011 አርባ ግቦችን በማስቆጠሩ የአውሮፓ እግር ኳስ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ በነበረበት ወቅት የወርቅ ጫማው በጨረታ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ተሸጦ በጋዛ ለትምህርት ቤቶች ማሰሪያ እንዲውል ማድረጉ ከብዙ የረድኤት ተግባሮቹ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው።
ሮናልዶ እነዚህን የረድኤት ተግባራት በተለያዩ ምክንያቶች ፈጽሞ ዓለምም የሚያውቅበት አጋጣሚ ቢፈጠርም ለታይታ ሳይሆን ከልቡ አምኖባቸው የሚፈጽማቸው በርካታ መልካም ምግባሮች አሉ። ብዙዎች የተነሱበትን የትናንት ማንነታቸውን እየረሱ በዛሬው ምቾታቸው ሲዘናጉ በሚስተዋልባት ዓለም ሮናልዶ ትናንትን የሚረሳ አይነት ተጫዋች አለመሆኑ ብዙዎችን ያስገርማል። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ከዚህ ውለታ መላሽ ኮከብ ጋር በተያያዘ አንድ አስደናቂ ታሪክን ይዳስሳል።
ታሪኩ ከፖርቹጋሉ ትልቅ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ይጀምራል። የትልቁ ስፖርቲንግ ሊዝበን የወጣት ተጫዋች መልማዮች እንደሚመጡ ሲሰማ ለምልመላ የተዘጋጁት ታዳጊዎች ጓጉተው ጠበቁ። የልጅነት ህልማቸው እውን እንዲሆን አጋጣሚው ከእንቁ በላይ ውድ ነበር። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የተባለው ታዳጊም በቡድኑ ውስጥ እንዳለው እኩያው አልበርት ፋንትሮ ሁሉ ምኞቱ ከዚህ የተለየ አልነበረም።
መልማዮቹ እንደመጡ ታዳጊው ሁሉ ራሱን ለገበያ ሊያቀርብ ያቺን ቀን ያለ የሌለ ብቃቱን ሁሉ አውጥቶ ሊያሳይ ቆረጠ። መልማዮቹ ማን የስፖርቲንግ ሊዝበንን አካዳሚ ነጻ የስልጠና ዕድል እንደሚያገኝ ለታዳጊዎቹ ‹‹የበለጠ ግቦችን ያስቆጠረ ይመለመላል›› ሲሉ አስገነዘቡ።
በጨዋታው ክሪስቲያኖ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ። አልበርት በአስደናቂ ቴስታ ሁለተኛውን ግብ በስሙ አስመዘገበ። ጨዋታው 2ለ0 ሆኖ ቀጠለ። ሶስተኛዋ ግብ ግን ተመልካቹን ሁሉ ያነጋገረች ሆነች። ከሁለቱ ተጫዋቾች አንድ ግብ የጨመረ በጨዋታው የሚፈለገውን የግብ የበላይነት ይይዛል። ፉክክሩ ልብ አንጠልጣይ በሆነበት ሰዓት አልበርት ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ–አንድ ተገናኘ። ራሱ ግቡን ማስቆጠርና ትልቁን እድል ለራሱ ማድረግ ይችላል። ከበረኛው ፊት ሲደርስ ግን ዕድሉን አሳልፎ ሰጠ።
ራሱን ነፃ አድርጎ ወደ ግብ ለተጠጋው ክሪስቲያኖ አመቻችቶ አቀበለው። ሮናልዶም ኳሷን ከመረቡ ውስጥ ዶላት። ጨዋታው 3ለ0 ሲያበቃ፣ ክሪስቲያኖ ለስፖርቲንግ አካዳሚ ስኮላርሺፕ ታጨ። ከጨዋታው በኋላ ሮናልዶ ወደ አልበርት ሄዶ ጠየቀው። ‹‹ከቶ እንዴት ዕድሉን አሳልፈህ ሰጠኸኝ?›› የአልበርት ምላሽ አጭርና ግልፅ ነበር። ‹‹ምክንያቱም አንተ ከእኔ የበለጠ ተሰጥኦ ስላለህ፣ ዕድሉ ላንተ ስለሚገባ ነው›› አለው።
ፈፅሞ የማይታመን ነበር። ከዓመታት በኋላ ሮናልዶ ይህን ታሪክ ሲናገር የሰማ ጋዜጠኛ የተባለው እውነት ለመሆኑ ማስረጃ ፍለጋ ወደ አልበርት ፋንትሮ ቤት ሄደ። የጎለመሰው አልበርት ፕሮፌሽናል ተጫዋች አልሆነም። ይባስ ብሎ ከዚያ ጨዋታ በኋላ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ሕይወቱ እንዳበቃ ለጋዜጠኛው ነገረው። አሁን የረባ ስራ እንኳን እንደሌለውም አስረግጦ አጫወተው።
ጋዜጠኛው ግራ ገባው። ‹‹እንዴ?… የረባ ስራ እንኳን የለህም። ግን ይህን በሚያክል የተንጣለለ ቪላ ውስጥ ትኖራለህ። የበርካታ መኪኖች ባለቤት ነህ። በተጨማሪ ቤተሰብህን አንደላቀህ ታኖራለህ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሀብቱ ከየት መጣ?›› አልበርት ለመልሱ አልተቸገረም። ‹‹ይህን ሁሉ ያደረገልኝ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው።›› አለው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014