ቅድመ-ታሪክ
እናት አባቱን በወጉ አያውቃቸውም፡፡ ገና በልጅነቱ በሞት የተነጠቁት ወላጆቹ ፍቅር ሳይለግሱት ተለይተውታል ፡፡ የሕጻንነት ዕድሜው ምቹ የሚባል አልነበረም፡፡ ገና በጠዋቱ፣ነፍስ ሳያውቅ ዘመድ እጅ የወደቀው ታዳጊ ለሕይወቱ የሚመች ኑሮን አላተረፈም።
መለሰ አዱኛ ትውልድና ዕድገቱ ወላይታ ‹‹ሰላም በር›› ከተባለ ስፍራ ነው፡፡ ገና በጠዋቱ ከዘመድ እጅ ቢወድቅ ቀጣይ ሕይወቱ ከአጎቱ ቤት ሆነ፡፡ አጎት ሕጻኑን ተረክበው ለማሳደግ ኃላፊነት ወደቀባቸው፡፡ ለእሳቸው ወላጅ አልባ ልጅን ወስዶ ማሳደግ ቀላል አልሆነም ፡፡ ከራስ ልጅ ሳያሳንሱ፣ ማጉረስ፣ ማልበስን ይጠይቃል። ለሌሎች ሳያደሉ ማስተማር፣ አደራን መወጣት ግድ ይላል፡፡
ሕጻኑ መለስ የአባቱን ስም በአጎቱ ቀይሮ መጠሪያቸው ሆነ፡፡ በቤታቸው መኖር ከጀመረ ወዲህ ግን ደስተኛ አልሆነም፡፡ እናት አባት ስለሌለው በየሰበቡ ይከፋል። በየምክንያቱ ያለቅሳል፡፡ ይህ እውነት ለአጎትየውና ለቤተሰቦቻቸው አላመቸም፡፡ በየአጋጣሚው ሲቆጡት፣ ሲገስጹት ባዕድነት ይሰማዋል፡፡ የትናንት ማንነቱን እያሰበ ቁጭት፣ ብስጭት ይይዘዋል፡፡ እንዲህ መሆኑ የመለስን ሕይወት ፈታኝና አስቸጋሪ አደረገው፡፡
መለስ የአጎት ቤት ሕይወት እንዳልተመቸው ቀጥሏል። በዕድሜው ትምህርት ቤት ሳይገባ ከቤት መዋሉ እየጎዳ ነው፡፡ ከእኩዮቹ መለየቱ በአቅሙ የታዘዘውን እንዳይሰራ አላገደውም ፡፡ በአሳዳጊዎቹ የሚሰጠውን ትዕዛዝ እየከወነ፣ሕይወቱን፣ኑሮውን ሊቀጥል ግድ አለው፡፡
ልጅነቱ ተጋምሶ በዕድሜው መብሰል ሲጀምር ውስጡ ብዙ ያስብ ጀመር፡፡ ከብቶች ይዞ ሜዳ ሲውል በነገር ይብሰለሰላል፡፡ ቤት ገብቶ አረፍ ሲል በትካዜ ይጨነቃል፡፡ ሁሌም የውስጥ ዕቅዱን እያወጣ፣ እያወረደ አርቆ ያልማል፡፡ የዛሬን ትቶ ስለነገው፣ ስለወደፊቱ ያስባል።
አሁን መለስ የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ሆኗል፡፡ ዛሬም ግን በአጎቱ ቤት ሕይወት መቀጠሉ እያሳሰበው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ባልተመቸ ዓለም መኖርን አይፈልግም፡፡ ሁሌ እንደሚሰማው ከእሱ ዕድሜ የሚያንሱ ልጆች ሰርተው፣ ለፍተው ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰብ ይተርፋሉ፡፡እሱም ቢሆን ከእነሱ ማነስ የለበትም፡፡
መለስ ይህን እውነት ካወቀ ወዲህ ልቡ ሸፍቷል፡፡ እሱም እንደሌሎች አዲስ አበባ ገብቶ ስራ መያዝ ገንዘብ መቁጠር ፈልጓል፡፡ ይህ ዕቅዱ ከእሱ ውሎ ሲያድር ለውሳኔው ፈጠነ ፡፡ የልቡን ምኞት ለመሙላት የቆየ ሕልሙን ለመፍታት ተጣደፈ፡፡
ኑሮ በአዲስ አበባ…
ሕጻኑ መለስ አዲስ አበባ ለመምጣት አልተቸገረም። በስፍራው ሲደርስ ሁኔታዎች በጎ ሆኑለት ፡፡ እነሱን መስሎ እንዲያድር የሻቱ የአገሩ ልጆች በወጉ ተቀብለው አስተናገዱት፡፡ ልጅ ቢሆንም ከሌሎች ተስማምቶ መኖር አልጠፋውም፡፡ ያገኘውን በልቶ፣ የአቅሙን ሰርቶ እንዲገባ መዋያ ተገኘለት፡፡
መለስ በአዲስ አበባ ኑሮ የቀን ስራ ውሎን ለመደ፡፡ በሚሰራው ልክ እየተከፈለውም ራሱን ማስተዳደር ቻለ። እንደሌሎች አገርቤት ስለሚልከው ገንዘብ አይጨነቅም። በጉልበቱ፣በላቡ ወዝ ከሚከፈለው ቆጥቦ ለራሱ ይጠቀማል፡፡ አብሮት ያደገው ችግር በአዲሰ አበባ ብርቅ አልሆነበትም፡፡ ደስታን ከኃዘን፣ማጣትን ከማግኘት አዛምዶ ብዙ አስተማረው ፡፡
መለስ በአዲስ አበባ ከልጅነት እስከ ጉልምስናው ዕድሜ ተጓዘ ፡፡ለፍቶ ከማደርና የድካሙን ከመቀበል ሌላ በትምህርት ለመዝለቅ አላሰበም ፡፡ ከአገር ቤት ሲወጣ እንደነበረው ሆኖ ሕይወትና ኑሮን ቀጠለ፡፡ እንጀራ የበላበትን የመጀመሪያውን ሥራ ሲለውጥ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው የጥበቃ ሙያ ሆነ፡፡
መለስ ዓመታትን በቆጠረበት የጥበቃ ሥራ ኃላፊነቱን ዘንግቶ አያውቅም፡፡ አጥሩን የሚጠጉ ፣.ዙሪያ ገባውን የሚቃኙ ቢኖሩ ቀድሞ ይጠራጠራል፡፡ ጥርጣሬው ይበልጥ ካየለ ቀርቦ ፣ ተጠግቶ ይጠይቃል፡፡ ሁኔታው ካላማረው በያዘው ዱላ እያስፈራራ፣እየዠለጠ ከቦታው ለማራቅ፣ የሚያግደው የለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማድ ከሥራው ባህርይ የወሰደው ተሞክሮ ነው፡፡
መስከረም 30 ቀን 2010 ዓም
የመስከረም ወር የመጨረሻው ቀን ነው፡፡ ያለፈው ወር ፀሐይ ዝናብና ንፋስ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። ተረኛ የሆነው የጥቅምት ወር ጊዜውን ሊረከብ ነውና ብርድና ውርጩ ማየል ጀምሯል፡፡ የምሽት ጥበቃውን በጊዜ የጀመረው መለስ በግቢው እየተዘዋወረ መቃኘቱን ይዟል፡፡
ብዙ ጊዜ ጨለማን ተተግነው ዝርፊያ የሚያስቡ አንዳንዶች አስቀድመው ጥግ እንደሚይዙ ያውቃል። እንዲህ በጠረጠረ ጊዜም አካባቢውን እየዞረ፣ መቃኘት ልማዱ ነው፡፡በዚህ ቀንም የሚጠብቀውን ግቢ እንደወትሮው እየዞረ መፈተሽ፣ ፈልጓል ፡፡ ይህን አስቀድሞ ከፈጸመ ጥበቃውን ያለስጋት ለማካሄድ ያመቸዋል፡፡
አሁን ከምሽቱ ሶስት ሰዓት እያለ ነው፡፡ ከረጅሙ የሌሊት ጊዜ ጋር ከመጨባበጡ በፊት ግቢውን እየዞረ መፈተሽ ጀምሯል፡፡ ቀድሞ የሥፍራውን ደህንነት ካወቀው ቀሪው ጊዜ አይቸገርም፡፡እንደልማዱ ወጣ ብሎ ፉት ለማለት፣ ተመልሶም በእንቅልፍ ለማሳለፍ ይተማመናል፡፡
መለስ የእጁን ዱላ እንዳጠበቀ በግቢው አንድ አቅጣጫ ፍተሻውን ጀመረ፡፡ ቦታው ለጨለማ የተጋለጠ አለመሆኑ ሁሉንም በግልጽ ያሳየዋል፡፡ ፊትና ኋላውን እየቃኘ፣ ግራቀኙን እያስተዋለ ዙሪያ ገባውን ፈተሸ፡፡ ስፍራው እንደወትሮው ሰላም መሆኑ እየተሰማው ነው ፡፡
ድንገቴው እይታ …
ጥበቃው የግቢውን ደህንነት አረጋግጦ ወደነበረበት መመለስ ጀምራል፡፡ ያሰበው ቦታ ከመድረሱ በፊት ግን ድንገቴ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ የግቢው በር ተከፍቶ አንድ ሰው ወደ ውጭ ሊወጣ ሲዘጋጅ ተመለከተው ፡፡ መለስ ዓይኖቹን ማመን አልቻለም፡፡ ውስጡን ድንጋጤና ብስጭት እንደያዘው ወደግለሰቡ ተንደረደረ፡፡ አጠገቡ እንደቀረበም ከፊት ለፊቱ አፈጠጠበት፡፡
ሰውዬው በጥበቃው ሁኔታ የተገረመ አይመስልም፡፡ ‹‹ማነህ? ከየት ነህ? ›› ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠትን አልወደደም፡፡ መለስ ዱላውን ይዞ ሲቀርበውና ጥያቄውን ሲደጋግም ‹‹ ምን አገባህ? ›› ሲል አመናጨቀው፡፡ ሁኔታው ያበሳጨው ጥበቃ መታገስ አልቻለም ፡፡አጠገቡ ደርሶ ጥያቄውን እንዲመልስለት ጮኸበት፡፡ ሰውዬው መልስ ከመስጠቱ በፊት እጁን ሰንዝሮ በቦክስ ቀደመው፡፡ መለስ የሰውዬው ቡጢ ድንገተኛና አስደንጋጭ ቢሆንበት ምላሹን ሊሰጥ እጁን ጨብጦ ፊቱ ላይ ሰነዘረ፡፡ ቦክሱ እንደሰውዬው ፈጣን አልሆነም፡፡ አመጣጡን ገምቶ ዝቅ ማለቱ በአየር ላይ እንዲስተው ዕድል ሰጠ ፡፡ እጁን ከአፉ አድርጎ ከንፈሮቹን ዳሰሳቸው፡፡ በሰውዬው ድንገቴ ምት ተሰንጥቀው መድማት ጀምረዋል፡፡ብሽቅ፣ብስጭት አለ ፡፡ ወዲያው ሰውዬው ከመሬት ጎንበስ ብሎ ድንጋይ ሲፈልግ አየው፡፡
መለስ ንዴትና እልህ ተፈታተኑት፡፡ ሰውነቱ እየ ተንቀጠቀጠ፣ ጥርሱ እየተፋጨ ዱላውን አጥብቆ ተጠጋው ፡፡ ሰውዬው በእጁ ሊመክት፣ ሊከላከል ሞከረ። አልሆነለትም ፡፡መለስ ቀድሞ የሰነዘረው ፈጣን ምት ከሽንጡ ላይ አረፈ፡፡ዱላውን እንዳጠበቀ፣ እግሩ ላይ ደገመው፡፡ ድንገቴው ዱላ ያደናገጠው የምሽት እንግዳ ፈጥኖ ለመሸሸ ሞከረ፡፡
ሰውዬው እየተንገዳገደ ከግቢው ወጣ፡፡ ከኋላ የሚከተለውን፣ሲያስብ ዳግም የሚያጋጥመውን እየገመተ መሮጥ ጀመረ ፡፡ በያዘው ፍጥነት ወደፊት ገሰገሰ፡፡ መንገዱን አልፎ ከአንድ ጥግ ሲደርስ ከፊት ለፊቱ የቆመ የመብራት ምሰሶ አጋጠመው፡፡ እሱን አልፎ የመሄድ ዕድል አላገኘም፡፡ በግንባሩ ተጋጭቶ ከመሬት ተዘረረ ። አባራሪው ዘብ ከኋላው ሲደርሰ ሰውዬው በወደቀበት በደም ተነክሮ ነበር፡፡ ዱላውን እንደያዘ ቁልቁል እያስተዋለው ጥቂት ቆየ፡፡ለመነሳት አቅም እንዳጣ ሲገባው ፊቱን አዙሮ ወደ ግቢው ጥበቃ ተመለሰ ፡፡
ደንብ አስከባሪው…
ቱሉ መገርሳ ተወልዶ ያደገው ሱሉልታ በአንድ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ ዕድለኛ ሆኖ ወላጆቹ ቀለም እንዲቆጥር ትምህርት ቤት አስገብተውታል፡፡እስከ ስምንተኛ ክፍል የዘለቀው ቱሉ ተከታዩን ክፍል ለመቀጠል አልተቻለውም፤በእሱና በቤተሰቦቹ ኑሮ አለመመቸት ትምህርቱን ሊያቋርጥ ተገደደ፡፡
ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ቱሉ በትውልድ ስፍራው አልቆየም፡፡ሥራ ይዞ ራሱን ለማገዝ አዲስ አበባ ዘለቀ። አዲስ አበባን በቀን ሥራ ተዋውቆ ዓመታትን እንደገፋ የታክሲ ረዳት ሆነ ፡፡ ይህ ሥራ ከብዙዎች አስተዋወቀው። አጋጣሚውን ተጠቅሞ ደንብ አስከባሪ ለመሆን አልተቸገረም፡፡ ሥራው የዕለት ገቢ ስላለው ተጠቃሚ አድርጎታል፡፡ መዋያውን መሳለሚያ እሳት አደጋ ከተባለው አካባቢ አድርጎ ግዴታውን ሲወጣ ይውላል፡፡
ቱሉ አዲስ አበባ ገብቶ ሕይወት ከጀመረ በኋላ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ተጣልቶ ያውቃል፡፡ከሁሉም ግን አንድ ጊዜ እሰከመታሰር ያደረሰውን ጠብና ድብድብ አይረሳም፡፡ይህ አጋጣሚ ለአንድ ወር በፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰርና በማስጠንቂያ እንዲለቀቅ አድርጎታል፡፤
አሁን ያለበት ሥራ ከብዙዎች የሚያጋጭና የሚያካስስ ነው፡፡ አንዳንዴም አስከመደባደብ ያደር ሳል፡፡ ያም ቢሆን ቱሉ ነገሮችን እንዳመጣጣቸው መመለስን አውቆበታል፡፡ በሰላምና በጠብ የሚቀርቡትን እንደሁኔታው፣ ይመልሳል፡፡
ከሥራ መልስ የሚያዘወትረው የመጠጥ መዝናኛ ከመለስ ጋር እንዲገናኙ ምክንያት ሆኗል፡፡ አንዳንዴ መለስ ከሥራው ወጣ እያለ ፉት እንደሚል የሚያውቀው ቱሉ ከእሱ ጋር ለማሳለፍ በእኩል ይታደማል፡፡ ብዙውን ጊዜ ሁለቱ የተቀዳለቸውን እየተጎነጩ የልባቸውን ያወጋሉ፡፡ ከሥራው ሰአዓት ሰርቆ ከመጠጥ የሚገኘው መለስ ቀድሞ ከሚያውቀው ቱሉ ጋር ቢቆይ ይወዳል፡፡ቱሉ አብዛኛውን ጊዜ መለስን እየጋበዘ ያዝናናዋል፡፤ከእሱ የተሻለ የዕለት ገቢ ስለሚያገኝ ለክፍያው አይግደረደርም፡፡
የዛን ቀን ምሽት ቱሉና መለስ እንደተለመደው ሲገባበዙ ቆይተዋል፡፤ውድቅት ላይ ጉዳያቸውን ጨርሰው ከመጠጥ ቤቱ ሲወጡ ቀድሞ ከመለስ የተጣላውን ሰው ፊት ለፊት አይተውታል፡፤መለስ ዱላውን እንደያዘ ወደ ሰውዬው ቀረበ፡፡ቱሉ ባልንጀራውን ተከትሎ ከኋላው ሲሮጥ ደረሰ፡፡
የፖሊስ ምርመራ…
ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓም ማለዳ ከመንገድ ዳር ወድቆ ስለተገኘው ሟች ፖሊስ ማጣራት ጀምሯል፡፡ ምሽቱን ተገድሎ ማደሩን በማወቁ የአካባቢውን ሰዎች እየጠየቀ መረጃ እያሰባሰበ ነው፡፡ፖሊስ የሟችን አስከሬን አንስቶ ተገቢውን ምርመራ ካጠናቀቀ በኋላ ተጠርጣሪዎቹን ማሰስ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ፖሊስ በፍለጋው እምብዛም አልራቀም ፡፡በወንጀሉ ተባብረዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦችን ፈልጎ በተለያዩ ቀናት ሁለቱን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ሳጂን ሙሉዓለም ደግአረገ አንደኛ ተጠርጣሪ ነው የተባለውን መለስ አዱኛን አቅርቦ ስለወንጀሉ እንዲናገር ጠየቀው፡፡መለስ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ አምኖ ብቻውን እንዳደረገው ተናገረ፡፡በዛን ቀን ምሽት አብሮት የነበረውና በወንጀሉ ተሳትፏል የተባለው ቱሉ መገርሳ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ነበር፡፡ፖሊስ ከብዙ ድካም በኋላ ሲያገኘው ጉዳዩን እንዲያስረዳ ጠየቀው፡፡
ቱሉ ምሽቱን ከመለስ ጋር አሳልፎ ከመዝናኛው ሲወጣ ሟችን መንገድ ዳር ወድቆ ስለማየቱ አልካደም። በድብደባው ያለመሳተፉንና በጉዳዩ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባው ሲናገር ግን በሙሉ እርግጠኝነት ሆነ ። መርማሪው የተጠርጣሪዎቹን ቃል በወንጀል መዝገብ ቁጥር 345/10 ላይ መዝግቦ ምሽቱን ስለተፈጸመው ወንጀል በአይኔ አይቻለሁ ያሉትን አዛውንት ለጥያቄ ጠራ፡፡
ለምስክርነት የቀረቡት ሽማግሌው አቶ ዘነበ ወርዶፋ በጥበቃ ሥራ ዓመታትን ዘልቀዋል፡፡እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ለተቀጠሩበት ዓላማ ኃላፊነቸውን በጥንቃቄ ይወጣሉ፡፡የዛን ቀን ምሽት መለስና ቱሉ ካልተያዘው ግብረአበራቸው ጋር በመሆን ሟችን እያንገላቱ ስለመግደላቸው በዝርዝር አስረዱ፡፡የተናገሩት ቃል የእውነት ስለመሆኑም በቃለ መሐላ ፈርመው አረጋገጡ፡፡ መርማሪው የምስክሩን ቃል አስፍሮ እንደጨረሰ ዶሴውን በመረጃዎች አዳብሮ ለዓቃቤ ሕግ ክስ አስተላለፈ፡፡
ውሳኔ…
ፍርድ ቤቱ በግድያ ወንጀል በተጠረጠሩት ሁለት ግለሰቦች ላይ የቀረቡ መረጃዎችን ሲያጣራ ሲመረምር ቆይቷል፡፡ለምስክርነት የተጠሩት አቶ ዘነበ ወርዶፋ አይቻለሁ ያሉትን እውነት እንዲያስረዱም ዕድል ሰጥቷል።ምስክሩ የዛን ቀን ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ መንገድ ላይ ወድቆ በነበረው ግለሰብ ላይ የመጀመሪያውን ዱላ ያነሳው መለስ አዱኛ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
እሱን ተከትሎ ቱሉ መገርሳና ያልተያዘው ግብረአበራቸው ሟችን በጭካኔ ሲቀጠቅጡት ቆይተዋል፡፡ ግለሰቡ ራሱን ስቶ በወደቀ ጊዜም ለሶስት እየጎተቱ አጥር ስር ሲጥሉት በሚያድሩበት የጥበቃ ቤት ቀዳዳ አጮልቀው ማየታቸውን አዛውንቱ ተናገሩ። በወቅቱ ፈርተው ስለነበር ለመገላገልና ለማስጣል አለመሞከራቸውን ምስክሩ አልሸሽጉም፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእሳቸውንና የሌሎች እማኝነትን ከሕክምና ማስረጃዎች ጋር አጣምሮ ማስረጃውን አጠናከረ፡፡የተጠርጣሪዎችን ጥፋተኝነቱን አረጋግጦም እንዲከላከሉ ዕድል ሰጠ፡፡ተከሳሾቹ የሚያቀርቡት መከላከያ አልነበረም፡፡
ፍርድ ቤቱ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓም የመጨረሻውን ውሳኔ ሊያስተላልፍ በችሎቱ ተሰየመ። በዕለቱ በሰጠው ፍርድም፡፡አንደኛው ተከሳሽ መለስ አዱኛ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የስምንት አመት ከአምስት ወር ጽኑ አስራት እንዲቀጣ ሲወስን ሁለተኛው ተከሳሽ ቱሉ መገርሳም በስድስት አመት ጽኑ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ፈርዷል፡፡
መልካም ስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014