እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ወዳጆች ብቻ ሳይሆን ብዙ ጠላቶችም ያሉንና ጥርስ የገባን ሕዝቦች ነን። እነዚህ በሩቅም በቅርብ ያሉ ጠላቶቻችን በቀጥታ የሚያገናኘን ነገር እንኳን ባይኖር «እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም» አይነት ዘመቻዎች ሲያደርጉብን ኖረዋል ፤እያደረጉብንም ይገኛሉ። በቀጥታ የሚያነካካን ነገር ሲያጡ ለዓመታት አንገታቸውን ደፍተው ይከርሙና እንደ አሜባ ምቹ ሁኔታ ሲያገኙ ሰተት ብለው ጓዳችን ለመግባት ይሞክራሉ።
ያጋጣሚ ነገር ሆኖ ከራሳችን ወገን የሚጋልቡት ፈረስ አጥተው አያውቁም። የእነዚህ ፈረሶቻቸው ኮርቻ ያልተደላደለ እንደሆነ ደግሞ ማዕቀብና ልብ የሚያርዱ ማስፈራሪያዎችን አከታትሎ መልቀቅ መንገዳቸው አድርገውታል። ልክ እንደኛዎቹ ይሁዳዎች የአንድ ወገንን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙላቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም አሏቸው። ከዚህ ሁሉ ጀርባ ሆኖ የተሟጠጠ ተስፋ የሚሰጣቸው በትንሽ በትልቁ የሚደነግጠውና የሚብረከረክላቸውም አይጠፋም።
ከወራት በፊት ግብጾች ሁለተኛው ሙሌት ከተከናወነ ነገሩን በዝምታ እንደማያልፉትና ለኢትዮጵያም ጥሩ ነገር እንደማይፈጠር አጠንክረው ሲናገሩ ነበር። የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ መሪም ቃል በቃል ግብጽ የመጨረሻውን እርምጃ በመውሰድ የተለፋበትን ግድብ ከጥቅም ውጪ ልታደርገው እንደትችል በአደባባይ አውጀው ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያንም ነገሩ “የላዋቂ ሳሚ ዓይነት” እንደሆነ ለመረዳት ብዙም አልቸገራቸውም።
በርግጥም ከማስፈራራቱ ባለፈ ምን መጣ? ምንም?። በማስፈራራት ዓላማን የማሳካት አካሄድ የሚንበረከክ ቢኖር ኖሮ ከህዳሴው ግድብ ጋር የሚኖረን ነገር ዛሬ ካለበት በፍጹም የተለየ አሳዛኝ ይሆን ነበር ። መንግሥት የማስፈራሪያ ዘመቻውን ወደ ጎን በመተው በዲፕሎማሲውም ሙሌቱንም በማከናወኑ በኩል በተረጋጋ መንፈስ ሥራውን ስላከናወነው ዛሬ ላይ ለመድረስ በቅተናል።
አሁን እየዘመቱብን ያሉትም እነዚህኑ መንገዶች በመጠቀም ነው። ለግዜው ተጋላቢው ፈረስ ደግሞ ወያኔ ሲሆን፤ ወያኔ ደግሞ በሥሩ በረጅም ልጓም የያዛቸው ሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ፈረሶች አሉት። በእነዚህ ሁሉ አካላት ደመኛ ጠላቶች ተደርገው የተመዘገቡት ደግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ናቸው ።
ኢትዮጵያ የሚባለውን ስም ሲሰሙ ከሚያንዘፈዝፋቸው መካከል ወያኔና የእንጀራ ልጆቹ ዋነኞቹ ናቸው። ወያኔ እንደ ፓርቲ ራሱን ችሎ የቆመ ሲሆን ባሻው ግዜ እየጠራ የሚጋልባቸው ዘመንም ታሪክም የማያስተምራቸው የግለሰብና የቡድን ፈረሶች አሉት። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከምስረታቸው ጀምሮ የራሳቸው ግብ የሌላቸው ነግቶ በጠባ አዳዲስ ጥያቄዎችና እሮሮዎችን ማሰማት መለያቸው ነው።
የእነዚህ አካላት የሚያመሳስላቸው ከእነሱ ውጪ ሁሉንም ያወግዛሉ፤ የሀሳባቸውና የግብራቸው መነሻውም መድረሻውም የእነሱ ፍላጎትና ጥቅም ብቻ ነው። ከእነዚህ ተነጂዎች መካከል ደግሞ ኦነግ ሸኔ ደረጃ አንድ ሆኖ በርካታ አስርተ ዓመታትን አሷልፏል። ዛሬም ኮርቻውን አስተካክሎ እየተጠባበቀ ይገኛል።
ኦነግ ሸኔ ካለ ወያኔ መተንፈስ የሚችል አይመስልም ሌላው ቀርቶ ወያኔ በአሸባሪነት ፈርጃ እንደቅጠል ስታረግፋቸው የነበሩ ወገኖቹን እንኳን የሚያስታውስበት ወኔ ያለው አይመስልም። በተአምር አይሆንም እንጂ ወያኔ በለስ ቀንቷት ሥልጣን ላይ ብትፈናጠጥ ከጥይት የተረፈ የዘንባባ ዝንጣፊ ለኦነግ ሸኔ እንደማታበረክት የማያውቅ ያለ አይመስለኝም።
ሌላው የወያኔ ተስፋ ደግሞ እንደ ሸኔ ተደራጅቶ የዳቦ ስም ያልወጣለት ቢሆንም በየመንደሩ ከዛሬ ነገ መንግስት ይፈረካከሳል፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል ብሎ የሚጠብቀው የውስጥ ባንዳ ነው። ይህ ተስፈኛ ስብስብ በግለሰብ ደረጃ ያሉትን ጨምሮ ሙሉ ጆሮውን ለወያኔ የሰጠና ከአፍንጫው አርቆ የማያስብ የስግብግቦች መገኛ ነው። ሁሉም ሊባል በሚል ደረጃ አንድ የሚያደርጋቸው ህሊና ቢስ መሆናቸው ነው።
አንድ ቦታ የተከሰተች ነገር ካለች ዘላለም ለማይሞላ ሆዳቸው መጠቀሚያ ያደርጓታል። ያላቸውን ኃይልና የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ሕዝብ ያስለቅሳሉ። የንግድ እቃዎች ይደብቃሉ፤ ዋጋ ያስወድዳሉ፤ ቤት ኪራይ ይጨምራሉ፤ የትራንስፖርት ክፍያም በተመሳሳይ። ግን እነዚህም ይህን ሁሉ ነገር ለማድረግ መደላድሉን የሚፈጥሩት በሐሰት የሽብር ዜናዎችን በመልቀቅ ነው።
ወያኔዎች ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንዲሉ ሕዝብንና መንግሥትን ለማሸበር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ ወደፊትም መቀጠላቸው አይቀርም። የአሜሪካውያንና የሽርከኞቻቸው ጫናን ማባበስ ተመራጭ መንገድ አድርገውታል። በመሠረቱ
አሜሪካውያኑም ሆኑ ሽርከኞቻቸው የሚጋልቡት እስካገኙ ድረስ ልጓም ለመጨበጥ የሚቀድማቸው አይኖርም።
ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው ደግሞ በራሳቸው ለመወሰን እድሜያቸው ያልደረሱትን ሕጻናት እየገበሩ መጓዙን አጠናክረው ቀጥለውበታል። አሜሪካውያኑም አንዱ አካሄድ ሲነቃባቸው ሌላውን እየሞከሩ የበላይነታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የጀመሩት ጉዞ የግዛት አንድነቷ የተረጋገጠ ጠንካራ አገር እስከምትፈጠር ድረስ የሚቆም አይደለም።
ወያኔ ወንጀልና ሽብር ሲሰራ የነበረ ቡድን ብቻ ሳይሆን እየሰራ ያለና ለመቀጠልም የማያመነታ ቡድን ነው። ለዚህ ደግሞ እስከ ቅርብ ግዜ በትግራይ ሚድያ ሀውስ እየቀረቡ የያዙኝ ልቀቁኝ መልዕክት የሚያስተላልፉት የወያኔ መሪዎችና የጦር አበጋዞች መመልከት በቂ ነው። እነዚህ እኩዮች ማስወገድ ራስን ቤተሰብን ብሎም አገርን መታደግ እንጂ የፖለቲካ ልዩነትን አለመቻቻል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።
ስለዚህ የነገው ትውልድ ቢያንስ ያደገች እንኳን ባይሆን ዜጎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር እነዚህን ሳንካዎች ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። መንግስትም ልክ የህዳሴው ግድብ ሙሌትን ለማከናወን እንዳደረገው ሁሉ በሙሉ ቁርጠኝነትና ልባዊነት የጀመረውን የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እኛም እንደ ሕዝብ በየዘመኑ መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ አያት ቅድም አያቶቻችንን እያስታወስን የመጣውን ነገር ተጋፍጠን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን። በተጨማሪ በዘላቂነት ሰላምና ነጻነታችንን የምናገኘውም ሆነ ጠላቶቻችን ሙከራቸውን የሚያቆሙት ለድንፋታቸው የማንበረከክ መሆናችንን ሲገነዘቡ ብቻ ነው።
እዚህ ላይ አሸባሪው ኃይል በወረራ ከያዛቸው ቦታዎች ሲለቅ በንብረትም ሆነ በሰው ላይ የደረሱ የምንሰማቸው ደስ የማይሉ ነገሮች እንደሚኖሩ ይታወቃል። በመሆኑም ወገባችንን ጠበቅ አድርገንና በአንድነታችን ጸንተን በጀመርነው መልኩ ነገሮችን ማስኬድ ይጠበቅብናል። ዛሬም ይሁን ነገ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚመጣብን በሙሉ ጠላታችን ነው። ስለሆነም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ለጠላት ሊሰጥ የሚገባውን ነገር ከመስጠት መሰሰት የለበትም ፤ የእለቱ መልዕክቴ ነው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014