እጅ እግር ያለው ሊቋቋመው የማይችለው ፈተና በአካል ጉዳተኛ ላይ ሲደርስ በሕይወት ዘመን የሚፈጥረው ጫና እጅግ ከባድና ለማመን የሚቸግር ነው። ያውም በተፈጥሮ እጅ እግሩ የማይሠራ ሆኖ ለተወለደ ሰው የሚያሳድረው ስነልቦናዊ ጉዳት በቃላት አይገለፅም። ዕጣ ፈንታው የዕለት ጉርስን ለማግኘት ለምኖ ለመኖር ከሚያስገድድ ድህነት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ደግሞ ፈተናውን በእጅጉ ያከብደዋል። የሚያጎርሰው፣ የሚያለብሰው፣ የሚያፀዳዳው ብሎም ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ የሚረዳው ሰው ከሌለው የሚሆነውን ማሰቡ ሁሉ ያሳምማል።
ኅብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኛ ካለው የተዛባ አመለካከት ጋር ሲደመር ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራል። በብርቱ ያማርርና መፈጠርን ያስጠላል። በዚህ ዓይነቱ ሰው ላይ ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ሲወድቅበት ደግሞ የሚያሳድረው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ለማመን ያዳግታል። ፈተናውን አልፎ በሕይወት መቆየት ላያስችል ሁሉ ይችላል።
በ1964 ዓ.ም ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ልዩ ስሙ ቄስ ሠፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ። ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ በተፈጥሮ ሁለቱም እጆቹና እግሮቹ የማይንቀሳቀሱ ሆነው ተገኙ። እንዲህ ዓይነቱ ተፈጥሯዊ የአካል ጉዳት ዕጣ ፈንታ የገጠመው ሰዓሊ ዮሴፍ በቀለ ይባላል። ሰዓሊ ዮሴፍ ሰርክ ከእንቅልፉ ሲነሳ ‹‹ተመስጌን›› በማለት ለፈጣሪው ምስጋና በማቅረብ የዕለት ውሎውን ይጀምራል። ሆኖም በሁለት እግሩ ለመቆም ያስቻለው ወላጅ እናቱ፣ በሞት የተለየችው የቀድሞ ባለቤቱ እና በአሁኑ ወቅት የትዳር አጋር የሆነችው ባለቤቱ ጨምሮ እያደረጉለት ያለው ድጋፍ ነው።
ሰዓሊ ዮሴፍ እንዳጫወተን ሲወለድ ሁለቱም እጆቹና እግሮቹ አይሰሩም። መቆም ባለመቻሉ በሰው ትከሻ ነበር የሚንቀሳቀሰው። እናቱ፣ ታላቅ እህቱና በሕይወት የሌለው ታላቅ ወንድሙ 10 ዓመት ያህል አዝለውታል። ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኘው ቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል እስከ ንባብ ያስተማሩትም በዚህ ሁኔታ ነበር። በቀድሞ አጠራሩ አውራ ጎዳና ከሚባለው (መንገዶች ባለስልጣን) ውስጥ የወጥ ቤት ሰራተኛ ሆነው በየክፍለ አገሩ እየተዘዋወሩ የሚሰሩት አባቱ በወር ከሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ላይ ለዮሴፍ እናት ተቆራጭ የሚያደርጉላቸው 80 ብር ብቻ የነበረ ሲሆን አምስት ቤተሰብ ለማስተዳደር አይበቃቸው ነበር።
ዮሴፍ የሚተዳደረውና ቤተሰቡን የሚደጉመው ቤተክርስቲያን አካባቢ በመቀመጥ በሚያገኛት ምፅዋት ነበር። ቤተሰቦቹ በበዓላት ወቅት ቤተክርስቲያን በር ላይ ወስደው ያስቀምጡትና ሲለምን ይውላል። እነሱም አብረውት ይቀመጡ የነበሩ መሆኑን ያወሳል።
ሰዓሊ ዮሴፍ እንዳወጋን የካዛንቺሶቹ እነ ኦሜድላ፣ አድዋ፣ ኦሬንታልና ሌሎች ቡና ቤቶች እንዲሁም ፋይቭ ዶርስ የተባሉት ጭፈራ ቤቶች ከእንብርክኩ ጀምሮ ቆሞ መሄድ ከጀመረ በኋላም ሲመፀወትባቸው ከነበሩ ቦታዎች ይጠቀሳሉ።
በዚህ ሁኔታ ያደገው ዮሴፍ በሂደት አብሮ አደጉ ከሆነች የሠፈሩ ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙት ይጀምራል። ባለቤቱ ለእሱ የነበራት ፍቅር፣ በየሣምንቱ ፍልውሀ ይዛው በመግባት ከበሽታው እንዲፈወስ የምታደርግለት እንክብካቤና በፍቅር ያሳለፉት ጊዜ ሁሉ ዛሬም ከፊቱ ድቅን ይላል። ሆኖም ይሄን የድብቅ ፍቅራቸውን ያወቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከወላጆቿ ጀምሮ ለእነሱ የነበራቸው አመለካከት ጥሩ አልነበረም።
ባለቤቱ ላይ ከገዛ ወንድሞቿና እህቶቿ ወንድ አጥተሽ ነው ወይ እሱን ያፈቀርሽው የሚል ትችት ይሰነዘርባት ነበር። እሱም ስድቡንና ግልምጫቸውን አልቻለውም። ሁለቱ ፍቅረኛሞች ከቤተሰብ የሚደርስባቸውን ስድብና ግልምጫ ሲብስባቸው፣ ይለይላቸው ብለው ከምፅዋት የሚገኘውን ገቢ ተማምኖ ቤት ተከራይተው በመጋባት መኖር ጀመሩ። አንዲት ሴት ልጅም ወለዱ።
በዚህ ወቅት ኅብረተሰቡ የሚያደርስባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ይበልጥ እየተባባሰ ቀጠለ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ባለቤቱ የአራት ወር ህፃን ልጅ ጥላበት ሞተች። ሌላው እንክብካቤ ቀርቶ፣ ጡጦ ለመስጠትና አቅፎ ለመንከባከብ የሚያስችል እጅ ያለው ባለመሆኑ በዕጣ ፈንታው ለመጀመሪያ ጊዜ በእጅጉ ያዘነበት ወቅት ነበር።
የገጠመውን ችግር መቋቋም ሲያቅተው ከሟቿ ሚስቱ የወለዳትን ሕፃን ልጁን ይዞ ተመልሶ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ይዞ ገባ።
የሕፃንዋን ወተት ጨምሮ እናቱን ለማገዝ በየቡና ቤቱ እየዞረና እያመሸ ምፅዋት ማሰባሰብና ለእናቱ መስጠት ይጠበቅበት ነበር። ይሄን እያደረገ እራሱ ይመገብ የነበረው ሆቴል ነበር። ለዚህ ሲል በተለይ የበዓል ዋዜማ ዕለት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝና አስር ሰዓት መቆየት ነበረበት። በዚህ ሌሊት በር የሚከፍትለት አጥቶ ያውቃል። ለሦስት ዓመት ያህል በቃላት ሊገለፅ በማይችል ችግር ውስጥ ተዘፍቆ አሣለፈ።
‹‹ችግሩ ሲፀናብኝ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ሄጄ የሞተችውን ባለቤቴን በማስታወስ ለምን ሰጠኸኝና ነሳህኝ እያልኩ አለቅስ ነበር›› ይላል። በፈጣሪ ፀሎቱ ተሰማና ከሦስት ዓመት በኋላ የሚበላበት ሆቴል ውስጥ የምትሠራውን የዛሬዋን ባለቤቱን አገኘ።
ሁለት ልጆች የወለደችለት ባለቤቱ ወይዘሮ የኔነሽ ታዬ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው። እስከ 12ኛ ክፍል ጎበዝ ተማሪም ነበረች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ ጎበዝ በመሆኗ ስፔሻል ክላስ ገብታ የመማርም ዕድል አግኝታለች። ቤተሰቦቿ የታወቁ የሶዶ ጉራጌ ነጋዴዎችና ለሀብትና ለክብር ትልቅ ግምት የሚሰጡ ናቸው። ምግብ ቤት መሥራት የጀመረችው እጅግ ሀብታም ለሆነ ትልቅ ሰውዬ ሊድሯት መሆኑን ከሠራተኛቸው ሰምታ በአጥር ዘላ አምልጣ በመውጣቷ ነው።
ከዮሴፍ ጋር ፈቅዳና ደፍራ ታገባዋለች የሚል ግምት እንኳን ቤተሰቦቿ እሷም አልነበራትም። ሁሌ ጓደኞቹ ሲያጎርሱት ታየው ነበር። አንድ ዕለት ምግብ አዝዞ የሚያጎርሱት ጓደኞቹ አጠገቡ ስላልነበሩ የሚያጎርሰው ባጣበት አጋጣሚ እኔ ላብላህ ብላ ስታጎርሰው ለምን ሆቴል እንደሚበላ፣ ሚስት እንደነበረችው፣ የአራት ወር ህፃን ጥላ እንደሞተችበት ነገራት። እጅግ አዘነች። ሰርክ ታበላው ጀመር። እየመጣ እንዲጫወት ትጠራውም ነበር። በዚህ ተግባቡና ልክ የሞተችው ባለቤቱ እንዳለችው አብራው ለመኖር ፈቃደኛ መሆኗን ገለፀችለት። ቤት ተከራይታም ከሆቴሉ ወጣችና አብረው መኖር ጀመሩ።
የኔነሽ ባለሙያ በመሆኗና እሷ ካገባች በኋላ ሆቴሉ በመዘጋቱ የሆቴሉ ባለቤት አንተ ሠራተኛዬን ወስደህ ነው በማለት ዮሴፍን ሊገለው ደረሰ። በዚህ ራሱ ብዙ ጊዜ ተቸግሯል። እንደበፊቷ ባለቤቱ ሁሉ ቤተሰቦቿና የአካባቢው ሰው እንዴት እሱን ታገቢያለሽ ብለዋታል። በስድብና ትችትም ጎንትለዋታል።
ባለቤቱ ጥላበት የሞተችውን ሕፃን ልጅ ከእናቱ ጋር በማምጣት ከእሷና ከአባቷ ጋር እንድትኖር ስትጠይቅ ጫማና ልብስ ከመልበስና ምግብ ከመብላት ጀምሮ የእርሷን እርዳታ አብዝቶ የሚፈልገውን ሰዓሊ ዮሴፍን እንደ ሕፃን በመቁጠር ‹‹ሁለት ሕፃናት ማስተዳደር ትችያለሽ ወይ›› ያሏት የቤተሰብ ክፍሎች ነበሩ።
ልጃቸው ጎበዝ እንድትሆን የተሻለ ትምህርት ቤት ስታስገባት የትምህርት ወጪው ያሳሰበው ባለቤቷ ቄስ ትምህርት ቤት እንድትገባ ፍላጎት ነበረው። ነገር ግን የኔነሽ ዮሴፍን ለመንከባከብ ከሚተርፋት ጊዜ ስራ ሠርታ እሱም ከስዕል ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ክፍያውን እየሸፈኑላት ልጃቸውን ማስተማር ችለዋል።
ይህች ልጅ ዘንድሮ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛለች። የ20 ዓመቱ ወንዱ ልጃቸውም በዚሁ ዓመት በዲፕሎማ ተመርቋል። ትንሿም ልጃቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆናለች። ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለው በባለቤቱና በስዕል ሙያው እገዛ ነው።
የስዕል ሙያው ጥበብ ተስጥዖው ከሕፃንነት ይነሳል። ሰዓሊ ዮሴፍ ወደ ሕፃንነት ዕድሜው መለስ ብሎ እንዳጫወተን ቤታቸው ያኔ አባጣ ጎርባጣ በበዛበት የአጎዛ ወንዝ ዳርቻ የነበረ መሆኑ እሱን የመንከባከቡን ጉዳይ ለቤተሰቦቹ የበለጠ እንዲያስቸግራቸው እንዳደረገም ያስታውሳል።
‹‹በእኔ ብትበደልም በወለድኳቸው ልጆች ተካሰች›› የሚላቸው እናቱ በድህነት አቅማቸው ፈውስ እንዲያገኝ በመሻት ፀበል ለፀበልና የተለያዩ ሆስፒታሎች ተሸክመውት ተንከራትተዋል። ብዙ ደክመውበታል። ፈጣሪ ድካማቸውን ቆጥሮላቸው በ11 ዓመቱ አዲስ በፈለቀው የቅዱስ ፁራኤል ፀበል ተጠምቆ በእግሩ ለመቆም በቃ። አሁን ያሉበትና ቅርጫት ሰፈር እየተባለ ወደሚጠራው አካባቢ መግባታቸውም እንደ ልቡ መንቀሳቀስ አስችሎታል። እራስ መስፍን ሜዳ እየተባለ የሚጠራው ቦታ በመውጣት ከልጆች ጋር ብይና ጠጠር ተጫውቷል።
እርሳስና ወረቀት ስጡኝ በማለት በእግሩ ደብዳቤና የተለያዩ ጽሑፎችን መፃፍ እንዲሁም ስዕል መሳል የጀመረውም በዚሁ ጊዜ ነው። በፍጥነትም በእግሩ ይስልና ይፅፈው የነበረው ጽሑፍና ስዕል ወደ አፉ ተሸጋገረ ። ይህን አጋጣሚ ሲገልፀው አንድ ዕለት አጠገቤ የነበሩ ታላቅ እህቴና እናቴ ሞቅ ያለ ወሬ ይዘው ነበር።
ወረቀትና እርሳስ እንዲሰጡኝ ደጋግሜ በመጠየቄና ወሬያቸውን በማቋረጤ ተናድደው ወረቀትና እርሳስ ጠረጴዛ ላይ ወርውረውልኝ ወሬያቸውን ቀጠሉ። እኔ በእግሬ የምፅፈውና የምስለው መሬት ቁጭ ብዬ ቢሆንም እህቴን መሬት እንድታስቀምጥልኝ ስጠይቃት መልስ ስላልሰጠችኝ በቅጽበት ቆሜ ጠረጴዛ ላይ ባለው እርሳስና ወረቀት እናትና እህቴ እስኪገረሙብኝ ድረስ በአፌ መፃፍና መሣል ጀመርኩ ይለዋል።
ሰዓሊ ዮሴፍ እንዳወጋን አሁንም ስዕል ለመሣልና ለመፃፍ የሚጠቀመው አፉን ነው። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም መከታተሉ በዚህ አጋጣሚ ያገኘውን የስዕል ችሎታ በስልጠና እንዲያዳብር አግዞታል። እገዛውን ‹‹የብሩህ ተስፋ የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራም ላይ አንዲት በአደጋ ምክንያት ሁለት እግርና እጇን ያጣች አሜሪካዊት ልጅ በአፏ ስዕል በመሣል የአገሯን ስም ማስጠራቷን ሰማሁ›› ሲል ይገልፀዋል።
በዚህ በመነሳሳት ስዕል ትምህርት ቤት ገብቶ ተስጥዖውን የበለጠ ማዳበር እንዳለበት አሰበ። አጠያይቆም ሰባ ደረጃ ያለው ናዝሬት ስኩል ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኘው አቢሲኒያ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመሄድ ስዕል እንዲያስተምሩት ጠየቃቸው። በመገረም እንዴት ልትሰራው ነው አሉት። በአፉ እንደሚሠራ ነገራቸው። የስድስተኛና የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማስረጃ እንዲያመጣ ሲጠይቁት የለኝም አላቸው። የሚፈልገው ትምህርቱን ብቻ ከሆነና የትምህርት ማስረጃ እንዲሰጡትና እንዲያስመርቁት የማይፈልግ ከሆነ መማር እንደሚችል ሲነግሩት እጅግ ተደሰተ። ምንም ዓይነት መረጃ እንደማይጠይቅና መመረቅ እንደማይፈልግም አስፈረሙት። በአፉ የሚስልበት አቆሙለት። ሁለት እጅ የሌላቸውና ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን ያያቸው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ሲያስተምሩ ማየቱ ደግሞ የበለጠ አነቃቃው።
እዛው የምትማረው ልጃቸው ሰናይት ወርቁም ውሃ፣ እርሳስና ወረቀት በማቅረብ ትረዳው ነበር። ለሰባት ወር በእርሳስ ከተማረ በኋላ ወተር ከለር ግቡ ተባለ። ይሄንንም ገዝቶ መሥራት ጀመረ። ወተር ከለር እንኳን እጅ ለሌለው እጅ ላላቸው ተማሪዎች መጠኑ ካልተጠበቀ ስለሚፈስ በእጅጉ ያስቸግር ነበር።
ብዙ ተማሪዎች ከብዷቸው አቋርጠዋል። ሆኖም እሱ መጠኑን ጠብቆ በመሥራቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስኬታማ ለመሆን በቃ።
ለመማር ካለው ጉጉት የተነሳ ከአስተዳደር ቢሮ ሲጠራ መረጃ ስለሌለህ ትምህርትህን አቋርጠህ ውጣ ሊሉት እየመሰለው ይሳቀቅ እንደነበርም ያስታውሳል። አንድ ቀን ግን የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የሆነችው ገነት አስጠራችው። ቢሮም ሲሄድ በጭራሽ ያልጠበቀውን ዜና ሰማ። ‹‹ዓመት አልፎሃልና ልትመረቅ ስለሆነ የጋዎን 50 ብር ክፈል ስትለኝ ማመን አልቻልኩም። ሰውነቴን የደስታ ስሜት ወረረኝ›› ሲልም ያስታውሳል።
ሰዓሊው ዮሴፍ ከተመረቀና የስዕል ጥበቡን ገቢ ማግኛ ካደረገ 16 ዓመት ሆኖታል። ለባዛር የሚሆን ስዕል ሲታዘዝም የቤቱን ጥበት ዓይቶ የፈቀደለት የተማረበት የአቢሲኒያ ትምህርት ቤት ውስጥ ይሠራል።
በስዕል ሥራው ያገኘው ገንዘብ አጥጋቢ ባይሆንም የስዕል ሥራውን በአገር ውስጥና በውጪ ሸጧል። ሸራተን አዲስና ሌሎች ሆቴሎች ላይ በተዘጋጀ የሥዕል ኤግዚቢሽንም ተሣትፏል።
ነገር ግን እናቱ ካለቻቸው አንዲት ክፍል ላይ ቆርሰው የሰጡት ጠባቧ ቤት ውስጥ የሚሰራው ሥራ እንደ ብዙዎቹና ከባባዶቹ ፈተናዎች ማለፍ አላስቻለውም። የአጥሩን በር ከፈት እንዳደረጉልን የሰዓሊው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ዘው ለማለት ሁለት እርምጃ እንኳን መራመድ አልተጠበቀብንም። የአምስቱ ቤተሰብ የዕለት ምግብ የሚበስለውም በዚችው ሁለት እርምጃ በማትሞላ ቤት ውስጥ ነው።
ልታሳልፈን የቻለችው ምግብ የሚበስለው ወጪ ገቢ በሌለበት ሰዓት በመሆኑ ነው። የዘለቅንባት ክፍል ፅዳቷ ማራኪ ቢሆንም ከመጥበቧ የጣሪያዋ ቅርበት ይገርማል። እንኳን ረጅም አጭር ሰውም አታስቆም። በልኳ ታዘው የተሰሩ የሚመስሉ ሁለት ተሰካኪ አልጋዎች ብትይዝም አንዱ ከጣራው ጋር ሊገጥም ምንም ስለማይቀረው ቤተሰቡ ተቸግሮ በመውጣት እንደሚተኛበት ያሳብቃል። ለአምስት ስለማትበቃ ቀሪው የሚተኛው መሬት እንደሆነ አያጠራጥርም። ቁመቷና ስፋቷም ቢሆን ተጣጥፎ እንጂ ዘርጋና ዘና ብሎ መተኛት እንደማያስችል ግልፅ ነው።
በስተኋላ ሰዓሊው ያጫወተንም ይሄንኑ ነበር። ጠባቧ ክፍል ስዕል ለመሣልና አሁን እያዘጋጀው ያለውን በጥቅል ሕይወቱ ላይ የሚያጠነጥነውን መፃፍ ለመፃፍም ሆነ ሌሎች መጽሐፍቶችን ለማንበብ አትመቸውም። ስዕል የሚሠራው በትልቅ ሣጥን ላይ ወንበሮች ደራርቦ በመሆኑ በእጅጉ እያጠማዘዘች ታሰቃየዋለች። በዚህና በኮሮና ምክንያት ሥዕል ሥራውን ካቆመ ሁለተኛ ዓመቱ ሆኖታል። ይህን ችግሩን ቤቷ ከምትገኝበት ቀበሌ 32 እና ወረዳ 8 እስከ ክፍለ ከተማ አሳውቋል። ቢሆንም ይህን ያህል ዓመት መፍትሔ አልሰጡትም።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014